ለቅዱሳን ፓትርያርኮችና ለብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት መታሰቢያ ጸሎተ ፍትሐት ተደረገ

ጥቅምት 8 ቀን 2006 ዓ.ም. 

በእንዳለ ደምስስ

 

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ሲመሩ ለነበሩና ከዚህ ዓለም በሞት ለተለዩ ቅዱሳን ፓትርያርኮችና ሊቃነ ጳጳሳት በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ጥቅምት 10 ቀን 2006 ዓ.ም. የመታሰቢያ ጸሎተ ፍትሐትና ቅዳሴ ተካሔደ፡፡

በጸሎተ ፍትሐትና ቅደሴ ሥነ ሥርዓት ላይ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፤ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፤ የ32ኛው የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ተሳታፊዎች በመርሐ ግብሩ ላይ ተገኝተዋል፡፡

ጸሎተ ፍትሐቱ በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም ካህናት የተመራ ሲሆን ቅዱስነታቸው ባስተላለፉት ቃለምእዳን “ይህ ታላቅ በዓል ነው፡፡ ቅዱሳን ፓትርያርኮቻችንና ብፁዓን አባቶቻችንን ልንዘክር ይገባል” በማለት የተናገሩ ሲሆን ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩትን የአራቱን ቅዱሳን ፓትርያርኮችና የብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ስም በመጥራት ታስበዋል፡፡

በእለቱ ምሽትም ማኅበረ ቅዱሳን በየዓመቱ የሚያዘጋጀውን የቅዱሳን ፓትርያርኮችና ሊቃነ ጳጳሳት መታሰቢያ /ዝክረ አበው/ በጠቅላይ ቤተ ክህነት ስብከተ ወንጌል አዳራሽ የእራት መርሐ ግብር ተካሒዷል፡፡ በመርሐ ግብሩ ላይም ቅዱስ ፓትርያርኩን ጨምሮ ሊቃነ ጳጳሳትና የ32ኛው መንፈሳዊ ጉባኤ ተሳታፊዎች ተገኝተዋል፡፡

ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ የሰሜን ወሎና የዋግ ሕምራ አኅጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ባስተላለፉት መልእክት “የሃይማኖት ጉዳይ በመምሰል ሳይሆን በመሆን ነው የሚገለጸው፡፡ መከራውን የምትጋፈጡት የሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጆች፤ ወረዳ ሥራ አስኪያጆችና በየአጥቢያው ያላችሁት ናችሁ፡፡ ነገር ግን የስብከተ ወንጌል ጉዳይ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ ስብከተ ወንጌል በቄሱ፣ በሰባኪያኑና በዲያቆናቱ መሰበክ አለበት፡፡ ቤተ ክርስቲያን ራሷን ቻለች የምንለው ቄሱም፣ ሰባኪውም ሆነ ዲያቆናቱም መስበክ ሲችሉ ነው” ብለዋል፡፡

በመጨረሻም ብፁዕ አቡነ ናትናኤል በሰጡት ቃለምዕዳን “ማኅበረ ቅዱሳን በቅዱስ ሲኖዶስ ፈቃድ የተመሠረተ የቤተ ክርስቲያን አርበኛ ነው፡፡ በርቱ” በማለት ማኅበሩ በአገልግሎት እንዲበረታ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
በተያያዘ ዜና ጥቅምት 9 ቀን 2006 ዓ.ም. ምሽት የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ ለ32ኛው አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ተሳታፊዎች ባዘጋጀው የእራት መርሐ ግብር ጉባኤውን ለማካሔድ ድጋፍ ላደረጉ አካላት የምሥክር ወረቀት ሰጠ፡፡

የማኅበረ ቅዱሳን ዋናው ማእከልም የተዘጋጀለትን የምሥክር ወረቀት ከቅዱስ ፓትርያርኩ እጅ ተቀብሏል፡፡
የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያው ለብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ያዘጋጀውን የመስቀል ሥጦታ የማኅበረ ቅዱሳን ልማት ተቋማት አስተዳደር ጽ/ቤት 24 ሺህ ብር የሸፈነ ሲሆን ቀሪውን /ግማሹን/ ደግሞ በመምሪያው ወጪ መደረጉን የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ ሓላፊ ሊቀ ማእምራን ፋንታሁን ሙጬ ለጉባኤው ገልጸዋል፡፡ ለጉባኤው መሳካትም ትብብር ላደረጉ አካላት ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

ለሊቀ ማእምራን ፋንታሁን ሙጬ ለጉባኤው መሳካት ላደረጉት ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ መምሪያ ሠራተኞችና የስብከተ ወንጌል መምሪያ ሥጦታ አበርክተውላቸዋል፡፡