«እርሳቸው የያዙት መንገድ ሙሉ በሙሉ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን ማዳከም ነው፡፡ » ማኅበረ ቅዱሳን

 ግንቦት 9/2003ዓ.ም
ማኅበረ ቅዱሳን ተመሥርቶ በሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ሥር አገልግሎት ከጀመረ አንስቶ ወደ 10 የሚጠጉ የመምሪያ ኃላፊዎች ተፈራርቅዋል፡፡ እስከ አሁን ምንም ያልተባለለት የማኅበሩና ማደራጃ መምሪያው ግንኙነት፣ የአሁኑ የመምሪያው ኃላፊ አባ ሠረቀብርሃን ከመጡ ከ6 ዓመት በፊት ጀምሮ፣ ችግሮች እየገጠሙት እንደሆነ ይነገራል፡፡ ማኅበሩም አሁን ያሉት የመምሪያው ኃላፊ አላሠራኝ አሉ በማለት ይወቅሳል፡፡ ይህንን በተመለከተ ከማኅበሩ ዋና ጸሐፊ ዲ/ን ሙሉጌታ ኃ/ማርያም ጋር ቆይታ አድርገናል፡፡ መልካም ንባብ፡፡
 
    ቅዱስ ሲኖዶስ ባጸደቀውና በተሻሻለው መተዳደሪያ ደንብ መሠረት የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያና የማኅበረ ቅዱሳን ግንኙነት ምን መምሰል አለበት?

የማኅበሩ መተዳደሪያ ደንብ በ1994 ዓ.ም በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ በጸደቀው መሠረት ማኅበሩና ማደራጃ መምሪያው የሚያከናውኗቸው ተግባራት በግልጽ ተቀምጠዋል፡፡ የማኅበሩ ተግባርና ኃላፊነት፥ ማኅበሩ ለማደራጃ መምሪያው ማድረግ የሚገባው ነገር፥ ምን መሥራት እንዳለበት በግልጽ ተቀምጠዋል። በተለይ ማኅበሩ የበላይ ተጠሪው ማደራጃ መምሪያው እንደመሆኑ የሚሠራቸውን ዕቅዶች የማሳወቅ፣ ዕቅዶችንም ካሳወቀና በጠቅላላ ጉባኤው ላይ እንዲገኘ አድርጎ አስተያየት እንዲሰጥ ካደረገ በኋላ አስተካክሎ ያንን ማቅረብና ወደ ሥራ መግባት፥ ወደ ሥራ ከገባ በኋላ በየ6 ወሩ የአፈጻጸም ሪፓርት ማቅረብ የሚሉ ነገሮች ናቸው የተካተቱት፥ ይህ እንግዲህ የመጀመሪያውና ትልቁ ነገር ነው፡፡

ከዚያ ሪፖርት ተነሥቶ ማደራጃ መምሪያው በሚሰጠው ግብረ መልስ /Feed back/ እና መመሪያ መሠረት እየተነጋገረ ወደ ማስተካከያ ተግባሩ ይሄዳል ማለት ነው፡፡
 
የአንድ ተቋም ተጠሪነት ሲባልም ከዚያ ያለፈ አይደለም፡፡ ሙሉ በሙሉ እቅድ ላይ የሚሳተፍ፥ የተሠራውን ሥራም የማቅረብ ነው፡፡

ከዚያም ውጭ በአብዛኛው የማደራጃ መምሪያው በማኅበሩ አገልግሎት ላይ ድጋፍ የማድረግ ነገር ነው ያሉት፥ ለምሳሌ ማኅበሩ ከጠቅላይ ቤተ ክህነትና ከሌሎች ሦስተኛ አካላት ጋር የሚያደርገው ግንኙነት ችግር ቢገጥመው በማደራጃ መምሪያው ከዚያም አልፎ በጠቅ/ቤ/ክ አማካኝነት እነዚያ ግንኙነቶች እንዲስተካከሉና እንዲሰምሩ ይደረጋል፡፡

ማኅበሩ የባንክ አካውንት ሲከፍት በራሱ ስም ነው። የማኅበሩ ሕጋዊ ሰውነት ደግሞ በቤተ ክርስቲያኑ ነው፡፡ ይሄን አካውንት ደግሞ ቀጥታ ወደ ባንክ ቤት በመሄድ ራሱ አይከፍትም ። ማደራጃ መምሪያው ቢጽፍለትም እንኳን አይከፍትም፡፡ ስለዚህ ማኅበሩ ለማደራጃ መምሪያው ደብዳቤ ይጽፋል፡፡ እነዚህ… እነዚህ አካውንቶች ይከፈቱልኝ በማለትም ይጠይቃል፡፡ ከዚያም ማደራጃ መምሪያው ለጠቅላይ ቤተ ክህነት ይጽፋል፡፡ በዚያ መሠረት ይከናወናል፡፡ እንደገናም ማኅበሩ ከመንግሥት አካላት ሆነ መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማትም ግንኙነት ፈልጎ ችግር ቢገጥመው ወይም ሕጋዊ ሰውነቱ ላይ ጥያቄ ቢኖራቸው፣ ይሄ የሚፈታው በቤተ ክርስቲያን በኩል ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ደግሞ ይሄን ለማሳለጥ የመደበችው ማደራጃ መምሪያው ነው፡፡

ስለዚህ በሚሠሩት ሥራዎች በሙሉ እየተገኘ መመሪያዎችን የመስጠት፣ የማሳለጥ /facilitation/ ሥራዎችን የመሥራት፣ ሀገረ ስብከቶችና ጠቅላይ ቤተ ክህነት አስፈላጊው ትብብር እንዲያደርግ ኃላፊነት የተሰጠው ለማደራጃ መምሪያው ነው፡፡

በዚህ ዓይነት ግንኙነት ማደራጃ መምሪያው ለማኅበሩ የሚሠራው አለ፡፡ ማኅበሩ ለማደራጃ መምሪያው የአገልግሎት ማኅበር ስለሆነ ሪፖርት ነው የሚያቀርብለት፡፡ ሌላ ምንም ሊያደርግለት አይችልም፡፡

ስለሆነም ግንኙነታቸው እንዲህ በግልጽ የተቀመጠ ነው። በማንኛውም ተቋም የበላይና የበታች እንዴት እንደሚሠራ እንደተቀመጠው የተቀመጠ ነው፡፡

•    በመተዳደሪያ ደንቡ አንቀጽ 9 ቁጥር 1 መሠረት ማደራጃ መምሪያው ማኅበረ ቅዱሳን የሚያበረክተውን አገልግሎት በቅርብ ይከታተላል፣ ይቆጣጠራል፣ ተገቢውን መመሪያ ይሰጣል ይላል። ይህን እንዴት ነው ማኅበሩ የሚተረጉመው?

ማኅበሩ በዕቅድ የሚመራ ማኅበር ነው፡፡ ዕቅድ አለው በዚያ መሠረት ሥራውን ይሠራል፡፡ ማኅበሩ ጠቅላላ ጉባኤ ሲያደርግ የማደራጃ መምሪያው ኃላፊ በተገኙበት እያንዳንዱ አንቀጽ፥ እያንዳንዱ በጀት እያንዳንዱ ዕቅድ እያንዳንዱ አካሄድ ይታያል፤ ይገመገማል፡፡ የመጨረሻውን ዕቅዱን ዶክመንት ለማጽደቅ እንኳን ሦስት ቀን ይፈጃል፡፡ በዚያን ጊዜ ተገኝተው በእያንዳንዱ ጉዳይ ላይ መመሪያ ይሰጣሉ ማለት ነው፡፡ በነገራችን ላይ ከአባ ሠረቀ በፊት የነበሩ መምሪያ ኃላፊዎች በሙሉ በጠቅላላ ጉባኤ እየተገኙ መመሪያ ይሰጡ ነበር፤ ይከታተሉ ነበር፤ ምን እንደተወሰነ ያውቃሉ፡፡ ከዚያ በኋላ ደግሞ በተወሰነው መሠረት የ6 ወር ሪፖርት ሲቀርብላቸው ይሄ ለምን ተሠራ? ይሄ ለምን አልተሠራም? ይሄ ለምን ቀረ? ብለው ያያሉ በማኅበሩ ጽህፈት ቤት እየተገኙ የማኅበሩን የጽህፈት ቤት አሠራር ይጎበኛሉ፤ ይመለከታሉ። እርሳቸው ግን በ6 ዓመት ውስጥ ጽህፈት ቤቱን እንኳን አይተውት አያውቁም፡፡ እንዲመጡ ቢጋበዙም እኔ አውቃለሁ በማለት ነው እዛው ቁጭ የሚሉት፡፡ ይሄንን የመምሪያው ምክትል ኃላፊም የማኅበሩን ጽህፈት ቤት ጎብኝቶ ምንድን ነው የሚሠራው? እንዴት ነው የሚሠራው? ምን አገልግሎት ነው ያለው? ምን ድካም ነው ያለው? የሚሉትን ነገሮች አይቶ አያውቅም፡፡ እነዚህን ሰዎች በግድ ጎትቶ ማምጣት አይቻልም፡፡ ይሄ የእነርሱ ኃላፊነት ነው። በቅርብ ለመገኘት ይከታተላል ይቆጣጠራል ማለት በዕቅዱ በሪፓርቱ ብቻም አይደለም፡፡ በአካልም የመስክ ጉብኝቶችን በማድረግ እየተገኘ ማስተማር መመሪያ መስጠት የእነርሱ ኃላፊነት ነው። ይሄንን ከዚያ በፊት የመምሪያ ኃላፊ የነበሩት እነ ሊቀ ካህናት ኃይለ ሥላሴ አዲስ አበባ ብቻ አይደለም፤ ከማዕከላት ጋር ይወያዩ ነበር፡፡ በግቢ ጉባኤያት ተገኝተው ያስተምሩ፣ ይመክሩ፣ በርቱ ይሉ ነበር፡፡ እነዚህ ሰዎች ግን የት ቦታ ማኅበረ ቅዱሳን እንዳለ፥ ምን እንደሚሠራ አያውቁም፡፡ 

አሁንም ለቅዱስ ሲኖዶስ በቅርቡ የምናቀርበው ጥያቄ ኃላፊነታቸውን ያልተወጡ ሰዎች ስለሆኑ ውሳኔ ይሰጥልን ይሆናል፡፡ ይሄንን ጥያቄ አሁንም ከ 6 ዓመት በኋላ በድጋሜ እናቀርባለን፡፡ የማደናቀፍ ሥራ ብቻ ነው እየሠሩ ያሉት እንጂ አልተቆጣጠሩም፣ አልመሩም አልተከታተሉምና ሊመራ የሚችል አካል ለእኛ ብቻ አይደለም፥ በኢትዮጵያ ለሚገኙ ለመላው ሰንበት ትምህርት ቤት ያስፈልጋል፤ የሚል ጥያቄ ለማቅረብ በዝግጅት ላይ ነው፡፡

•    ማኅበረ ቅዱሳን አሁን ያሉት የመምሪያው ኃላፊ አላሠራኝ አሉ በማለት ይወቅሳል።  እንዴት ነው አላሠራ ያሉት? ከዚያ በፊት ከነበሩት የማደራጃ መምሪያ ኃላፊዎች ጋር የነበረው ግንኙነት ምን ይመሥል ነበር?

በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ካሉት መምሪያዎች አንዱ የሰንበት ትምህርት ቤት ማደራጃ መምሪያ ነው። በ1956ዎቹና 1960ዎቹ የሰንበት ትምህርት ቤት ማደራጃ መምሪያ ሲቋቁምና ሲዋቀር፥ በተለይ በ1960ዎቹ ወደ ተግባር ሲመጣ፥ የተሰጠው ኃላፊነት ሕፃናትንና ወጣቶችን እንዲያስተምር ነው፡፡ በዚህ የማስተባበርና የማደራጀት ሥራ እንዲሠራም ነው፡፡ በእያንዳንዱ አጥቢያ ላይ ሰንበት ትምህርት ቤትና የወጣቶች ክፍል እንዲኖር የማስቻል ሥራ ነው የሚሠራው፡፡ በዚህ መሠረት ሲሠራ ቆይቶ፣ ከዩኒቨርሲቲ የተመረቁ በዩኒቨርሲቲ የተማሩ ወጣቶችን ይዞ ሲመጣ፥ የት ቦታ ነው መግባት ያለበት የሚለውን በማሰብ፥ ማኅበሩ ራሱ ነው በማደራጃ መምሪያው ስር ብደራጅና ቁጥጥር ቢደረግብኝ ይሻላል በማለት የሄደው፡፡ ስለዚህ በወቅቱ የነበሩትን የማደራጃ መምሪያ ኃላፊዎች ማኅበሩ አነጋገረ፣ እነርሱም ፈቃደኞች ሆኑ። በዚህ ምክንያት ማኅበረ ቅዱሳን በሰንበት ትምህርት ቤት ማደራጃ መምሪያ እውቅና ተሰጥቶት ግንቦት 2 ቀን በ1984 ዓ.ም ይፋ ሆነ። ስለዚህ ተጠሪው /አለቃው/ ማደራጃ መምሪያው ሆነ ማለት ነው፡፡ በጊዜው የነበሩት ኃላፊዎች አንድ ዓመትም አልሠሩ ከኃላፊነት ተነሱ፡፡ ቀጥለው ከነበሩት ኃላፊዎች ጋር በመግባባት መንፈስ ሥራዎችን ቀጠለ፡፡ እንዲህ እያለ ማኅበረ ቅዱሳን እስከ 1998 ዓ.ም ወደ 10 የሚሆኑ የመምሪያ ኃላፊዎች ሲፈራረቁ ቆይተዋል፡፡ ከሁሉም የማደራጃ መምሪያ ኃላፊዎች ጋር በመግባባት በትብብር ነው የሠራው። ስህተቶች ሲኖሩ የሚያርሙ መመሪያዎች ሲያስፈልጉ መመሪያ የሚሰጡ፣ የሥራ ትብብሮች ሲኖሩ የሚተባበሩ ለአገልግሎት ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ በመሯሯጥ የሚሠሩና የምናስታውሳቸው የመምሪያ ኃላፊዎች ተሹመዋል፡፡ እግዚአብሔር ይመስገን በምንኩስናው የነበሩት ብዙዎቹ ወደ ጵጵስና ማዕረግ ደርሰዋል፡፡ ከእነዚህ ሁሉ ማኅበሩ እንደ አባትና ልጅ እንደ አለቃና ታዛዥ በመሆን ነው ሲሠራ የነበረው፡፡

አባ ሠረቀ ብርሃን የዛሬ 6 ዓመት ነው ወደ ማደራጃ መምሪያ በኃላፊነት የመጡት፡፡ ወደ ቦታው ከመጡበት ከመጀመሪያው ቀን ጀምሮ፤ እኔ የማኅበረ ቅዱሳንን ሰነዶች አይቻለሁ እስከ ዛሬ የሚሠራው ሥራ ልክ አይደለም፡፡ ኃላፊዎችም ልክ አልሠሩም በማለት ነው የጀመሩት፡፡ የመጀመሪያው አስተያየታቸውም እስከ አሁን የነበሩት የመምሪያ ኃላፊዎች ማኅበረ ቅዱሳንን በትክክል አልመሩትም፡፡ ኃላፊነታቸውንም አልተወጡም ከእንግዲህ በኋላ እኔ ነኝ የምወጣው ብለው ነው የጀመሩት፡፡

በዚህም የተነሣ ልክ እንደተቀመጡ የማኅበሩን አባላት ዝርዝር መረጃ ላኩልኝ ነበር ያሉት። ማኅበረ ቅዱሳን ከ120,000 በላይ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ተማሪዎችን አስተምሮ አስመርቋል። ሁሉን አባል አድርጎ ባይዝና ባይመዘግብም፥ ብዙዎች እንኳ ሳይመዘገቡ እኛ የማኅበረ ቅዱሳን አባላት ነን የሚሉ እጅግ ብዙ ናቸው፡፡ እነዚህ በሙሉ ስም ዝርዝራቸውን በHard copy /በጽሑፍ ተባዝቶ/ እንዲሄድላቸው ነው የአባ የመጀመሪያ ጥያቄ፡፡ እንግዲህ ማኅበሩ ከአገር ውጭ፣ ከውስጥም እስከ ገጠር ያሉትን አባላት ዝርዝር እንዲያመጣ ነው የተፈለገው፡፡

አሁን ጥያቄው፥ ምንድን ነው ጥቅሙ? እንዲህ ዓይነት መመሪያስ አለ ወይ? የሚለው ነው። ይሄ አላስፈላጊ ነው፤ ባይሆን የአመራሩን ዝርዝር እንላክ፤ የሚል ሐሳብ ስናነሣ ይሄ በፍጹም አይሆንም፤ ዝርዝራቸውን ካላገኘን አሉ። በተጨማሪም ሌሎችን በፍጹም ከኃላፊነት ጋር ያልተገናኙ ጥቃቅንና ከቁጥጥር ጋር ያልተገናኙ ጥያቄዎችን ያቀርባሉ፡፡ እኛም እንደዚህ አይደለም በማለት እንመልሳለን፡፡ በተቀመጡ 6 ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ወደ 5 ደብዳቤ ነው ለማኅበረ ቅዱሳን አከታትለው የጻፉት። ስለዚህ ግንኙነታችን በጣም የማይሆን የደብዳቤ ልውውጥ ሆኖ ሲገኝ፥ አንድ ዓመት እንኳ ሳይሠሩ ወደ ቅዱስ አባታችን አቤቱታ አቀረብን። በአካልም በመገኘት «በመምሪያ ኃላፊነት የተመደቡት አባት ተባብሮ ከማሠራት ይልቅ ሥራ እያደናቀፉ ነው ያሉት፥ ለእኛ ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ በኢትዮጵያ የሚገኙትን ሰንበት ትምህርት ቤቶች ለማደራጀት ብቃት የላቸውም፥ ስለዚህ ከኃላፊነት ተነስተው ሌላ ሰው ይመደብልን ቅዱስነትዎ የሚያምኑበትን ሲያሠራና ሊሠራ የሚችል ሰው ይመድቡልን» ብለን ጥያቄአችንን አቀረብን፡፡ ቅዱስነታቸው “እናንተ ብዙ ሰዎችን ማሳመን የምትችሉ፣ አንድ ደካማ መነኩሴ ይነሣ ብላችሁ ጥያቄ ማቅረብ የለባችሁም ይሄ ከእናንተ ደረጃ በታች ነው፡፡ ስለዚህ አሳምኑ” የሚል ሐሳብ ነው የሰጡን። በዚህ ጊዜ «በቅዱስ አባታችን በተቀመጡ በ6 ወራቸው 5 ደብዳቤ ጽፈዋል፡፡ ስለዚህ ደብዳቤ መጻፍ ነው ሥራቸው የምንሰጣቸውንም መልሶች እየሰሙና በአግባቡ እየመሩን አይደለም፡፡” የሚል ጥያቄ አቅርበናል፡፡ አሁን ላይ ሆነን ስናየው የዛሬ 6 ዓመት ይሄን ጥያቄ ማቅረባችን ትክክል ነበር፡፡ በወቅቱ ገና አጀማመራቸው ማኅበረ ቅዱሳንን የመቆጣጠር ሳይሆን የማቆም ዕቅድ ነው ያላቸው ይሄን ደግሞ በይፋ እየሠሩት እንደነበር አይተናል፡፡

እንግዲህ ከዚያ በኋላ ኃላፊው ማንኛውም ጥናትና ማኅበረ ቅዱሳንን የሚመለከት ነገር ወደ ቅዱስነታቸው ሲያቀርቡ፥ ለማኅበረ ቅዱሳን ግልባጭ አያደርጉም፤ በስውር ነው የሚጽፉት፡፡ ከ25 ገጽ ያላነሰ ጥናት የሚባል ነገር ከሌሎች የተሐድሶ ቡድንና የሃይማኖት አበው አባላት ጋር በመሆን ጥናት የሚመስል ነገር አቅርበዋል፡፡ ባቀረቡት ጥናት ላይም ማኅበረ ቅዱሳን የሚለው ክፍል አያስፈልግም፡፡ ወጣቶች በሙሉ በአንድ ተጠቃለው መመራት አለባቸው፡፡ ሐመርና ስምዐ ጽድቅንም እኛ እናዘጋጃለን፤ እኛ እንረከበው፡፡ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ተማሪና የሰንበት ተማሪ ብሎ መከፋፈል አያስፈልግም። በአንድነት ወጣቶችን ሰብስበን ልናስተምር እንችላለን፡፡ ለዚህ የሚያሰፈልጉ ወደ 300 የሚጠጉ የነገረ መለኮት /theology/ ምሩቃንን ከነበጀቱ ይመደቡልን፡፡ ጠቅላላ እኛ እናስተምራለን፡፡ የሚል ጥያቄ የዛሬ 4 ዓመት ነው ያቀረቡት፡፡ ያ ጥናት በወቅቱ ባለመመለሱ ተከታታይ ደብዳቤ ለቅዱስነታቸው ጽፈዋል፡፡ እነዚያ ደብዳቤዎችም፥ ተስፋ ቆርጫለሁኝ ስለዚህ ወደ ትምህርት መመለስ አለብኝ፡፡ እሠራለሁ ብዬ ነበር የመጣሁት፥ ስለዚህ ተግባራዊ እየሆነልኝ አይደለም ያለው የሚል አቤቱታ ያዘለ ደብዳቤ ሲያቀርቡ ቆይተው በአሁኑ ወቅት ያለን ግንኙነት ከተሐድሶ ማንሠራራት ጋር ተያይዞ የቤተክርስቲያኒቷን አደረጃጀት በውስጥም በውጭም እየያዙ ሲመጡ አሁን በትብብር የሚሠራበትና አንድ ላይ ሆነው የሚያጠቁበት ደረጃ ላይ ነው የደረሱት። በዚህ ምክንያት ማኅበረ ቅዱሳን ላይ ተደጋጋሚ የሆኑ ደብዳቤዎችን የመጻፍ፣ የማይሆኑ ትዕዛዞችን የማዘዝ፣ ተፈጻሚ ሊሆኑ የማይችሉ መመሪያዎችን የማስተላለፍ፣ ሥራ የማገዝና ተፈጻሚ እንዲሆኑ የማቀላጠፍ ሳይሆን የማደናቀፍ የማቆም፣ የኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ስብከተ ወንጌል እንዳይካሄዱ እንቅፋት የመፍጠር፣ ወጣቶች እንዲማሩ ሳይሆን እንዲበተኑ የማድረግ ሥራዎች ነው እየተሠሩ ያሉት በዚህ በጣም እናዝናለን፡፡

የእኛን ሥራ የመደገፍ ይቅርና የተመደቡበትን ሰንበት ትምህርት ቤቶችን እንኳ ዘወር ብሎ ለማየትና አንዱም ቦታ ላይ የማስተማሪያ መጻሕፍትም ይሁን መምህራን ተመድበው የሌለበት ቦታ ነው። አሳዛኝ በሆነ ሁኔታ ትውልዱን የሚመራው ክፍል እንደዚህ ሆኖ ይገኛል፡፡ እንግዲህ ያለን ግንኙነት ይሄንን ይመስላል፡፡
•    የማደራጃ መምሪያው ኃላፊ ማኅበረ ቅዱሳን በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ላይ ከፍተኛ ስጋት እየተፈጠረ እንደሆነ በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን እየገለጹ ይገኛሉ፡፡ እውነት ሥጋት ነው? እርሳቸው እንዲህ የገለጹት በምን ምክንያት ይመስልዎታል፡፡

ለአባ ሠረቀ ማኅበረ ቅዱሳን ለቤተ ክርስቲያን ከፍተኛ አደጋ አለው፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቷን እየተካት ነው። የማኅበረ ቅዱሳን አወቃቀርና አደረጃጀት አጠቃላይ ቤተ ክርስቲያኒቷን መዋቅር የተመለከተ ነው፡፡ ይኸውም ማለት እንግዲህ በቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠውን መዋቅር ነው እንዲህ እያሉ ያሉት። ቅድም እንደገለጽኩት 25 ገጽ ጥናት ለቅዱስ ፓትርያርኩ ሲያቀርቡ፣ በጥናቱ ውስጥ ለማኅበረ ቅዱሳን የተሰጠው መተዳደሪያ ደንብ በቂ አይደለም፥ ቅዱስ ሲኖዶስ ተሳስቷል ነው የሚለው፡፡ እንዲህ ዓይነት መተዳደሪያ ደንብ ለማኅበረ ቅዱሳን መሰጠት አልነበረበትም፤ ስለዚህ ስህተት ተፈጽሟል፤ ይሄ ስህተት መታረም አለበት፡፡ ለመታረም ደግሞ ደንቡ ይሻሻል ሳይሆን ጭራሽ መቆም አለበት የሚል አስተሳሰብ ነው፡፡ ስለዚህ ቅዱስ ሲኖዶስን ነው የሚወቅሰው። እንዲያውም መተዳደሪያ ደንቡ ማደራጃ መምሪያውን ለማኅበረ ቅዱሳን ሎሌ አድርጎታል፥ ጭራሽ ጉዳይ አስፈጻሚ አድርጎታል እንጂ አለቃነቱን የሚያሳይ አይደለም በሚል ነው የቅዱስ ሲኖዶስን ውሳኔ እየተቃወሙ ያሉት፡፡

ይሄን እንዳለ ትተነው ለቤተ ክርስቲያኒቱ አደጋ ነው በማለት የሚያስቀምጡት የራሳቸውን ሥጋትና አስተሳሰብ ነው፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን ለቤተ ክርስቲያኒቱ አጋዥ ነው፡፡ ክፍተቷን የሚሞላ የሚደግፍ ነው፡፡ ምዕመናን እንዳይበተኑ በተለይም የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ተማሪዎች እንዳይበተኑ እያደረገ ነው፡፡ ይሄንን አባ ሠረቀ ብርሃን አዛብቶ በማቅረብ ቤተ ክርስቲያኒቷን እየተካ ነው፡፡ የሚል የራሳቸውን የሥጋት ስሜት ሌሎቹም ላይ ለመጫን ነው፡፡

እንደማነጻጸሪያ የሚያቀርቡት የማኅበረ ቅዱሳንን አወቃቀርና የቤተ ክርስቲያኒቷን አወቃቀር ነው፡፡ እርሳቸው በራሳቸው የተሳሳተ መንገድ ነው እያቀረቡት ያለው፡፡ ለምሳሌ የማኅበረ ቅዱሳን ጠቅላላ ጉባኤ ከቅዱስ ሲኖዶስ ጋር እኩል ነው፤ የማኅበረ ቅዱሳን ሥራ አመራር ጉባኤ የቋሚ ሲኖዶስ ጉባኤ አቻ ነው፤ የማኅበረ ቅዱሳን ሥራ አስፈጻሚ ጠቅላይ ቤተ ክህነት እንደማለት ነው በማለት ራሳቸው ፈጥረው ነው ያቀረቡት፡፡ እኛ ጋር የሌሉ ክፍሎችን ሁሉ እያነጻጸሩ ነው ማኅበረ ቅዱሳን ለቤተ ክርስቲያኒቷ አደጋ ነው፤ እየተካትም ነው፡፡ እያለ የሚል አስተሳሰብ የሚያንጸባርቁት፡፡ ስለዚህ ይሄ አስተሳሰብ ሙሉ በሙሉ የአባ ሠረቀ ነው፡፡

አባ ሠረቀ ይሄንን ስጋት ከየት አመጡት? ከተባለ ከዓላማቸው አኳያ ነው፡፡ በፍጹም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን የማሳደግና ወጣቶችን የመሰብሰብ የማስተማር ፍላጎት የላቸውም። ቤተ ክርስቲያኒቷ እንድትጠናከር እየሠሩ ነው ማለትም አይቻልም፡፡ ተግባሮቻቸውም የሚያሳዩት የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ወጣቶች፣ የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ተማሪዎች ትምህርታቸውን እንዳይማሩ የሚሰጠውን የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ማስቆም ነው፡፡ ይሄ በምንም ዓይነት ምክንያት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ተልዕኮ ማስፈጸም ነው ተብሎ አይታመንም፡፡ ማኅበረ ቅዱሳንም በዚህ አያምንም፡፡ እርሳቸው የያዙት መንገድ ሙሉ በሙሉ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን ማዳከም ነው፡፡ ትውልድ የማሳጣት ሥራዎችን የመሥራት ነው፡፡ ይሄ ደግሞ የሌሎች ተልዕኮ ነው። ስለሆነም ሌላ የተጫኑት ተልዕኮ አለ ብለን ነው የምናምነው፡፡ ከሌሎች የተጫኑት ቤተ ክህነቱን የማዳከም ተልዕኮ አላቸው። የማኅበረ ቅዱሳን ሥራ ቤተ ክርስቲያኒቷን የሚያጠናክር ከሆነ፥ ማኅበረ ቅዱሳንን ማቆም ቤተ ክርስቲያኒቷ እንዳትጠናከር አንድ እርምጃ ብለው ስለሚያስቡ በተቻላቸው መጠን ስም በማጥፋት ለቤተ ክርስቲያኒቷ ስጋት ነው በማለት ማቅረብና የሁሉንም ትኩረት እንዳያገኝ የማድረግ ሥራ ነው የሚሠሩት። በዚህ ተግባር ላይ ተሠማርተው ነው ያሉት በአሁኑ ወቅት፡፡
•    ሌላው የሚነሳው ጉዳይ፣ መስከረም 12 ቀን 2002 ዓ.ም ከመንግሥት ባለሥልጣናት፣ ከሊቃነ ጳጳሳትና ከቅዱስ ፓትርያርኩ ጋር በተደረገው ስብሰባ ላይ ማኅበረ ቅዱሳንን በመክሰስ ሂደት ላይ እርሳቸው አንድ ተሳታፊ እንደነበሩ ይነገራል፡፡ በወቅቱ ሁኔታው እንዴት ነበር? የእሳቸው ሚናስ ምንድን ነበር?

በእርግጥ በአጋጣሚ አልተገኘሁም፡፡ የመስከረም 12 ጉባኤ ከመደረጉ በፊት መኖሩን አናውቅም ነበር፡፡ ነገ ጠዋት እንድትገኙ ነው የተባለው፡፡ እኔ በሰማሁትና በነበሩት ሪፓርቶች ሁኔታ፥ በጉባኤው ላይ አባ ሠረቀ ብርሃን ዋነኛው የጉባኤው ከሳሽ ሆነው ነው የቀረቡት፡፡ ሁሉም እንደሚያስታውሰው በወቅቱ ማኅበረ ቅዱሳን የተከሰሰው በሁለት ጉዳዮች ነው፡፡ በፓለቲካ ውስጥ ገብቷልና የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ውስጥ ጣልቃ ገብቷል የሚል ነው፡፡ ሁለቱም ምንም ዓይነት መሠረት የሌላቸው ናቸው። ማኅበረ ቅዱሳን ፖለቲካ ውስጥ ገብቷል ያሉት በተለያዩ ጊዜ የተጻፉ ዘገባዎችን በማንሣት ጥፋተኛ እንደሆነ ለማሳየት ነው የተሞከረው፡፡ ይሄ የጽሑፍ ሥራ ነው፡፡ እነዚህ ጽሑፎች ሙሉ በሙሉ ሲተረጎሙ ምንም ዓይነት አንድምታ /impact/ አይኖራቸውም ብሎ ማለት ላይቻል ይችላል፡፡     ነገር ግን ሆን ተብሎ የፖለቲካ አቅጣጫ ውስጥ ለመግባት የተሠራ ሥራ አይደለም። ትምህርት የማስተማር፣ ስብከተ ወንጌልን የማስፋፋት፣ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን የመጠበቅ፣ ሠላም እንዲኖር የማድረግ ኃላፊነቶችን እንደ ዓላማ አድርጎ ነው የሚሠራው። ዳሩ ግን እነዚህን በመያዝና ጉዳዩን መንግሥት በልዩ ትኩረት እንዲያየው ለማድረግ በማሰብ ከስም ማጥፋት ተግባሮች እንደ አንዱ ሆኖ የቀረበው ነው። ማኅበረ ቅዱሳን ሲጀመር ጀምሮ የስም ማጥፋቶች ሲሠሩ ነበር፤ በተለይ በቤተ ክርስቲያን ጠላቶች፡፡ ካለፉት 5 እና 6 ዓመታት ወዲህ የአባ ሠረቀ ወደዚህ ኃላፊነት መምጣት ይሄንን የስም ማጥፋት ዘመቻ የበለጠ ለማጧጧፍ ጉዳዩን መንግሥትም እንደ አደጋ እንዲያየው ለማድረግ የተጠቀሙበት ዘዴ ነው፡፡ ዓላማቸውንም ለማሳካት ሌላ ኃይልን በሙሉ የማሰባሰብ ነው፡፡ ልክ ጌታን ሮማውያን እርምጃ እንዲወሰዱበት በአይሁድ በፖለቲካ እንደተከሰሰው። ያልሠራውን ሠራ ግብር እንዳይከፍል ከልክሏል ሲባል እንደነበረው። አሁንም ተመሳሳይ የስም ማጥፋት ዘመቻና ቤተ ክርስቲያንን የማሳደድ ዘመቻ ነው ያለው፡፡ በዚህ ምክንያት ነው ማኅበረ ቅዱሳን የተከሰሰው እንጂ፥ በእንደዚህ ዓይነት አቋም ማኅበረ ቅዱሳን በምንም ዓይነት መልኩ በፖለቲካ ጣልቃ ገብነት የለውም፥ አይኖረውም። ይሄ በመተዳደሪያ ደንቡ የተገለጠ ነው።

የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ላይም ቢሆን ቅዱስ ሲኖዶስ እስከሚያጸድቀው ድረስ ማኅበረ ቅዱሳን ጣልቃ አይገባም የሚል አንቀጽ ነበረው፡፡ የአባቶች ኮሚቴ ሲነጋገር፥ ቅዱስ ሲኖዶስ ሲያጸድቅም፥ ‹‹ግቡም አትግቡም›› የሚል እዚህ ቦታ ላይ አያስፈልግም። አስፈላጊ ሲሆን ማኅበረ ቅዱሳን ቤተ ክርስቲያንን በአስተዳደር መርዳት ይኖርበታል። መደገፍ ይኖርበታል። ‹‹ደንቤ አይፈቅድልኝም›› እያለ ዳር ቆሞ ማየት የለበትም በማለት ቅዱስ ሲኖዶስ በምልዐተ ጉባኤ ሲያጸድቅ ይሄን አንቀጽ አስተካክሎ ነው ያጸደቀው። ይሁን እንጂ ማኅበረ ቅዱሳን ካለው ልምድ በመነሣት በቤተ ክርስቲያን አስተደደር ላይ ‹‹እከሌ ይሾም፣ እከሌ ይውረድ እገሌ እንዲህ ነው›› የሚል ነገር አንስቶም አያውቅም። እስከ ዛሬው ሰዓት ድረስ ‹‹ደንቤ ይከለክለኛል፤ አይፈቅድልኝም›› በሚል መንገድም ሄዶ አያውቅም።
 
በ2002 ዓ.ም የተደረገው ስብሰባ ምን ማለት እንደሆነ ራሱ ግልጽ አይደለም። ምን አልባት በቅዱስ ሲኖዶስ ሲነሱ የነበሩ ውዝግቦችን መሠረት አድርጎ ይሆናል፡፡ በዚያን ጊዜም ቢሆን ማኅበር ቅዱሳን አቋሙ ግልጽና ግልጽ ነው። ቅዱስ ሲኖዶሱ በሚወስነው ውሳኔ ይሄዳል የሚል ነው። ያን ሁሉ ውዝግብ የፈጠረው ማኅበረ ቅዱሳን ነው የሚል ስሜት በአባቶቻችንና በሌሎች ሰዎች ለማሳደር የተወጠነ ነው። እንኳን በቅዱስ ሲኖዶስ ጉዳይ ይቅርና በአንድ አጥቢያ ጉዳይ ማኅበረ ቅዱሳን ጣልቃ ገብቶ አያውቅም፡፡ የመግባትም ፍላጎት የለውም። ትልቁ የስብከተ ወንጌል ጉዳይ እንጂ የገንዘብና የአስተዳደር ነገር ዋነኛ ጉዳይ ነው ብሎ አስቦበት አያውቅም።

ሌላው በአባ ሠረቀና በሌሎችም የቀረበው ክስ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን ከአክራሪዎች እንዲጠበቁና ራሳቸውን እንዲከላከሉ በንቃት ዙያቸውን እንዲያዩ፣ የተጎዳውን በመርዳት በኩል እንዲተባበሩ፣ ቤታቸው የተቃጠለባቸውን እንዲሠሩ፣ የተጎዳ ተጎድቶ እንዳይቀር ሁሉም እንዲነሳሳ የሚያደርጉ መልእክቶችን በስምዐ ጽድቅ ጋዜጣና በሐመር መጽሔት ላይ በ1999 ዓ.ም አክራሪዎች ባደረሱት ጥቃት ምክንያት የጻፍነውን በማንሳት፥ ‹‹ይሄ ቀስቅሷል›› የሚል ከሌላ አካል አይደለም ከራሳችን የቤተ ክርስቲያን አካላት ከአባ ሠረቀና ከሌሎች አካላት በዚያው ዕለት ቀርቦ ነበር፡፡ 

ለተነሱት ጉዳዮች በሙሉ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትም ሁሉም በቂ መልስ ሰጥተዋል። ካጠፋም ማኅበረ ቅዱሳንን እኛ ነው የምንመክረው፤ በቅዱስ ሲኖዶስ ነው የምንመክረው። ከእኛ አቅም በላይ አይደለም የሚል ሐሳብ ተንጸባርቆ ነው የዛን ቀን ስብሰባዎቹ የተደመደሙት። ስለዚህ ያን እንደሌላ ድልና ውጤት በመቁጠር ማኅበረ ቅዱሳንን ለመወንጀልም ስሙን ለማጥፋት የሚሄድበትና የዚያን ጊዜም እድል ተሰጥቶት አልታረመም በሚል ነው እየከሰሱት ያሉ።

•    የተሃድሶ መናፍቃን እንቅስቃሴ ለመግታት ዘመቻ የተያዘበት ወቅት ነው፡፡ ዳሩ ግን ኃላፊው የግለሰቦችን ስም መዋቅር ሳይጠብቅ ተሃድሶ መናፍቅ ወዘተ እያለ ያመጣል የተለያዩ ጉዳዮችን ያነሣል? በሚል ክስ ያቀርባሉ ስለዚህ ክስ ማኅበሩ ያለው አቋም ምንድን ነው?

ከዚህ በፊት በግልጽ ፕሮቴስታንት መሆናቸው የታወቁ፥ በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ገብተው የነበሩና የተባረሩ አሉ። አንዱ ‹‹ዲ/ን›› ሙሉጌታ ወ/ገብርኤል የሚባል ነው። ይህ ግለሰብ እዛው ኮሌጅ ውስጥ በመባረር በሂደት ላይ እያለ፣ ከወጣ በኋላም «ማኅበረ ቅዱሳን ወይስ ማኅበረ ሠይጣን›› የሚል መጽሐፍ ጻፈ። ለመጽሐፉ ሰነድ የወሰደው ከማደራጃ መምሪያው ነው። እርሱንም የሰጡት አባ ሠረቀ ብርሃን ናቸው። የእርሱ ማሳተም ብቻ አይደለም ቁም ነገሩ፤ ከዚያ በኋላ የመጽሐፉ ስርጭት ላይም ተሳታፊ ነበሩ። እኛ አስቁሙ ብለን ደብዳቤ ስንጽፍላቸው ማቆም አልቻሉም። በዚህም የተነሣ ከተሐድሶ መናፍቃን ጋር ያላቸው ጥምረት እጅግ በጣም የጠበቀ ሆኖ እናገኘዋልን። ሌሎችንም ተጨማሪ ማስረጃዎች ማቅረብ ይቻላል፡፡ 

አሁን የተሃድሶ መናፍቃን እንቅስቃሴ እየጠነከረ በሄደበት ወቅት ላይ ለማደራጃ መምሪያና ሌሎች ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በተገኙበት ገለጻ አድርገናል። አባ ሠረቀ ግን በእኛ መርሐ ግብር ላይ አይገኙም። ቢጋበዙም አይመጡም። ማኅበሩ በሚያዘጋጃቸው መርሐ ግብሮች ላይ ጥናቶች ላይ አይገኙም። ስለዚህ እኛ ለሊቃነ ጳጳሳት ሳናሳውቅ ለቅዱስ ሲኖዶስ ሳናሳውቅ ሥራዎችን አልሠራንም። እንቅስቃሴውንም በሚመለከት ከ10 በላይ ለሚሆኑ /ተጨማሪ?/ ሊቃነ ጳጳሳት አሳውቀናል። በጽሑፍም ከ25 በላይ ለሚሆኑ ሊቃነ ጳጳሳት አሳውቀናል። እንግዲህ በቀጣይነት ወደ ቅዱስ አባታችን ገብተን ለማሳወቅ ፕሮግራም ይዘን ባለንበት ወቅት ነው የተሃድሶ መናፍቃኑ ቡድኑ ማዋቅሩን ዙርያውን በመያዝ ወደ ኋላ በመጎተት የስም ማጥፋት ዘመቻዎችን በማኅበሩ ላይ በማካሄድ ከቅዱስነታቸው ጋር ለማጣላትና ለማራራቅ ሙከራዎችን የሚያደርጉት። እኛ አሁን በቅዱስነታቸው መመሪያ ሰጭነት በዚህ በተሕድሶ ጉዳይ ላይ ቤተ ክርስቲያን መፍትሔ ታገኛለች የሚል እምነት አለን፡፡ 

ማደራጃ መምሪያውም ‹‹እኔ ነኝ ማወቅ ያለብኝ። ማንም ሰው መስማት የለበትም።›› የሚለው ይሄ ስሕተት ነው። የአፈጻጸም ሪፓርት አይደለም የምናቀርበው፥ ጥናት ነው ያቀረብነው፡፡ ዓውደ ጥናት ላይ የመንግሥትም መንግሥታዊ ያልሆኑ ባለስልጣናትም ሌሎችም ሰዎች በተገኙበት ጥናት ይቀርባል። ይሄ እንደ አንድ ግኝት፣ ጥናትና እንቅስቃሴ የሚቀርብ እንጂ እኔ ሳላምንበት የሚለው ያልታየ አዲስ አካሄድ ነው። የማደራጃ መምሪያውም በተለይ አባ ሠረቀ ብርሃንም ይሄን ጥናት ደግፈው ይጓዛሉ የሚል እምነትም የለንም። የዓላማ ጉዳይ ስለሆነ ከዚህ በተጻራሪ ቆመው ነው ያሉት። ስለሆነም ጥያቄያቸው እኔ ሰምቼ ለምን አላስቆምኩትም ነው እንጂ፥ ጥናትን ለማቅረብ የግድ የማደራጃ መምሪያው ፈቃድ የሚያስፈልገው ሆኖ አይደለም፡፡ አሁንም በጥናትና ምርምር ማዕከላችንም ሆነ በሌሎች ብዙ ጥናቶችን እናቀርባለን። እነዚህ ጥናቶች በዓመት ዕቅድ ተይዞላቸው የሚቀርቡ ናቸው። የተሐድሶ መናፍቃን እንቅስቃሴ ግን ቤተ ክርስቲያኒቷን ከፍተኛ የሆነ አደጋ ላይ እየጣለ ያለ ጉዳይ ስለሆነ በዚህ ጉዳይ ላይ ብፁዓን አባቶች አይተው፣ ሰምተውት ሕዝቡም ማወቅ አለበት የሚለውን ሐሳብ ሰጥተውበትና እነርሱም በጽሑፍ ደርሷቸው ተረድተውት የቀጠልነው ነው። ቅዱስ አባታችን ጋርም አሁንም እስከ ሲኖዶስ ስብሰባ ባለው ጊዜ ውስጥ በተቻለ መጠን ጉዳዩን ተረድተውት አውቀውት የእነዚህን ሰዎች ተንኮልና አካሄድ እንዲያስቆሙ ለማድረግ አሁንም ጥረታችንን እየቀጠልን ነው፡፡
•    ምንም እንኳን ቀሲስ ዶ/ር ሙሉጌታ በ2002 የሥራ ክንውን ሪፖርታቸው ቢገልጹትም አሁንም በኃላፊው መግለጫ ላይ ማኅበረ ቅዱሳን ሂሳቡን ኦዲት አያስደርግም? የባንክ ሂሳቡንም ለማደራጃ መምሪያው ለማሳወቅ ፍቃደኛ አይደለም የሚል ይገኝበታል ስለዚህ ምን ይላሉ? 

በእውነቱ ቅድም እንደጠቀስኩት ማኅበረ ቅዱሳን የሚከፍተው የሂሣብ አካውንት በሙሉ በጠቅላይ ቤተ ክህነት ታውቀው የሚከፈቱ ናቸው፡፡ ሂሣቡን አያሳውቅም የሚለው ሩቅ ላለ ሰው አስደንጋጭ የሆነ የውሸት ክስ ነው፡፡ ሙሉ በሙሉም ሐሰት ነው፡፡ በጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ ፊርማ ከዚህ በፊት በነበሩት መምሪያ ኃላፊዎች ጥያቄ ለጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ እየቀረበ የሚከፈተውን የባንክ አካውንት ማኅበረ ቅዱሳን ምስጢር አድርጎ እንደያዘው ሁሉ የባንክ አካውንቱን አያሳውቅም ማለት ምዕመናንን ለማስደንገጥ የታሰበ ነው፡፡ ምዕመናንም ለገዳማትም ለሌሎች አገልግሎቶችም የምትሰጡትን ገንዘብ ለእኛ እያሳወቀ አይደለም በማለት ስም ለማጥፋትና አስደንግጦ ወደ ኋላ ዘወር ለማድረግ የታሰበ ነው እንጂ የማኅበረ ቅዱሳን አካውንት ይታወቃል። ከዚያም በፊትና ከብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ ጀምሮ የነበሩት ጠቅላይ ሥራ አስኪያጆች ናቸው ደብዳቤ ጽፈው ፈቅደው የባንክ አካውንት የሚከፈተው እኔ አላውቀውም የሚሉ ከሆነ የጠቅላይ ቤተ ክህነት መዝገብ ቤትን ማየት በቂ ነው።

ሁለተኛው ኦዲት አያስደርግም ለሚለው በማኅበሩ መተዳደሪያ ደንብ የተቀመጠው፣ የማኅበሩ ኦዲትና ኢንስፔክሽን በየዓመቱና በየጊዜው የማኅበሩን ኦደት ይሠራል ኢንስፔክት ያደርጋል፤ የሚል ደንብ በቅዱስ ሲኖዶስ ተሰጥቶታል። አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ የማኅበሩ ሥራ አመራር ጉባኤ በውጭ ኦዲተር የማኅበረ ቅዱሳንን ሂሣብ ኦዲት እንዲደረግ ያደርጋል። ማኅበሩ ዓለም አቀፍ እውቅና ባላቸው የውጭ ኦዲተሮች፣ በመንግሠት የምሥክር ወረቀት የተሰጣቸው /licensed የሆኑ/፣ ግብር የሚከፈሉ፣ በሥራቸውም ጥፋት ቢያጠፉ ሊጠየቁ በሚችሉ ኦዲተሮች አስመርምሯል። ለወደፊትም ያስመረምራል። ይሄንንም ሪፖርት ለጠቅላይ ቤተ ክህነት፣ ለማደራጃ መምሪያውና ለሚመለከታቸው አካላት አስገብቷል። የማኅበረ ቅዱሳንን የኦዲት ሪፖርት አሠራር ውድቅ ሊያደርግ የሚችል አላየሁበትም በማለት አሳውቋል። ስለዚህ ይህ በሆነበት የማኅበረ ቅዱሳን ሂሣብ አይታወቅም አይደረግም ማለት በጣም ከፍተኛ የሆነ ስም የማጥፋት ሥራ ነው። ወይም ስለ ኦዲት ያለመረዳት ችግሮች አይኖርም ብለን አናስብም፡፡
•    ይሄ አለመግባባት ችግር እስከመቼ ይቀጥላል? ማኅበሩስ አቋሙ ምንድን ነው? 

በእነዚህ ስም የማጥፋት ዘመቻዎችና ሁኔታዎች ማኅበረ ቅዱሳን አይደናገጥም። ማኅበሩ የተመሠረተው የቤተ ክርስቲያኒቷን ክፍተት ለመሙላት፣ ድጋፍ ለማድረግ ነው። ሁላችን የሰበካ ጉባኤ አባላት ነን፣ የሰንበት ትምህርት ቤትም አባላት ነን፣ አጥቢያ አለን፣ ቤተ ክርስቲያን አለችን አናስቀድሳለን፣ እንቀድሳለን፣ እናስተምራለን አገልግሎትም እናገኛለን ከአንድ ምእመን የሚጠበቀውን አገልግሎት እንሰጣለን። ማኅበረ ቅዱሳን የመጣው ተጨማሪ ሥራዎችን ለመሥራት፣ ተጨማሪ ጊዜ ለመስጠት፣ ተጨማሪ ጉልበት ለመሥጠት፣ ተጨማሪ ገንዘብ ለማውጣት ነው እንጂ ሌላ ምንም ጥቅም ኖሮት አይደለም። ቤተ ክርስቲያን ተጨማሪ ሥራ ለምን ያስፈልጋታል ከተባለ የዛሬ 20 ዓመትም፥ 25 ዓመትም የነበሩት ችግሮች ዛሬም አልተፈቱም። ገዳማት እየተዘጉ ነው ያሉት፣ ስብከተ ወንጌል በአግባቡ እየተሥፋፋ አይደለም፡፡ ሰንበት ትምህርት ቤቶች ሥርዓተ ትምህርት የላቸውም። ሰንበት ትምህርት ቤት የተቋቋመባቸውና ያልተቋቋመባቸው ቢታዩ 25% አይሆኑም፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎችን ለማስተማር አካል ያስፈልጋል እነዚህ ናቸው ማኅበረ ቅዱሳንን እንዲመጣ ያደረጉት። 

ይሄ በራሷ በቤተ ክርስቲያኒቷ መዋቅር ለምን አልተሠራም? ካልን ወደ ዘመናዊው ጊዜ ስንመጣ ያልተለወጡ የተወሰኑ ነገሮች አሉ። ስልት /Strategy/ የለም፣ ዕቅድ የለም፤ በእነዚህ ሥራዎች ላይ መሥራት አልተጀመረም። ከዚያም ይልቅ ሥራን ማደናቀፍ በጣም ትልቅ ሥራ ሆኖ ነው የምንመለከተው። አጠቃላይ የቤተ ክርስቲያኒቷን አስተዳደር አካሄድ አሠራር በተቀናጀና ዕቅድ ባለበት ሁኔታ ለመምራት በጣም ብዙ ሥራዎች ይቀራሉ። ከሚሠሩ ይልቅ የሚያደናቅፉ በጣም ብዙ እንዳሉ እናውቃለን። ቤተ ክርስቲያኒቷንም የማዳከም ሥራ የሚሠሩ ብዙ እንዳሉ እናውቃለን። ይሄን ሠርታችኋል በርቱ ከመባል ይልቅ አቁሙ አቁሙ እንደምንባል ጥንትም እናውቃለን ስንጀምርም እንዲያ ነበር ዛሬም ያው ነው። 

ፈተና ሳይኖር ደግሞ መንፈሳዊ አገልግሎት ሊቀጥል አይችልም ይህ ከሰው ብቻ የሚመነጭ ሳይሆን ከራሱ ከጥሩ ነገር ጠላት ከዲያብሎስም የሚመነጭ ነው። ፈተና ምንም አያስፈልግም ካልን የምንሠራው መንፈሳዊ አገልግሎት /ሥራ/ አይደለም ማለት ነው። ስለዚህ የምንሠራው ሥራ መንፈሳዊ ሥራ ነው። መንፈሳዊ ሥራ ደግሞ የሠይጣን ፈተና አለበት። ሥራችንን እንድናቆም ይፈልጋል እስከ ዛሬ ሲታገለን ቆይቋል ዛሬም ደግሞ አጠንክሮ ይታገላል። የበለጠ በጠነከርን ቁጥር የበለጠ ፈተና ይመጣል። ይሄንን ከቅዱሳት መጻሕፍት እናውቃለን ከታሪክ እናውቀዋለን። ከራሳችንም ሕይወት እናውቃለን። በመሆኑም ይሄ ፈተና እስከመቼ ይቀጥላል ካልን፥ አገልግሎታችን አስከቀጠለ ድረስ ይቀጥላል። ፈታኞቹ ወደ ልቦናቸው ተመልሰው ወደ ሥራ ሲገቡ ሠይጣን ሌላ ፈታኝ ያዘጋጃል። አባ ሠረቀ እንኳን ቢያቆሙና ወደ ትክክለኛው የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ቢመለሱ ሰይጣን ሌላ ፈታኝ ያመጣል ይሄ እስከ ክርስቶስ ምጽአት ድረስ የማይቀር ጉዞ ነው። ስለዚህ ይሄ መቼ ይቆማል ብለን የሚቆምበትን ቀን ተስፋ አናደርግም፤ የሚቆመውም መንፈሳዊ አገልግሎታችንን ስናቆም ነው። ስለዚህ ይሄንን ይዘን እንሄዳለን።

ነገር ግን ይሄ ፈተና የሚቀጥል ነው ብለን ችላ ማለት የለብንም። በእኛ በኩል ማድረግ የሚገባንን በሙሉ እናደርጋለን “ከእንግዲህ ከማኅበሩ ጋር አልሠራም” የሚል ደብዳቤ ጽፈዋል። “ማኅበሩ የሚሰጠውን ደብዳቤ በሙሉ አልመልስለትም” በማለት ለጠቅላይ ቤተ ክህነት አቤቱታ አቅርበዋል። ይሁን እንጂ አሁንም ማኅበሩ ጥያቄ ያቀርብላቸዋል። እንደማይመልሱም እየታወቀ ትክክለኛ መንገድ ተከትለን እንሄዳለን። ስንመልስላቸው አልተመለሰልንም ብለው ያቀርባሉ እኛም መልሰን እንመልስላቸዋለን። ሁል ጊዜም ግን ለፋይል እንዲመቻቸው ‹‹አልተመለሰልኝም፣ አልታዘዘኝም፣ አልታዘዘኝም›› ነው የሚሉት። እኛ ግን እየታዘዝን፣ እየታዘዝን እንቀጥላለን። እየተቀበልን መፈጸም የሚገባንን እንቀጥላለን። 

አሁን በመሠረቱ ማኅበረ ቅዱሳን ከፍተኛ ገንዘብ እንዳለው ያስወራሉ። የምዕመኑ ገንዘብም ወደዚህ እንደመጣ አድርገው ይናገራሉ። ስለዚህ የመቀራመትና የመውሰድ ስሜት ነው ያላቸው። ማኅበረ ቅዱሳን ገንዘብ የለውም፤ አንዳንድ ዕቅዶችንም እየሰረዘ ነው የሚሠራው ባንክ አካውንቱን አያሳውቅም ይላሉ እንጂ ባንክ አካውንቱን ማየት ይችላሉ። በማኅበረ ቅዱሳን በየወሩና በየሁለት ወሩ በምትሰበስብ ገንዘብ ሥራ እየሠራን ነው የምንቀጥለው። እዚህ የሚሰጠው አገልግሎት በአበልና በደመወዝ የተንበሸበሹ አድርገው ነው የሚያስቡት። ይሄ በሙሉ ግን የተሳሳተ ነው። ስለዚህ ከፍተኛ ገንዘብ አለና ያንን ገንዘብ እንቆጣጠራለን የሚል ስሜት እንዳለ አንዳንድ ፍንጮችን እያየን ነው። ስለዚህ ማኅበረ ቅዱሳን ጋር ያለውን ግልጽ አሠራር አሁንም የበለጠ ግልጽ እያደረገ አባቶችም እንዲረዱ እያደረግን፥ ለቅዱስ ሲኖዶስም እያሳወቅን እንቀጥላለን። በተለይም በአሁኑ ሲኖዶስ የመናፍቃንን እንቅስቃሴ ጉዳይ እና ለዚህ ተባባሪ ሆነው እየሠሩ ያሉትን የመምሪያው ኃላፊዎች ጉዳይ አጀንዳ ሆኖ እልባት መስጠት አለበት ብለን እናስባለን። ውሳኔ ያገኛሉ ብለንም እናስባለን። ማኅበረ ቅዱሳንም በተሰጠው መተዳደሪያ ደንብ መሥራት አለመሥራቱን ቅዱስ ሲኖዶስ ራሱ ማረጋገጥ የሚችለው ጉዳይ ነው። በየሀገረ ስብከቱ ከአባቶች ጋር ነው የምንሠራው አየር ላይ አይደለም እየሠራን ያለነው። የማኅበሩን አገልግሎት ብፁዓን አባቶች አቅም አላቸው ሥልጣኑም የቅዱስ ሲኖዶስ ነው። መወሰን የሚችለውም ቅዱስ ሲኖዶስ ነው ብለን እናምናለን።
•    በመጨረሻም ቀረ የሚሉት ካለ?

በሚጻፉና በሚባሉ በሚሰራጩ የውሸት ፕሮፓጋንዳዎችና የስም ማጥፋት ዘመቻዎች ምእመናንም ሆኑ የማኅበሩ አባላት መረበሽ የለባቸውም። የፈለገ ያህል ፈተና ቢመጣ ደግሞ ፈተና እንደሚኖር ማወቅ አለባቸው፡፡ ከፈተና የራቀ አገልግሎት የለም። ስለዚህ የሚነሡትን ነገሮች በሙሉ በመከታተልና በማወቅ ለግንዛቤ ከመያዝ ባሻገር፥ ሥራን ለማቆም አገልግሎትን ለመተው ማሰብ የለባቸውም። በእልህም ደግሞ ወደ ሌላ መጥፎ ተግባር ውስጥ መግባት የለባቸውም፤ ይገባሉ ብዬም አልጠብቅም፡፡ ሁል ጊዜም በትክክለኛና በሕጋዊ መንገድ ቤተ ክርስቲያንን ለማገልገል ዛሬም ወደፊትም ጠንካራ ሆኖ መንቀሳቀስ ይጠበቅባቸዋል። ከዚህ የበለጠ ፈተና ሠይጣን ሊያመጣባቸው ይችላል። ሙሉ በሙሉም የማኅበሩ አገልግሎት በከፍተኛ ሁኔታ የማደናቀፍ ሥራ ሊፈጥር ይችላል ብለን ብናስብ እንኳን ይሄ በሙሉ የሠይጣን ፈተና መሆኑን አውቀን ከመንፈሳዊ አገልግሎታችን ምንጊዜም ቢሆን ወደኋላ ማለት የለብንም። በአጥቢያችን፣ በወረዳችን፣ በሀገረ ስብከታችን ቤተ ክርስቲያንን በማገልገል ትጉዎች መሆን ነው ያለብን፤ ለስም አይደለም የምንሠራው፣ ለማኅበረ ቅዱሳንም አይደለም የምንሠራው ለቤተ ክርስቲያናችን ነው። የምንሠራው በተጨማሪም አጽራረ ቤተ ክርስቲያንን ነቅተን መጠበቅና ምላሽ ለመስጠት ዝግጁዎች መሆን ይጠበቅብናል:: ይሄን ነው ለማስተላለፍ የምወደው፡፡
•    እግዚአብሔር ይስጥልን፡፡

እኔም እግዚአብሔር ይስጥልኝ፡፡