ማእከላቱ ጠቅላላ ጉባኤያቸውን አካሄዱ

ኅዳር 11 ቀን 2005 ዓ.ም.

በዲ/ን ዮሴፍ ይኲኖ አምላክ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን  ማኅበረ ቅዱሳን  የአሰላ፣ የአምቦ፣ የፍቼ፣ የደብረ ብርሃን፣ የወሊሶ እንዲሁም የወልቂጤ ማእከላት ከጥቅምት 25  እስከ ኅዳር 2 ቀን 2005 ዓ.ም ባሉት ጊዜያት ጠቅላላ ጉባኤያቸውን ከወረዳ ማእከላት፣ ከግንኙነት ጣቢያዎች፣ ከግቢ ጉባኤያት የተወከሉ አባላት፣ የየሀገረ ስብከቱ ተወካዮች፣ የወረዳ ሊቃነ ካህናት፣ የአድባራት አስተዳዳሪዎች፣ የሰንበት ትምህርት ቤት ተወካዮች እና  የማኅበረ ቅዱሳን የዋናው ማእከልና የመሐል ማእከላት ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ልዑካን በተገኙበት አካሂደዋል፡፡

 

ለጉባኤያቱ በወጣው  መርሐ ግብር መሠረት በ2004 ዓ.ም  ማእከላቱ ያከናወኗቸው የዕቅድ ክንውን ዘገባዎች የቀረቡ ሲሆን፤ በዘገባዎቹ ላይ ውይይት እና አስተያየት ተሰጥቷል፡፡ በሌላ በኩል የማኅበሩን የአራት ዓመት ስልታዊ ዕቅድ መፈጸም ይቻል ዘንድ የማእከላቸውን ነባራዊ ሁኔታ ባማከለ የየራሳቸውን  ድርሻ በመውሰድ አጽድቀዋል፡፡

በአሰላ ማእከል ጠቅላላ ጉባኤ ላይ በመገኘት የማኅበረ ቅዱሳን መልእክት ያቀረቡት ቀሲስ ዶ/ር ሙሉጌታ ስዩም ናቸው፡፡ ጠቅላላ ጉባኤው በተመረጡ የመወያያ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ውይይት አድርጓል፡፡ በመርሐ ግብሩ ላይ የወረዳ ማእከላት የልምድ ልውውጥ አካሂደዋል፡፡ የማእከሉ የ2005 ዓ.ም ሥራ እና የበጀት ዕቅድ ቀርቦ አሳብ ከተሰጠበት በኋላ ጸድቋል፡፡ በመርሐ ግበሩ ፈጻሜ ላይም ከዋና ማእከል የተገኘውን የንዋያተ ቅዱሳት እርዳታ ለገጠር አብያተ ክርስቲያናት ታድሏል፡፡

በተያያዘ ዜና፥ የአምቦ ማእከል የራሱን ጽሕፈት ቤት ለማስገንባት ያዘጋጀውን የመነሻ አሳብ፥ ጉባኤው ሰፊ ውይይት ካካሄደበት በኋላ፤ የቀረበውን አሳብ በማጽደቅ ዝርዝር አፈጻጸሙን የሥራ አስፈጻሚው እንዲመለከተው ወስኗል፡፡ በስልታዊ ዕቅድ ዘመኑም የግንባታው 5% ለመፈጸም መታቀዱን ከማእከሉ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡