abnet 2006 2

ለአብነት ተማሪዎች የአልባሳትና የንጽሕና መጠበቂያ ድጋፍ በመደረግ ላይ ነው

 ሐምሌ 28 ቀን 2006 ዓ.ም.

እንዳለ ደምስስ

  • በ150 አብነት ትምህርት ቤቶች ውስጥ ለሚገኙ ለ10 ሺህ የአብነት ትምህርት ተማሪዎች ለማዳረስ ሥርጭቱ ይቀጥላል፡፡

  • “ያለኝ አንድ የተቀደደ ሱሪና አንድ ሸሚዝ ብቻ ነበር ፤ ቅያሪ ስለሌለኝ በመጨነቅ ላይ ሳለሁ በመድረሳችሁ እግዚአብሔር ይስጥልኝ” ከአብነት ተማሪዎች አንዱ::

abnet 2006 2
በማኅበረ ቅዱሳን የቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ዋና ክፍል አስተባባሪነት “ሁለት ልብሶች ያሉት” በሚል መሪ ቃል ከምእመናን አልባሳትና ቁሳቁሶችን በማሰባሰብ በየአኅጉረ ስብከቱ ለሚገኙ የአብነት ትምህርት ተማሪዎች የአልባሳትና የንጽሕና መጠበቂያ ቁሳቁስ ድጋፍ በመደረግ ላይ ይገኛል፡፡

“ሁለት ልብሶች ያሉት” በሚል መሪ ቃል ለሁለተኛ ጊዜ ከሐምሌ 18 ቀን 2006 ዓ.ም. ጀምሮ በመካሔድ ላይ ባለው የሥርጭት መርሐ ግብር የቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ክፍል ውስጥ በሚገኙ አገልጋዮችና በየማእከላቱ ተወካዮች አማካይነት በየአኅጉረ ስብከቱ በመንቀሳቀስ በማሰራጨት ላይ ይገኛሉ፡፡

abnet 2006 1በዚህም መሠረት በደቡብ ወሎ ሀገረ ስብከት /ለሐይቅ እስጠፋኖስ አቡነ ኢየሱስ ሞዓ አንድነት ገዳም፤ ለቦሩ ደብረ ብርሃን ሥላሴ፤ ለከሚሴ ደብረ ገነት ቅዱስ ገብርኤል አብያተ ክርስቲያናት/፤ በሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት /ለመርሳ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን፤ ለራማ ደብረ ሲና ኪዳነ ምሕረት አንድነት ገዳም/፤ በሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት /ለደብረ ብርሃን ሥላሴ፤ ለአቡን ቤት ቅዱስ ገብርኤል፤ ለአበራ ቅዱስ ጊዮርጊስ፤ ለመንበረ መንግስት መድኃኔዓለም፤ ለግምጃ ቤት ቅድስት ማርያም አብያተ ክርስቲያናት/ ውስጥ ለሚገኙ የአብነት ትምህርት ተማሪዎች የአልባሳትና የሳሙና ድጋፍ ተደርጎላቸዋል፡፡

በደቡብ ጎንደር /ለመንበረ ልዑል አስቻ ቅዱስ ሚካኤል፤ ለጽርሐ አርያም ዙር አባ አቡነ አረጋዊ ገዳም፤ ለቅድስት ቤተልሔም፤ ለደብረ ልዑላን መድኃኔዓለም፤ ለእስቴ ደብረ ሃይማኖት መካነ ኢየሱስ፤ መሸለሚያ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ፤ አባይ ማዶ ቅዱስ ገብርኤል፤ ለማቢ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ፤ ለቆማ ፋሲለደስ፤ ለእስቴ ቅዱስ ሚካኤል ወቅዱስ ጊዮርጊስ አብያተ ክርስቲያናት/፤ በምዕራብ ጎጃም /ለናዳ ቅድስት ማርያም ገዳም፤ ለብጡላ ኢየሱስ፤ ለቆጋ ቅዱስ ጊዮርጊስ/፤ እንዲሁ ተመሳሳይ ድጋፍ የተደረገላቸው ሲሆን፤ በአራቱ ጉባኤያትና በማስመስከሪያ ትምህርት ቤቶች ከአልባሳትና ከሳሙና በተጨማሪ የጫማ፤ የክብሪት፤ የውኃ አጋርና ልብስ መስፊያ ክሮች አሠራጭቷል፡፡

የአብነት ትምህርት ተማሪዎች የሚያጋጥማቸውን የአልባሳት እጥረት ለመቅረፍ ከምእመናን አልባሳትን “ሁለት ልብሶች ያሉት” በሚል መሪ ቃል በማሰባበስብ እየተሠራጨ በሚገኝበት ወቅት ከየማእከላቱ በተውጣጡ የጤና ባለሙያዎች የአብነት ተማሪዎች እንዴት የአካባቢና የግል ንጽሕናቸውን መጠበቅ እንደሚገባቸው ትምህርት እየተሰጣቸውም ይገኛል፡፡

በ150 አብነት ትምህርት ቤቶች ውስጥ ለሚገኙ 10 ሺህ ተማሪዎች የአልባሳትና የንጽሕና መጠበቂያ ቁሳቁስ ለማሠራጨት ታቅዶ እየተሠራ ሲሆን፤ በዚህ ሥርጭት እስካሁን በ23 አድባራትና ገዳማት ውስጥ ለሚገኙ 4110 /አራት ሺህ አንድ መቶ አሥር/ በላይ ለሚሆኑ የአብነት ትምህርት ተማሪዎች ለማዳረስ ተችሏል፡፡ ሥርጭቱ በየአኅጉረ ስብከቱ የሚገኙ አብነት ትምህርት ቤቶችን ያካተተ በመሆኑ እንቅስቃሴው ቀጥሏል፡፡

የደቡብ ጎንደር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ እንድርያስ በደብረ ልዑላን መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ለአብነት ተማሪዎቹ አልባሳትና የንጽሕና መጠበቂያ ቁሳቁስ ሲሰጥ ተገኝተዋል፡፡ ብፁዕነታቸው ባስተላለፉት መልእክት “ሥጦታው መልካም ነው፤ መሆንም የሚገባው ነው፡፡ ንቃትና ትጋት ከተማሪዎች የሚጠበቅ ሲሆን፤ ጤናቸው ተጠብቆ ውጤታማ ሆነው እንዲወጡ ማስተማርም ያስፈልጋል” ብለዋል፡፡

በሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት በመርሳ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን የቅኔ መምህር የሆኑት መጋቤ ምሥጢር መምህር ፍሬ ስብሐት ምሥጋናው በበኩላቸው “በችግር ምክንያት ትምህርታቸውን ሳይጨርሱ በሚወጡትና ወደ ከተማ ኮብልለው በሚቀሩት ተማሪዎች ባዝንም፤ አንድ ገበሬ አርሶ ፍሬውን ሲሰበስብ እንደሚደሰተው ሁሉ ተማሪዎቼ ለጥሩ ውጤት ሲበቁ ነፍሴ ይደሰታል፡፡ ያሳደገኝም፤ ያስተማረኝም ማኅበረ ቅዱሳን ነው፡፡ እንድማር፤ እዚህ ደረጃ እንድደርስ ድጎማ እያደረገልኝ ለዚህ አብቅቶኛል፡፡ የተዘረጋው ወንበር በችግር ምክንያት እንዳይታጠፍ ማኅበሩ ለተማሪዎች ባደረገው ድጋፍ በጣም ተደስቻለሁ” ብለዋል፡፡

“መምህራኖቻችን በችግር ውስጥ ይገኛሉ፡፡ እኛም ተምረን የእነሱ እጣ እንዳይደርሰን እንሠጋለን፡፡ ችግሩን መቋቋም የተሳናቸው ወደ ከተማ እየኮበለሉ በጥበቃ ወይም በቀን ሠራተኛነት እየተቀጠሩ ነው፡፡ እኛ ግን የልብሳችንና የቀለባችን መሸፈን ተስኖናል፡፡ እኔን እንደ ምሳሌ መውሰድ ይቻላል፤ ያለኝ አንድ የተቀደደ ሱሪና አንድ ሸሚዝ ብቻ ነበር፤ ቅያሪ ስለሌለኝ በመጨነቅ ላይ ሳለሁ በመድረሳችሁ እግዚአብሔር ይስጥልኝ” ሲል በሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት በራማ ደብረ ሲና ኪዳነ ምሕረት abenet 2006 4አንድነት ገዳም ከሚገኙ የቅዳሴ ተማሪዎች አንዱ ይገልጻል፡፡

በቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ዋና ክፍል አስተባባሪነት የመጀመሪያው ዙር “ሁለት ልብሶች ያሉት” በሚል መሪ ቃል የአልባሳት ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር በ2003 ዓ.ም. በማካሔድ ለበርካታ አብነት ትምህርት ተማሪዎች ማዳረስ መቻሉ ይታወሳል፡፡

ይህ መርሐ ግብር ወደፊትም እንደሚቀጥል ከዋና ክፍሉ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡