hawir hiwot ticket

የሐዊረ ሕይወት ትኬት ሽያጭ ተጠናቀቀ!

hawir hiwot ticket 

በዚህ ጉዞ  ለመርሀ ግብሩ ቅድመ ዝግጅት ሲባል ትኬቶች  አሰቀድመዉ እንደሚጠናቀቁ የሚታወቅ ሲሆን   መኪናዎችንና ምግብ ለማዘጋጀት እንዲያመች ትኬቱ  ባያልቅ እንኳ በታቀደው መርሀ ግብር መሰረት ሽያጭ እንዲቆም ይደረጋል፡፡   ይሁንም እንጂ ከጉዞው አንድ  ሳምንት አስቀድሞ የተዘጋጁት 5000 ትኬቶች ሙሉ በሙሉ የተሸጡ ሲሆን ትኬት ሽያጩም በተያዘው መርሀ ግብር መሰረት መጋቢት 16 /2005  ተጠናቅቋል፡፡

የጉዞ ኮሚቴው በየጊዜው እየጨመረ የመጣውን የተሳታፊ ፍላጎት በማየት 1000 ተጨማሪ ትኬት ቢዘጋጅም  ፍላጎቱ እየናረ መጥቷል፡፡ የትኬት ሽያጩ ከተጠናቀቀ በኋላ እንኳን ትኬቱን ፍለጋ የሚመጡ ምዕመናን ቁጥር ከፍተኛ ነው፡፡

 በዚህ ጉዞ መሳተፍ ፈልጋችሁ ትኬቱን አስቀድማችሁ ያልገዛችሁና በተለያየ ምክንያት በጉዞው መሳተፍ ላልቻላችሁ በሙሉ ለሚቀጥለው  ጉዞ  በሰላም ያድርሳችሁ እያልን የዕለቱን መርሐግብር በማኅበሩ መካነ ድር(www.eotcmk.org) ና ማኅበራዊ ኔትወርክ አድራሻና ገጽ(www.facebook.com/mahiberekidusan)  የቀጥታ ሥርጭት እንድትከታታሉ እንጋብዛችኋለን፡፡

ትኬቱን ለገዛችሁ

1.ትኬታችሁን በጥንቃቄ መያዝ ይኖርባችኋል፡፡
2. እንደተገለጸው ክርስቲያናዊ አለባበስ እና ዝግጅት ይኑረን
3. ቀድሞ የደረሰ ቀድሞ ይጓዛል
4. ሌሊት ስንመጣ ጫና ስለሚፈጥርመኪናው መሳፈሪያ አካባቢ መጠባበበቅ  ባይኖር ይመረጣል፡፡
6. መርሓግብሩ የተዘጋጅው ከመካነ ጸሎት ውጭ ስለሆነ ማንም ሰው በምንም ምክንያት መቅረት አይገባም፡፡

እስከ መርሀ ግብሩ ፍጻሜ ድረስ  በጸሎት ያስቡን፡፡

በሐዊረ ሕይወት መርሐ ግብር ላይ እንዲመለሱ የቀረቡ ጥያቄዎች

የተወደዳችሁ የሐዊረ ሕይወት አዘጋጆች ሰላመ እግዚአብሔር ይብዛላችሁ፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን ለማንኛውም ጥያቄ መልስ ለመስጠት ዝግጁ እንደሆነች አምናለሁ፡፡ እናም ሁለት በአእምሮየ የሚመላለሱ ጥያቄዎች አሉኝ፡፡

የመጀመሪያው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ዓለምን እንደሚያድን ለሐዋርያት በሚያስተምርበት ወቅት ከአስራ ሁለቱ ሐዋርያት አንዱ የሆነው ቅዱስ ጴጥሮስ ጌታ ሆይ ይህስ አይሁንብህ ብሎ በተናገረ ጊዜ ጌታችን አንተ ሰይጣን ከዚህ ሂድ ብሎ በጴጥሮስ ላይ አድሮ የክርስቶስን የማዳን ሥራ የተቃወመውን ዲያብሎስን ተቃውሞታል፡፡ እኔ እንደገባኝ ከሆነ የቅዱስ ጴጥሮስ ሀዘኔታ ተገቢ እንዳልነበ ነው በጌታችን የማዳን መንገድ ልንደሰት ይገባል እንጅ በስቅለት ወቅትና በሌሎችም ጊዜያት ስለ ጌታችን ስቅለት የሚደረገው የሐዘን ስሜት ከክርስትና አስተምሮ አንጻር ተገቢ ነው ወይ?
ሁለተኛው ጥያቄ ከአስራ ሁለቱ ሐዋርያት ስለነበረው ስለአስቆሮቱ ይሁዳ ነው፡፡ እንደምናውቀው ይሁዳ አባቱን እንደሚገድል፣ እናቱን እንደሚያገባና መምህሩን እንደሚሸጥ አስቀድሞ በትንቢት እንደተነገረና የተነገሩት ትንቢቶች በሙሉ እንደተፈጸሙ አባቶቻችን አስተምረውናል፡፡ ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ የሰውን ልጅ የማዳን መንገድ በፍርድ አደባባይ ለመቆም ይሁዳ እንደምክንያት ባይሆን ኖሮ የጌታችን የሰውን ልጅ የማዳን ሥራ በምን ዓይነት መንገድ ይፈጸም ነበር? እንደተማርኩት ከሆነ ጌታችን በባህርይው አስገዳጅ ስለሌለው የሰውን ልጅ የማዳን ሥራ የፈጸመው በፈቃዱ ነው፡፡ ይህ ከሆነ ይሁዳና ሌሎች በስቅለቱ ላይ የተባበሩት አይሁዳውያን ጥፋታቸው ምኑ ላይ ነው?

እባካችሁ ምስጢሩን እንዲገልጽልኝ በጸሎታችሁ አስቡኝ፡፡

ምኅርካ ድንግል
ከአዲስ አበባ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሀዱ አምላክ አሜን ፡፡

በመጀመሪያ ይህንን አድራሻ ያገኘሁት ለጉዞ ካዘጋጃችሁት ትኬት ላይ ነው ፡፡ በወቅቱ በጐዞው ላይ ለመሳተፍ ባለመቻሌ ጥያቄዬን ማቅረብ አልቻልኩም እናም ከተቻለ ለዚህ አወዛጋቢ ለሆነብኝ ጥያቄ መልስ እንደምትሰጡኝ ተስፋ በማድረግ ጥያቄዬን አቅርቤያለሁ፡፡

ጥያቄ አንድ ፡ በዕድሜ የሚበላለጡ ጥንዶች ለትዳር መተጫጨት ይችላሉ?
ጥያቄ ሁለት ፡ የሚችሉ ከሆነ የዕድሜው ልዩነት ከ _ እስከ ይኖረዋል?
ጥያቄ ሦስት ፡ በአብዛኛው የተለመደው ወንዱ ከሴቷ በዕድሜ የበለጠ ነው፡፡ እኔን ደግሞ ያጋጠመኝ ሴቷ (እኔ) ከወንዱ በ 5 ዓመት የምበልጠው ሲሆን የፍቅር ጥያቄውን በዚህ
ምክንያት ለመመለስ አልቻልኩም ፡፡ እግዚአብሔር ሄዋንን ከአዳም ጐን ሲያበጃት (ሲፈጥራት) ቀድሞ አዳም ተፈጥሮ ነበርና በእኔ መረዳት ግማሽ አካሌ ነው ለማለት ከእኔ በፊት መፈጠር አለበት የሚል ግንዛቤ ስለወሰድኩ ነው፡፡
ጥያቄ አራት ፡ ድንግልናውን/ዋን የጠበቀ/ች ድንግልናውን/ዋን ካልጠበቀ/ች ጋር ትዳር መመስረት ይችላሉ? ከቻሉስ የተክሊል ስርአት ሊፈጸምላቸው ይችላል?

ስለምትሰጡኝ ትክክለኛ ምላሽ ከወዲሁ በእግዚአብሔር ስም ላመሰግናችሁ እወዳለሁ ፡፡ እግዚአብሔር ለሁላችንም አስተዋይ ልቦናን ይስጠን አሜን ፡፡

 

ዘፈን ስለ መዋደድ፣ መተሳሰብ፣ ሀገር ፍቅር ከሆነ ችግር የለውም ይባላል፤ እንዴት ነው? ባጠቃላይ ዘፈን በቤተ ክርስቲያን እንዴት ይገለጻል?

 

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሀዱ አምላክ አሜን ፡፡

1. አስራትና በኩራት መስጠት የሚቻለው ለአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ብቻ ነው ወይስ ለተቸገሩ የትኛውም ገዳማት እና አድባራት መስጠት ይቻላል?
2. በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እግርን አነባብሮ መቀመጥ አይቻልም የሚባለው ከአክብሮት አንጻር ብቻ ነው ወይስ ሌላ ምክንያት አለው?
3. አንድ ወንድ ህልመ ሌሊት ከታየው በኋላ ወደ ቤተ ክርስቲያን መሔድ የሚችለው መቼ ነው (መቅደስ ገብቶ ማስቀደስ የሚችለው)?


በሰላም ለጉዞው አድርሶን የበረከቱ ተካፋይ ያድርገን አሜን!!


 


ሐዊረ ሕይወት ማለት…

ይህ ሁለት ቃል ተናቦ ፫ ሱባዔ (፳፩) ትርጉምን ይሰጠናል።
፩.    ቃል በቃል የሕይወት ጉዞ ማለት ነው።
፪.    የሕይወት ኑሮ ማለት ይሆናል።
“ሕይወት እንተ አልባቲ ሞት = ሞት የሌለባት የሕይወት ፍሬ/ኑሮ።” ዕዝ. ሱቱ. ፭፥፲፫
ደግሞም “ይኄይስ መዊት እመራር ሕይወት = ከመራር ኑሮ ሞት ይሻላል።” ሢራ ፴፥፲፯
፫.    የመዳን ጉዞ፣ ወይም የደኅንነት ጉዞ፣
“ዛቲ ይእቲ ቀዳሚት ሕይወት = ይህች የመጀመሪያዋ ትንሣኤ ድኅነት ናት።” ራእ ፳፥፭
ደግሞም “መጻእኪ ለሕይወትኪ = ለሕይወትሽ፣ ለደኅንነትሽ መጣሽ።” ዮዲ. ፲፮፥፫
፬.    የፈውስ ጉዞ፣ ወይም የጤንነት ጉዞ፣
“ወሰሚዖሙ ሕይወተ እሙታን = ከሙታን ተለይቶ መነሣትንም በሰሙ ጊዜ” ግ.ሐዋ. ፲፯፥፴፪
፭.    የመኖር ጉዞ፣

፮.    የመሥራት ጉዞ፣
“ዘለዓለም ዘየሐውር በጽድቅ = ለዘለዓለም ሕግን የሚሠራ” ኢሳ. ፴፫፥፲፭
፯.    የዕድሜ ልክ ጉዞ
“እሴብሖ ለእግዚአብሔር በሕይወትየ = በሕይወቴ ዘመን ሁሉ እግዚአብሔርን አመሰግነዋለሁ።” መዝ ፻፵፭፥፪
፰.    የትንሣኤ ወይም የመታደስ ጉዞ፣
፱.    የጸሎተ ምሕላ ወይም የመማፀን የምጥንታ ጉዞ
፲.    የደስታ ጉዞ “ሐይወ ልቡ ወነፍሱ ለያዕቆብ = የያዕቆብ ልቡናው ሰውነቱ ደስ አላት ታደሰች።” ዘፍ ፵፭፥፳፮
፲፩.    የነፍስ ጉዳይ ጉዞ፣ ወይም የሰውነት ጥበቃ ጉዞ
፲፪.    መልአካዊ ጉዞ
፲፫.    ክርስቶሳዊ ጉዞ
፲፬.    የአካላዊ ሕይወት፣ የልብሰ ሕይወት፣ የእሳተ ሕይወት፣ የብርሃነ ሕይወት፣ የመንፈስ ቅዱስ ጉዞ፣
፲፭.    የክርስቲያን ጉዞ
፲፮.    የቀና ልብ ወይም የመልካም ሐሳብ ጉዞ
፲፯.    የነፍስ ዕውቀት ማለት የብልኅነት ጉዞ
፲፰.    የትዕግሥት፣ የጸጥታ ጉዞ
፲፱.    ትምህርታዊ ጉዞ
፳.     የመንፈሳዊ ፈቃድ ጉዞ
፳፩.    የምክር፣ የጉባኤ ጉዞ
፳፪.    የሥልጣናዊ ምርጫ የችሎታ ጉዞ ማለት ሁሉ ነው።

 

hawir hiwot

===== ዜና ሐዊረ ሕይወት ======

hawir hiwot
የሐዊረ ሕይወት ጉዞ አዘጋጅ ኮሚቴ ወደ ደብረ ኤዶም ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን በመሄድ የመንገዱንና የቦታውን ምቹነት አረጋግጦ መጣ፡፡
ዝግጅቱ በከፍተኛ ሁኔታ እየተከናወነ ሲሆን የትኬት ሥርጭቱም በመጠናቀቅ ላይ ይገኛል፡፡


አጫጭር መረጃዎች

 

ደብረ ኤዶም ቅዱስ ገብርኤል፡-

 

ቦታው : ከአዲስ አበባ ወደ አምቦ መስመር ላይ 40(?) ኪ.ሜ ርቀት ላይ የሚገኝ ሲሆን የመንገዱ ጥራት ለማንኛውም ተጓዥ ምቹ መሆኑ ታይቷል፡፡

የእግር መንገድ? መኪና እስከ ቤተክርስቲያኑ የሚደርስ በመሆኑ የእግር መንገድ አይኖረውም፡፡ ይህም የዐቅም እና የጤና ችግር ላለባቸው ጥሩ ዜና ነው፡፡\

የመኪና ማቆሚያ? እስካሁን ከተደረጉት ጉዞዎች ከ100 በላይ መኪና ሊያስተናግድ የሚችል ሰፊና ውብ የሆነ ቦታ እንዳለው ተረጋግጧል፡፡


የተዘጋጁ ትኬቶች ስንት ናቸው? የተጓዥ ብዛትስ?

5000 ቲኬቶች ተዘጋጅተዋል(ካለፈው ዓመት በአንድ ሺህ ቁጥር ጭማሪ ይኖረዋል)፡፡በመሆኑም በዚህ ጉዞ ከአስተናጋጆች ጋር ከ5500 በላይ ተሣታፊዎች እነደሚኖሩ ይጠበቃል፡፡

የትኬት ሥርጭት፡- የተዘጋጁት ትኬቶች ውስጥ 4800 በላይ ትኬቶች ከአዘጋጅ ኮሚቴው እጅ የተሰራጩ ሲሆን ሽያጩም ካለው ጊዜ አኳያ በሚያስገርም ሁኔታ በፍጥነት በመከናወን ላይ ይገኛል፡፡hawir hiwot 2005

ስንት አሰተናጋጆች ይኖራሉ? ይህን ጉዞ ስኬታማ ለማድረግ ከአበው ጸሎት ጋር ትኬት በመሸጥ ፣ በምግብ ዝግጅት፣ በመኪና ላይ መስተንግዶ፣ በመዝሙር ፣በሕክምና በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ ኤሌክትሪክ፣ጽህፈት እና ሌሎችም ከ400 በላይ አገልጋዮች ይኖራሉ፡፡

ትኬቱ የት ይገኛል?
በማስታወቂያ በተገለጹበት ቦታዎችና እንዲሁም በየወረዳ ማእከላቱ ይገኛል፡፡ ከጥቂት ቀናት በኋላ በማኅበሩ ሕንጻ ላይ የሚሸጠው ትኬት ይጠናቀቃል፡፡
ምን ዝግጅቶች አሉ?

ምግብ፡- ለተጓዦች የሚስማማ ምግብ እየተዘጋጀ ሲሆን በጥንቃቄ ለሁሉም ጤና በሚስማማ መልኩ የሚዘጋጅ ይሆናል፡፡
ድንኳን፡– ከ5000 – 6000 ሰው የሚይዝ ድንኳን ይዘጋጃል፡፡
ጀኔሬተር፡ መብራት ቢጠፋ ለመጠቀም የሚያስችል ጀኔሬተር ይኖራል፡፡
ሕክምና፡- በጉዞው ላይም ሆነ በቦታው ለሚፈጠሩ የጤና ችግር ልዩ የሕክምና ቡድን ከአስፈላጊ መድሃኒቶችና የሕክምና መሳሪያ ጋር ይኖራል፡፡
ቀጥታ ሥርጭት፡- ሥርጭቱ በመላው ዓለም ለሚገኙ ምዕመናን ከስፍራው በቀጥታ ለማስተላለፍ ዝግጅት ይደረጋል፡፡

ማሳሰቢያ፡- ከአ.አ ውጭ ያሉ ተጓዦች ከወዲሁ ትኬት ሣያልቅ እንዲመዘገቡ ጥሪ እናስተላልፋለን፡፡

ባለፈው ዓመት ከአ.አ ውጭ ከሰንዳፋ፣ ወሊሶ፣ አምቦ፣ ጅማ፣ ደ/ዘይት፣ ሞጆ፣ ባህር ዳር፣ መቀሌ፣ ደሴ፣ አፋር አዳማ(ናዝሬት)በርካታ ተጓዦች እነደነበሩ ይታወሳል፡፡

የአዘጋጅ ኮሚቴው ስጋት! በባለፉት ጉዞዎች እንደታየው ትኬቱ አስቀድሞ ስለሚያልቅ ትኬት ፈላጊ ምዕመናንን ማስተናገድ አለመቻል ነው፡፡

ማሳሰቢያ፡- በክርስቲያናዊ ሕይወትዎ እንዲመለስልዎት የሚፈልጉትን ማንኛውንም ጥያቄ በe-mail፡ hawirehiywot@yahoo.com አድራሻ ያቅርቡ፡፡ አባቶች በዕለቱ ከልምዳቸው በመነሳት መልስ ይሰጥዎታል፡፡ (hawirehiywot@yahoo.com)

ልብ ይበሉ! መረጃዎችን መከታተል ትኬቱን ይዞ ነው!

የድምጽ ማስታወቂያውን ለማድመጥ እዚህ ይጫኑ!

++++++ በጸሎትዎ ያስቡን! ++++++