Entries by Mahibere Kidusan

የጋብቻ ሕይወት እና የሩካቤ ሥርዓት – ክፍል ፱

ባልና ሚስት በፅንስ፣ በአራስነትና በወር አበባ ወቅት፤ እንደዚሁም በበዓላትና በአጽዋማት ቀን ሩካቤ ሥጋ ማድረግ እንደማይገባቸው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ታስተምራለች፡፡ ከዚህ በተረፈ ግን ሰይጣን የሚፈትንበትን ክፍተት እንዳያገኝ ባልና ሚስት ሊለያዩ አይገባም፡፡ “ለጸሎት ትተጉ ዘንድ ተስማምታችሁ ለጊዜው ካልኾነ በቀር እርስ በርሳችሁ አትከላከሉ፤ ራሳችሁን ስለ አለመግዛት ሰይጣን እንዳይፈታተናችሁ ደግሞ አብራችሁ ኹኑ፤” እንዳለ ቅዱስ ጳውሎስ (፩ኛ ቆሮ. ፯፥፭)፡፡ ይህ የሐዋርያው ትምህርት “ሰውነታችሁን ንጹሕ አድርጋችሁ በምትጾሙበት፣ በምትጸልዩበት ጊዜ ነው እንጂ ሥራችሁን ከፈጸማችሁ በኋላ ግን ወደ ፈቃዳችሁ ተመለሱ፡፡ የምትሹትን ስላጣችሁ ሰይጣን ድል እንዳይነሳችሁ” ተብሎ በፍትሐ ነገሥትም ተጠቅሷል (አን. ፲፭፣ ቍ. ፳፬)፡፡ ይህም ባልና ሚስት፣ የጾም፣ የጸሎት፣ የበዓል ወቅት ካልኾነ በቀር ሳይለያዩ ፈቃዳቸዉን መፈጸም እንደሚገባቸው ያስገነዝባል፡፡

የጋብቻ ሕይወት እና የሩካቤ ሥርዓት – ክፍል ፰

ግጭት፣ ሐሜት፣ አሉባልታ፣ ጭቅጭቅ፣ ቅናት፣ ሱስና የመሳሰሉ ጎጂ ልማዶች ጋብቻን ከሚፈታተኑ ችግሮች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ እነዚህ ልማዶች የትዳር ሕይወትን አሰልቺ ሊያደርጉት ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ለፍቺ የሚያበቁ አይደሉም፡፡ ምክንያቱም በሁለቱ ጥንዶች መካከል ውስጣዊ መናበብ ካለ ለችግሮቹ መፍትሔ ማምጣት ይቻላልና፡፡ ለዚህም መፍትሔው ከጸሎት ቀጥሎ የችግሩን መንሥኤ በትክክል መረዳትና መውጫ መንገዱን መፈለግ ነው፡፡ በመሠረቱ በጋብቻ ሕይወት የሚያጋጥሙ መሰናክሎችን እንደ መልካም አጋጣሚ መውሰድ እንችላለን፡፡ እንዴት ከተባለ የትዳራችንን መሥመር ለማስተካከል በምናደርገው ጥረት ውስጥ ልዩ የፍቅር ጕዞ ልንጀምር ስለምንችል፡፡ ለምሳሌ ከጥንዶች አንዱ እያመሸ የሚገባ፣ በሱስ የተጠመደ፣ የሚጨቃጨቅ፣ የሚሳደብ፣ ወዘተ ከኾነ ከመቈጣትና ከማጥላላት ይልቅ ከዚህ ልማድ እንዲወጣ ልዩ ክብካቤ ማድረግ ውጤቱ ጥሩ ይኾናል፡፡ ይህም ትዳሩን ይበልጥ እንዲወድና ራሱን እንዲያይ ሊያግዘው ይችላል፡፡ ፍቅር፣ የጠብ ዂሉ መድኀኒት ናትና፡፡

የጋብቻ ሕይወት እና የሩካቤ ሥርዓት – ክፍል ፯

የፍትወት ፆር ከመበርታቱ የተነሣ ከትዳር አጋር አልፎ ወደ ሌላ የሚሔድ ካለ ስለ አንደኛው ደኅንነትና ስለ ጋብቻ ክቡርነት፣ እንደዚሁም ስለ ሥጋ ወደሙ ቅድስና ሲባል መፋታት ይፈቀዳል፡፡ አምላካችን “ኢትዘሙ፤ አታመንዝር” በማለት እንዳስተማረን ዝሙት መሥራት ኃጢአት ነው (ዘፀ. ፳፥፲፬)፡፡ ቢቻል ከኀጢአት ተለይቶ ለመኖርና በጽድቅ ሥራ ለመትጋት መሽቀዳደም ተገቢ ነው፤ ኾኖም ኀጢአት እየሠሩ አብሮ ከመኖር ተለያይቶ በጽድቅ መኖር ይገባልና ከመዘሞት መፋታት ይሻላልና፡፡ ደግሞም በአንድነት ወደ ገሃነመ እሳት ከመጣል ይልቅ ተለያይቶ ወደ መንግሥተ ሰማያት መግባት ይመረጣል፡፡ “… ሁለት ዓይና ኾነህ ወደ ገሃነመ እሳት ከምትገባ ይልቅ አንድ ዐይና ኾነህ ወደ መንግሥተ ሰማያት ብትገባ ይሻልሃልና” ተብሎ እንደ ተጻፈ (ማቴ. ፭፥፳፱-፴)፡፡

ይህ ሲባል ግን የሐሰት ወሬ በመስማትና በይኾናል (በጥርጥር) ብቻ ለመፋታት መወሰን ተገቢ አይደለም፡፡ ከተጋቢዎቹ አንዱ ወይም ሁለቱም በዝሙት እየወደቁ ከኾነና በንስሐ መመለስ ካልቻሉ ፍቺ ይፈጸማል፡፡ በጋብቻ ወቅትም ይኹን ከጋብቻ በፊት ወይም በኋላ መዘሞት (መሴሰን) አስነዋሪ ድርጊት ነው፡፡ ስለዚህም መፋታት ከሚቻልባቸው መንገዶች አንዱ ዝሙት እንዲኾን ተደንግጓል፡፡ ይህም ዝሙት ቊርባንን ከማፍረሱም ባለፈ ከጋብቻ ውጪ ልጅ መውለድን፣ እንደዚሁም በጥንዶቹም፣ በልጆቻቸውም ላይ ሞትን ያመጣልና የሰውን ልጅ ከጥፋት ለመታደግ ነው፡፡

የጋብቻ ሕይወት እና የሩካቤ ሥርዓት – ክፍል ፮

የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ በፍቅርና በአንድነት መኖርን የሚሰብክ በመኾኑ ፍቺን አጥብቆ ይከለክላል፡፡ ከተጋቡ በኋላ የሕይወት መሰናክሎችን በመፍታት አብሮ መኖር እንጂ መለያየት ክርስቲያናዊ ሥርዓት አይደለምና፡፡ በመኾኑም ችግሮችን በውይይት በመፍታት፣ በመመካከርና በመፈቃቀር ተስማምቶ እስከ ሞት ድረስ መኖር ተገቢ ነው፡፡ ነገር ግን በትዳር ሕይወት እጅግ የከበደና መፍትሔ የሌለው ችግር ሊመጣ ይችላል፡፡ በዚህ ጊዜ ለጉዳዩ መፍትሔ በሚያመጣ መልኩ መወያየት፣ ከንስሓ አባት ጋር መመካከር፣ በጾም በጸሎት መትጋትና እግዚአብሔርን መማጸን ይገባል፡፡

ኾኖም በመካከላቸው በሃይማኖት ወይም ሊፈታ በማይችል ልዩ ልዩ ምክንያት ለጉዳትና ለሞት የሚያደርስ ግጭት በተደጋጋሚ ከተከሠተ፤ አንዳቸው ወይም ሁለቱም ከትዳር ውጪ ከሔዱ (ዝሙት ከፈጸሙ) እነዚህን ችግርች በምክክር መፍታት፣ በንስሓም ማጽዳት ካልተቻለ መፋታት ይፈቀዳል፡፡ ከዂሉም በላይ ከሁለቱ አንዱ በሞት ከተለየና በሕይወት የቀረው አካል ጋብቻ መመሥረት ከፈለገ ሁለተኛ ማግባት ይቻላል፡፡ ያም ኾኖ ግን በሕገ ቤተ ክርስቲያን ከተጠቀሰው ምክንያት በቀር መፋታት አይገባም (ፍትሐ ነገ. አን. ፳፬፣ ቍ. ፲፩-፲፯)፡፡

የጋብቻ ሕይወት እና የሩካቤ ሥርዓት – ክፍል ፭

ምሥጢረ ተክሊል ለደናግል ማለትም ክብረ ንጽሕናቸውን ጠብቀው ለኖሩ ክርስቲያኖች ብቻ የሚፈጸም ሥርዓት ነው፡፡ ሥርዓቱ በዓላማ ጸንተው ክብራቸውን ጠብቀው ለቆዩ ዲያቆናትና ምእመናን ይፈጸማል፡፡ ከዚህ ላይ የዲያቆናት የጋብቻ ሥርዓት ከምእመናን የተለየ መኾኑን ለመጠቆም እንወዳለን፡፡ ምክንያቱም ወደ መዓርገ ቅስና የሚሸጋገሩበት አንዱ መሥፈርት ነውና፡፡ በሕግ የተወሰኑ ማለትም ትዳር የመሠረቱ ዲያቆናት (ቀሳውስት) በሞት ወይም በሌላ አስገዳጅ ምክንያት ከትዳር አጋራቸው ጋር ቢለያዩ ሁለተኛ ሚስት ማግባት አይፈቀድላቸውም፡፡ ካገቡም በመዓርገ ክህነት ማገልገል አይችሉም፡፡ ስለዚህም ዲያቆናት ሚስት በሚያጩበት ጊዜ ከምእመናን በተለየ መልኩ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡

በእርግጥ ምእመናን እንዲሁ ሳይጠናኑ ይጋቡ ለማለት ሳይኾን የክህነት ሕይወት ከምእመንነት ሕይወት ስለሚለይ ዲያቆናት አስተውለው ወደ ሕይወቱ እንዲገቡ ለማስታዎስ ነው፡፡ ምእመናን ከትዳር አጋራቸው ጋር በሞት ወይም በሌላ ምክንያት ቢለያዩ ሁለተኛ ማግባት ይፈቀድላቸዋል፤ ዲያቆናት (ቀሳውስት) ግን ከአንድ ጊዜ በላይ ሚስት ማግባት አይችሉም፡፡ በክህነታቸው ለመቀጠል የግድ መመንኰስ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ሕጉን ተላልፈው ወይም ፈቃደ ሥጋቸዉን ማሸነፍ አልችል ብለው ሁለተኛ ጋብቻ ከመሠረቱም ሥልጣነ ክህነታቸው ይያዛል (ይሰረዛል)፡፡ ከቀሳውስት (ዲያቆናት) በተለየ ሥርዓት ምእመናን ከትዳር አጋሮቻቸው ጋር ቢፋቱ የተለያዩበት ምክንያት ተጣርቶ ሁለተኛ ጋብቻ መመሥረት ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ሁለተኛ ጋብቻ በቍርባን እንጂ በተክሊል አይፈጸምም፡፡ ምክንያቱም ምሥጢረ ተክሊል ተጋቢዎቹ (ሁለቱም) ድንግልናቸውን አክብረው ከቆዩ ብቻ የሚፈጸምና የማይደገም ሥርዓት ነውና፡፡

የጋብቻ ሕይወት እና የሩካቤ ሥርዓት – ክፍል ፬

ጋብቻ ለመመሥረትና የትዳር አጋር ለመምረጥ የሚያስችል ዕድሜ ላይ የደረሱ ሰዎች ለጋብቻ ከተፈቃቀዱና ከተስማሙ በኋላ በቅድሚያ ለመምህረ ንስሓቸው ይነግራሉ፡፡ ከዚያም ለወላጆቻቸው (ለአሳዳጊዎቻቸው) ያሳውቃሉ፡፡ ጋብቻ የሚመሠረተው ከዚህ በኋላ ነው፡፡ እስከዚያው ድረስ ግን ግንኙታቸው ወደ ኀጢአት እንዳይወስዳቸውና ከመጋባታቸው በፊት በሩካቤ ሥጋ እንዳይወድቁ መጠንቀቅ ይገባቸዋል፡፡ ምክንያቱም እጮኛ መምረጥ ማለት መጋባት ማለት አይደለምና፡፡ የመተጫጨት ባህልና ሥርዓትን መጠበቅም ይገባል፡፡ ይህም ፈቃድና ስምምነትን፣ ዕድሜን፣ ዝምድናን፣ እንደዚሁም ሃይማኖትን ያገናዘበ መኾን ይኖርበታል፡፡

በመተጫጨት ጊዜ ሊታሰብበት የሚገባው ሌላኛው ጉዳይ የሚጋቡት ጥንዶች የዕድሜ ደረጃ ነው፡፡ የመተጫጫና የመጋቢያ ዕድሜም የወንዶች ከሃያ ወይም ከሃያ አምስት፤ የሴቶች ደግሞ ከዐሥራ አምስት ወይም ከዐሥራ ስምንት ዓመት በላይ ሊኾን እንደሚገባው በሕገ ቤተ ክርስቲያን ተደንግጓል (ፍት. ነገ. አን. ፳፬፣ ምዕ. ፫፣ ክፍ. ፪)፡፡ ተጋቢዎቹ በዕድሜ ብዙ የተራራቁ ከኾነ በጋብቻቸው ላይ ችግር ሊያስከትል ይችላል፡፡ በተጋቢዎች መካከል ምንም ዓይነት ዝምድና እንዳይኖርም መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ በቤተ ክርስቲያን ሥርዓት መሠረት ሥጋዊና መንፈሳዊ ዝምድናን ለማስጠበቅ ሲባል እስከ ሰባት ትውልድ ድረስ መጋባት አይፈቀድም፡፡

የጋብቻ ሕይወት እና የሩካቤ ሥርዓት – ክፍል ፫

በሰርግ ቤት ደስታ፣ ጨዋታ፣ መብልና መጠጥ፣ የሙሽራውና የሙሽሪት አንድነት ይከናወንበታል፤ የሙሽራውና የሙሽሪት ዘመዶች አንድ ይኾኑበታል፡፡ መብልና መጠጡ የትምህርተ ወንጌል (የሥጋ ወደሙ)፤ ደስታና ጨዋታው የተአምራት፤ የሙሽራውና የሙሽሪት ተዋሕዶ የትስብእትና የመለኮት አንድነት ምሳሌዎች ናቸው፡፡ በሰርግ የሙሽራውና የሙሽሪት ዘመዶች አንድ እንደሚኾኑባት ዂሉ፣ በድንግል ማርያምም ሰውና መላእክት፣ ሰውና እግዚአብሔር፣ ነፍስና ሥጋ፣ ሕዝብና አሕዛብ አንድ ኾነውባታል፡፡ ስለዚህም ቅዱስ ኤፍሬም እመቤታችንን ‹‹ሙሽራዋ ንጹሕ የሚኾን የሰርግ ቤት›› ይላታል (የረቡዕ ውዳሴ ማርያም፣ አንድምታ ትርጓሜ)፡፡

ቅዱስ ኤፍሬም ዳግመኛም “ከመ ከብካብ ዘአልቦ ጥልቀት መንፈስ ቅዱስ ኀደረ ላዕሌኪ፤ እንደ ሰርግ ቤት አደፍ፣ ጉድፍ የሌለብሽ ኾነሽ ቢያገኝሽ መንፈስ ቅዱስ አድሮብሻል” በማለት እመቤታችንን ጋብቻ በሚፈጸምበት ንጹሕ የሰርግ ቤት መስሎ አመስግኗታል፡፡ ይህም በተመሳሳይ መልኩ የጋብቻን ክቡርነት የሚያመለክት ነው (ውዳሴ ዘቀዳሚት)፡፡ ለዚህም ነው ቅዱስ ጳውሎስ “ይህ ምሥጢር ታላቅ ነው፤ እኔ ግን ይህን ስለ ክርስቶስና ስለ ቤተ ክርስቲያን እላለሁ” በማለት ጋብቻ የክርስቶስና የቤተ ክርስቲያን ተዋሕዶ ምሳሌ መኾኑን ያመሠጠረልን (ኤፌ. ፭፥፴፪)፡፡ በአጠቃላይ ጋብቻ፣ ይከብርበትና በጋራ ይኖርበት ዘንድ እንደዚሁም ራሱን ከኃጢአት ይጠብቅበት ዘንድ እግዚአብሔር አምላክ ለሰው ልጅ ያዘጋጀው መንፈሳዊ ሥርዓት ነው፡፡

የጋብቻ ሕይወት እና የሩካቤ ሥርዓት – ክፍል ፪

የጋብቻ ክቡርነትና ምሥጢር ይህ ኾኖ ሳለ አንዳንዶቻችን ለጋብቻ የምንሰጠው ትርጕም ግን ዝቅ ያለ ይመስላል፡፡ በስውር ከጋብቻ ውጪ ፈቃዳቸዉን የሚፈጽሙ ምእመናን መኖራቸውም ከዚህ አመለካከት የመነጨ ነው፡፡ ከዚህ የተሳሳተ ግንዛቤ በመውጣትና ንጽሕናን በመጠበቅ አንድም ጋብቻ መመሥረት፤ ካለዚያም ራስን ጠብቆ በድንግልና ጸንቶ መኖር ከክርስቲያኖች የሚጠበቅ ግዴታ ነው፡፡ ስለ ጋብቻ ሕይወት ሲነገር ከጋብቻ ዓላማዎች አንደኛው ከዝሙት ጠንቅ ለመሸሽ ነው፡፡ ይህም በሕጋዊ ሥርዓት ሩካቤ ሥጋን ለመፈጸም ያስችላል፡፡

ሩካቤ ሥጋ የተለየ ዓላማና ምሥጢር አለው፡፡ አፈጻጸሙም በሥርዓተ ተክሊል ወይም በሥርዓተ ቍርባን ይጸናል፡፡ በሕጋዊ ጋብቻ ተወስነን ካልኾነ በቀር ከጋብቻ በፊትም ኾነ በኋላ ካገኘነው ዂሉ ጋር ፆታዊ ግንኙነት መፈጸም ክቡራን ኾነን ተፈጥረን ሳለ በግብራችን ግን ከእንስሳት ጋር እንድንመሳሰል ያደርገናል፡፡ ቅዱስ ዳዊት “ሰብእሰ እንዘ ክቡር ውእቱ ኢያእመረ ወኮነ ከመ እንስሳ ዘአልቦ ልብ ወተመሰሎሙ፤ ሰውስ ክቡር ኾኖ ሳለ አላወቀም፤ ልብ እንደሌላቸው እንስሳትም መሰለ” በማለት እንደ ተናገረው (መዝ. ፵፰፥፲፪)፡፡

የጋብቻ ሕይወት እና የሩካቤ ሥርዓት – ክፍል ፩

ቅዱስ ጳውሎስ የጋብቻን ታላቅነትና ልዩ ምሥጢር ባስተማረበት መልእክቱ “ይህም ምሥጢር ታላቅ ነው፤ እኔም ይህንኑ ስለ ክርስቶስና ስለ ቤተ ክርስቲያኑ እናገረዋለሁ፤” በማለት የባልና የሚስት ጥምረት ወይም አንድነት የክርስቶስና የቤተ ክርስቲያን ምሳሌ መኾኑን ይናገራል (ኤፌ. ፭፥፴፪)፡፡ በተመሳሳይ መልኩ ጋብቻ የመለኮት እና የትስብእት (የሰውነት) ምሳሌ መኾኑን መምህራነ ቤተ ክርስቲያን ያስተምራሉ፡፡ በዓለ ኀምሳ፣ ቤተ ክርስቲያንን በደሙ የመሠረታት የመድኀኒታችን ክርስቶስ ትንሣኤ የሚታሰብበት፣ ምሥጢረ ሥጋዌና ምሥጢረ ትንሣኤ ሙታን በስፋት የሚሰበክበት ወቅት ከመኾኑ አኳያ በእርግጥም በዚህ የደስታ ሰሙን የተዋሕዶ ምሳሌ የኾነውን ጋብቻን በቤተ ክርስቲያን መፈጸም ለምሥጢር የተመቸ መልእክት አለው፡፡

የዛሬዉን ትምህርታዊ ጽሑፍ በጋብቻ ዙርያ ያደረግነው ወቅቱን ለመዋጀት በማሰብ ነው፡፡ በእርግጥ ስለ ጋብቻ በልዩ ልዩ መንገድ ብዙ ጊዜ ተምረናል፡፡ ኾኖም ጉዳዩ የሕይወት ጉዳይ ነውና ደጋግመን መማማሩ ይጠቅመናል፡፡ አንዳዶቹ በማወቅም፣ ባለማወቅም ከሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ውጪ ጋብቻቸውን ሲፈጽሙ ይስተዋላል፡፡ ስለ ጋብቻ በተደጋጋሚ መማማራችንም በማወቅ ወይም በግድየለሽነት ከሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ውጪ ትዳር የሚመሠርቱ ምእመናንን ለመመለስና ሌሎችም እንዳይስቱ ለመጠቆም ይረዳናል፡፡ ስለዚህም በዚህ ዝግጅት ስለ ጋብቻ አመሠራረት፣ ክቡርነት፣ ምሥጢር እና ዓላማ የሚያትት ተከታታይ ትምህርት ይዘን ቀርበናል፡፡ ትምህርቱን ትከታተሉ ዘንድ መንፈሳዊ ግብዣችንን እናስቀድማለን፡፡

አቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ

በረከት ለመቀበል ወደ ገዳሙ ለመሔድ ከወልድያ እስከ ዳውንት በመኪና የስምንት ሰዓታት መንገድ ይወስዳል፡፡ ከዳውንት ከተማ ወደ ገዳሙ አቅራቢያ የሚያደርሱ አነስተኛ ተሸከርካሪዎችም ይገኛሉ፡፡ ወደ ገዳሙ ለመግባት ለጠነከሩ የአንድ ሰዓት ያህል የእግር ጕዞ ይኖረዋል፡፡ የጻድቁ በዓለ ዕረፍት በሚከበርበት ዕለት (ሚያዝያ ዘጠኝ ቀን) ከወልድያ እስከ ገዳሙ የሚያደርሱ መጓጓዣዎች ስለሚገኙ ሕዝበ ክርስቲያኑ ወደ ገዳሙ በመሔድ ከበረከቱ ተሳታፊ እንዲኾኑ ገዳሙ ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡