ልጆችሽ

በመዝሙርና ሥነጥበባት ክፍል

እንደ ዕንቊ የሚያበሩ ከዋክብት ልጆችሽ

ምስክሮች ሁነው ዘመን አሻገሩሽ

ዛሬም በኛ ልብ ውስጥ ጸንተሽ ትኖሪያለሽ

የአብራክሽ ክፋዮች ቢቆጠር ዘራቸው

       በገድል በትሩፋት ይኸው በእኛ ዘንድ የታወቁ ናቸው

ነገሥታት ነበሩ ጠፍር የታጠቁ

በጥበብ የላቁ ምሥጢርን ያራቀቁ

ወልድ ዋሕድ ብለው ሃይማኖት ያጸኑ

ሰውን ሰው ያደረጉ ሀገርን ያቀኑ

በአጥንታቸው ድንበር ቅጥሩን የቀጠሩ

በደማቸው ድርሳን ታሪክ የዘከሩ

 ገዳም የገደሙ ደብር የደበሩ

መስቀል የተከሉ ዕለት የወቀሩ

ፊደል በገበታ ቆጥረው የቀመሩ

የሰማይን ሥርዓት በምድር የሠሩ

እኒያ ብርቱ ልጆች እንደ ዕንቊ ያበሩ

  የአምላክን ሰው መሆን የልደቱን ምሥጢር

  የክርስቶስ ፍቅሩን የመስቀሉን ነገር

  ውለታውን ሰፍሮ ለመክፈል ብድሩን

   ቢተጉ ቢያስሱት ገጸ በረከቱን

መክፈል አይቻልም ዘለዓለም ይመስገን

የያሬድን መዝሙር የመላእክትን ስብሐት

  በቀንና ሌሊት ሲያዜሙ ሲቀኙት

ልባቸው ይረካል ይነዳል በፍቅር

ከአርያም ደርሶ ከመላእክት ሀገር

ሊቁ ቅዱስ ያሬድ ግብሩ ሰማያዊ

ጥዑመ ልሳን ማሕሌታዊ

‹‹ዋይ ዜማ ዘሰማዕኩ እምሰማይ›› እያለ

    በረቂቅ ምስጋናው መልአክን መሰለ

 ባኮስ ጃንደረባ ቀዳማዊ ሐዋርያ

     ሕጽዋ ለሕንደኬ ንግሥተ ኢትዮጵያ

አፄ ካሊብ መናኝ ንግሥናው በርሃ

ቅዱሳን ነገሥታት አብርሃ ወአጽብሃ

ገብረ ማርያም ላሊበላ ነአኩቶ ለአብ ይምርሐ

የጻድቅ ከተማ የጥበባት ማዕድ

አቡነ ኢየሱስ ሞዐ ዘደብረ ነጐድጓድ

የወንጌል ገበሬ አርበኛ መነኮስ

ተክለ አብ ተክለ ወልድ ተክለ መንፈስ ቅዱስ

የዕውቀት ብርሃን የምሥራቅ ፀሐይ መውጫ

ዓምደ ሃይማኖት አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ

ጸሎት ትሩፋቱ መጠለያ አንባ

አቡነ ሳሙኤል ዘምድረ ዋልድባ

በግብፅ ንሂሳ ምስራች ተሰማ

ገና በማሕፀን ጌታው የመረጠው የወንጌል አውድማ

ገብረ መንፈስ ቅዱስ እንደተወለደ

   ልክ እንደመላእክት ምስጋናን ወደደ

     ለሰው ልጆች አምባ ተጋዳይ አርበኛ

    በበረሃ ኖረ አንበሳና ነብሩን አድርጎ ጓደኛ

ገዳምን ገደመ ልጆቹን አጸና

ገብረ መንፈስ ቅዱስ ኢትዮጵያን ባረከ ዝቋላን አቀና

የሰው ልጅ እንዳይወድቅ በኃጢአት ጐዳና

 ዲያብሎስ እንዲማር አምላኳን ተማፅና

  ሲኦልን ያንኳኳች እንደ ሐዋርያ

  ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ እንተ አቅሌስያ

እንደ ዕንቊ የሚያበሩ ከዋክብት ልጆችሽ

 ምስክሮች ሁነው ዘመን አሻገሩሽ

 ዛሬም በኛ ልብ ውስጥ ጸንተሽ ትኖሪያለሽ