አስተርእዮ

በመምህር  ለማ በእርሱፈቃድ

ጥር ፲ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

አስተርእዮ ማለት መታየት፣ መገለጥ  የመሳሰሉትን ፍች ይይዛል፡፡ ቃሉ አስተርአየ ታየ፤ ተገለጠ ከሚለው የግእዝ ግሥ የተገኘ ነው፡፡ የጥር ወር በሙሉ ዘመነ አስተርእዮ በመባል ይታወቃል፡፡ ምክንያቱም ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በገባው ቃል ኪዳን መሠረት በሥጋ የተገለጠበት (የታየበት) ወቅት በመኾኑ ከልደት በዓል እስከ ጥር መጨረሻ ያለው ጊዜ ዘመነ አስተርእዮ ይባላል፡፡ ይህ ብቻም ሳይኾን የእግዚአብሔር አንድነት፣ ሦስትነት የተገለጠው በዚሁ ወር ነውና ወቅቱ ዘመነ አስተርእዮ ተብሎ ይጠራል፡፡ በዚህ ጽሑፍ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውን ልጅ ሥጋ ለብሶ የመታየቱ (የመገለጡ) ዋና ዋና ምክንያቶችን ምንድን ናቸው የሚሉ ነጥቦችን በአጭሩ እንመለከታለን፤

፩. የገባውን ቃል ኪዳን ይፈጽም ዘንድ

እግዚአብሔር አምላካችን ሰውን በምሳሌው ፈጥሮ የሚያስፈልገውን ዅሉ አዘጋጅቶ በክብር ይኖር ዘንድ ገነትን አወረሰው፡፡ በማየት የሚደሰትበትና የሚማርበትንም ሥነ ፍጥረትን ፈጠረለት፤ የሚበላውንና የማይበላውንም ለይቶ ሰጠው፡፡ ነገር ግን አትብላ የሚለውን አምላካዊ ትእዛዝ ሳይጠብቅ የተከለከለውን ዕፀ በለስ በመብላቱ ምክንያት ከገነት ተባረረ /ዘፍ.፪፥፲፮/፡፡ በዚያን ጊዜ ነው ርኅራኄ የባሕርዩ የኾነ አምላካችን ‹‹ከአምስት ሺሕ አምስት መቶ ዘመን በኋላ ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለው›› የሚለውን የተስፋ ቃል ኪዳን ለአዳም የሰጠው /ሲራ.፳፬፥፮/፡፡

ነቢያቱም ‹‹ጌታ ራሱ ምልክትን ይሰጣችኋል፤ እነሆ ድንግል ትፀንሳለች፤ ወንድ ልጅም ትወልዳለች፡፡ ስሙንምአማኑኤል› ብላ ትጠራዋለች፤›› እያሉ ትንቢት ሲናገሩ ቆይተዋል /ኢሳ.፯፥፲፬/፡፡ አዳምም ከነልጆቹ ለአምስት ሺሕ አምስት መቶ ዘመናት ይህንን ቃል ኪዳን ሲጠባበቅ ኖሯል፡፡ ‹‹ቁጣው እስኪያልፍ ድረስ ጥቂት ጊዜ ተሸሸግ፤›› ተብሎ እንደ ተጻፈው /ኢሳ.፳፮፥፳/፣ ይህችን ቃል ኪዳን ይፈጽማት ዘንድ ወልደ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ በተለየ አካሉ በሥጋ ተገለጠ ማለት ሥጋን ተዋሐደ፡፡

፪. የዲያብሎስን ሥራ ያፈርስ ዘንድ

‹‹ወዘሰ ይገብራ ለኀጢአት እምነ ጋኔን ውእቱ እስመ ቀዳሚሁ ለሰይጣን አበሰ ወበእንተ ዝንቱ አስተርአየ ወልደ እግዚአብሔር ከመ ይስዐር ግብሮ ለጋኔን፤ ኀጢአትን የሚሠራትም ከዲያብሎስ ወገን ነው፡፡ ጥንቱንም ሰይጣን በድሎአልና ስለዚህ የእግዚአብሔር ልጅ በሥጋ ተገለጠ፡፡ የዲያብሎስን ሥራ ይሽር ዘንድ፤›› በማለት ሐዋርያው እንደ ገለጸው /፩ኛዮሐ.፫፥፰/፣ ሰይጣን የሰውን ልጅ እግዚአብሔርን ያህል ጌታ፣ ገነትን የመሰለ ቦታ እንዲያጣ፤ ከደስታ ወደ ዘለዓለም ኀዘን፣ ከነጻነት ወደ ግዞት፣ ከብርሃን ወደ ጨለማ እንዲገባ ረቂቅ ሥራ ሠርቶ ነበርና ይህንን የዲያብሎስን ሥራ ያፈርስ ዘንድ እግዚአብሔር በሥጋ ተገለጠ፡፡

ዲያብሎስ በሥጋ ከይሲ (በእባብ ሥጋ) ተሰውሮ ነገት ገብቶ አዳምና ሔዋንን እንዳሳተ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም የሰውን ልጅ ሥጋ ተዋሕዶ የዲያብሎስን ሥራ አፍርሶበታል፡፡ ዲያብሎስ አዳምና ሔዋንን አስቶ የግብር ልጆቹ ይኾኑ ዘንድ ‹‹አዳም ገብሩ ለዲያብሎስ ሔዋን አመቱ ለደያብሎስ›› ብለው የፈረሙትን ደብዳቤ፣ በዮርዳኖስና በሲዖል የቀበረውን የጥፋት የተንኮል ሥራውን ያፈርስ ዘንድ አምላክ ሰው ኾኖ ተገለጠ፡፡

ይህንን የዲያብሎስ ሥራም በዮርዳኖስ ባሕር የተቀበረውን በጥምቀቱ፤ በሲዖል የተቀበረውን በስቅለቱ፣ በሞቱ ደምስሶበታልና ‹‹ወነሰተ ዐረፍተ ማእከል እንተ ጽልዕ በሥጋሁ፤ በመካከል የነበረውን የጥል ግድግዳ በለበሰው ሥጋ አፈረሰው፤›› በማለት ሐዋርያው እንደ ተናገረው /ኤፌ.፪፥፲፬/፣ የዲያብሎስን ክፉ ሥራ የጥል ግድግዳ ያፈርስ ዘንድ ክርስቶስ በሥጋ ተገለጠ፡፡

፫. አንድነቱን፣ ሦስትነቱን ይገልጥ ዘንድ

የምሥጢረ ሥላሴ ትምህርት በብሉይ ኪዳን ዘመን በግልጥ አይታወቅም ነበር፡፡ የተገለጠ፣ የታወቀ፣ የተረዳ የአንድነቱን፣ የሦስትነቱን ትምህርት በሚገባ ለማስተማር የተቻለው ጌታችን ሥጋ ለብሶ ከተጠመቀ ጊዜ ጀምሮ ነው፡፡ ‹‹ወርእየ መንፈሰ እግዚአብሔር እንዘ ይወርድ በአምሳለ ርግብ ወናሁ መጽአ ቃል እምሰማይ ዘይብል ዝንቱ ውእቱ ወልድየ ዘአፈቅር ዘቦቱ ሠመርኩ፤ የእግዚአብሔር መንፈስ በርግብ አምሳል በራሱ ላይ ሲቀመጥ አየ፡፡ እግዚአብሔር አብ በደመናየምወደው፣ ለመሥዋዕትነት የመረጥኩት ልጄ ይህ ነው› አለ፤›› ተብሎ እንደ ተጻፈ /ማቴ.፫፥፲፯፤ ሉቃ.፫፥፳፩/፣ ጌታችን የአዳምና የሔዋንን የዕዳ ደብዳቤ ለመሻር በዮርዳኖስ ወንዝ በተጠመቀ ጊዜ የአንድነት እና ሦስትነት ምሥጢር ተገልጿል፡፡ ይህ ምሥጢር ከጥንተ ዓለም ጀምሮ በግልጽ ሳይታወቅ፣ ሳይገለጥ ተሰውሮ ይኖር ነበር፡፡ ‹‹በእንተ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘኅቡእ ኅርመቱ እምቅድመ ዓለም፤ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ዓለም ሳይፈጠር ተሰውሮ ነበር፡፡ ከነቢያት ቃል የተነሣ በዚህ ዘመን ተገለጠ፤›› እንዲል /ሮሜ.፲፮፥፳፬/፡፡

፬. ፈጽሞ እንደ ወደደን ለመግለጽ

እግዚብሔር ሰውን ምን ያህል እንደ ወደደው ለመረዳት እግዚብሔር ዓለምን ከፈጠረበት ጥበቡ ይልቅ ዓለምን ያዳነበት ጥበቡን በሚገባ መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም ዓለምን ከፈጠረበት ጥበቡ ይልቅ ያዳነበት ጥበቡ እጅግ ዕፁብ ድንቅ ነውና፡፡ ማንም ሳያስገድደው፤ ሰው ኹን ብሎ ሳይጠይቀው በገባው ቃል ኪዳን መሠረት ዘመኑን ጠብቆ እግዚአብሔር ሰው ኾኖ ከኀጢአት በስተቀር ዅሉን ፈጽሞ፣ በገዛ ፈቃዱ መከራ ሥጋን ተቀብሎቈ ሥጋውን ቈርሶ፣ ደሙን አፍሶ የዘለዓለም ሕይወትን ለሰው ልጅ በመስጠቱ ምን ያህል ፍጹም ፍቅሩን እንደ ገለጸልን እንረዳለን፡፡ ‹‹አልቦ ዘየዐቢ እምዝ ፍቅር ከመ ዘቦ ዘይሜጡ ነፍሶ ህየንተ አእርክቲሁ፤ ስለ ወዳጆቹ ሕይወቱን አሳልፎ የሚሰጥ ያለ እንደ ኾነ ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር የለም፤›› እንዳለ ወንጌላዊው /ዮሐ.፲፭፥፲፪/፡፡

በደል የሠራው የሰው ልጅ ይሰቀል ይሙት ሳይል እኔ ልሙት ማለቱ የእግዚአብሔር የፍጹም ፍቅሩ መገለጫ ነው፡፡ ሰው ሰውን የሚወደው ገንዘቡንና የመሳሰሉትን እስከ መስጠት ሊኾን ይችላል፡፡ ሕይወቱን እስከ መስጠት የሚወድ ማንም የለም፤ አልነበረም፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የወደደውን የሰውን ሥጋ ለብሶ መኪራ ሥጋን ተቀብሎ ሰውን በሞቱ ያድን ዘንድ ሞትን የሞተው ፈጽሞ እንደ ወደደን ለመግለጥ ነው /፩ኛዮሐ.፬፥፱/፡፡ ይህም ፍቅሩ ይቃወቅ ዘንድም በሥጋ ተገለጠ፡፡ ስለዚህም ሊቃውንቱ ይህንን ወቅት ‹‹አስተርእዮ›› በማለት ሰይመውታል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ማስገንዘቢያ፡- ይህ ትምህርት ጥርቀን ፳፻፭ .ም በድረ ገጻችን ቀርቦ ነበር፡፡

አስተርእዮተ እግዚአብሔር በፈለገ ዮርዳኖስ

bb

ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲጠመቅ

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

ጥር ቀን ፳፻፱ .

የተወደዳችሁ የድረ ገጻችን ተከታታዮች! እንደሚታወቀው በየዓመቱ ጥር ፲፩ ቀን በዓለ ጥምቀትን እናከብራለን፡፡ በቅድሚያ ለብርሃነ ጥምቀቱ እንኳን በሰላም አደረሳችሁ እያልን በዛሬው ዝግጅታችን እግዚአብሔር አምላካችን በሐዲስ ኪዳን ካደረጋቸው መገለጦች ወይም ከታየባቸው መንገዶች መካከል በዮርዳኖስ ወንዝ ያደረገው መገለጥ (አስተርእዮ) አንደኛው መኾኑን የሚያስገነዝብ ትምህርት በአጭሩ ይዘን ቀርበናል፤

‹‹አስተርእዮ›› የሚለው ቃል ‹‹አስተርአየ (አርአየ) = አሳየ፣ ገለጠ፣ ታየ፣ ተገለጠ›› ከሚለው የግእዝ ግስ የተገኘ ሲኾን፣ ትርጕሙም ‹‹መታየት፣ መገለጥ፣ ማሳየት፣ መግለጥ›› ማለት ነው /የኪዳነ ወልድ ክፍሌ መዝገበ ቃላት/፡፡ ‹‹አስተርእዮተ እግዚአብሔር በፈለገ ዮርዳኖስ›› የሚለው ሐረግም ‹‹የእግዚአብሔር በዮርዳኖስ ወንዝ መገለጥ፣ መታየት›› የሚል ትርጕም አለው፡፡

ከዚህ ላይ ‹‹አስተርእዮተ እግዚአብሔር›› ስንል የአብ፣ የወልድ፣ የመንፈስ ቅዱስ መገለጥ ማለታችን መኾኑን ለማስታዎስ እንወዳለን፡፡ ‹‹እግዚአብሔር›› የሚለው ቃል ሦስቱም አካላት (ቅድስት ሥላሴ) በጋራ የሚጠሩበት መለኮታዊ ስያሜ ነውና፡፡ ‹‹አንሰ ሶበ እቤእግዚአብሔር እብል በእንተ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ከመ በአሐዱ ስም ሥሉሰ ያምልኩ፤ እኔ እግዚአብሔር በአልሁ ጊዜ ስለ አብም፣ ስለ ወልድም፣ ስለ መንፈስ ቅዱስም እናገራለሁ፤ (ምእመናን) በአንዱ ስም (በእግዚአብሔር) ሦስቱ አካላትን ያመልኩ ዘንድ፤›› እንዳለ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ነባቤ መለኮት /ሃይማኖተ አበው/፡፡

ቅዱሳት መጻሕፍት እንደሚነግሩን እግዚአብሔር አምላክ በብሉይም ኾነ በሐዲስ ኪዳን በአንድነቱ በሦስትነቱ በግብር (በሥራ)፣ በራእይና በገቢረ ተአምራት በልዩ ልዩ መንገድ ለቅዱሳኑ ተገልጧል፡፡

በብሉይ ኪዳን ልዩ ልዩ ምልክት በማሳየት፤ በቅዱሳን ነቢያትና በመሳፍንት፣ በነገሥታት፣ በካህናትና በነቢያት ላይ በማደር ወይም በራእይ በማነጋገር፤ በተጨማሪም በጻድቃኑ ላይ ቸርነቱን በማሳየት፣ በክፉ አድራጊዎች ላይ ደግሞ ኀይሉን በማሳየት ሲያደርጋቸው በነበሩ ተአምራቱና ሥራዎቹ ይገለጥ ነበር፡፡

በሐዲስ ኪዳን ደግሞ ለአዳምና ለልጆቹ በገባው ቃል መሠረት የሰውን ሥጋ ለብሶ፣ በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ በአካለ ሥጋ ተገልጦ በገቢረ ተአምራቱ፣ በትንሣኤውና በዕርገቱ አምላክነቱን አሳይቷል፡፡

የብሉይ ኪዳኑ መገለጥ በምልክት፣ በራእይ፣ በድምፅና በመሳሰሉት መንገዶች የተደረገ መገለጥ ነበር፤ የሐዲስ ኪዳኑ መገለጥ ግን ወንጌላዊው ዮሐንስ ‹‹መቼም ቢኾን እግዚአብሔርን ያየው አንድ ስንኳ የለም፤ በአባቱ እቅፍ ያለ አንድ ልጁ እርሱ ተረከው›› /ዮሐ.፩፥፲፰/ በማለት እንደ ገለጸው አምላካችንን በዓይነ ሥጋ ያየንበት አስተርእዮ ስለ ኾነ ከመገለጦች ኹሉ የተለየ ጥልቅ ምሥጢር አለው፡፡

ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እግዚአብሔር በሥጋ ያደረገውን አስተርእዮ (መገለጥ) ከምሥጢረ ሥላሴ ጋር በተያያዘ መልኩ በሦስት መንገድ ይገልጹታል፤ ይኸውም በእመቤታችን ማኅፀን፤ በዮርዳኖስ ወንዝ እና በደብረ ታቦር ተራራ ላይ እንደ ኾነ ያስረዳሉ፡፡

ይህንንም ‹‹በላዕሌኪ ወበዮርዳኖስ ወበታቦር ሥልሰ ጊዜያተ፤ ዘአልቦ ተውሳከ ወአልቦ ሕጸተ፤ ለውሉደ ሰብእ ያርኢ ዘሥላሴሁ ገጻተ፤ ጽጌኪ ድንግል ተአምሪሁ ከሠተ፤ ወበፀዳሉ አብርሀ ጽልመተ፡፡›› በማለት ይገልጹታል /ማኅሌተ ጽጌ/፡፡

ትርጕሙም ‹‹እግዚአብሔር አምላክ ጭማሬም ጉድለትም የሌለበትን ሦስትነቱን ለሰው ልጆች ያሳይ ዘንድ በአንቺ (በእመቤታችን በድንግል ማርያም) በዮርዳኖስ እና በደብረ ታቦር ሦስት ጊዜ በመገለጥ አበባሽ (ልጅሽ) ኢየሱስ ክርስቶስ ተአምራቱን (አምላክነቱን፣ ብርሃነ መለኮቱን፣ አንድነቱን፣ ሦስትነቱን) አሳየ፡፡ በብርሃነ መለኮቱም ጨለማውን አስወገደ (ብርሃን አደረገ)›› ማለት ነው፡፡

ይህም ጌታችን በለበሰው ሥጋ በእመቤታችን ማኅፀን ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን መወሰኑን በዮርዳኖስ ወንዝ በተጠመቀበት ዕለት ምሥጢረ ሥላሴን መግለጡን (እግዚአብሔር አብ ‹‹የምወደው ልጄ እርሱ ነው፤ እርሱን ስሙት›› ብሎ  ሲመሰክር፣ መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል ወርዶ ራሱ ላይ ሲያርፍ ማለት ነው)፤ እንደዚሁም በደብረ ታቦር ብርሃነ መለኮቱን ሲገልጥ መለኮታዊ አንድነቱና አካላዊ ሦስትነቱ መታወቁን ያመለክታል፡፡

በአጭሩ ይህ ድርሰት እግዚአብሔር በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፣ በዮርዳኖስና በደብረ ታቦር ላይ ያደረገውን አስተርእዮ የሚገልጽ ነው፡፡ ይህ ትምህርትም ጥር ፲፩ ቀን በሚነበበው መጽሐፈ ስንክሳር በተመሳሳይ መልኩ ተጠቅሷል፡፡

ክብር ይግባውና በአካለ ሥጋ የተገለጠው እግዚአብሔር ወልድ (ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ) እከብር አይል አምላከ ክቡራን፣ አክባሬ ፍጥረታት፤ እቀደስ አይል አምላከ ቅዱሳን፣ ቀዳሴ ፍጥረታት ኾኖ ሳለ ለኛ የጥምቀትን ሥርዓት ሊሠራልን ሥጋ ከለበሰ ሠላሳ ዓመት ሲሞላው በመጥምቀ መለኮት በቅዱስ ዮሐንስ እጅ በዮርዳኖስ ወንዝ ተጠመቀ፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተጠምቆ ከወንዙ ሲወጣም እነሆ ሰማያት ተከፈቱ፤ መንፈስ ቅዱስም በርግብ አምሳል ወርዶ በራሱ ላይ ተቀመጠ፡፡ በዚህ ጊዜ የሚሰሙትን ዅሉ ያስደነገጠ፣ ምድራዊ ፍጥረት ሊሸከመው የማይቻል ‹‹ዝንቱ ውእቱ ወልድየ ዘአፈቅር ዘሎቱ ሠመርኩ፤ በእርሱ ደስ የሚለኝ፣ ልመለክበት የወደድሁት፣ ለተዋሕዶ የመረጥሁት ልጄ ይህ ነው!›› የሚል ግሩም ቃል ከሰማይ መጣ /ማቴ.፫፥፲፯/፡፡

ይህ እግዚአብሔር አብ የኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ አባት መኾኑን የመሰከረበት ቃልም ጌታችን ብርሃነ መለኮቱን በደብረ ታቦር በገለጠበት ዕለት በተመሳሳይ መንገድ ተነግሯል /ማቴ.፲፯፥፭፤ ሉቃ. ፱፥፴፮፤ ፪ኛ ጴጥ.፩፥፲፯/፡፡ ከዚህ በፊት በልዩ ልዩ ምሳሌና ኅብር ሲገለጥ የነበረ ምሥጢረ ሥላሴ በዮርዳኖስ ወንዝ በግልጥ ታየ፤ እግዚአብሔር ወልድ በለበሰው ሥጋ በዮርዳኖስ ወንዝ ሲጠመቅ፤ እግዚአብሔር አብ ‹‹የምወደው ልጄ ይህ ነው›› ብሎ አባትነቱን ሲመሰከር፤ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስም በርግብ አምሳል ከሰማይ ወርዶ በራሱ ላይ ሲያርፍ ፍጡራን በዓይናቸው አዩ፡፡

ይህንን ድንቅ ምሥጢር የተመለከቱ ዅሉ የእግዚአብሔርን ሥራ አደነቁ፤ በአምላክነቱም አመኑ፡፡ ሰይጣን ልቡናቸውን ያሸፈተባቸው መናፍቃን ግን በክርስቶስ የባሕርይ አምላክነት ባለማመናቸው የተነሣ ለክብሩ በማይመጥን የአማላጅነት ቦታ ያስቀምጡታል፡፡ እኛ ግን ቅዱሳን ሐዋርያት እንዳስተማሩን፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንም እንዳስረዱን አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ አንድ መለኮት፣ አንድ ሥልጣን፣ አንድ አገዛዝ አላቸው፤ ኢየሱስ ክርስቶስም ከሦስቱ አካላት አንዱ አካል እግዚአብሔር፣ በሦስትነት በአንድነት የሚመለክ፣ አምላክ ወልደ አምላክ ነው ብለን እናምናለን፤ አምነንም እንመሰክራለን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ዕርገተ ኤልያስ ነቢይ

elias

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

ጥር ፭ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በየዓመቱ ታኅሣሥ ፩ ቀን የነቢዩ ኤልያስን በዓለ ልደት፤ ጥር ፮ ቀን ደግሞ ዕለተ ዕርገቱን በመንፈሳዊ ሥርዓት ታከብራለች፡፡ የነቢዩን ታሪክ በአጭሩ ለማስታወስ ያህልም የሚከተለውን ዝግጅት አቅርበናል፤

ነቢዩ ኤልያስ በገለአድ አውራጃ በቴስብያ፣ በእግዚአብሔር ትእዛዝና ሕግ ጸንተው ይኖሩ ከነበሩ ጻድቃን ወላጆቹ ከሌዊ ወገን ከሚኾን አባቱ ከኢያሴንዩ እና ከእናቱ ቶና ታኅሣሥ ፩ ቀን ተወለደ፡፡ በተወለደ ጊዜም እግዚአብሔር ከእናቱ ማኅፀን ጀምሮ መርጦታልና መላእክተ ብርሃን ሰገዱለት፤ በጨርቅ ፈንታም በእሳት ጠቀለሉት፡፡ እናትና አባቱም በኹኔታው ከመፍራታቸው የተነሣ ወደ እርሱ መቅረብን ፈሩ፡፡ በስምንተኛው ቀን ሥርዓተ ግዝረት ሲፈጽሙለትም ስሙን ‹ኤልያስ› አሉት፡፡

ነቢዩ ኤልያስ ሕገ ኦሪትን እየተማረ ካደገ በኋላ እናቱንና አባቱን፣ ዘመዶቹንም፣ ገንዘቡንም ዅሉ ትቶ በበረሃ ተቀመጠ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ በዕብራውያን መልእክቱ ፲፩፥፴፯-፴፰ ‹‹… ማቅ፣ ምንጣፍና የፍየል ሌጦ ለብሰው ዞሩ፤ ተጨነቁ፤ ተቸገሩ፤ መከራ ተቀበሉ፤ ተራቡ፤ ተጠሙም፡፡ ዓለም የማይገባቸው እነዚህ ናቸው፤ ዱር ለዱርና ተራራ ለተራራ፣ ዋሻ ለዋሻና ፍርኩታ ለፍርኩታም ዞሩ፤›› በማለት እንደ ተገናረው ነቢዩም ከዓለማዊ ኑሮ ተለይቶ ማቅ ለብሶ በየተራራው፣ በየፍርኵታውና በየዋሻው መኖር ጀመረ /ገድለ ኤልያስ ነቢይ ዘታኅሣሥ፣ ቍ.፩-፱/፡፡

የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት እንደሚያስረዳው ‹‹ኤልያስ›› የሚለው ስም ‹‹እግዚአብሔር አምላክ ነው›› የሚል ትርጕም አለው፡፡ በመጽሐፈ ገድሉ እንደ ተጠቀሰው ደግሞ የስሙ ትርጓሜ ‹‹የወይራ ዘይት፣ የወይራ ተክል›› ማለት ነው፡፡ የወይራ ዘይት በጨለማ ላሉት ዅሉ እንዲያበራ ኤልያስም ለእግዚአብሔር ቤት መብራት ነውና፡፡ እስራኤላውያን ሕገ እግዚአብሔርን በመጣስ፣ ጣዖታትን በማምለክ ጨለማ በተዋጡ ጊዜ ነቢዩ ኤልያስ ደርሶ ሰማይን በመለጎም፣ የምንጮችን ውኃ በማድረቅና ሌሎችንም ድንቅ ድንቅ ተአምራት በማሳየት ልቡናቸውን ብሩህ አድርጎ ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር መልሷቸዋልና፡፡ ዳግመኛም ኤልያስ ማለት ‹‹ዘይት (ቅባት)፣ መፈቃቀር›› ማለት ነው፡፡ ዘይት (ቅባት) የተባለውም የሰው ፍቅር ሲኾን ይኸውም ነቢዩ ኤልያስ በገቢረ ተአምራቱ በእግዚአብሔርና በእስራኤል መካከል ሰላምንና ፍቅርን ማስፈኑን ያመላክታል /የገድለ ኤልያስ መቅድም፣ ቍ.፱-፲፱/፡፡

ነቢዩ በእግዚአብሔር ኀይል ካደረጋቸው ታላላቅ ተአምራት መካከልም ዝናም ማቆሙና ዳግመኛ እንዲዘንም ማድረጉ (፩ኛ ነገ.፲፯፥፩-፪፤ ፲፰፥፵፮-፵፰)፤ የደሃዋን ቤት በበረከት መሙላቱ (፩ኛ ነገ.፲፯፥፲፮-፳፬)፤ የሞተውን ልጅ ማስነሣቱ (፩ኛ ነገ.፲፯፥፳-፳፫)፤ በካህናተ ጣዖት ፊት መሥዋዕቱን ወደ እግዚአብሔር ማሳረጉና የጣዖቱ ካህናትን ማሳፈሩ (፩ኛ ነገ.፲፰፥፳-፵)፤ እና ጠላቶቹን በእሳት ማቃጠሉ (፪ኛ ነገ.፩፥፱-፲፫) ተጠቃሾች ናቸው፡፡

አንድ ቀን ነቢዩ ኤልያስ ጸሎት እያደረገ ሳለ መልአኩ ቅዱስ ራጉኤል ተገልጾ፡- ‹‹ኃላፊ፣ ጠፊ የኾኑ ሕሊናትን ያሸነፍህ፤ ሞትንም ድል ያደረግህ ተጋዳይ ሆይ ፈጽሞ ደስ ይበልህ፡፡ ወደ ሰማይ የምታርግበት ዘመን ደርሷልና፡፡ ፍጹም ደስታ፣ ፈገግታ፣ ተድላ ከሰፈነበት አገር ትኖራለህ፡፡ ደዌ፣ በሽታ፣ ሞት፣ ኀዘን ከሌለበት፤ በረከት፣ ከሞላበት ቤትም ትገባለህ፡፡ በዚያም የልዑል እግዚአብሔርን ትእዛዝ የሚጽፍ እንደ አንተ ያለ ሄኖክ አለ፡፡ አሁንም ተነሥና ዮርዳኖስን ተሻግረህ ሒድ›› አለው፡፡

እግዚአብሔር ኤልያስን ወደ ሰማይ የሚያሳርግበት ጊዜ ሲደርስም ነቢዩ ከጌልጌላ ተነሥቶ ወደ ኢያሪኮ ሲሔድ ደቀ መዝሙሩ ኤልሳዕ ‹‹በሕያው ነፍስህ እምላለሁ፤ አንተን አልለቅህም፤›› በማለት ተከትሎት ሔደ፡፡ ኢያሪኮ በደረሱ ጊዜም በኢያሪኮ ያሉ ደቂቀ ነቢያት መጡ፡፡ የኤልያስ ዕርገት በመንፈስ ቅዱስ ጥበብ ተገልጾላቸው ኤልሳዕን፡- ‹‹ዛሬ እግዚአብሔር ጌታህን ከአንተ እንደሚወስደው ታውቃለህን?›› አሉት፡፡ እርሱም፡- ‹‹አውቃለሁ፤ ዝም በሉ፤›› አላቸው፡፡ ከዚያም ኤልያስ ኤልሳዕን ‹‹እግዚአብሔር ወደ ዮርዳኖስ ልኮኛልና ከዚህ ተቀመጥ›› ባለው ጊዜ አሁንም ‹‹በሕያው ነፍስህ እምላለሁ፤ አንተን አልለቅህም፤›› በማለት አብሮት ሔደ፡፡

ከነቢያት ወገንም አምሳ ወንዶች ከእነርሱ ጋር በአንድነት ሔደው ከፊት ለፊታቸው ቆሙ፡፡ ኤልያስም በመጠምጠሚያው የዮርዳኖስን ውኀ ቢመታው ውኀው ከሁለት ተከፈለ፡፡ ኤልያስና ኤልሳዕም ወንዙን በደረቅ ተሻገሩ፡፡ ወጥተውም ከምድረ በዳ ቆሙ፡፡ ወንዙን ከተሻገሩ በኋላም ኤልያስ ደቀ መዝሙሩ ኤልሳዕን ‹‹ከአንተ ሳልወሰድ ላደርግልህ የምትፈልገውን ለምነኝ፤›› አለው፡፡ ኤልሳዕም ‹‹በአንተ ላይ ያደረው መንፈስ ቅዱስ እጥፍ ኾኖ በእኔ ላይ እንዲያድር ይኹን፤›› ብሎ መለሰ፡፡ ኤልያስም ‹‹ዕፁብ ነገርን ለመንኸኝ፡፡ ነገር ግን እኔ ከአንተ ተለይቼ በማርግበት ጊዜ ካየኸኝ እንዳልኸው ይደረግልሃል፡፡ በማርግበት ሰዓት ካላየኸኝ ግን አይደረግልህም፤›› አለው፡፡

ሁለቱም እየተነጋገሩ ሲሔዱ የእሳት ሠረገላ፣ የእሳት ፈረስ በመካከላቸው ገባና ለያያቸው፡፡ ኤልያስም በዐውሎ ነፋስ፣ በንውጽውጽታ፣ በእሳት ሠረገላ ዐረገ፡፡ ኤልሳዕም የኤልያስን ወደ ሰማይ መወሰድ አይቶ ጮኸ፤ ‹‹የእስራኤል ኀይላቸው፣ ጽንዓታቸው አባ፣ አባት ሆይ›› አለ፡፡ ከዚያ በኋላ ዳግመኛ አላየውም፡፡ ኤልያስም ልብሱን ከሁለት ከፈለው፡፡ መጠምጠሚያውንም ለኤልሳዕ ጣለለት፡፡ የኤልያስ ጸጋና በረከትም በኤልሳዕ ላይ አደረ፡፡

ይህም ምሳሌ ነው፤ ኤልያስ የዮርዳኖስን ወንዝ ተሻግሮ ወደ ብሔረ ሕያዋን እንደ ገባ ዅሉ፣ ከውኀና ከመንፈስ ቅዱስ የሚወለዱ ምእመናንም የእግዚአብሔርን መንግሥት ይወርሳሉ፡፡ ‹‹ዳግመኛ ያልተወለደ ሰው የእግዚአብሔርን መንግሥት ለማየት አይችልም፤›› እንዳለ ጌታችን በወንጌል /ዮሐ.፫፥፫/፡፡

በአጠቃላይ ነቢዩ ኤልያስ በዘመነ ኦሪት ከነበሩት ዐሥራ አምስቱ ነቢያት (ሙሴ፣ ኢያሱ፣ ሳሙኤል፣ ዮናታን፣ ጋድ፣ ዳዊት፣ ሰሎሞን፣ ኤልሳዕ፣ ዕዝራ፣ ኢሳይያስ፣ ዳንኤል፣ ኤርምያስ፣ ሕዝቅኤል እና መጥምቁ ዮሐንስ) መካከል አንደኛው ነቢይ ነው፡፡ ይህ ቅዱስ በአካለ ሥጋ ከጌታችን ጋር በደብረ ታቦር የተነጋገረ ነቢይ፤ የጣዖታትን መሥዋዕት አፈራርሶ ለልዑል እግዚአብሔር እውነተኛ መሥዋዕትን ያሳረገ ካህን፤ ሥርዓተ ምንኵስናን የጀመረ ባሕታዊ፤ ስለ እግዚአብሔር ለፍርድ መምጣት አስቀድሞ የሚሰብክ ሐዋርያ ነው /የገድለ ኤልያስ ነቢይ መቅድም፣ ቍ.፩-፮/፡፡

ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስን ታላቅነት ሲመሰክር ዮሐንስን ‹ኤልያስ› ብሎታል፡፡ ዮሐንስ ልብሱ የግመል ፀጉር እንደ ኾነ ዅሉ፣ ኤልያስም ፀጕራም መኾኑ፤ ሁለቱም መናንያን፣ ጸዋምያን፣ ተሐራምያን /ፈቃደ ሥጋን የተዉ/፣ ዝጉሐውያን /የሥጋን ስሜት የዘጉ/፣ ባሕታውያን መኾናቸው፤ በተጨማሪም ዮሐንስ ሄሮድስና ሄሮድያዳን እንደ ገሠፃቸው ዅሉ፣ ኤልያስም አክአብና ኤልዛቤልን መገሠፁ፤ ዮሐንስ ከክርስቶስ ቀዳሚ ምጽአት /በአካለ በሥጋ መገለጥ/ አስቀድሞ እንዳስተማረ ዅሉ፣ ኤልያስም ከክርስቶስ ዳግም ምጽአት አስቀድሞ የሚያስተምር መኾኑ ያመሳስላቸዋልና ጌታችን ዮሐንስን ‹ኤልያስ› ብሎ ጠርቶታል /ትርጓሜ ወንጌል፣ ማቴ.፲፩፥፲፬፤ ፲፯፥፲-፲፫/፡፡

መምህራነ ቤተ ክርስቲያን እንዳስተማሩን ነቢዩ ኤልያስ ከጌታችን ዳግም ምጽአት አስቀድሞ የእግዚአብሔርን መንግሥት ለዓለም በመስበክ በሰማዕትነት ይሞታል፡፡ አንዳንዶቹ ይህንን ትምህርት ይዘው ‹‹ኤልያስ መጥቷል›› እያሉ ምእመናንን ያሰናክላሉ፤ ነቢዩ እነርሱ እንደሚሉት በስውር ሳይኾን ዓለም እያየው በግልጽ እንደሚመጣ ስለምናምን ኤልያስ ወደዚህ ምድር የሚመጣው የምጽአት ቀን ሲቃረብ መኾኑን አስረግጠን እንናገራለን፡፡

በመጨረሻም ዅላችንም እንደ ነቢዩ ኤልያስ በአካለ ሥጋ ሳይኾን በክብር ከፍ ከፍ እንል ዘንድ በሕሊና ልናርግ ማለትም በመልካም ምግባር ልንጐለምስ ያስፈልጋል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ እንደ ነቢዩ ኤልሳዕ የአባቶቻችን ጸጋ በላያችን ላይ ያድርብን ዘንድ ከቅዱሳን እግር ሥር እና ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን ቅፅር፤ እንደዚሁም ከተዋሕዶ ሃይማኖታችን አስተምህሮ መውጣት የለብንም፡፡

ከዚሁ ዅሉ ጋርም የእግዚአብሔርን መንግሥት እንወርስ ዘንድ ሕገ እግዚአብሔርን ጠብቀን፣ በክርስቲያናዊ ምግባር ጸንተን መኖር ይገባናል፡፡ ‹‹… ጌታውን የሚጠብቅ ይከብራል፤›› ተብሎ ተጽፏልና /መጽሐፈ ተግሣፅ ፫፥፲፰ (ምሳሌ ፳፯፥፲፰)/፡፡ የነቢዩ ረድኤትና በረከት አይለየን፡፡

ምንጭ፡-

መጽሐፈ ስንክሳር፣ ታኅሣሥ ፩ እና ጥር ፮ ቀን የሚነበብ፡፡

የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት፣ ኢ.መ.ቅ.ማ፤ 2002 ዓ.ም፣ አዲስ አበባ፤ ገጽ 173፡፡

ገድለ ኤልያስ ነቢይ፣ መ/ር ተስፋ ሚካኤል ታከለ፤ ፳፻፭ ዓ.ም፣ አዲስ አበባ፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

በዓለ ግዝረት

our-lord

በዝግጅት ክፍሉ

ጥር ፭ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

ክብር ምስጋና ይድረሰውና የጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ግዝረት በየዓመቱ ጥር ፮ ቀን በቤተ ክርስቲያናችን ይከበራል፡፡ ጥር ፮ ቀን በሚነበበው መጽሐፈ ስንክሳር ተጽፎ የሚገኘውን የጌታችንን የግዝረት ታሪክም በሉቃስ ወንጌል አንድምታ ትርጓሜ ከተቀመጠው ትምህርት ጋር በማጣቀስ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፤

ልሳነ ዕፍረት ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ጌታ ክርስቶስ በሥጋው ግዝረትን ተቀበለ፡፡ ለአባቶች የተሰጠውን ቃል ኪዳን ይፈጽም ዘንድ፤›› በማለት እንደ ተናገረው /ሮሜ.፲፭፥፰/፣ የክብር ባለቤት መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ቤተ ግዝረት በመግባት የኦሪትን ሕግ ፈጽሟል፡፡ በቅዱስ ወንጌል እንደ ተጻፈ በስምንተኛው ቀን እንደ ኦሪቱ ሥርዓት ግዝረት ይፈጸምለት ዘንድ ሕፃኑ ጌታችንን ወደ ቤተ መቅደስ ወሰዱት፡፡ ስሙም ገና በሥጋ ሳይፀነስ የእግዚአብሔር መልአክ ባወጣለት ስም ‹‹ኢየሱስ›› ተብሎ ተጠራ /ሉቃ.፪፥፳፩-፳፬/፡፡ መጥምቁ ዮሐንስ ሲገረዝ የሊቀ ካህን ልጅ ነው ብለው ሊገርዙት ወደ እርሱ መጡ፡፡ ጌታችን ግን ወደ ምድር የመጣው ለትሕትና ነው እንጂ ለልዕልና አይደለምና ወሰዱት አለ /ትርጓሜ ወንጌለ ሉቃስ/፡፡

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም አረጋዊው ዮሴፍን ‹‹እንደ ሕጉ ልጄን እንዲገርዘውና ስሙንም እንድንሰይመው ብልህ የኾነ ገራዥ ሰው አምጣልኝ፤›› አለችው፡፡ ጻድቁ ዮሴፍም እንዳዘዘችው የሚገርዝ ባለሙያ ይዞ መጣ፡፡ ባለሙያውም በእናቱ በንጽሕት ድንግል ማርያም ክንድ ላይ ሕፃኑ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ባየው ጊዜ ‹‹እንድገርዘው በጥንቃቄ ያዙት›› አላቸው፡፡ ጌታ ኢየሱስም ‹‹ባለሙያ ገራዥ ሆይ! ደሜ ሳይፈስ ልትገርዘኝ ትችላለህን? በዕለተ ዓርብ በመስቀል ስሰቀል ካልኾነ በስተቀር ደሜ አይፈስምና፡፡ ጐኔን በጦር ሲወጉኝ ያን ጊዜ ውኀና ደም ይፈሳል፡፡ ይኸውም ለአዳምና ለሚያምኑ ልጆቹ መድኀኒት ይኾናል፤›› አለው፡፡

የክብር ባለቤት ጌታችን የተናገረውን ይህን ቃል ባለሙያው በሰማ ጊዜም አደነቀ፡፡ ዕቃውንም ሰብስቦ ተነሣና ከጌታችን እግር በታች ወድቆ ሰገደ፡፡ ያንጊዜም ምላጮቹ በእጁ ላይ እንዳሉ እንደ ውኀ ቀለጡ፡፡ ክብርት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምንም ‹‹ከሴቶች ተለይተሽ አንቺ የተባረክሽ ነሽ፡፡ የማኅፀንሽም ፍሬ የተባረከ ነው፡፡ ይህ ልጅሽ ስለ እርሱ ነቢያት ትንቢት የተናገሩለት የሕያው አምላክ ልጅ ነው፤›› አላት፡፡

ጌታችንም ባለሙያውን ‹‹እኔ ነኝ! ትገዝረኛለህን ወይስ ተውክ? ወይስ የአባቶቼ አባቶች እንዳደረጉ ላድርግ?›› አለው፡፡ ባለሙያውም መልሶ ‹‹የአባቶችህ አባቶች እነማን ናቸው?›› ሲል ጠየቀው፡፡ ጌታችንም አብርሃም፣ ይስሐቅ፣ ያዕቆብ የሕዝቡ ዅሉ አባት እንደ ኾኑ ካስገነዘበው በኋላ ‹‹ለእነርሱም ይህ ግዝረት አስቀድሞ ከአባቴ ዘንድ ተሰጣቸው›› በማለት የግዝረትን ሕግ አስረዳው፡፡ ባለሙያውም ይህን ምሥጢር ሲሰማ ‹‹እኔ ከአንተ ጋር እነጋገር ዘንድ አልችልም፡፡ በአንተ ህልውና መንፈስ ቅዱስ አለና፤›› ብሎ የኢየሱስ ክርስቶስን የባሕርይ አምላክነት መሰከረ፡፡

በዚህ ጊዜ ጌታችን ዐይኖቹን ወደ ሰማይ አቅንቶ ‹‹አባት ሆይ ለአብርሃም፣ ለይስሐቅ፣ ለያዕቆብ አስቀድሞ ግዝረትን የሰጠሃቸው፤ ያቺን ግዝረት ዛሬ ለእኔ ስጠኝ›› አለ፡፡ ያንጊዜም ያለ ሰው እጅ በጌታችን ላይ ግዝረት ተገለጠ (የግዝረት ምልክት ታየ)፡፡ ከዚህ ላይ ጌታችን ወደ አባቱ ወደ እግዚአብሔር አብ ልመና ማድረሱ የለበሰው ሥጋ የአብርሃም፣ የይስሐቅ፣ የያዕቆብ መኾኑንና ጸሎት ማቅረብ የሚስማማው ሥጋን መልበሱን ለማጠየቅ ነው እንጂ በእርሱና በአብ መካከል ልዩነት ኖሮ አይደለም፡፡

ጌታችን ድንግልናዋን ሳያጠፋ ከድንግል ማኅፀን እንደ መውጣቱ ግዝረቱም አይመረመርም፡፡ በተዘጋ ቤት ወደ ሐዋርያት እንደ ገባና እንደ ወጣ ዅሉ እርሱ በሚያውቀው ረቂቅ ጥበብ ከሥጋው ምንም ምን ሳይቈረጥ፣ ምንም ደም ሳይፈሰው መገረዙ ተገለጠ፡፡

ገራዡም የጌታችንን ቃል ከመስማቱ ባሻገር በሥጋው ላይ የተደረገውን ተአምር ባየ ጊዜ እጅግ አደነቀ፡፡ ከክብር ባለቤት ከጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እግር በታች ወድቆም ሦስት ጊዜ ሰገደና ‹‹በእውነት አንተ የእግዚአብሔር ልጅ፣ የእስራኤልም ንጉሥ ነህ!›› በማለት በክርስቶስ አምላክነት አመነ፡፡ ከዚህ በኋላ ያየውንና የሰማውን ዅሉ እየመሰከረ ወደ ቦታው ተመለሰ፡፡

በዚህች ዕለት ‹‹መሲሑን ሳታይ አትሞትም›› ተብሎ የተነገረለት፤ በንጉሥ በጥሊሞስ መራጭነት መጻሕፍተ ብሉያትን ከዕብራይስጥ ወደ ጽርዕ (ግሪክ) ቋንቋ ከመለሱ ሰባው ሊቃናት አንዱ የኾነውና ትንቢተ ኢሳይያስን ወደ ጽርዕ ቋንቋ የመለሰው ነቢዩ ስምዖን ጌታችንን በታቀፈው ጊዜ ከሽምግልናው ታድሷል፤ የእግዚአብሔርን ማዳን በማየቱና በተደረገለት ድንቅ ተአምር በመደሰቱም ‹‹አቤቱ ባሪያህን ዛሬ አሰናብተው›› እያለ እግዚአብሔርን ተማጽኗል፡፡

በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝቶም የክርስቶስን የዓለም ቤዛነትና ክርስቶስ በሥጋው በሚቀበለው መከራ እመቤታችን መራራ ኀዘን እንደሚደርስባት፤ እንደዚሁም ጌታችን ለሚያምኑበት ድኅነትን፣ ለሚክዱት ደግሞ ሞትን  የሚያመጣ አምላክ እንደ ኾነ የሚያስገነዝብ ትንቢት ተናግሯል /ሉቃ.፪፥፳፭-፴፭/፡፡ በተመሳሳይ መልኩ ነቢዪት ሐናም በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝታ የክርስቶስን ሥራ እያደነቀች ቸርነቱን ለሕዝቡ ዅሉ መስክራለች /ሉቃ.፪፥፴፮-፴፱/፡፡

የእግዚአብሔር አብ ጸጋ፣ የእግዚአብሔር ወልድ ፍቅር፣ የእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስም ኅብረት በክርስቶስ የባሕርይ አምላክነት ያለ ጥርጥር በፍጹም ልባችን ከምናምን ምእመናን ጋር ይኹን! /፪ኛቆሮ.፲፫፥፲፬/፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡  

ሥጋዌ – የድኅነት ቍልፍ – የመጨረሻ ክፍል

በመምህር ፀሐዬ ዳዲማስ

ታኅሣሥ ፳፰ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

ቅዱስ ያሬድ ቅዱሳን መላእክት በምስጋናቸው የተናገሩለትን ሰላም ያስተማረውና የተረጐመው ከድኅነት ጋር አያይዞ ነው። የመላእክቱን አዲስ ምስጋና በተረጐመበት አንቀጸ ብርሃን በተባለው የድርሰቱ ክፍልም፡- ‹‹ወዓዲ ርእዩኪ በውስተ በዓት ለኪ ለባሕቲትኪ ምስለ ሕፃንኪ ወይቤሉ ሰላም በዲበ ምድር ወሶበ ርእዩ እንዘ ይለብስ ሥጋ ዚአነ ዘነሥአ እምኔኪ ሰገዱ እንዘ ይብሉ ለእጓለ እመሕያው ሠምሮ፤ እንደ ገናም ከሕፃኑ ልጅሽ ጋር አንቺን ብቻሽን በበረት ውስጥ ባዩሽ ጊዜ ‹በምድር ላይ ሰላም [ኾነ]› አሉ፤ ከአንቺ የነሣውን የእኛን ሥጋ ተዋሕዶ ባዩት ጊዜም ‹የሰውን ልጅ ወደደው› እያሉ ሰገዱ፤›› ሲል ተናግሮአል (መጽሐፈ ምዕራፍ፣ አንቀጸ ብርሃን፣ ገጽ ፻፳፯)። በዚህ ድርሰቱም የመላእክቱን ምስጋና፣ የሰው ልጆችን ድኅነት እንድንረዳ ቅዱስ ያሬድ በጥልቀት አስተምሮናል።

ቅዱስ ያሬድ ስለ ሰላም ሲነግረን ስለ ድኅነት እየመሰከረ እንደ ኾነ እና ከልደተ ክርስቶስ ጋር ያለውን ግንኙነት እያስረዳን መኾኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። ይህን የቅዱሳንን ልቡና ለመረዳት መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብና ሊቃውንትን በመጠየቅ የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮን ማገናዘብ እጅግ ጠቃሚ ነው። ቅዱስ ጳውሎስ የኤፌሶን ሰዎችን፡- ‹‹አሁን ግን እናንተ በፊት ርቃችሁ የነበራችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ ኾናችሁ በክርስቶስ ደም ቀርባችኋል። እርሱ ሰላማችን ነውና፤ ሁለቱን ያዋሐደ በአዋጅ የተነገሩትንም የትእዛዛትን ሕግ ሽሮ በመካከል ያለውን የጥል ግድግዳን በሥጋው ያፈረሰ፤ ይህም ከሁለታቸው አንድን አዲስን ሰው በራሱ ይፈጥር ዘንድ ሰላምንም ያደርግ ዘንድ፤›› በማለት በክርስቶስ የተገኘውን ሰላም አስተምሯቸዋል (ኤፌ. ፪፥፲፫-፲፭)፡፡ በዚህም የሐዋርያው መልእክት ክርስቶስ የሰጠንም ድኅነት ሰላም እንደተባለ እናስተውላለን።

የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዐርበኛ ሐዋርያዊው ቅዱስ አትናቴዎስም፡- በማቴዎስ ወንጌል ፲፩፥፳፰ ላይ በሚገኘው ‹‹ወደ እኔ ኑ፤››  እና በሉቃስ ወንጌል ፲፥፳፪ ላይ በተጻፈው፡- ‹‹ዅሉ ከአባቴ ዘንድ ተሰጥቶኛል›› በሚሉት ጌታችን ባስተማራቸው የወንጌል ቃላት ላይ ተመሥርቶ ባቀረበው ትምህርት የድኅነትን ሰላምነት እንዲህ በማለት ያስረግጥልናል፤ ‹‹አስቀድሞ ሰው አልነበረምና በኋለኛው ዘመን ግን ሰውን ያድን ዘንድ ሰው ኾነ። በመጀመርያው ቃል ሥጋ አልነበረም፤ ከዘመናት በኋላ ሥጋ ኾነ እንጂ፡፡ ሐዋርያት እንደ ነገሩን ከእርሱ ጋር የነበረብንን ጠላትነት ያስታረቀልን፣ በእኛ ላይ ተቀምጠው የነበሩትን ትእዛዛት ያጠፋልን በዚህ ሥጋ ነው፡፡ ይህን በማድረጉም ሁለቱን አንድ አዲስ ሰው ያደርግ ዘንድ፣ ሰላምን ያሰፍን ዘንድ፣ ሁለቱንም አንድ አድርጎ ከአብ ጋር ያስታርቅ ዘንድ ነው፤›› (NPNF V2-04፣ ገጽ 300-301)።

ስለ ኾነም ቅዱስ ያሬድ በክርስቶስ ልደት የተቀበልነውን ሰላም እንድንከተል፣ በክርስቶስ ሥጋ መልበስ ያገኘነውን ድኅነት ገንዘብ እንድናደርግ በምስጋናው ዅሉ ይመክረናል፡፡ ዘማሪው በተጨማሪም ክርስቶስ ይህን ሰላም የሰጠን በደላችንን ይቅር ብሎ፣ … ከኃጢአት በስተቀር ሰው የሚኾነውን ኾኖ እንደ ኾነ በማስረገጥ፤ እንደዚሁም እግዚአብሔር ሰው ኾኖ ሰውን ለማዳን ያበቃው ይቅር ባይ ባሕርዩ እንደ ኾነ እንድናምን ያስረዳናል። በሌላኛው የምስጋና ድርሰቱም ‹‹ብርሃን መጽአ ኀቤነ ከመ ያርኢ ምሕረቶ በላዕሌነ ውእቱ ኢየሱስ ክርስቶስ … ርእዩ ዘከመ አፍቀረነ እግዚአብሔር፤ በእኛ ላይ ምሕረቱን ያሳይ ዘንድ ብርሃን ወደ እኛ መጣ፤ እርሱ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ እግዚአብሔር ምንኛ እንደ ወደደን ተመልከቱ፤›› በማለት ሊቁ ዘምሯል (ድጓ ዘዘመነ ልደት)፡፡ ይህም እግዚአብሔር ሰዎችን እንዲያድን ያደረገው ለሰው ልጆች ያለው ልዩ ፍቅር እንደ ኾነ የሚያስገነዝበን ድንቅ ትምህርት ነው። በሊቁ ትምህርት መሠረት የሰው ልጆችን ለድኅነት ካበቁት የእግዚአብሔር ባሕርያት መካከል ይቅር ባይነት እና ፍቅር ዋና ዋነኛዎቹ እንደ ኾኑ ለመረዳት እንችላለን፡፡

በአጠቃላይ የሰዎችን ሥጋ ተዋሕዶ ሰዎችን እንዲያድን የፈቀደ ራሱ እግዚአብሔር አምላካችን ነው። ይህ ደግሞ አምነን የምንቀበለውና በተወደደው የድኅነት መንገድ ለመጓዝ መንገዳችንን የሚያቀናልን እንጂ መርምረን የምንደርስበት ምሥጢር አይደለም። ይልቁንም እኛ ድነን ለዘመናት አጥተናት ወደ ነበረችው ገነት እንድንመለስ እና በራሳችን ስሕተት በእኛና በእግዚአብሔር መካከል ተፈጥሮ የነበረው የጥል ግድግዳ ፈርሶ ከእግዚአብሔር ጋር እንድንኖር የእግዚአብሔር ሰው መኾን (ሥጋዌ) እጅግ አስፈላጊ እንደ ነበረ፣ እግዚአብሔር ሰው ኾኖ ሰውን እንዲያድን ካገበሩት ባሕርያቱ መካከልም ይቅር ባይነቱ (መሐሪነቱ) እና ፍቅሩ መኾናቸውን እያሰብን ከቅዱስ ያሬድ ጋር ‹‹አናኅስዮ አበሳነ አፍቂሮ ኪያነ ፈነወ ለነ ወልዶ መድኅነ፤ በደላችንን ይቅር ብሎ እኛን ወዶ አዳኝ ልጁን ወደኛ ሰደደልን፤›› እያልን በማመስገን የመድኃኒታችንን በዐለ ልደት በደስታ እናከብራለን።

በዐሉን ስናከብርም እንደ መላእክቱ እና እንደ ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት አዲስ ምስጋናን ለእግዚአብሔር በመቀኘት እንጂ ከእግዚአብሔር በሚለዩን በዓለም ዳንኪራዎች እንዳይኾን ራሳችንን መግዛት ይኖርበታል፡፡ ሥጋችንን ተዋሕዶ ለድኅነት የተገለጠልንን መድኃኒታችንን እያሰብን ድኅነታችንን ገንዘብ በምናደርግበት በታላቁ በዓላችን ወቅት ዘመን በወለዳቸው ኃጢአቶች ድኅነታችንን እንዳናጣ ከመጠንቀቅ ጋርም በዓሉን የበረከት በዓል ልናደርገው እንደሚገባን አንርሳ፡፡ አምላካችን ከጥልቅ ፍቅሩ የተነሣ ለድኅነታችን የተገለጠውን መድኅን የምንዘክርበትን በዓላችንን ዓለም ዅሉ ወደ ድኅነት የሚቀርብበት በዓል ያድርግልን፡፡

በማይጠቀለል ሦስትነት፣ በማይከፋፈል አንድነት ጸንቶ የኖረ እና የሚኖር፤ አስቀድሞ በአርአያውና በአምሳሉ የፈጠረውን ሥጋ በመዋሐድ ለሰው ልጆች ያለውን የማይለካና በቃላት ሊገለጥ የማይችል ፍቅር ያሳየ፤ በእያንዳንዷ ቅጽበት ከቸርነቱ ብዛት፣ ከጸጋው ምልአት የተነሣ ፍጥረታትን የሚመግብ፤ ልሳናት ዅሉ የሚያመሰግኑት፤ ጕለበቶች ዅሉ የሚንበረከኩለት ልዑል እግዚአብሔር ክብር ምስጋና ይድረሰው! ተወልዶ እንዲያድነን አንድያ ልጁን ለላከልን ለእግዚአብሔር አብ፤ ከአባቱ ዕቅፍ ሳይለይ ሥጋችን ተዋሕዶ ላዳነን ለእግዚአብሔር ወልድ፤ በዅሉም የሚኖር፣ ዅሉንም ለሚያከናውን ለእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ክብር፣ ምስጋና ይዅን፤ አሜን፡፡

ማስገንዘቢያ፡-

የተወደዳችሁ የድረ ገጻችን ተከታታዮች! ይህ ትምህርት ከታኅሣሥ ፲፮ – ፴ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም በወጣው ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ በዓውደ ሃይማኖት ዓምድ ሥር ‹‹አዳኝ ልጁን ወደ እኛ ሰደደልን›› በሚል ርእስ ለንባብ መብቃቱን ለማስገንዘብ እንወዳለን፡፡

ሥጋዌ – የድኅነት ቍልፍ – ክፍል ሁለት

በመምህር ፀሐዬ ዳዲማስ

ታኅሣሥ ፳፯ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

በስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን በምስጋናው ብርሃን ያበራው ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድም ነገረ ሥጋዌ ከሰው ልጆች ድኅነት ጋር ያለውን ቍርኝነት ጥልቅ ምሥጢር ባለው በመጽሐፈ ድጓ ድርሰቱ ጽፎልን እናነበዋለን። ቅዱስ ያሬድ በምስጋናው አንሥቶ ከማይጠግባቸው ምስጋናዎች መካከል የአምላክ ሥጋዌ (ሰው መኾን) እና ነገረ ስቅለት ቀዳሚዎች ሲኾኑ የሚያነሣቸውም ከነገረ ድኅነት ጋር በተያያዘ ምሥጢር ነው፡፡ የእግዚአብሔር ሰዎችን የማዳን ተግባራት ከሚመለከቱ ድርሰቶቹ መካከል ለአብነት የሚከተለውን ትምህርት መጥቀስ እንችላለን፤

‹‹ዘዲበ ኪሩቤል ይነብር ወበአርያም ይሴባሕ እምሰማያት እምልዑላን ወረደ አምላክ ያድኅን ዓለመ መጽአ ይክሥት ብርሃነ ይናዝዝ ኅዙናነ ወልድ ተወልደ ለነ ወሠርዐ ሰንበተ ለሰብእ ዕረፍተ ውእቱኬ ወልደ አምላክ ውእቱ ወልድ ዋሕድ ውእቱ፤ በኪሩቤል ላይ የሚኖር በአርያምም የሚመሰገን ከሰማያት ከልዑላን ወረደ፤ አምላክ ዓለምን ያድን ዘንድ መጣ፤ ብርሃንን ይገልጥ ዘንድ፣ ያዘኑትን ያጽናና ዘንድ፣ [እግዚአብሔር] ወልድ ተወለደልን፡፡ ለሰዎች ዕረፍትም ሰንበትን ሠራ፤ እሱም የአምላክ ልጅ ነው፡፡ [እሱም] በተዋሕዶ የከበረ [እግዚአብሔር] ወልድ ነው፤›› (ድጓ ዘዘመነ ልደት)፡፡

እነዚህ የቅዱስ ያሬድ የምስጋና ቃላት እግዚአብሔር ወልድ የሰውን ሥጋ ለብሶ ሰው መኾኑን ከማስረዳታቸውም ባሻገር እግዚአብሔር አምላካችን ሰው በመኾኑ የሰው ልጆች ያገኙትን ጥቅምም የሚያስረግጡ ናቸው። ዘማሪው አምላክ ወልደ አምላክ ዓለምን ያድን፣ ብርሃንን ይገልጥ፣ ያዘኑትንም ያጽናና ዘንድ ከሰማያት እንደ ወረደ እና ወደ ዓለም ወይም ወደ ሰዎች እንደ መጣ ሲነግረን የተለያዩ ጽጌያትን እንደሚቀስም ንብ መጽሐፍ ቅዱስን በማጣቀስ እንደ ኾነ ስንረዳም የአበው ሊቃውንት መጽሐፍ ቅዱሳዊ አስተምህሮን ልብ እንድንል ያስችለናል።

እግዚአብሔር አብ አንድያ ልጁን እግዚአብሔር ወልድን ወደ ዓለም የላከው ዓለም በልጁ እንዲድን እንደ ኾነ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለኒቆዲሞስ ያስተማረውን ትምህርት ቅዱስ ዮሐንስ በወንጌሉ ጽፎልናል (ዮሐ. ፫፥፲፮)። የነቢያት ትንቢት በክርስቶስ መፈጸሙን ደጋግሞ በማውሳት የሚታወቀው ሐዋርያው እና ወንጌላዊው ቅዱስ ማቴዎስም የነቢዩ የኢሳይያስ ትንቢት በሥግው ቃል በክርስቶስ እንደ ተፈጸመ በሚያስረዳ የወንጌሉ ክፍል ‹‹‹በጨለማ የተቀመጠው ሕዝብ ታላቅ ብርሃን አየ፤ በሞት አገርና ጥላ ለተቀመጡትም ብርሃን ወጣላቸው› የተባለው ይፈጸም ዘንድ ይህ ኾነ›› በማለት ጽፏል (ማቴ. ፬፥፲፬-፲፮ ኢሳ. ፱፥፪)።

ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስም በተመሳሳይ መልኩ የነቢዩን የኢሳይያስን ትንቢት ጠቅሶ ክርስቶስ በዘመነ ስብከቱ ስለ ራሱ እና ሰው ስለ ኾነበት ምክንያት ሲያስረዳ የተናገረውን ‹‹የነቢዩንም የኢሳይያስን መጽሐፍ ሰጡት፤ መጽሐፉንም በተረተረ ጊዜ ‹የጌታ መንፈስ በእኔ ላይ ነው፤ ለድሆች ወንጌልን እሰብክ ዘንድ ቀብቶኛልና፤ ለታሰሩትም መፈታትን፣ ለዕውሮችም ማየትን እሰብክ ዘንድ፤ የተጠቁትንም ነጻ አወጣ ዘንድ፤ የተወደደችውንም የጌታን ዓመት እሰብክ ዘንድ ልኮኛል› ተብሎ የተጻፈበትን ስፍራ አገኘ። መጽሐፉንም ጠቅልሎ ለአገልጋዩ ሰጠውና ተቀመጠ፤ በምኵራብም የነበሩት ዅሉ ትኵር ብለው ይመለከቱት ነበር። እርሱም ‹ዛሬ ይህ መጽሐፍ በጆሮአችሁ ተፈጸመ› ይላቸው ጀመር፤›› (ሉቃ. ፬፥፲፯-፳፩) በማለት ትንቢቱ መፈጸሙን ተናግሯል።

የነቢዩን ቃላት በምልአት ስንመለከታቸው ‹‹የጌታ የእግዚአብሔር መንፈስ በእኔ ላይ ነው፤ ለድሆች የምሥራችን እሰብክ ዘንድ እግዚአብሔር ቀብቶኛልና፤ ልባቸው የተሰበረውን እጠግን ዘንድ፤ ለተማረኩትም ነፃነትን፣ ለታሰሩትም መፈታትን እናገር ዘንድ ልኮኛል። የተወደደችውን የእግዚአብሔርን ዓመት፣ አምላካችንም የሚበቀልበትን ቀን እናገር ዘንድ፤ የሚያለቅሱትንም ዅሉ አጽናና ዘንድ፤ እግዚአብሔር ለክብሩ የተከላቸው የጽድቅ ዛፎች እንዲባሉ ለጽዮን አልቃሾች አደርግላቸው ዘንድ፤ በአመድ ፋንታ አክሊልን፣ በልቅሶም ፋንታ የደስታ ዘይትን፤በኀዘን መንፈስ ፋንታም የምስጋና መጐናጸፊያን እሰጣቸው ዘንድ ልኮኛል፤›› የሚሉ ናቸው (ኢሳ. ፷፩፥፩)።

እነዚህን አጠቃልሎ ቅዱስ ያሬድ ድኅነተ ሰብእን ሲያመለክት ‹‹ዓለምን ያድን ዘንድ መጣ፡፡ብርሃንን ይገልጥ ዘንድ፤ ያዘኑትን ያጽናና ዘንድ፤ [እግዚአብሔር] ወልድ ተወለደልን፤›› በማለት በዝማሬ አመሰገነ። እግዚአብሔር የሰውን ሥጋ ለብሶ ሰውን ያድን ዘንድ ያስገደደው የገዛ ባሕርዩ ነው፡፡ እግዚአብሔር ሰውን ለማዳን ወደ ዓለም የመጣበትን ምክንያት ብዙ ሊቃውንት በብዙ መንገድ ጽፈዋል። አንዳንዶቹም የማይረገጠውን ረግጠው በድፍረት ‹‹መጽአ በኵርሕ፣ ተገዶ መጣ›› ብለው እስከ ማስተማር በመድረሳቸው ከቤተ ክርስቲያን አንድነት ተለይተዋል። ፍጹማን የኾኑት የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ግን እግዚአብሔር የሰው ልጆችን እንዲያድን ያደረገው ባሕርዩ እንደ ኾነ በምስጋና ድርሰቶቻቸው ጽፈውልናል።

ቅዱስ ያሬድ በበዐለ ኖላዊ ሳምንት በሚደርሰው የድጓ ድርሰቱ ‹‹አናኅስዮ አበሳነ አፍቂሮ ኪያነ ፈነወ ለነ ወልዶ መድኅነ፣ በደላችንን ይቅር ብሎ እኛን ወዶ አዳኝ ልጁን ወደኛ ሰደደልን፤›› በማለት ክርስቶስ ወደ ዓለም የመጣው እኛን ለማዳን መኾኑን ነግሮናል። ሊቁ በዚህ ድርሰቱ እግዚአብሔር አብ እግዚአብሔር ወልድን ለድኅነት ወደ እኛ ወደ ሰዎች የላከልን በይቅር ባይ እና ፍቅርን መሠረት ባደረገው ባሕርዩ እንደ ኾነ ያስረዳል። እጅግ ጥልቅ በኾነ ምሥጢር ነገረ ድኅነትን የሚገልጠውን ሌላኛውን የቅዱስ ያሬድን ምስጋና እናንሣ፤ ‹‹ይእዜኒ ንትልዋ ለሰላም እስመ ተወልደ ክርስቶስ ዮም በሀገረ ዳዊት አናኅስዮ አበሳነ ወልዱ ለአብ ቀዳሜ በኵሩ ኃይሉ ለአብ መጽአ ኀቤነ ይክሥት ብርሃነ ተመሲሎ ኪያነ ሰብአ ዘይከውን ኵሎ ኮነ ዘእንበለ ኃጢአት ባሕቲታ፤›› (ድጓ ዘዘመነ ልደት)፡፡ ትርጕሙም፡- ‹‹እንግዲህማ ሰላምን እንከተላት፤ ዛሬ ክርስቶስ በዳዊት አገር ተወልዷልና፡፡ በደላችንን ይቅር ብሎ የአብ አንድያ ልጁ፣ የአብ ኃይሉ፣ ወደ እኛ መጣ፤ ብርሃንን ይገልጥ ዘንድ፣ እንደ እኛ ሰው ኾነ፡፡ ከብቻዋ ከኃጢአት በቀር ሰው የሚኾነውን ዅሉ ኾነ፤›› ማለት ነው፡፡

ከዚህ የምስጋና ክፍል እንደምንረዳው የጌታችን ልደት የሰላም ምንጭ መኾኑን ነው። ይህ ሰላም ደግሞ ዓለም የምትሰጠው ሰላም አይደለም፤ ድኅነተ ሰብእን የሚያሳይ ሰላም፤ ሰዎች ከእግዚአብሔር ጋር የነበራቸው ልዩነት ተወግዶ ዕርቅ መመሥረቱን የሚያሳይ ሰላም ነው እንጂ። በክርስቶስ ልደት ለዓለም የተሰጠው ሰላም ደግሞ የሚሠራው ሰዎች ዅሉ ሲሹትና ሲከተሉት ነውና ‹‹ንትልዋ ለሰላም›› እያለ በረጅሙ ይሰብካል። ለዚህም ነው መላእክቱ ከእረኞቹ መካከል ተገኝተው፣ ከሰዎች ጋር በአንድነት ኾነው በአዲስ ምስጋና ሲያመሰግኑ ‹‹ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይኹን! ሰላምም በምድር፤ ለሰውም በጎ ፈቃድ፤›› በማለት የዘመሩት (ሉቃ. ፪፥፲፬)።

ይቆየን

ሥጋዌ – የድኅነት ቍልፍ – ክፍል አንድ

በመምህር ፀሐዬ ዳዲማስ

ታኅሣሥ ፳፮ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

ጌታችን የሰው ልጆችን የሚያድንበት የማስተማር ሥራው (ወንጌልን መስጠቱን) ሲጀምርም ሲፈጽምም በነገረ ድኅነት ትምህርት ነው። የስብከቱ መነሻ የትምህርተ ድኅነት መዳረሻ የኾነው የመንግሥተ ሰማያትን ነገር ማውሳት ነበር፡፡ ‹‹መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሓ ግቡ እያለ ይሰብክ ጀመር፤›› እንዲል (ማቴ. ፬፥፲፯)። ከሰማያት የወረደበትንና ሰው የኾነበትን የድኅነት ሥራውን ፈጽሞ በትንሣኤው የሰው ልጆችን ሕያውነት አረጋግጦና የዘለዓለምን ሕይወት አውጆ ወደ አባቱ ያረገው ‹‹ወደ ዓለም ዅሉ ሒዱ፤ ወንጌልንም ለፍጥረት ዅሉ ስበኩ። ያመነ የተጠመቀም ይድናል፤ ያላመነ ግን ይፈረድበታል፤›› በማለት ትምህርተ ድኅነታዊ ትእዛዝን ለሐዋርያት በመስጠት ነበር (ማር. ፲፯፥፲፭-፲፮)።

ቅዱስ ጳውሎስም ትምህርተ ክርስትና ከድኅነት ጋር ያለውን የጠበቀ ቍርኝት፣ የማይነጣጠል አንድነት የሚያመለክቱ ኃይለ ቃላትን በመልእክታቱ አስፍሮ ይገኛል። ‹‹የሰበክሁላችሁን ደግሞም የተቀበላችሁትን በእርሱም ደግሞ የቆማችሁበትን በእርሱም ደግሞ የምትድኑበትን ወንጌል አሳስባችኋለሁ›› (፩ቆሮ. ፲፭፥፩) በማለት የቆሮንቶስ ክርስቲያኖችን ሲያሳስብ፣ ‹‹የእውነትን ቃል፣ ይኸውም የመዳናችሁን ወንጌል፤ ሰምታችሁ ደግሞም በክርስቶስ አምናችሁ፣ በተስፋው መንፈስ በመንፈስ ቅዱስ ታተማችሁ›› (ኤፌ. ፩፥፲፫) በማለት ደግሞ ለጊዜው ኤፌሶናውያንን፤ ለፍጻሜው ዳግም የሰው ልጅን ዅሉ ድኅነት መክሯል፡፡ ወንጌላዊው ማርቆስም ስለ አጠቃላይ የክርስትና ትምህርት ምንነት ሲያስረዳ ‹‹ለዘለዓለም ድኅነት የኾነውን የማይለወጠውን ቅዱስ ወንጌል›› በማለት ነው የሚገልጠው (ማር. ፲፮፥፰)።

የክርስትና ትምህርት የድኅነት ትምህርት ነው። ከጅምሩ እስከ ፍጻሜው የሰው ልጆችን መዳን ቁልፍ መጠቅለያውና ማጠንጠኛው ነው። አቀራረቡም ‹‹ነገረ ድኅነታዊ›› ነው – የክርስትና ትምህርት። ከጥንት ጀምሮ ሐዋርያትና ሊቃውንት የወንጌላውያኑን እና የሐዋርያትን አሰረ ፍኖት በመከተል የክርስትናን ትምህርት የጠበቁት ነገረ ድኅነትን አምልቶና አስፍቶ በማስተማር ነው።

ኢትዮጵያውያን ሊቃውንትም እንደዚሁ ትምህርታቸውንና ዝማሬአቸውን ዅሉ ነገረ ድኅነታዊ በማድረግ የክርስቶስ ተከታይነታቸውን፣ የሐዋርያትና የሊቃውንት ልጅነታቸውን አስመስክረዋል። በዚህ አጭር ጽሑፍም ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት የጌታችንን ልደት አስመልክተው ያቀረቡአቸውን የነገረ ድኅነት ትምህርቶች በአጭሩ እናቀርባለን፡፡

በክርስትና ትምህርት ከመጀመርያዎቹ የክርስትና ዘመናት ጀምሮ የሊቃውንትን ከፍተኛ ትኩረት የሳበው የእግዚአብሔር ሰው መኾን ነው። ሰው ሊድን የሚችለው በእግዚአብሔር ነው፣ እግዚአብሔር ደግሞ  የወደቀውን ሰው ለማዳን የወደደው ራሱ የሰዎችን ሙሉ (ፍጹም) ማንነት፣ ከኃጢአት በቀር፣ ወስዶ (ተዋሕዶ) ነው። ስለዚህ የድኅነት መነሻ ቍልፉ የእግዚአብሔር ፍጹም ሰው መኾን ነው። ቅዱስ አግናጥዮስ ምጥው ለአንበሳ ‹‹እግዚአብሔር ለሰዎች ሰው እንደ ኾነ መሰላቸው እንጂ እሱ ሰው ሊኾን አይችልም›› በማለት ለሚያስተምሩት ለዶሰቲስቶች (Docetists) መቃወምያ አድርጎ ባቀረበው እና ለትራልዮን ሰዎች በጻፈው መልእክቱ የሚከተለውን ጽሑፍ አበርክቶልናል፤

‹‹ከእግዚአብሔር የራቁ እምነት የሌላቸው ሰዎች ‹ሰውን መሰለ እንጂ የሰውን ፍጹም ሥጋ ለራሱ አልወሰደም (አልለበሰም)፣ የሞተውም በምስል ነው እንጂ እሱ በትክክል መከራ አልተቀበለም› እንደሚሉት ከኾነ [እጄንና እግሬን] ለምን [በሰንሰለት] እታሰራለሁ ይመስላችኋል? ለምንስ ለተራቡ አናብስት ለመሰጠት ይናፍቀኛል?… ድንግል ማርያም የፀነሰችው ሥግው ቃለ እግዚአብሔርን ነው። እግዚአብሔር ቃልም በእውነት ከድንግል ተወለደ፣ የለበሰውም ሥጋ ለእኛ [ለሰዎች] ያለንን ሁሉ ያለው ነው፤›› (ወደ ትራልዮን ሰዎች ምዕራፍ ፲)።

ይህም የሚያሳየን ለሰዎች መዳን የእግዚአብሔር ቃል ከሰማይ መውረድና ከድንግል መወለድ ብቻ ሳይኾን የክርስቶስ ፍጹም አምላክ ሳለ ፍጹም ሰው መኾን አስፈላጊ ነው። አስቀድመን የጠቀስነው ሊቅ ትምህርቱን ሲያጠናክረውም ‹‹ሕፃናትን በማኅፀን የሚሠራቸው እርሱ በማኅፀን አደረ፣ ከድንግል ሥጋና ነፍስን ነሥቶ ያለ ወንድ ዘር አምላክ ሳለ ሰው ኾነ›› በማለት ክርስቶስ የተዋሐደው ሥጋ ከድንግል የነሣው ፍጹም የሰው ልጆች ሥጋ መኾኑን አረጋግጦልናል። ቅዱስ አግናጥዮስስ በመልእክቱ ላስተማራቸውም ይህ እውነት ባይኾን ኖሮ ራሱን ለተራቡ የበረሃ አናብስት የሚሰጥ ሞኝ እንዳልኾነ በማስረገጥ ያዳነው እና የሚያመልከው ክርስቶስ ፍጹም አምላክ፣ ፍጹም ሰው መኾኑን ያስረዳቸዋል (ዝኒ ከማሁ)፡፡

ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫም የ‹‹ለፌ እማርያም›› የእግዚአብሔር ወልድን ቅድምና በሚያመሠጥርበት እና አስተማሪውን ፎጢኖስን በሚዘልፍበት አንቀጹ የሥጋዌን ምሥጢር እንዲህ በማለት አስቀምጦልናል፤ ‹‹ዳግመኛም ድንግል መልአኩን እንዳልኸኝ ይኹንልኝ አለችው። ያን ጊዜም ቃል ከእርሷ ሥጋን ተዋሐደ [ሥጋን ነሣ] … በዚያ [በሰማይ] በአባቱ ቀኝ አለ፤ በዚህም [በምድር] በእናቱ ማኅፀን ውስጥ አለ። … በዚያ ያለ እናት አባት አለው፤ በዚህም ያለ ምድራዊ አባት እናት አለው። በዚያ ገብርኤል በፍርሃት ይቆማል፣ በዚህም ገብርኤል በሐሴት የምሥራች ይናገራል፤ በዚያ በጽርሐ አርያም የሚደነቅ ከማይታይ አብ የመወለድ ምስጋና፤ በዚህም በቤተ ልሔም የሚደነቅ ከድንግል የመወለድ ምስጋና … በሰው መጠን ጐልማሳ ባይኾን፣ በሰው ልጆችም አካል ባይገለጥ እኛን ስለ ማዳን ማን መከራ በተቀበለ ነበር። እነሆ  ከሰማይ ትጉሃን ይልቅ የሰው ልጅ ከበረ፤ እግዚአብሔር ከሴት (ከእመቤታችን) ተወልዷልና፤›› (መጽሐፈ ምሥጢር፣ የልደት ምንባብ)።

የድኅነት ወይም የሰው ልጆች መክበር እና የሥጋዌን የጠበቀ ቍርኝት ተመለከታችሁ! እነዚህ ቅዱሳን አበው የሚነግሩን እግዚአብሔር ሰውን ለማዳን ሰው ባይኾን የሰው ልጆች ድኅነት ጥያቄ ውስጥ ይገባ እንደ ነበር ነው። አግናጥዮስ ‹‹እግዚአብሔር ፍጹም ሰው ባይኾን ሞቴ ከንቱ በኾነ››፤ አባ ጊዮርጊስም ‹‹እግዚአብሔር በሰው ሥጋ ባይገለጥ ማን ባዳነን?›› በማለት የክርስቶስን ሥጋዌ የድኅነተ ሰብእ ቍልፍ መለኮታዊ ተግባር መኾኑን ያስረዳሉ።

ይቆየን

ዝክረ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ጻድቅ

ታኅሣሥ ፳፫ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

t

ቅዱሳን ጻድቃን በመንፈሳዊ አርአያነታቸው፣ በጸሎታቸውና በትምህርታቸው ከከበቡን የነፍስ ጠላቶች፤ ከርኲሳን መናፍስትና ከጨለማው ልጆች፣ ከክፉ ሰዎች ሽንገላና ተንኰል ለመሰወርና ለመጠበቅ ከእግዚአብሔር የተቀበሉት ሥልጣን ምን ጊዜም ይሠራል፡፡ በጻድቃን መኖር ሀገር ከጥፋት ትድናለች፡፡ የጻድቃንን ስም ጠርቶ እግዚአብሔርን በመለመን በረከትና ረድኤት ይገኛል፡፡ ስለ ጻድቃን ብሎ እግዚአብሔርም ምሕረቱን ያድላል፡፡ ጻድቃንን ማሰብ ሥራቸውን መዘከር ክርስቲያናዊ ሕይወታችንን ያጐለምሳል፡፡ በነፍስ በሥጋ ይታደገናል፤ ይረባናል፤ ይጠቅመናል፡፡

ስለዚህም ነው ቤተ ክርስቲያናችን ጻድቃንን እንድናስባቸው፣ በስማቸውም ለድሆችና ለጦም አዳሮች እንድንመጸውት፣ መታሰቢያቸውን እንድናደርግ የምትመክረን፤ የምታስተምረን /ማቴ.፲፥፵፩-፵፪/፡፡ ቅዱሳን ጻድቃን በሕይወተ ሥጋ ሳሉም ኾነ ከሞቱ በኋላ በዐጸደ ነፍስ ኾነው በጸሎታቸው ለሚታመኑ፣ በቃል ኪዳናቸው ለሚማጸኑ ምእመናን በመጸለይና ወደ እግዚአብሔር በማማለድ ድኅነተ ሥጋ፣ የድኅነት ነፍስን የሚያስገኙልን የችግር ጊዜ አማላጆቻችንና አስታራቂዎቻን ናቸው፡፡ ከእነዚህ ቅዱሳን መካከል ኢትዮጵያዊው ጻድቅ አቡነ ተክለ ሃይማኖት አንደኛው ናቸው፡፡

‹ተክል› ማለት ፍሬያማ ዕንጨት፣ ዛፍ፣ ቅመም፣ ቅጠላ ቅጠል፣ የሚበላ፣ የሚሸተት፣ ገነታዊ ዕፅ፣ እንዲሁም ሕግ ሥርዓት ማለት ነው /ማቴ.፲፭፥፲፫/፡፡ ‹ሃይማኖት› ማለት ደግሞ በሀልዎተ እግዚአብሔር፣ እግዚአብሔር የዅሉ አስገኚ መኾኑን፣ በሥላሴ አንድነትና ሦስትነት፣ በቅዱሳን ተራዳኢነት ማመን አምኖም መመስከር ማለት ሲኾን ተክለ ‹ሃይማኖት› የሚለው ሐረግም የሃይማኖት ተክል፣ ይኸውም የጽድቅ ፍሬን ያፈራ፣ ከኃጢአት ሐሩር ማምለጫ ዛፍ፣ ምእመናንን በቃለ ወንጌል ያጣፈጠ ቅመም፣ መዓዛ ሕይወቱ የሚማርክ፣ ቢመገቡት ረኃበ ነፍስን የሚያስወግድ ቅጠል፣ የጻድቃን መጠለያ ዕፅ የሚል ትርጕም አለው፡፡ ገድለ ተክለ ሃይማኖትም ‹‹ተክለ ሃይማኖት ማለት የአብ፣ የወልድ፣ የመንፈስ ቅዱስ ተክል ማለት ነው›› ሲል የጻድቁን ስም ይተረጕመዋል፡፡

ጻድቁ አባታችን ሕይወታቸዉን ሙሉ ለእግዚአብሔር በመስጠት፣ እንደ በሬ ተጠምደው፣ እንደ ገበሬ ታጥቀው፣ ይህንን ዓለም ንቀው፣ በጾም በጸሎት ተወስነው በብሕትውና በመኖራቸው፤ እርሳቸው በአሚነ ሥላሴ ጸንተው ሌሎችንም እንዲጸኑና እንዲያምኑ በማድረጋቸው፤ እንደዚሁም እንደ ቅዱሳን ሐዋርያት ወንጌልን በመላው ኢትዮጵያ እየተዘዋወሩ በመስበክ በጌታችን በመድኀኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ድውያነ ሥጋን በተአምራት፣ ድውያነ ነፍስን በትምህርት የፈወሱ ሰባኬ ወንጌል በመኾናቸው ‹‹ተክለ ሃይማኖት›› ተብለው ይጠራሉ፡፡

አቡነ ተክለ ሃይማኖት በእግዚአብሔር ድንቅ ጥበብ፣ በሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ብሥራት፤ በኢትዮጵያ ምድር በሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት ልዩ ስሙ ኢቲሳ በሚባል ቦታ ከአባታቸው ከካህኑ ጸጋ ዘአብና ከእናታቸው ከቅድስት እግዚእ ኀረያ መጋቢት ፳፬ ቀን ተፀንሰው ታኅሣሥ ፳፬ ቀን ፲፪፻፲፪ ዓ.ም ተወለዱ፡፡ በተወለዱ በሦስተኛው ቀን እሑድ ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት ከእናታቸው ዕቅፍ ወርደው ‹‹አሐዱ አብ ቅዱስ፤ አሐዱ ወልድ ቅዱስ፤ አሐዱ ውእቱ መንፈስ ቅዱስ፤ አንዱ አብ ቅዱስ ነው፤ አንዱ ወልድ ቅዱስ ነው፤ አንዱ መንፈስ ቅዱስ ቅዱስ ነው›› በማለት ሥላሴን አመስግነዋል፡፡ ወላጆቻቸው ያወጡላቸው ስም ‹‹ፍሥሐ ጽዮን›› የሚል ሲኾን ‹‹ተክለ ሃይማኖት›› ደግሞ የእግዚአብሔር መልአክ ቅዱስ ሚካኤል ያወጣላቸው ስም ነው፡፡ በተወለዱ በ፲፭ ዓመታቸው ዲቊናን፤ በ፳፪ ዓመታቸው ደግሞ ቅስናን ከግብፃዊው ጳጳስ ከአባ ጌርሎስ (ቄርሎስ) ተቀብለዋል፡፡

አንድ ቀን ወደ ጫካ ለአደን በሔዱበት ዕለት ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱ ክርስቶስ ተገልጦላቸው ጸጋ መንፈስ ቅዱን ካሰደረባቸው፤ እንደዚሁም ሐዲስ ሐዋርያ› ብሎ ወንጌል ወዳልተዳረሰበት ቦታ እንደሚልካቸው ከነገራቸው፤ ቅዱስ ሚካኤልም ከአውሬ አዳኝነት ሰውን ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ለመመለስ እንደ ተመረጡና አጋንንትን የማውጣት፣ ተአምራትን የማድረግ ሥልጣን እንደ ተሰጣቸው፤ ስማቸውም ተክለ ሃይማኖት እንደሚባልና ትርጓሜውም ተክለ አብ፣ ተክለ ወልድ፣ ተክለ መንፈስ ቅዱስ ማለት እንደ ኾነ ካስረዳቸው በኋላ ወደ ቤታቸው ተመልሰው ያላቸውን ንብረት ኹሉ ለቤተ ክርስቲያንና ለነዳያን ሰጥተው ‹‹አቤቱ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ! የመንግሥተ ሰማያትን በር ትከፍትልኝ ዘንድ እነሆ ቤቴን እንደ ተከፈተ ተውኩልህ›› በማለት ቤታቸውን ትተው ወንጌልን ለማስተማር ፈጥነው ወጡ፡፡ ከዚያ ጊዜ ጀምረው በመላው ኢትዮጵያ እየተዘዋወሩ ወንጌልን በመስበክና ተአምራትን በማድረግ ብዙ አሕዛብን ከአምልኮተ ጣዖት ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር፤ ከገቢረ ኀጢአት ወደ ገቢረ ጽድቅ መልሰዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያንንም አንጸዋል፡፡ ‹ሐዲስ ሐዋርያ› የተባሉትም በዚህ ተልእኳቸው ሲኾን፣ ትርጕሙም ሐዲስ ኪዳንን ወይም ሕገ ወንጌልን እየተዘዋወረ የሚያስተምር ሰባኬ ወንጌል፤ በክርስቶስ ስም ድንቅ ድንቅ ተአምራትን የሚደርግ የክርስቶስ ተከታይ (ሐዋርያ) ማለት ነው፡፡

በአጠቃላይ አባታችን ተክለ ሃይማኖት ሕይወታቸዉን ሙሉ ለእግዚአብሔር በመስጠት፣ እንደ በሬ ተጠምደው፣ እንደገበሬ ታጥቀው ይህንን ዓለም ንቀው በጾም በጸሎት ተወስነው በብሕትውና ከመኖራቸው በተጨማሪ እንደቅዱሳን ሐዋርያት ወንጌልን በመላው ኢትዮጵያ እየተዘዋወሩ የሰበኩ፣ በጌታችን በመድኀኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ድውያነ ሥጋን በተአምራት፣ ድውያነ ነፍስን በትምህርት የፈወሱ ሐዋርያ ናቸው፡፡ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ከሚታወሱባቸው በዓላት መካከልም ታኅሣሥ ፳፬ ቀን የሚከብረው በዓለ ልደታቸው አንደኛው ነው፡፡ መጽሐፈ ስንክሳር ዜና ልደታቸውን ሲናገር ‹‹ብፁዕ ወቅዱስ ሐዲስ ሐዋርያ›› በማለት በክብር ጠርቷቸዋል፡፡

ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ ‹‹እናንተን የሚቀበል እኔን ይቀበላል፤ እኔንም የሚቀበል የላከኝን ይቀበላል፡፡ ነቢይን በነቢይ ስም የሚቀበል የነቢይን ዋጋ ያገኛል፡፡ ጻድቅንም በጻድቅ ስም የሚቀበል የጻድቁን ዋጋ ያገኛል፡፡ ማንም ከእነዚህ ከተናናሾቹ ለአንዱ ቀዝቃዛ ጽዋ ብቻ በደቀ መዝሙር ስም የሚያጠጣ እውነት እላችኋለሁ፤ ዋጋው አይጠፋበትም፤›› /ማቴ.፲፥፵-፵፪/ በማለት የተናገረውን መለኮታዊ ቃል ኪዳን ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን መሠረት አድርጋ መጋቢት ፳፬ ቀን ፅንሰታቸውን፤ ታኅሣሥ ፳፬ ቀን ልደታቸውን፤ ጥር ፳፬ ቀን ስባረ ዐፅማቸውን፤ ግንቦት ፲፪ ቀን ፍልሰተ ዐፅማቸውን፣ ነሐሴ ፳፬ ቀን ደግሞ ዕለተ ዕረፍታቸውን በመንፈሳዊ ሥርዓት በደስታ ታከብራለች፡፡

የአቡነ ተክለ ሃይማኖትና የኹሉም ጻድቃን ጸሎትና በረከት ረድኤትና ምልጃ በመላው ሕዝበ ክርስቲያን ላይ ለዘለዓለሙ ጸንቶ ይኑር፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ምንጭ፡-

መለከት መጽሔት ፲፰ኛ ዓመት፣ ቍጥር ፱፡፡

መጽሐፈ ስንክሳር (ታኅሣሥ ፳፬፣ ጥር ፳፬፣ መጋቢት ፳፬፣ ግንቦት ፲፪ እና ነሐሴ ፳፬ ቀን)፡፡

ገድለ አቡነ ተክለ ሃይማኖት፡፡

ሠለስቱ ደቂቅን ከእሳት ያዳናቸው መልአክ ማን ነው? – ክፍል ሦስት (የመጨረሻ ክፍል)

 በዲያቆን ብርሃኑ አድማስ

ታኅሣሥ ፳፫ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

ሙት ላነሣውና ብዙ ተአምራትን ላደረገው ቅዱስ ጴጥሮስ አሁን ግን ይህን ዅሉ ጥበቃ የሚያደርግለት መልአኩ ነው፡፡ ይህ መልአክ የቅዱስ ጴጥሮስ ጠባቂ መልአክ እንደ ኾነ ብዙ ሊቃውንት በትርጓሜአቸው አስተምረዋል፡፡ በዚሁ ታሪክ ላይም፡- ‹‹ጴጥሮስም የደጁን መዝጊያ ባንኳኳ ጊዜ ሮዴ የሚሉአት አንዲት ገረድ ትሰማ ዘንድ ቀረበች፤  የጴጥሮስ ድምፅ መኾኑንም ባወቀች ጊዜ ከደስታዋ የተነሣ ደጁን አልከፈተችም፤ ነገር ግን ወደ ውስጥ ሮጣ ጴጥሮስ በደጅ ፊት ቆሞ እንዳለ አወራች። እነርሱም፦ ‹አብደሻል› አሏት። እርስዋ ግን እንዲሁ እንደ ኾነ ታስረግጥ ነበር። እነርሱም፦ ‹መልአኩ ነው› አሉ፤›› ተብሎ ተጠቅሷል /ቍ.፲፫-፲፭/፡፡ ከቤት ውስጥ የነበሩትም ‹‹ጴጥሮስ አይኾንም፤ መልአኩ ነው›› ያሏት ‹‹እርሱን ሊመስልሽ የሚችለው ጠባቂ መልአኩ ነው›› ማለታቸው ነበር፡፡ ይህም የኾነው በጥንት ክርስቲያኖች ዘንድ የጠባቂ መላእክት ጥበቃና መገለጥ በሰፊው ይታወቅ ስለ ነበረ ነው፡፡ በመጽሐፈ ጦቢት ላይም ቅዱስ ሩፋኤል ሰው መስሎ ለጦብያና ለቤተሰበው እንደዚሁም ለራጉኤልና ለቤተሰቡ ቀድሞ ጸሎታቸውን በማሳረግ፣ በኋላም ከፈተናቸው በማዳንና ሕይወታቸውን በመባረክ ተገልጦ አይተነዋል፡፡

እነዚህ ሁለት ታሪኮች የሚያስረዱን ጠባቂ መላእክት በድኅነታችን ውስጥ ትልቅ ስፋራ የሚሰጣቸውና በእርግጥም እነርሱ የሌሉበት ድኅነት የሌለ መኾኑን ነው፤ ልዩነቱ በአንዳንዶቹ ታሪኮች ላይ መገለጣቸው፣ በአንዳንዶቹ ላይ ደግሞ ተገልጠው ለሰው አለመታየታቸው ብቻ ነው፡፡ ጌታችንም በወንጌል ‹‹ከእነዚህ ከታናናሾቹ አንዱን እንዳትንቁ ተጠንቀቁ፤ መላእክቶቻቸው ዘወትር በሰማያት ያለውን የአባቴን ፊት ያያሉ እላችኋለሁና፤›› በማለት የተናገረው ስለ ጠባቂ መላእክቶቻችን ነው /ማቴ.፲፰፥፲/፡፡ በእያንዳንዱ እንቅስቃሴአችንና ፈተናችን ላይ ወደ እግዚአብሔር እያመለከቱ የሚጠብቁን፣ የሚያድኑን፣ የሚያስፈርዱልን ወይም የሚያስፈርዱብንም እነርሱ (ቅዱሳን መላእክት) ናቸውና፡፡ እንደናቡከደነፆር ያለውን አስፈርደውበት አውሬ አድርገው ሣር ያስግጡታል፡፡ እርሱ ራሱም ‹‹አንድ ቅዱስ ጠባቂ ከሰማይ ሲወርድ አየሁ፤›› ብሎ አሁንም እውነቱን አረጋግጧል /ዳን.፬፥፲፫/፡፡ እንደ ሄሮድስ ያለውን ደግሞ ‹‹ለእግዚአብሔርም ክብር ስላልሰጠ ያን ጊዜ የጌታ መልአክ መታው፤ በትልም ተበልቶ ሞተ፤›› ተብሎ እንደ ተጻፈው /ሐዋ.፲፪፥፳፫/፣ በእግዚአብሔር አስፈርደው ይቀሥፉታል፡፡

እንደ ዳንኤል፣ ቅዱስ ጴጥሮስ፣ ጻድቁ ዮሴፍ፣ ሠለስቱ ደቂቅ ያሉትን ደግሞ በጠባቂነታቸው ያድኗቸዋል፡፡ ‹‹… እርሱ ከአዳኝ ወጥመድ፣ ከሚያስደነግጥም ነገር ያድንሃልና። በላባዎቹ ይጋርድሃል፤ በክንፎቹም በታች ትተማመናለህ፡፡ እውነት እንደ ጋሻ ይከብሃል። ከሌሊት ግርማ፣ በቀን ከሚበርር ፍላጻ፣ በጨለማ ከሚሔድ ክፉ ነገር፣ ከአደጋና ከቀትር ጋኔን አትፈራም። በአጠገብህ ሺሕ በቀኝህም ዐሥር ሺሕ ይወድቃሉ፤ ወደ አንተ ግን አይቀርቡም። በዓይኖችህ ብቻ ትመለከታለህ፤ የኀጥአንንም ብድራት ታያለህ። አቤቱ አንተ ተስፋዬ ነህና ልዑልን መጠጊያህ አደረግህ። ክፉ ነገር ወደ አንተ አይቀርብም፤ መቅሠፍትም ወደ ቤትህ አይገባም። በመንገድህ ዅሉ ይጠብቁህ ዘንድ መላእክቱን ስለ አንተ ያዝዛቸዋልና፤ እግርህም በድንጋይ እንዳትሰናከል በእጆቻቸው ያነሡሃል … ›› ተብሎ ተጽፏልና /መዝ.፺፥፩-፲፪/፡፡

ሠለስቱ ደቂቅንም ጠባቂ መላእክቶቻቸው የሚያድኗቸው ቢኾንም ‹‹ለናቡከደነፆር የታየው አንድ  መልአክ ኾኖ ሳለ ሦስቱ መላእክት እንዳዳኗቸው ተደርጎ ለምን ይገለጻል?›› የሚል ጥያቄ ልናነሣ እንችላለን፡፡ እንዲህ ያሉትን ምሥጢራት መረዳት የምንችለው በቅዱሳት መጻሕፍት ያሉትን ተመሳሳይ ታሪኮችና ይህ የሚኾንበትን ምክንያት ስናውቅ ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል የጌታችንን ትንሣኤ አራቱም ወንጌላውያን መዝግበውልናል፤ አራቱም የመዘገቡበት መንገድ ተቃርኖ ባይኖረውም ልዩነት ግን አለው፡፡ ዐበይት ልዩነቶቹም ሦስት ነገሮች ላይ ይስተዋላሉ፤ ይኸውም የተገለጹት መላእክት፣ ወደ መቃብሩ የመጡት ሴቶች ማንነት እና ሴቶቹ የመጡበት ሰዓት በአዘጋገብ ይለያያል፡፡ ለርእሰ ጉዳያችን ቅርበት ባለው ትምህርት ላይ ትኩረት አድርገን ጥቂት ምሳሌዎችን እንደሚከተለው እናቀርባለን፤

ቅዱስ ማቴዎስ፡- ‹‹እነሆም የጌታ መልአክ ከሰማይ ስለ ወረደ ታላቅ የምድር መናወጥ ኾነ፤ ቀርቦም ድንጋዩን አንከባሎ በላዩ ተቀመጠ። መልኩም እንደ መብረቅ ልብሱም እንደ በረዶ ነጭ ነበረ። ጠባቆቹም እርሱን ከመፍራት የተነሣ ተናወጡ እንደ ሞቱም ኾኑ። መልአኩም መልሶ ሴቶቹን አላቸው፤ ‹እናንተስ አትፍሩ፤ የተሰቀለውን ኢየሱስን እንድትሹ አውቃለሁና፡፡ እንደ ተናገረ ተነሥቶአልና በዚህ የለም፡፡› የተኛበትን ስፍራ ኑና እዩ። ፈጥናችሁምዱና ከሙታን ተነሣ፤ እነሆም ወደ ገሊላ ይቀድማችኋል፡፡ በዚያም ታዩታላችሁ፤› ብላችሁ ለደቀ መዛሙርቱ ንገሯቸው፤›› ሲል የገለጸውን /ማቴ.፳፰፥፪-፯/፣ ቅዱስ ማርቆስ፡- ‹‹ወደ መቃብሩም ገብተው ነጭ ልብስ የተጐናጸፈልማሳ በቀኝ በኩል ተቀምጦ አዩና ደነገጡ …›› በማለት መዝግቦታል /ማር.፲፮፥፭/፡፡ ቅዱስ ሉቃስ ደግሞ ‹‹እነርሱም በዚህ ሲያመነቱ እነሆ ሁለት ሰዎች የሚያንጸባርቅ ልብስ ለብሰው ወደ እነርሱ ቀረቡ ፤›› ብሎ ጽፎታል /ሉቃ.፳፬፥፬/፡፡

ቅዱስ ዮሐንስም ስለ ትንሣኤው ብዙ ነገር ካተተ በኋላ ‹‹ማርያም ግን እያለቀሰች ከመቃብሩ በስተ ውጭ ቆማ ነበር። ስታለቅስም ወደ መቃብር ዝቅ ብላ ተመለከተች፤ ሁለት መላእክትም ነጭ ልብስ ለብሰው የኢየሱስ ሥጋ ተኝቶበት በነበረው አንዱ በራስጌ ሌላውም በእግርጌ ተቀምጠው አየች፤›› ሲል መዝግቦልናል /ዮሐ.፳፥፲፩-፲፪/፡፡ እነዚህን አገላለጾች ስናያቸው የአዘጋገብ ልዩነት ቢታይባቸውም ተቃርኖና የእውነታ ልዩነት ግን የላቸውም፡፡ ቅዱስ ማቴዎስና ቅዱስ ማርቆስ ስለ አንድ መልአክ ሴቶችን ማነጋገር ቢገልጹም ሌላ መልአክ እንዳልነበረ ግን አላመለከቱም፡፡ ወንጌላውያኑ ስለ አንድ መልአክ መታየት ይመዝግቡልን እንጂ የተናገሩት ግን ስለ ተለያዩ መላእክት ነው፡፡ ቅዱስ ማቴዎስ ከመቃብሩ ወጭ ድንጋዩን አንከባሎ ስለ ተቀመጠው መልአክ ዘግቦ ከመቃብሩ ውስጥ በቀኝ በኩል (በራስጌ ወይም በግርጌ) ስላለው መልአክ አልመዘገበም፡፡ ቅዱስ ማርቆስ ደግሞ ወደ ውስጥ ከገቡ በኋላ ስላለው መልአክ መዝግቦ ከውጭ በኩል ስላለው ወይም የመቃብሩ ድንጋይ ላይ ስላለው መልአክ አልመዘገበም፡፡ ሁለቱም ግን ‹‹ሌላ መልአክ አልነበረም›› በሚያሰኝ መንገድም አልገለጹልንም፡፡

ቅዱስ ሉቃስና ቅዱስ ዮሐንስ ደግሞ ሁለቱም መላእክት መኖራቸውንና በግርጌና በራስጌ መኾናቸውን ገልጸውልናል፡፡ ስለዚህ ዅሉም ትክክል ናቸው ማለት ነው፡፡ የተለያዩና የማይቃረኑ የተባለውም ስለዚህ ነው፡፡ የተለያዩትስ ለምንድን ነው ስንል ደግሞ አንድ መሠረታዊ መልእክት እናገኛለን፤ ይኸውም ስለ መላእክቱ የተለያየ ዓይነት መገለጥ የገለጹት ለተለያዩ ሰዎች በትንንሽ የጊዜ ልዩነት የታየውን መገለጥና ለአንዳንዶችም በተቀራራቢ፣ ነገር ግን በተለያየ ጊዜ የተገለጠውን ስለ መዘገቡ ነው፡፡ ለምሳሌ ቅዱስ ዮሐንስ ለመግደላዊት ማርያም የተደረገውን የአንድ ጊዜ መገለጥ ብቻ ሲነግረን፣ ቅዱስ ሉቃስ ደግሞ ለሌሎች ሴቶች የተደረገውን (ምክንያቱም ተመላልሰው ያዩም አንድ ጊዜም ያዩ አሉ፤ እንደዚሁም ብዙ ታሪኮች በውስጡ አሉና) እያሉ ከነሰዓቱ ስለ መዘገቡ እንጂ አንዱን ነጠላ ድርጊት ለያይተውና አሳሰተው መዝግበውት አይደለም፡፡ በዚህ መሠረት በዚህ ጽሑፍ መጀመሪያ ክፍል ላይ እንዳየነው ከመንፈስ ቅዱስ መገለጥ ተሰጥቷቸውና በጊዜው የነበረውን እውነተኛውን ትውፊት ከሐዋርያትና ከነበሩት ቅዱሳን ተምረው ከተረጐሙት መምህራን ሳይረዳ ልክ እንደነዚያ ርኩሳን እንደ ተባሉት እንስሳት ሳያመሰኳ ወይም እውነታውን ሳይቆነጥጥ ወይም እንደ ዓሣዎቹ ሐዋርያት የእምነት መከላከያ ቅርፊት (ጋሻ) እና ምሥጢራትን የሚረዳበት ክንፈ ጸጋ ሳይኖረው በአመክንዮ (ሎጂክ) ብቻ እረዳለሁም፣ አስረዳለሁም ቢል ይሳሳታል፡፡

ስለዚህ የሠለስቱ ደቂቅ ድኅነትን በተመለከተ በድርሳነ ሚካኤል ላይ ሚካኤል፤ በድርሳነ ገብርኤል ላይ ገብርኤል፤  በድርሳነ ሩፋኤል ላይ ደግሞ ሩፋኤል አዳናቸው ተብሎ መገለጹ ከላይ በወንጌል እንዳየነው ትውፊቱን ለያይቶ መዘገብ እንጂ ተቃራኒ ነገር አይደለም፡፡ በዚሁ መሠረት ሦስቱን ሕፃናት አናንያ፣ አዛርያና ሚሳኤልንም ያዳኗቸው ጠባቂ መላእክቶቻቸው፤ እነዚህም ቅዱስ ሚካኤል፣ ቅዱስ ገብርኤልና ቅዱስ ሩፋኤል ናቸው፡፡ ልክ ሥላሴ ለአብርሃም በተገለጹለት መንገድ ሦስት ኾነው ከሦስቱ በስተጀርባ ቆመው መታየት ነበረባቸው ካላልን በስተቀር ከጥንት ጊዜ ጀምሮ በተላለፈው ትውፊት ሦስቱ መላእክት የሦስቱ ሕፃናት ጠባቂ መላእክት ነበሩ፡፡ እንኳን ሰዎቹ ሦስት ኾነው ይቅርና አንድም ሰው ቢኾን ሦስትና ከዚያ በላይ መላእክት ሊገኙ ይችላሉ፡፡

ዮናታን ወልደ ሳዖል ‹‹በብዙ ወይም በጥቂት ማዳን እግዚአብሔርን አያስቸግረውምና፤›› እንዳለው /፩ኛሳሙ.፲፬፥፮/፣ በአንድም በብዙም መንገድ ማዳን የእግዚአብሔር ፈቃድና ምሥጢር እንጂ የመላእክቱ የማነስና የመብዛት ጉዳይ የሚከራክር አይደለም፡፡ እንዲህ ያለው ነገር እንኳን በመላእክት ዘንድ ቃል ኪዳን ተቀብለው በሚያማልዱ፣ በሚያድኑ ሰማዕታትና ቅዱሳንም ታሪክ ላይ በተደጋጋሚ የተገለጸ መኾኑን ከተለያዩ ገድላት ለመረዳት ይቻላል፡፡ ለምሳሌ አንድ ዓሣ አስጋሪ ሰው ‹‹መርምሕናም እርዳኝ?›› እያለ ቅዱስ መርምሕናምን ሲማጸን ቅዱስ ጊዮርጊስና ቅዱስ መርምሕናም በአንድነት መጥተው ዓሣ አስጋሪውን እንደ ረዱት ‹‹ወበጊዜሃ መጽኡ ኅቡረ ቅዱስ ጊዮርጊስ ወቅዱስ መርምሕናም ተጽዒኖሙ ዲበ አፍራሲሆሙ ….›› ተብሎ በተአምረ ጊዮርጊስ ተጽፎ ይገኛል፡፡ ይህ ግን በዋናነት ሊገለጽ የሚችለው በገድለ መርምሕናም እንደ ኾነ የታወቀ ነው፡፡ ስለዚህ በቅዱሳን ዘንድ አንዱ ብቻ ነው እንጂ ሌሎቹ የሉም የሚያስብል ታሪክም ድርጊትም የለም፤ ሊኖርም አይችልም፡፡ ልዩነት ያለ የሚመስለን መገለጦችን የምንረዳበት ሒደት አነስተኛ ሲኾን ብቻ ነው፡፡

የዚህ ጽሑፍየዚህ ጽሑፍ ማጠቃለያም፡- ‹‹ይህ ከኾነ ታዲያ በሠለስቱ ደቂቅ የድኅነት ታሪክ ውስጥ ቅዱስ ገብርኤል ጐልቶ ለምን ይወጣል? ዕለቱ (ታኅሣሥ ፲፱ ቀን) በዓል ኾኖ የሚከበረው ለቅዱስ ገብርኤል፤ በሥዕልም ላይ ‹አራተኛው ሰው› ተብሎ በናቡከደነፆር የተገለጸው የቅዱስ ገብርኤል ሥዕል የሚሣለው ለምንድን ነው?›› ለሚለው የብዙዎቹ ጥያቄ ምላሽ የሚሰጥ ይኾናል፡፡

ይህ የኾነበት ምክንያት ዝም ብሎ ወይም በአጋጣሚ አይደለም፡፡ እግዚአብሔር ሥጋዌውን አስቀድሞ የገለጸው መላእክትንም በሰው አምሳል እንዲገለጹ በማድረግም ጭምር ነው፡፡ ለምሳሌ ለሙሴ መጀመሪያ የተገለጠለት በዚሁ መንገድ ነበረ፡፡ ‹‹የእግዚአብሔርም መልአክ በእሳት ነበልባል በእሾኽ ቍጥቋጦ መካከል ታየው፤ እነሆም ቍጥቋጦው በእሳት ሲነድ፣ ቍጥቋጦውም ሳይቃጠል አየ፤›› ተብሎ ተጽፏልና /ዘፀ.፫፥፪/፡፡ ይህም ነገረ ተዋሕዶን ወይም ምሥጢረ ሥጋዌን የሚያስረዳ መገለጥ ነው፡፡ እግዚአብሔር ራሱን በመላእክት አምሳል ሲገልጥ ደግሞ ቅድሚያውን ስፍራ የሚይዘው ቅዱስ ገብርኤል ነው፡፡ ምክንያቱም ገብርኤል ማለት ‹‹ቃለ እግዚአብሔር›› እንደዚሁም ‹‹ሰውና አምላክ›› ማለት ስለ ኾነ ነው፡፡ እመቤታችንን ሊያበሥር የተላከውም በዚሁ ምክንያት ነው፡፡ ስለዚህ ‹‹አራተኛ ሰው አያለሁ›› እስኪል ድረስ እግዚአብሔር ለናቡከደነፆር ሥጋዌውን (ሰው መኾኑን) ገልጦ ያሳየው ከሦስቱ ሊቃነ መላእክት መካከል ይህን የተዋሕዶ ምሥጢር በስሙም በተልእኮውም ቅዱስ ገብርኤል የተሸከመው በመኾኑ ነው፡፡

ስለዚህም ሦስቱም ሊቃነ መላእክት በጠባቂ መላእክትነታቸውና ረቂቃን ኃይላት በመኾናቸው በአዳኝነት ቢጠቀሱም እግዚአብሔር ሊገልጠው ለፈለገው ታላቅ ምሥጢር ተስማሚ የኾነውን መልአክ (ራሱ ገብርኤል መኾኑ ትርጕምና መልእክት ያለው ነውና) የነገሥታትን ልጅ በሚመስል ጐልማሳ አምሳል የንጉሠ ሰማይ ወምድር የእግዚአብሔር የባሕርይ ልጅ ምሳሌ ኾኖ እንዲገለጽለት አድርጓል፡፡ በዓሉ ለገብርኤል የተሰጠውና ሥዕሉ የእርሱ የኾነበት ምክንያትም ይኸው ምሥጢር ነው፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንም ይህን የተዋሕዶ ምሥጢር መሠረት አድርጋ በዓሉ በቅዱስ ገብርኤል ስም በታላቅ ሥርዓት እንዲከበር፣ በሥዕሉም ቅዱስ ገብርኤል ጐልቶ እንዲታይ በማድረግ ነገረ ሥጋዌውንም፣ የሕፃናቱን ተጋድሎም፣ የመላእክቱን ጠባቂነትም ስትገልጽበትና ስታስረዳበት ትኖራለች፡፡ መጽሐፍ ቅዱስን በምልዓት መረዳት ያለውም በእውነተኛው የሐዋርያትና የሊቃውንት ትምህርት ትውፊትና ሥርዓተ አምልኮ ጸንታ በምትኖረው በዚህች ቅድስት ተዋሕዶ ሃይማኖት ነው፡፡

የእግዚአብሔር ቸርነት፤ የንጽሕት ቅድስት ድንግል ማርያም ልዩ አማላጅነት፣ የሊቃነ መላእክቱ ጥበቃና የቅዱሳን ዅሉ ምልጃ አይለየን፤ አሜን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ሠለስቱ ደቂቅን ከእሳት ያዳናቸው መልአክ ማን ነው? – ክፍል ሁለት

በዲያቆን ብርሃኑ አድማስ

ታኅሣሥ ፳፪ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

እንድንበላቸውና እንዳንበላቸው የታዘዝናቸው እንስሳት ከላይ በተገለጸው መንገድ እኛን የሚወክሉ መኾንና አለመኾናቸውን የሚያረጋግጥ የቅዱሳት መጻሕፍት ምስክርነት ወይም የሐዋርያዊው ትምህርት ትውፊት አለ ወይ? ከተባለ አዎን፤ በእርግጥ አለ፡፡ ሰፊውና ዋነኛው ምስክርም ቅዱስ ጴጥሮስ ያየው ራእይ ነው፡፡

በሐዋርያት ሥራ ‹‹… ተርቦም ሊበላ ወደደ፤ ሲያዘጋጁለት ሳሉም ተመስጦ መጣበት፡፡ ሰማይም ተከፍቶ በአራት ማዕዘን የተያዘ ታላቅ ሸማ የሚመስል ዕቃ ወደ ምድር ሲወርድ አየ፤ በዚያውም አራት እግር ያላቸው ዅሉ አራዊት፣ በምድርም የሚንቀሳቀሱ የሰማይ ወፎችም ነበሩበት፡፡ጴጥሮስ ሆይ፣ ተነሣና አርደህ ብላ!› የሚልም ድምፅ ወደ እርሱ መጣ፡፡ ጴጥሮስ ግን ‹ጌታ ሆይ አይሆንም፤ አንዳች ርኩስ የሚያስጸይፍም ከቶ በልቼ አላውቅምና› አለ፡፡  ደግሞም ሁለተኛ ‹እግዚአብሔር ያነጻውን አንተ አታርክሰው› የሚል ድምፅ ወደ እርሱ መጣ፡፡ ይህም ሦስት ጊዜ ኾነ፡፡ ወዲያውም ዕቃው ወደ ሰማይ ተወሰደ፤›› ተብሎ እንደ ተጻፈው /ሐዋ.፲፥፲-፲፮/፣ ቅዱስ ጴጥሮስ ይህን ራእይ ደጋግሞ ካየ በኋላ ራእዩ በቀጥታ ምግብ ሳይኾን ምሥጢራዊ መልእክት እንዳለው ተረድቶ ‹‹ትርጕሙ ምን ይኾን?›› እያለ ሲያስብ ነበር፡፡

በኋላም መንፈስ ቅዱስ ምሥጢሩን ገለጸለት፤ ‹‹… ጴጥሮስም ስለ ራእዩ ሲያወጣ ሲያወርድ ሳለ መንፈስ እነሆ ሦስት ሰዎች ይፈልጉሃል፤ ተነሥተህ ውረድ፡፡ እኔም ልኬአቸዋለሁና ሳትጠራጠር ከእነርሱ ጋር ሒድ አለው፤›› እንዲል /ቍ. ፲፱-፳/፡፡ ከታዘዘው ቦታ ከደረሰ በኋላም ‹‹አይሁዳዊ ሰው ከሌላ ወገን ጋር ይተባበር ወይም ይቃረብ ዘንድ እንዳልተፈቀደ እናንተ ታውቃላችሁ፤ ለእኔ ግን እግዚአብሔር ማንንም ሰው ‹ርኩስና የሚያስጸይፍ ነው› እንዳልል አሳየኝ፤›› በማለት ምስክርነቱን አስቀደመ /ቍ. ፳፯/፡፡ በዚህ ራእይ ያያቸው የማይበሉ እንስሳትም ምሳሌነታቸው ከእምነት ውጪ ላሉ ሰዎች እንደ ኾነ አረጋገጠ፡፡

ጌታችንም በዘመነ ሥጋዌው በሚያስተምርበት ጊዜ ‹‹… መንግሥተ ሰማያት ወደ ባሕር የተጣለች ከዅሉም ዓይነት የሰበሰበች መረብን ትመስላለች፤ በሞላችም ጊዜ ወደ ወደቡ አወጧት፡፡ ተቀምጠውም መልካሙን ለቅመው በዕቃዎች ውስጥ አከማቹ፤ ክፉውን ግን ወደ ውጪ ጣሉት፤›› በማለት /ማቴ.፲፫፥፵፯-፵፰/፣ መረብ የተባለችው ቤተ ክርሰቲያን ዅሉንም እንደምታጠምድ (ወደ እርሷ እንደምታቀርብ)፤ የዓሣዎቹ ሐዋርያትን ትምህርታቸውን ንቀው ከቤተ ክርስቲያን ወጥተው የሚወድቁት ደግሞ መናፍቃንና ኀጥአንን እንደሚወክሉ በምሳሌ አስተምሮናል፡፡

ለመሥዋዕት የሚቀርቡት እንስሳትም የሰማዕታትና የቅዱሳን ምሳሌዎች መኾናቸውን ቅዱስ መጽሐፍ ያስረዳናል፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት ‹‹አቤቱ ስለ ምን ለዘወትር ጣልኸኝ? በማሰማርያህ በጎች ላይስ ቍጣህን ስለ ምን ተቈጣህ?›› በሚለው መዝሙሩ መምለክያነ እግዚአብሔር እስራኤልን በጎች ብሎ ጠርቷቸዋል /መዝ.፸፬፥፩/፡፡  ‹‹እንደ በጎች ሊበሉን ሰጠኸን፤ ወደ አሕዛብም በተንኸን፤›› ዳግመኛም ‹‹ስለ አንተ ዅልጊዜም ተገድለናል፡፡ እንደሚታረዱም በጎች ኾነናል›› በማለት ሰማዕትነታቸውና ተጋድሏቸው እንደ መሥዋዕት በጎች እንደሚያስቈጥራቸው ተናግሯል /መዝ.፵፬፥፲፩-፳፪/፡፡  ይህ ቃል በእርግጥ ስለ ሰማዕታት የተነገረ መኾኑንም ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ስለ አንተ ቀኑን ዅሉ እንገደላለን፤ እንደሚታረዱ በጎችም ተቈጠርን፤›› በማለት አረጋግጦልናል /ሮሜ.፰፥፴፮/፡፡

ቅዱስ ጳውሎስ የደረሰበትን መከራና ሰማዕትነቱን ሲገልጽ ‹‹በመሥዋዕት እንደሚደረግ የእኔ ሕይወት ይሠዋልና፤ የምሔድበትም ጊዜ ደርሷል፤›› በማለት ሕይወቱን በመሥዋዕት መስሎ መናገሩም /፪ኛጢሞ.፬፥፮/፣ ጥንቱንም እነዚህ የመሥዋዕት እንስሳት የቅዱሳን፣ የንጹሐን ምእመናን፤ ርኩሳን የተባሉት ደግሞ የማያምኑትና የመናፍቃን ምሳሌዎች መኾናቸውን አመላካች ነው፡፡ ጌታችንም በነቢዩ በሕዝቅኤል ላይ አድሮ ‹‹‹እናንተም በጎቼ፣ የማሰማርያዬ በጎች ሰዎች ናችሁ፤ እኔም አምላካችሁ ነኝ› ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤›› በማለት በተናገረው ቃል /ሕዝ.፴፬፥፴፩/ እስራኤልን ‹‹በጎቼ›› ብሏቸዋል፡፡ ነቢያትም ዅሉ ይህን ቃል ደጋግመው ተናግረውታል፡፡ ጌታችንም በዘመነ ሥጋዌው ቃሉን አጽድቆታል፡፡ በመጨረሻው ዕለትም ‹‹በዚያን ጊዜ ኢየሱስ፦ በዚች ሌሊት ሁላችሁ በእኔ ትሰናከላላችሁ፡፡ ‹እረኛውን እመታለሁ፤ የመንጋውም በጎች ይበተናሉ› የሚል ተጽፎአልና፤›› /ማቴ.፳፮፥፴፩/ ያላቸው ቅዱሳኑ፣ ንጹሐኑ የመሥዋዕቱ እንስሳት የሚያመሰኩትና ቆንጥጦ ለመርገጥ የሚያስችል ስንጥቅ ሰኮና ያላቸው እነርሱ በመኾናቸው ነው፡፡

ስለዚህ በዘመነ ኦሪት ከሁለቱም ወገን የሚመደቡ እንስሳትን የሚያርዱና የሚበሉ ሰዎች የነበሩ ቢኾንም እግዚአብሔርና የእርሱ የኾኑት የሚቀበሉት ግን ከንጹሐን ወገን የኾኑትን እንስሳት ብቻ ነበር፡፡ ይህም ምሳሌ ስለ ኾነ ዛሬም ከሁለቱም ወገን የሚመደብ አለ፤ እግዚአብሔርና የእግዚአብሔር የኾኑት የሚቀበሉትም በንጹሐን እንስሳት ከተመሰሉት ከሐዋርያት፣ ከሰማዕታት፣ ከቅዱሳን ሊቃውንትና ከእውነተኞች መምህራን የሚገኘውን ትምህርት ብቻ ነው፡፡ ቀደም ብለን እንደ ገለጽነው እነዚህ ቅዱሳን በበግና በመሳሰሉት የተመሰሉት ሰኮናቸው የተሰነጠቀ እንስሳት በትክክል መሬትን ጨብጦ ወይም ቆንጥጦ መርገጥ እንደሚችሉት እንደዚሁ ሃይማኖታቸውን በሥራ ገልጠው ከእነርሱ የሚጠበቀውን መሥዋዕትነት ወይም ሰማዕትነት በገቢር ገልጸው የሚኖሩ በመኾናቸው ነው፡፡ በባሕር ውስጥ በሚኖረው ቅርፊትና ክንፍ ባለው ዓሣ የተመሰሉትም በዚህ እንደ ባሕር በሚነዋወጥ ዓለም ውስጥ እየኖሩ ወደ ከፍተኛው ጸጋና ክብር ብቻ ሳይኾን ወደ ላይኛው መለኮታዊ ምሥጢር ብቅ የሚሉበት ክንፈ ጸጋ፣ የዚህን ዓለም አለማመን፣ ክሕደትና ኑፋቄ ድል የሚነሡበት በቅርፊት የተመሰለ የእምነት ጋሻና ጦር ስላላቸው ነው፡፡

እኛንም ‹‹በዅሉም ላይ ጨምራችሁ የሚንበለበሉትን የክፉውን ፍላጻዎች ሁሉ ልታጠፉ የምትችሉበትን የእምነትን ጋሻ አንሡ፤›› ሲሉ አስተምረውናልና /ኤፌ.፮፥፲፮/፣ የእምነት ጋሻችንን እናነሣለን፡፡ ደግሞም  ‹‹የጦር ዕቃችን ሥጋዊ አይደለምና፥ ምሽግን ለመስበር ግን በእግዚአብሔር ፊት ብርቱ ነው፤›› /፪ኛቆሮ.፲፥፬/ ተብሎ እንደ ተጻፈው መሣሪያችንም ሥጋዊ የጦር ትጥቅ ሳይኾን የዲያብሎስን የተንኮልና የክሕደት ምሽጎች ለመስበር የበረታው የእግዚአብሔር ቃል ነው፡፡ ስለዚህ ከእነዚህ ክንፍና ቅርፊት የሌላቸው ከተባሉት፤ ያለ መከላከያ ኾነው ራሳቸውን አስማርከው እኛንም ወደ እነርሱ ጥርጥርና ክሕደት ሊስቡ ወደሚሮጡት፤ ዳግመኛም የእግዚአብሔርን ቃል ምሥጢራት ወደማያመላልሱትና ሰኮና በተባለ ክሳደ ልቡናቸው መሬት ገቢርን ወደማይጨብጡት እንዳንጠጋ ‹‹እነርሱ ዅልጊዜም በነፍስ ርኩሳን ናቸው፤›› ተብሎ ተጽፎልናል፡፡ ‹‹ሠለስቱ ደቂቅን ከእሳት ያወጣቸው ማን ነው?›› ለሚለውን ጥያቄ ምላሽ የምንሰጠውም ‹‹ያመሰኳሉ›› የተባሉ ቅዱሳን የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ቃሉን እያመላለሱ መርምረው፣ ምሥጢሩን ከእግዚአብሔር ዘንድ ተረድተው እንደ ጻፉልን በማመንና በዚሁ (በእነርሱ) መንፈስ ይኾናል ማለት ነው፡፡

በእርግጥ ሠለስቱ ደቂቅን ከእሳት ያዳናቸው መልአክ ማን ነው?

መጀመሪያውንም መጽሐፍ ቅዱሱ ሠለስቱ ደቂቅን ከእሳት ያወጣቸው ‹‹ገብርኤል ነው›› አይልም፡፡ መጽሐፍ ቅዱሱ የሚለው የሚከተለውን ነው፤ ‹‹የዚያን ጊዜም ንጉሡ ናቡከደነፆር ተደነቀ ፈጥኖም ተነሣ፤ አማካሪዎቹንም፡- ‹ሦስት ሰዎች አስረን በእሳት ውስጥ ጥለን አልነበረምን?› ብሎ ተናገራቸው። እነርሱም፡- ‹ንጉሥ ሆይ እውነት ነው› ብለው ለንጉሡ መለሱለት። እርሱም፡- ‹እነሆ እኔ የተፈቱ በእሳቱም መካከል የሚመላለሱ አራት ሰዎች አያለሁ፤ ምንም አላቈሰላቸውም የአራተኛውም መልክ የአማልክትን ልጅ ይመስላል ብሎ መለሰ፤›› /ዳን.፫፥፳፬-፳፭/፡፡ በዚህ አገላለጽ መሠረት አራተኛውን ሰው ያየው ንጉሡ ናቡከደነፆር ሲኾን የጨመረበት ቃል ቢኖር ‹‹አራተኛው የአማልክትን ልጅ ይመስላል›› የሚለው ነው፡፡

ለመኾኑ አራተኛውን ሰው እርሱ ብቻ ለምን አየው? ሌሎቹ ለምን አላዩትም? የጥያቄው ቍልፍ ምሥጢር ያለው ከዚህ ላይ ነው፡፡ እውነቱን ለመናገር ይህ ሰው ጥንቱንም ሠለስቱ ደቂቅን ወደ እሳት የጣላቸው ሕዝቡን ለራሱ ምስል በማሰገድ ራሱን አምላክ አድርጎ ሊያስመልክ አስቦ ነበር፡፡ ታዲያ ራሱንና እርሱን የመሰሉትን አማክት አድርጎ የሚቈጥር ከኾነ የሚያየውን አራተኛውን  ሰው ‹‹የእኛን ልጅ ይመስላል›› ወይም ‹‹እኛን ይመስላል›› ለምን አላለም? ከዚያ ይልቅ አርቆ ሌሎች አማልክትን የሚያመልክ አስመስሎ ‹‹የአማልክትን ልጅ ይመስላል›› ያለበት ምሥጢር ምንድን ነው? ንጉሡ ይህን ያለበት ምክንያት እነርሱ ሳያዩት ከሠለስቱ ደቂቅ ጋር አራተኛ ሰው ወደ እሳቱ ገብቶ ሳይኾን ነገሩ የወልደ እግዚአብሔርን በሥጋ መገለጥ የሚያመላክት ምሥጢር ሳለለው ነው፡፡

በብሉይ ኪዳን ከተገለጹት ታላላቅ ሦስት የእግዚአብሔር መገለጦች ውስጥ ሦስተኛው ይህ የሠለስቱ ደቂቅ የድኅነት ታሪክ ነው፡፡ አንደኛው መገለጥ በመምሬ የአድባር ዛፍ ሥር እግዚአብሔር ለአብርሃም በሦስት ሰዎች አምሳል የተገለጠው መገለጥ ሲኾን /ዘፍ.፲፰/፣ ሁለተኛውም እግዚአብሔር ለአባታችን ለያዕቆብ በጐልማሳ አምሳል ተገልጾ ሲታገለው ያደረበት ታሪክና ያዕቆብም መጀመሪያ ‹‹ካልባረከኝ አልለቅህም›› ብሎ ከተባረከ በኋላ ‹‹‹እግዚአብሔርን ፊት ለፊት አየሁ፤ ሰውነቴም ድና ቀረች› ሲል የዚያን ቦታ ስም ‹ጵንኤል› ብሎ ጠራው፤›› ያሰኘው መገለጥ ነው /ዘፍ.፴፪፥፳፭-፴፪/፡፡ ሦስተኛው መገለጥ ደግሞ አላዊው የባቢሎን ንጉሥ ሠለስቱ ደቂቅን ወደ እቶነ እሳት በጣለበት ወቅት ያደረገው መገለጥ ነው፡፡

ሦስቱም መገለጦች የሚያመሳስሏቸው ሁለት ጠባይዓት አሏቸው፡፡ የመጀመሪያው በሦስቱም መንገድ እግዚአብሔር በሰው መልክና አምሳል መገለጡ ሲኾን ሁለተኛውና ዋነኛው ቃለ እግዚአብሔር በሥጋዌ (ሰው በመኾን) ተገልጦ ለሰው ፍጹም ድኅነት የሚሰጥ መኾኑን አስቀድሞ በምሳሌ መግለጥ ነው፡፡ መሠረታዊ መልእክቱ ደግሞ አምላክ ሰው ከኾነ በኋላ የሚያድነው የተስፋውን ዘር እስራኤልን ብቻ ሳይኾን አሕዛብንም ጭምር መኾኑን ለማሳየትና አሕዛብም የሥጋዌው ነገር ቀድሞ የተገለጠው ለእስራኤል ብቻ ስለ ኾነ እኛ ልናምንበት አይገባም እንዳይሉ ለዚህ ደንዳናና ጨካኝ ናቡከደነፆርም ጭምር ተገለጠለት፡፡

የነነዌ ሰዎች ታሪክም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ኾኖ የተቀመጠውና እግዚአብሔር ለአሕዛብም ድኅነት ይፈጽም እንደ ነበር የተመዘገበው እግዚአብሔር የእስራኤል ብቻ ሳይኾን የዅሉም አምላክ መኾኑን ራሱ ብሉይ ኪዳንም ምስክር እንዲኾን ነው፡፡ እነዚህን የመሰሉ ሌሎች ታሪኮችና ምሳሌዎችም በብዛት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይገኛሉ፡፡ በዚህ በሠለስቱ ደቂቅ ድኅነት ውስጥ የታየው መገለጠጥ ዋነኛው ምሥጢርና መልእክትም የእግዚአብሔርን ሰው መኾንና አዳኝነት፤ እንደዚሁም እንደ ሠለስቱ ደቂቅ እሳትና ስለት፣ ሰይፍና ጐራዴ፤ እስራትና ግርፋት የሚቀበሉ ሰማዕታትን ዅሉ የሚያድናቸው እርሱ መኾኑን መግለጽ ነው፡፡ ታዲያ ዋነኛው መልእክቱና ምሥጢሩ ይህ ከኾነ ገብርኤልም ኾነ ሌሎቹ መላእክት ለምን ሠለስቱ ደቂቅን ከእሳት አወጡ (አዳኑ) ይባላሉ? በቅዱሳት መጻሕፍት ምስክርነት መሠረት ለሰዎች ከጊዜያዊና ምድራዊ አደጋና ሰዎች ከሚያመጡባቸው መከራ ድኅነት ሲደረግላቸው ድኅነታቸውን የሚፈጽሙላቸው ቅዱሳን መላእክት ማለትም ጠባቂ መላእክቶቻቸው ናቸው፡፡

ይህም ምንም እንኳን አንዳንድ ጊዜ በግልጽ፣ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ በምሥጢር ቢገለጽም የእግዚአብሔር መላእክት ከሚጠብቋቸው ሰዎች ተለይተው አያውቁም፡፡ ለምሳሌ በሐዋርያት ሥራ ላይ ቅዱስ ያዕቆብን ያስገደለው ሄሮድስ ቅዱስ ጴጥሮስንም ለመግደል ባሰረው ጊዜ በዚያ ወቅት እንዲሞት እግዚአብሔር ስላልፈቀደ መልአኩ እንዲያድነው አድርጓል፡፡ ‹‹እነሆም የጌታ መልአክ ቀረበ፤ በቤትም ውስጥ ብርሃን በራ፡፡ ጴጥሮስንም ጎድኑን መትቶ አነቃውና ‹ፈጥነህ ተነሣ› አለው። ሰንሰለቶቹም ከእጁ ወደቁ። መልአኩም፡- ‹ታጠቅና ጫማህን አግባ› አለው፤ እንዲሁም አደረገ። ‹ልብስህንም ልበስና ተከተለኝ› አለው። ወጥቶም ተከተለው፡፡ ራእይንም የሚያይ ይመስለው ነበር እንጂ በመልአኩ የሚደረገው ነገር እውነት እንደ ኾነ አላወቀም። የመጀመሪያውንና የሁለተኛውንም ዘብ አልፈው ወደ ከተማ ወደሚያወጣው ወደ ብረቱ መዝጊያ ደረሱ፤ እርሱም አውቆ ተከፈተላቸው፡፡ ወጥተውም አንዲት ስላች አለፉ፡፡ ወዲያውም መልአኩ ከእርሱ ተለየ። ጴጥሮስም ወደ ልቡ ተመልሶ፦ ‹ጌታ መልአኩን ልኮ ከሄሮድስ እጅና የአይሁድ ሕዝብ ይጠብቁት ከነበረው ዅሉ እንደ አዳነኝ አሁን በእውነት አወቅሁ› አለ፤›› ተብሎ እንደ ተጻፈ /ሐዋ.፲፪፥፯፲፩/፡፡

ይቆየን