የ፳፻፱ ዓ.ም በዓለ ትንሣኤን አስመልክቶ ከብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ የተበረከተ ቃለ ምዕዳን

img_0028

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ

ሚያዝያ ፯ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

ቃለ በረከት ዘብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ዘተናገረ በእንተ በዓለ ትንሣኤ ቅድስት ዘእግዚእነ ወአምላክነ ወመድኃኒነ ኢየሱስ ክርስቶስ ሎቱ ስብሐት

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን

  • በአገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፤
  • ከአገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትገኙ፤
  • የአገራችንን ዳር ድንበር ለመጠበቅና ለማስከበር በየጠረፉ የቆማችሁ፤
  • በሕመም ምክንያት በየጠበሉና በየሆስፒታሉ ያላችሁ፤
  • እንዲሁም የሕግ ታራሚዎች ኾናችሁ በየማረሚያ ቤቱ የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት፤

በትንሣኤው ኃይል በመቃብር ውስጥ በስብሶ መቅረትን ሽሮ ትንሣኤ ሙታንን ያበሠረ ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳን ለሁለት ሺሕ ዘጠኝ ዓመተ ምሕረት በዓለ ትንሣኤው በሰላም አደረሳችሁ!!

‹‹ወሰበረ ኆኃተ ብርት ወቀጥቀጠ መናሥግተ ዘሐፂን፤ የናስ ደጆችን ሰባበረ፡፡ የብረት መወርወሪያዎችንም ቀጥቅጦ ቈራረጠ፤›› (መዝ. ፻፯፥፲፮)፡፡

ይህ አምላካዊ ኃይለ ቃል ወልደ እግዚአብሔር የኾነ ኢየሱስ ክርስቶስ በመሥዋዕትነቱ ብቃት እንደ ናስ የጠነከሩትን የኃጢአት ደጆች እንደሚሰባብር፤ እንደ ብረት የጸኑትን የሞት ብረቶች ቀጥቅጦ በመቈራረጥ እንሚያስወግድ መንፈስ ቅዱስ በዳዊት አንደበት የተናገረው ቃለ ብሥራት ነው፡፡ የኃይለ ቃሉ ምሥጢራዊ ይዘት በጠንካራ ነገር የተገዙና በጽኑ መወርወሪያዎች ክርችም ብለው የተዘጉ ደጆች መኖራቸውን ጠቁሞ እነዚህን ሰባብሮና ቀጥቅጦ በሩን የሚከፍት አንድ ኃያል መሢሕ እንደሚመጣ የሚያመለክት ነው፡፡

በመጀመሪያው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል እንደምናነበው የሰው መኖሪያ የነበረው ገነተ ኤዶም በኃጢአተ ሰብእ ምክንያት በፍትሐ እግዚአብሔር ሲዘጋ፣ በሰይፈ ነበልባል እንደ ተከረቸመ፤ ኪሩባውያን ኃይላትም በጥበቃ እንደ ተመደቡበት በግልጽ ተመዝግቦአል፡፡ ይህ የጽድቅ የክብርና የሕይወት ደጅ በዚህ ኹኔታ ሲዘጋ፣ ለሰው ልጅ የቀረለት መኖሪያ ለሰይጣንና ለሠራዊቱ የተዘጋጀው፤ እሳቱ የማይጠፋ፣ ትሉ የማያንቀላፋ የእቶነ እሳት ከተማ ነበረ፡፡

ለመለኮታዊ ሱታፌና ለዘለዓለማዊ ሕይወት ታድሎ የነበረው የሰው ልጅ ለእግዚአብሔር ባለመታዘዙ ምክንያት ለአምስት ሺሕ አምስት መቶ ዓመታት ያህል የተጋዘው ከላይ በተጠቀሰው የዲያብሎስ ከተማ ነበር፡፡ የዚህ ከተማ ደጆችና በሮች፣ መዝጊያዎችና መወርወሪያዎች ኃጢአት፣ ፍትሐ ኵነኔ እና ሞተ ነፍስ ወሥጋ ነበሩ፡፡ የሰው ልጅ ኃጢአትን ስለ ሠራ እግዚአብሔር የቅጣት ፍርድን ፈረደበት፤ ቅጣቱም የነፍስና የሥጋ ሞት ነበረ፡፡ እነዚህ ነገሮች እርስበርስ እንደ ሰንሰለት ተያይዘው የዲያብሎስን ከተማ የናስና የብረት ያህል ጠንካራ ደጅ እንዲኾን አድርገውታል፡፡

ይህንን በር ሰብሮና ፈልቅቆ የሰዎችን ነፍሳት ከዲያብሎስ ከተማ መዞ ለማውጣት ለፍጡር ፈጽሞ የማይቻል ነበረ፤ ሦስቱም ነገሮች ከፍጡራን ዓቅም በላይ በመኾናቸው አምላካዊ ኃይል የግድ አስፈላጊ ኾነ፡፡ በዚህም ምክንያት ጌታችን ሥጋችንን ተዋሕዶ በዚህ ዓለም በመገለጥ እኛ ከኃጢአት፣ ከፍትሐ ኵነኔ እና ከሞት ነፍስ የምንድንበት መንገድ እርሱ ብቻ መኾኑን በአጽንዖት አስተማረ፡፡

በመጨረሻም እንደ ትምህርቱና እንደ ቃሉ በመስቀሉ ኃይል ወይም በመሥዋዕትነቱ  ብቃት ሦስቱ ነገሮች ማለትም ኃጢአት ፍትሐ ኵነኔ እና ሞተ ነፍስ ከሰው ጫንቃ ላይ እንዲወገዱ አደረገ፡፡ ለሰው የማይቻል የነበረ ይህ ግብረ አድኅኖ፣ በተዋሕዶ አምላክም ሰውም ለኾነ ለጌታችን ለአምላካችንና ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ የሚቻል ነበርና በእርሱ መሥዋዕትነት እውን ኾነ፡፡

ጥንቱንም ለሰው ልጅ ሕይወትና ክብር ጠንቆች የነበሩ እነዚህ ሦስቱ ነበሩና እነርሱ ተሰባብረውና ተቀጥቅጠው ሲወገዱ በሲኦል ይኖሩ የነበሩ ሰዎች ነፍሳት በአጠቃላይ ዓለም ከመፈጠሩ በፊት ወደ ተዘጋጀላቸው ወደ መንግሥተ እግዚአብሔር ተመልሰው ገቡ፡፡ ከክርስቶስ ሞት በኋላ የነፍሳተ ሰብእ ጉዞ ወደ ዲያብሎስ ከተማ ወደ ሲኦል መኾኑ ቀርቶ ወደ እግዚአብሔር ከተማ ወደ ጽዮን መንግሥተ ሰማያት ኾነ፡፡

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት

እኛ ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች በዓለ ትንሣኤን ከምንም በላይ በላቀ ኹኔታ የምናከብርበት ምክንያት ኃጢአት፣ ፍትሐ ኵነኔ እና ሞተ ነፍስ ወዲያ ተሽቀንጥረው በምትካቸው በክርስቶስ ቤዛነት ጽድቅን፣ ይቅርታንና ሕይወተ ነፍስን የተቀዳጀንበትና ከድል ዅሉ የበለጠ የድል ቀን በመኾኑ ነው፡፡ ዅላችንም መገንዘብ ያለብን ዓቢይ ነገር የክርስቶስ ድርጊቶች በሙሉ ለሰው ድኅነት ሲባል ብቻ የተደረጉ እንጂ ለእግዚአብሔር የሚፈይዱት አንዳች ምክንያት የሌላቸው መኾኑን ነው፤ ይህም ማለት በክርስቶስ የተፈጸሙ ድርጊቶች በሙሉ ለእኛ ሲባል የተደረጉ መኾናቸውን መገንዘብ አለብን ማለት ነው፡፡

ክርስቶስ ተሰቀለ፤ ሞተ፤ ተቀበረ፤ ተነሣ ሲባል፣ እኛ ተሰቀልን፤ ሞትን፤ ተቀበርን፤ ተነሣን ማለት እንደ ኾነ ልብ ብለን ልናስተውል ይገባል፡፡ እኛ ተሰቅለን ሞተንና ተቀብረን የኃጢአታችንን ዕዳ የመክፈል ዓቅም ስላጣን ለእኛ ያልተቻለውን ጌታችን ስለ እኛ ብሎ፣ በእኛ ምትክ ኾኖ ለኃጢአታችን መከፈል የነበረበትን ዋጋ ዅሉ ከፍሎ አድኖናልና ነው፡፡ እኛ በክርስቶስ ቤዛነት ነጻነታችንን ተቀዳጅተን ወደ እግዚአብሔ መንግሥት ዳግመኛ መግባት የቻልነው ክርስቶስ የከፈለው መሥዋዕትነት ለእኛ ተብሎ፣ ስለ እኛ የተደረገ በመኾኑ ነው፡፡

የክርስቶስ ትንሣኤ የእርሱ ትንሣኤ ብቻ እንደ ኾነ አድርገን የምንገነዘብ ከኾነ ታላቅ ስሕተትም ነው፤ ኃጢአት፣ ኵነኔ እና ሞተ ነፍስ የሌለበት እርሱማ ምን ትንሣኤ ያስፈልገዋል? ትንሣኤ ለሚያስፈልገን ለእኛ ተነሣልን እንጂ፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ይህንን አስመልክቶ ሲያስተምር፣ ‹‹እግዚአብሔር በምሕረቱ ባለ ጸጋ ስለ ኾነ በኢየሱስ ክርስቶስ አስነሣን፡፡ ከእርሱ ጋርም በሰማያዊ ሥፍራ አስቀመጠን፤›› ብሎአል (ኤፌ. ፪፥፬-፯)፡፡ ከዚህ አኳያ የቀን ጉዳይ ካልኾነ በቀር የትንሣኤያችን ጉዳይ በክርስቶስ ትንሣኤ የተረጋገጠና ያለቀለት ነገር እንደ ኾነ ማስተዋል፣ መገንዘብ፣ መረዳትና ማመን ይገባናል፡፡

የጌታችን ትንሣኤ ለሰው ልጅ ተብሎ የተደረገ በመኾኑ የእኛ ትንሣኤ ነው ብለን ዅሌም መውሰድና መቀበል አለብን፤ ምክንያቱም የክርስቶስ ትንሣኤ የመጨረሻ ግቡ የሰው ልጆች ትንሣኤን ማረጋገጥ ነውና፡፡ የትንሣኤ ዕድል በክርስቶስ ቤዛነት ለዅሉም ተሰጥቶአል፤ አዋጁም ሕጉም በክርስቶስ ትንሣኤ ጸድቆአል፡፡ የቀረ ነገር ቢኖር የመጨረሻው ተግባራዊ ፍጻሜ ነው፤ እርሱም ቀነ ቀጠሮ የተያዘለት ስለ ኾነ ወደዚያው በእምነትና በሥነ ምግባር መገስገስ ነው፡፡ ሰውን ለዚህ ዐቢይ ጸጋና ዕድል ላበቃ ለእግዚአብሔር አምላካችን ክብርና ምስጋና ለእርሱ ይኹን፡፡

      የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት

ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሠራውና ያስተማረው ዅሉ ምን ለማግኘት ነበረ? ተብሎ ቢጠየቅ በአጭር ዐረፍተ ነገር ‹‹ሰውን ለማዳን ነዋ!›› ብሎ መመለስ ይቻላል፡፡ እውነቱም ሐቁም ይህና ይህ ብቻ ነው፡፡ ይህን ያህል ውጣ ውረድ፣ ይህን ያህል ዋጋ ያስከፈለ የሰው መዳን በእግዚአብሔር ዘንድ ምን ያህል ተፈላጊ እንደ ኾነ በአድናቆት መመልከትና መቀበል ታላቅ አስተዋይነት ነው፡፡

በዚህ ሰውን የማዳን የእግዚአብሔር ክንውን እኛ ሰዎች የእግዚአብሔር ልጆች ለመኾን በቅተናል፤ ልጆቹም ኾነናል፡፡ ታድያ ልጅ በጠባይም፣ በመልክም፣ በሥራም አባቱን ቢመስል ጌጥም የክብር ክብርም ነውና በዅሉም ነገር አባታችንን መከተልና መምሰል ከእኛ ይጠበቃል፡፡ እግዚአብሔር አባታችን እንደ መኾኑ፣ እኛም ልጆቹ እንደ መኾናችን መጠን የአባታችንን ተቀዳሚ፣ መደበኛና ቀዋሚ ሥራ የኾነውን ሰውን የማዳን ሥራ ሳናቋርጥ የማስቀጠል ግዴታ አለብን፡፡

ዛሬም ዓለማችን የሚያድናት፣ እስከ ሞት ድረስም ደርሶ ቤዛ የሚኾናት፣ ሰላምንና ነጻነትን የሚያቀዳጃት የእግዚአብሔርን ልጅ ትፈልጋለች፡፡ የጌታችን ትንሣኤ ከመቃብር በመነሣትና ሙታንን በማስነሣት ብቻ የሚገለጽ አይደለም፡፡ ጌታችን ከመሞቱና ከመነሣቱ በፊት ብዙ ሰዎችን ከረኃብ፣ ከበሽታ፣ ከሥነ ልቡና እና ውድቀት አስነሥቷል፤ ከተሳሳተ አመለካከት፣ ከጭካኔ ከመለያየት አባዜም በተአምራትም በትምህርትም አድኗል፡፡ ጌታችን ሰውን ለማዳን ሥራ በእርሱ ብቻ ተሠርቶ እንዲቀር አላደረገም፤ እኛም እንድንሠራውና እንድንፈጽመው አዘዘን እንጂ፡፡

ከዚህ አንጻር በክርስቶስ ዘመን እንደ ነበረው ዅሉ ዛሬም ብዙ በሽተኞች የሚያድናቸው አጥተው በየጎዳናው፣ በየሰፈሩ፣ በየመንገዱ ወድቀው ይሰቃያሉ፤ እነዚህን ማን ያድናቸው? የተመጣጠነና በቂ ምግብ አጥተው ብዙ ሕፃናት፣ እናቶችና አረጋውያን በረኃብ አለንጋ ይገረፋሉ፤ ኅብስቱን አበርክቶ እነሱን ማን ይመግባቸው? በተሳሳተ አመለካከት ለሥነ ልቡና ውድቀት፣ ለቀቢፀ ተስፋ እንደዚሁም ለስሑት ትምህርተ ሃይማኖት ተጋልጠው ሃይማኖታቸውንና ታሪካቸውን በመፃረር የሚገኙ ብዙ ናቸው፤ እነዚህን ማን አስተምሮ ወደ እውነቱ ይመልሳቸው? በእግዚአብሔር ዘንድ እነዚህን ሥራዎች መሥራትና ማስተካከል የሕዝበ ክርስቲያኑና የመምህራነ ወንጌል ግዴታዎች ናቸው፡፡

በማኅበረሰቡ ሥር ሰደውና ተስፋፍተው የሚታዩትን እነዚህን መሰል ሃይማኖታዊና ማኅበራዊ ችግሮች በወሳኝነት ለመቋቋም ትምህርትና ልማት መተኪያ የሌለውን ሚና ይጫወታሉ፤ ለአገራችን ደህንነት መወገድ ቍልፍ መፍትሔ ሃይማኖትና ልማትን አጣምሮ ለመያዝና በእነርሱ ጸንቶ መኖር አማራጭ የሌለው ነው፡፡ ከእነዚህ ውጭ የኾነ ኑሮ ምንም ቢኾን ምሉእ አይደለም፤ ጣዕምም የለውም፡፡ የሰውን ዅለንተናዊ ሕይወት ለማዳን ሁለቱንም በተግባር መተርጐም ያስፈልጋል፡፡

አገራችን ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ በእነዚህ ነገሮች የታደለች እንደ ነበረችና እነዚህን አጣምራ በመያዝ የት ደርሳ እንደ ነበር በአገሪቱ ውስጥ ያሉ የሚታዩና የማይታዩ መረጃዎች ምስክርነታቸውን በመስጠት ዛሬም አልተገቱም፡፡ በአሁኑ ጊዜ አገራችን የተያያዘችውን የልማትና የሰላም ጉዞ አጠናክራ እስከ ቀጠለች ድረስ ሕሙማን የሚፈወሱባት፣ ሩኁባን ጠግበው የሚኖሩባት፣ በመንፈሳዊና በዘመናዊ ዕውቀት የበለጸጉ ዜጎች የሚታዩባት አገር የማትኾንበት ምክንያት ምንም የለም፡፡

መላው የአገራችን ሕዝቦች በኑሮአቸውና በሕይወታቸው መሠረታዊ ለውጥ ማምጣት የሚችሉት በሌላ ሳይኾን፣ እነርሱ ራሳቸው እንደ ቀድሞ አባቶቻቸው በራስ በመተማመንና በልበ ሙሉነት፣ በትጋትና በቅንነት፣ በፍቅርና በስምምነት፣ በእኩልነትና በወንድማማችነት፣ በሰላምና በአንድነት፣ በመቻቻልና በአብሮነት ኾነው በሚያስመዘግቡት የልማት ውጤት እንደ ኾነ መርሳት የለባቸውም፡፡ አገርን ለማልማትና የጠላትን ጥቃት በብቃት ለመመከት በአንድነት ኾኖ ከመታገል የተሻለ አማራጭ የለም፤ ስለዚህ ሕዝባችን እነዚህን እስከ መቼውም ቢኾን በንቃት ሊከታተላቸውና ሊጠብቃቸው ይገባል፡፡ በአእምሮ የላቁ ኾኖ መገኘት በራሱ እውነተኛ ትንሣኤ ነውና፡፡

በመጨረሻም

የጌታችን ትንሣኤ ሰውን የማዳን የእግዚአብሔር ዓላማን ያሳካ ፍጻሜ እንደ ኾነ ዅሉ የትንሣኤ ልጆች የኾንን እኛም ሰውን ለማዳን በሚደረገው መንፈሳዊና ልማታዊ ርብርቦሽ ተሳትፏችንን አጠናክረን እንድንቀጥል መንፈሳዊና አባታዊ መልእክታችንን በእግዚአብሔር ስም እናስተላልፋለን፡፡

መልካም በዓለ ትንሣኤ ያድርግልን፡፡

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ዘሕዝቦቿን ይባርክ፤ ይቀድስ፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፤ አሜን፡፡

አባ ማትያስ ቀዳማዊ

ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ

ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት

ሚያዚያ ፰ ቀን ፳፻ወ፱ ዓ.ም

አዲስ አበባ ኢትዮጵያ