፲፪ኛው ዙር ሐዊረ ሕይወት ደረሰ

መጋቢት ፰ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

mk-logo11

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን ፲፪ኛ ዙር የሐዊረ ሕይወት መርሐ ግብሩን ለማካሔድ ዝግጅቱን አጠናቋል፡፡ በጉዞውም ከዐሥራ ሁለት ሺሕ በላይ ምእመናን ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ማኅበሩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመመካከር የጕዞው ቅድመ ኹኔታዎችን ያመቻቸ ሲኾን፣ በመርሐ ግብሩም ከአሁን ቀደም እንደሚደረገው ዅሉ ትምህርተ ወንጌልና ምክረ አበው በቤተ ክርስቲያን መምህራን፤ ያሬዳዊ ዝማሬ በተጋባዥና በማኅበሩ መዘምራን ይቀርባሉ፡፡

‹‹ዅላችሁም በዚህ ልዩ መርሐ ግብር በመሳተፍ ነፍሳችሁንቃለ እግዚአብሔር አስደስቱ›› ሲል ማኅበረ ቅዱሳን በቤተ ክርስቲያን ስም መንፈሳዊ ግብዣውን ያቀርባል፡፡

  • የመርሐ ግብሩ ቦታ፡- ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት በቾ ወረዳ ቤተ ክህነት የምትገኘው ቱሉ ጉጂ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን
  • ጉዞው የሚደረግበት ዕለት፡ እሑድ መጋቢት ፳፬ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም
  • መነሻ ቦታ፡ አምስት ኪሎ የሚገኘው የማኅበሩ ሕንጻ
  • መነሻ ሰዓት፡- ከጠዋቱ 12፡00
  • መመለሻ ሰዓት፡- ከምሽቱ 12፡00

 የጕዞው ቲኬት የሚገኝባቸው ቦታዎች፡-

  • በማኅበሩ ሕንጻ
  • በማኅበሩ ንዋያተ ቅድሳት መሸጫ ሱቆች (መርካቶ ደ/ኃ/ቅራጉኤል፣ ፒያሣ ገ/ጽ/ቅ/ጊዮርጊስ፣ ቦሌ ሰአሊተ ምሕረት ማርያም)
  • በአቡነ ጎርጎርዮስ ትምህርት ቤቶች (አቧሬ፣ ሲኤምሲ፣ ለቡ)

 ማሳሰቢያ፡

ለመስተንግዶና ለቍጥጥር ያመች ዘንድ የትኬት ሽያጩ መጋቢት ፲፭ ቀን ፳፻፱ . ስለሚጠናቀቅ ምእመናን ከተጠቀሰው ቀን በፊት ትኬቱን እንድትገዙና በጉዞው ዕለትም መነሻ ሰዓቱን አክብራችሁ በቦታው እንድትገኙ የሐዊረ ሕይወቱ ዐቢይ ኰሚቴ ያሳስባል፡፡

የበለጠ መረጃ ለማግኘት በስልክ ቍጥሮች፡-

09 11 89 89 90

09 11 47 35 05

09 11 34 03 86

በመደወል መጠየቅ ይቻላል፡፡

ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን!

ማኅበረ ቅዱሳን፡፡

የስብከተ ወንጌል አገልግሎቱንና ሰባክያኑን እንደግፍ

የካቲት ፱ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

ሞተር

በገጠርና ጠረፋማው የአገራችን ክፍል ተበታትነው የሚኖሩ ብዙ ወገኖቻችን እውነተኛውን የወንጌል ብርሃን ሳይመለከቱ፣ ለሥላሴ ልጅነት ሳይበቁ፣ በጎውን ነገር ሳያዩ፣ ድኅነትን እንደ ናፈቁ ሞተ ሥጋ ይቀድማቸዋል፡፡

ጥቂት የእግዚአብሔርን ቃል ያወቁ ወንድሞች የምሥራቹን የእግዚአብሔርን ቃል ለማብሠር፤ ለወገኖቻቸው የወንጌል ብርሃንን ፈንጥቀው ወደ ዘላለማዊ ሕይወት ለማሸጋገር ሲሉ የበረኃው ንዳድ፣ የአራዊቱ ግርማ፣ ረኃቡና ጥሙ፣ ስቃዩና ሕመሙ ሳይበግራቸው፣ እንቅልፍ በዐይናቸው ሳይዞር የሐዋርያትን አሰር ተከትለው ከጠረፍ ጠረፍ እየተዘዋወሩ ወንጌልን ይሰብካሉ፡፡

የእናት ቤተ ክርስቲያናቸውን ርእይ በማንገብ ለወገኖቻቸው በጥምቀት የሥላሴ ልጅነትን ለማሰጠት ለቀናት በረኃውን በእግር ያቋርጣሉ፤ እነርሱ በእግር ሁለት፣ ሦስት ቀን የሚወጡ የሚወርዱበትን መንገድ ሌሎች የጥፋት መልእክተኞች (መናፍቃን) በዘመናዊ ተሽከርካሪ ገደል ኮረብታውን ጥሰው፣ በግል ሄሊኮፕተር ጭምር ያለ ችግር በረኃውን አልፈው ቀድመው በመድረሳቸው ብቻ ወገኖቻችንን ይነጥቃሉ፤ ያልዘሩትን ያጭዳሉ፡፡ ይህም ለእኛ ሰባክያነ ወንጌል ሌላ ድካም ይኾንባቸዋል፤ ቀድመው ባለ መድረሳቸው በወገኖቻቸው ላይ የተዘራውን ክፉ አረም ለመንቀል ጊዜም ጕልበትም ይፈጃልና፡፡

እነዚያ የበረኃ ሐዋርያት ‹‹ወልድ ዋሕድ›› ብለው ሲያስተምሯቸው፣ ስለ ቅዱሳኑ ምልጃ ሲነግሯቸው፣ የእግዚአብሔርን መንግሥት መውረሻ ስለኾነችው ዳግም ልጅነትን ስለምታሰጠው አሐቲ ጥምቀት ሲያበሥሯቸው ‹‹እስከዚህ ዕድሜያችን ድረስ ስንጠብቃችሁ ነበር፤ እኛ የምናምነው አያቶቻችን የነገሩንን የቄሶች ሃይማኖት ነው፡፡ አስተምሩን፤ አጥምቁን፤›› ይሏቸዋል፡፡

ሰባክያኑ ከዚህ ያለውን አረም ነቅለው ሌሎች ወገኖቻቸው ጋር ለመድረስ ሲነሡ በክንፍ አይበሩ ነገር እንዴት ይድረሱ? ሥጋ ለባሽ ናቸውና ከመንገድ ይመለሳሉ፡፡ እነዚህ የበረኃ ሐዋርያት በአንዲት ሞተር ሳይክል እጦት ምክንያት በጊንጥና በእባብ እየተነደፉ፣ አጋዥ አጥተው ለወገኖቻቸው ቃለ ወንጌልን ሳያዳርሱ ይቀራሉ፡፡

እነዚህ ሐዋርያት ያለምንም እገዛ በረኃውን በእግር እያቋረጡ ከ፹፮ ሺሕ በላይ ወገኖችን በጥምቀት የሥላሴ ልጅነትን እንዲያገኙ ማድረግ ከተቻላቸው፣ ድካማቸውን በትንሹም ቢኾን ብንቀንስላቸው ደግሞ በመቶ ሺሕ የሚቈጠሩ ወገኖችን እንደሚያስጠምቁ የታመነ ነው፡፡

በጕዞ የደከመ የሰባክያኑን ጕልበት ለማደስ ፍቱን መድኀኒቱ ሞተር ሳይክል ነውና እኛ ከቤታችን ኾነን በጕዞ ሳንደክም አንዲት ሞተር ሳይክል በመለገስ ተራራውንና ቁልቁለቱን፣ በረኃውንና ቁሩን ከሐዋርያቱ ጋር አብረን እንውጣ፤ እንውረድ፡፡ የስብከተ ወንጌል አገልግሎቱንና ሰባክያኑን በመደገፍ የበረከቱ ተሳታፊዎች እንኹን፡፡

ሞተር

ለድጋፋችሁና ሐሳቦቻችሁ በ 09 60 67 67 67 ደውሉልን

በማኅበረ ቅዱሳን የትምህርትና ሐዋርያዊ አገልግሎት ዋና ክፍል የስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ መርሐ ግብር

ታላቅ የምሥራች ለኦርቶዶክሳውያን ምእመናን!

app-01በአሜሪካ ማእከል

ጥር ፱ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

በማኅበረ ቅዱሳን የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ አገልግሎት ክፍል የተሠራው ‹‹ተዋሕዶ›› የተሰኘው የስልክ አፕሊኬሽን አንድሮይድ (Android) የተባለውን የቴክኖሎጂ ውጤት ለሚጠቀሙ ዘመናዊ ስልኮች እና የኪስ ኮምፒውተሮች አመቺ በኾነ መልኩ እንደገና ተሻሽሎ ቀረበ፡፡

ይህ አፕሊኬሽን በ፳፻፮ ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ ተዘጋጅቶ የነበረ ሲኾን፣ ክፍሉ ከተጠቃሚዎቹ የደረሱትን አስተያየቶች በማካተት ልዩ ልዩ ማሻሻያዎችን አድርጎ ለሁለተኛ ጊዜ እንዲቀርብ አድርጓል፡፡

አፕሊኬሽኑ በውስጡም የጸሎት መጻሕፍትን፣ ወቅታዊ የኾኑ መንፈሳዊ ትምህርቶችን፣ ዜናዎችን እና ልዩ ልዩ መረጃዎችን፤ ያሬዳውያን መዝሙሮችን፣ መንፈሳዊ የኪነ ጥበብ ዝግጅቶችን፤ እንደዚሁም የየዕለቱ ምንባባትን እና የሬዲዮ ሥርጭቶችን፤ የቀን መቍጠሪያዎችን፣ የበዓላትና አጽዋማት ማውጫዎችን፤ በተጨማሪም በሰሜን አሜሪካ፣ በካናዳ እና በአውሮፓ በሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት የሚከናወኑ መርሐ ግብራትንና ሌሎችንም አርእስተ ጉዳዮች አካቷል፡፡

በልዩ ልዩ የመገናኛ መንገዶችና ገጾች ላይ በሃይማኖት ስም የሚጻፉ የኑፋቄ ትምህርቶች በስፋት በሚለቀቁበት በዚህ ዘመን ይህ የቴክኖሎጂ ውጤት መዘጋጀቱ ለምእመናን ታላቅ የምሥራች ነው፡፡

ስለዚህም አንድሮይድ (Android) የተሰኘውን የቴክኖሎጂ ውጤት መጠቀም የሚችል ዘመናዊ ስልክ ወይም የኪስ ኮምፒዩተር ያላችሁ ምእመናን ዅሉ ከጎግል ፕለይ (Google Play) ውስጥ ተዋሕዶ (Tewahedo) የሚለውን ቃል በመፈለግ በዚህ አፕሊኬሽን እንድትጠቀሙና ኦርቶዶክሳዊ ይዘት ባለው ቃለ እግዚአብሔር ነፍሳችሁን እንድታጠግቡ፣ አእምሯችሁንም በመንፈሳዊ ዕውቀት እንድታጎለብቱ ስንል መንፈሳዊ ግብዣችንን እናቀርባለን፡፡

የማኅበረ ቅዱሳን ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ አገልግሎት ክፍል ይኼንኑ አፕሊኬሽን አይ ኦ ኤስ (IOS)ን ለሚጠቀሙ የእጅ ስልኮች እና የኪስ ኮምፒውተሮች ከአሁን በፊት ማቅረቡ የሚታወስ ነው፡፡