የመፃጉዕ ወንጌል(ዮሐ. 5÷1-24)

ከዚህም በኋላ በአይሁድ በዓል እንዲህ ሆነ፤ ጌታችን ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ፡፡ በኢየሩሳሌምም በበጎች በር አጠገብ መጠመቂያ ነበረች፤ ስምዋንም በዕብራይስጥ ቤተ ሳይዳ ይሉአታል፤ አምስት እርከኖችም ነበሩአት፡፡ በዚያም ዕውሮችና አንካሶች÷ ሰውነታቸውም የሰለለ ብዙ ድውያን ተኝተው የውኃውን መናወጥ ይጠባበቁ ነበር፡፡ የእግዚአብሔር መልአክ ወደ መጠመቂያው ወርዶ ውኃዉን በሚያናውጠው ጊዜ ከውኃው መናወጥ በኋላ በመጀሪያ ወርዶ የሚጠመቅ ካለበት ደዌ ሁሉ ይፈወስ ነበርና፡፡ በዚያም ከታመመ ሠላሳ ስምንት ዓመት የሆነው አንድ ሰው ነበር፡፡ ጌታችን ኢየሱስም ይህን ሰው በአልጋዉ ተኝቶ ባየ ጊዜ በደዌ ብዙ ዘመን እንደ ቆየ ዐውቆ÷ “ልትድን ትወዳለህን?” አለው፡፡ ድውዩም መልሶ÷ “አዎን ጌታዬ ሆይ÷ ነገር ግን ውኃው በተናወጠ ጊዜ ወደ መጠመቂያዉ የሚያወርደኝ ሰው የለኝም፤ እኔ በምመጣበት ጊዜ ሌላው ቀድሞኝ ይወርዳል” አለው፡፡ ጌታችን ኢየስስም÷ “ተነሥና አልጋህን ተሸክመህ ሂድ” አለው፡፡ ወዲያውኑም ያ ሰው ድኖ አልጋውን ተሸክሞ ሄደ፤ ያች ቀንም ሰንበት ነበረች፡፡

አይሁድም የዳነውን ሰው÷ “ዛሬ ሰንበት ነው፤ አልጋህን ልትሸከም አይገባህም” አሉት፡፡ እርሱም መልሶ÷ “ያዳነኝ እርሱ፡- አልጋህን ተሸክመህ ሂድ አለኝ” አላቸው፡፡

አይሁድም÷ “አልጋህን ተሸክመህ ሂድ ያለህ ሰውዬው ማነው?” ብለው ጠየቁት፡፡ ያ የተፈወሰው ግን ያዳነው ማን እንደ ሆነ አላወቀም፤ ጌታችን ኢየሱስ በዚያ ቦታ በነበሩት ብዙ ሰዎች መካከል ተሰውሮ ነበርና፡፡ ከዚህም በኋላ ጌታችን ኢየሱስ ያን የዳነውን ሰው በቤተ መቅደስ አገኘውና÷ “እነሆ÷ ድነሃል፤ ግን ከዚህ የባሰ እንዳያገኝህ ዳግመኛ እንዳትበድል ተጠንቀቅ” አለው፡፡ ያም ሰው ሄዶ ያዳነው ጌታችን ኢየሱስ እንደ ሆነ ለአይሁድ ነገራቸው፡፡ ስለዚህም አይሁድ ጌታችን ኢየሱስን ያሳድዱትና ሊገድሉትም ይሹ ነበር፤ በሰንበት እንዲህ ያደርግ ነበርና፡፡ ጌታችን ኢየሱስም መልሶ÷ “አባቴ እስከ ዛሬ ይሠራል፤ እኔም እሠራለሁ” አላቸው፡፡ ስለዚህም አይሁድ ሊገድሉት በጣም ይፈልጉ ነበር፤ “ሰንበትን የሚሽር ነው” በማለት ብቻ አይደለም፤ ደግሞም እግዚአብሔርን “አባቴ ነው ይላል፤ ራሱንም ከእግዚአብሔር ጋር ያስተካክላል” በማለት ነው እንጂ፡፡

ከዚህም በኋላ ጌታችን ኢየሱስ መልሶ እንዲህ አላቸው÷ “እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ ወልድ ከራሱ ብቻ ምንም ሊያደርግ አይችልም፤ አብ ሲያደርግ ያየውን ነው እንጂ፤ ወልድም አብ የሚሠራውን ያንኑ እንዲሁ ይሠራል፡፡ አብ ልጁን ይወዳልና የሚሠራውንም ሥራ ሁሉ ያሳየዋል፤ እናንተም ታደንቁ ዘንድ ከዚህ የሚበልጥ ሥራን ያሳየዋል፡፡ አብ ሙታንን እንደሚያስነሳቸው÷ ሕይወትንም እንደሚሰጣቸው እንዲሁ ወልድም ለሚወድዳቸው ሕይወትን ይሰጣል፡፡ አብ ከቶ በማንም አይፈርድም፤ ፍርዱን ሁሉ ለወልድ ሰጠው እንጂ፡፡ ሰዎች ሁሉ አብን እንደሚያከብሩ ወልድን ያከብሩ ዘንድ፤ ወልድን የማያከብር ግን የላከውን አብን አያከብርም፡፡