አስቀድመህ ከወንድምህ ጋር ታረቅ /ማቴ. 5፥24/

ታኅሣሥ 10 ቀን 2005 ዓ.ም.

  • ለቤተ ክርስቲያናችን አገልግሎት ስኬት የአባቶቻችን ስምምነት ወሳኝ ነው

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ በሥጋ ሕይወት በነበሩበት ባለፉት ዓመታት “ስደተኛ ሲኖዶስ” ተብሎ ከተጠራው በሰሜን አሜሪካ ከሚገኙ አባቶች ጋር ዕርቅ ለመፈጸም ጥረት ይደረግ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ ተጨባጭ ለውጥ መመዝገብ ሳይችል በእንጥልጥል እንዳለ ቅዱስነታቸው ዐረፉ፡፡

 

የእርሳቸው ዕረፍት ቀጣዩ የቤተ ክርስቲያኒቱ ፓትርያርክ ከመመረጣቸው በፊት በሰሜን አሜሪካ ከሚገኙ ተለይተው ከሚኖሩ አባቶች ጋር ውይይት ለመጀመር አስገዳጅ ሁኔታ አምጥቷል፡፡ ይህ እንዲታሰብ ግድ የሚያደርገውም ቀጣዩ ፓትርያርክ የሚሰየሙበት መንገድ ሁሉን የማያስማማ ከሆነ የነበረውን ልዩነት የሚያሰፋ ውዝግብ በዚህች ታሪካዊ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሊያስከትል እንደሚችል ከወዲሁ መገመት ስለሚቻል ነው፡፡ ይህንን ከግምት አስገብቶ የወቅቱን አንገብጋቢነት ተረድቶ ወደ ዕርቅ የሚያደርስ ውይይት ማድረግ ደግሞ የቤተ ክርስቲያኒቱን ወሳኝ አገልግሎቶች በብቃትና በስፋት ለመስጠት፣ ጠንካራ መሠረትም ለመገንባት ስለሚያስችል ነው፡፡

 

በመሠረቱ ሲኖዶስ ከሐዋርያት ዘመን ጀምሮ በጉልህ የተገለጠ ተግባሩ መለያየቶችን መፍታት ዘመኑን የዋጀ የአገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓት መትከል ነው፡፡ ስለዚህ ሲኖዶስ ሲታሰብ ሰላምና አንድነት ይታሰባሉ፡፡ ትሕትናና ፍቅር ይነግሣሉ፡፡ ይህ የሚሆንበት ዋናው ምክንያት ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰጠውን የሐዋርያዊ አገልግሎት አደራ መንጋውን የመጠበቅ ሓላፊነት ከመወጣት ሌላ ለሚሰበሰበው መንጋ አርአያነት ያለው ሕይወት አባቶቻችን እንዲኖራቸው፣ ብርሃናቸውም በዓለም እንዲያበራ ስለታዘዙም ነው፡፡

 

እነዚህ የክርስትና ዐበይት ተግባራት በአባቶቻችን ደግሞ ጎልተው እንዲገለጹ ይፈለጋል፡፡ አባቶች የክርስቶስን መልክ /እርሱን መምሰልን/ እንደያዙ በሚያስበው የእግዚአብሔር መንጋ፣ እንዲሁም የምድር ጨው ሆነን ሕይወታቸውን ለማጣፈጥ እንድንበቃ አደራ በተሰጡን የምድር አሕዛብ ሁሉ ላይ በጎ ተፅዕኖ ለማሳረፍ ብፁዓን አባቶች መልካሙን ጎዳና ሁሉ ሲከተሉ መገኘታቸው ታላቅ ሚና አለው፡፡

 

ከዚህ ጎዳና ወጥተን ፍቅርን በማጣት፣ በጠብ በክርክር ጸንተን ብንገኝ ፍቅር ከሆነ እግዚአብሔር ጋር ለመኖር ባለመፍቀዳችን ብቻ ሳይሆን ሌሎች ከእርሱ ጋር እንዳይኖሩ ማሰናከያ በመሆናችንም ጭምር ያዝናል፤ ይፈርዳል፡፡ ስለዚህ ለብፁዐን አባቶች ብቻ ሳይሆን በክርስቲያኖች ሕይወትም በፍቅር ጸንቶ መኖር፣ ከበደልንም በይቅርታና በዕርቅ ሕይወት ውስጥ ማለፍ ሃይማኖታዊ ግዴታ ነው፡፡ የዚህ ሕይወት መሠረቱ ከሞት ወደ ሕይወት የተሸጋገርንበት እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ያደረገው ዕርቅ ነው፡፡ ጠላቶቹ ከሆነው ከእኛ ጋር እግዚአብሔር ታረቀ መባሉ የሕይወታችን መሠረት ፍቅር መሆኑን የሚያመለክት ነው፡፡ ስለ ዕርቅ ሕይወት በብዙ ምሳሌና በብዙ ኃይለ ቃል ራሱ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያስተማረንም በመሆኑ በጉልሕ በሕይወታችን መንጸባረቅ የሚገባው የጽድቅ ሥራ ነው፡፡

 

ለእግዚአብሔር ከምናቀርበው ከየትኛውም ዓይነት መባዕ አገልግሎታችን በፊት ከወንድሞቻችን መታረቅ እንደሚገባ ጌታችን አበክሮ ያስተማረው የሕይወት ቃል ነው፡፡ “አስቀድመህም ከወንድምህ ጋር ታረቅ” ያለው የጌታ ቃል ይልቁንም በቤተ መቅደሱ ዕለት ዕለት መሥዋዕት ለሚያቀርቡ፣ ብዙዎችን በጸጋ እግዚአብሔር ባዕለ ጸጋ ለሚያደርጉ፣ ምስጢራትንም ሁሉ ለሚፈጽሙ፣ የሃይማኖትና የሥነ ምግባር ምልክት ለሆኑ ከሁለቱም ወገን ላሉ ብፁዐን አባቶች የሚያስተምሩት ብቻ ሳይሆን ዘወትር እንዲኖሩት የሚጠበቅ ክርስቲያናዊ ሕይወት ነው፡፡

 

ይህ በመሆኑም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አባቶች መካከል “ክርክርና መለያየት አለ” መባሉ ሳይሆን ክርክሩን መፍታት፣ ልዩነትን ወደ አንድነት ስምምነት ማምጣት አለመቻል ከላይ የጠቀስነውን ወሳኝ የሕይወት ቃል የሚፈታተን ይሆናል ማለት ነው፡፡ ከዚያም አልፎ ቤተ ክርስቲያኒቱን ለመምራት ባለን አቅምና በጎ ፈቃድ ላይ ጥያቄ የሚያሥነሣ ይሆናል፡፡ በዚህ የማይደሰተው እግዚአብሔርም ብቻ አይደለም፡፡ ከሕፃን እስከ አዋቂ ያሉ የክርስቶስ ቤተሰቦችም ናቸው፡፡

 

ስለዚህ ቤተ ክርስቲያናችንን ወደ አንድነት የሚያመጣ ዕርቀ ሰላም መፈጸም ከሃይማኖታዊ ሥነ ምግባር አንጻር፣ ለቤተ ክርስቲያን ደኅንነት ከማሰብ አንጻር፣ መንጋውን ከማነጽና ሐዋርያዊ አገልግሎትን ከማቅናት አንጻር ለአባቶቻችን ግዴታ ይሆንባቸዋል፡፡ የሚፈለገው ዕርቀ ሰላም እውን እንዲሆንም ለእግዚአብሔር ፈቃድ፣ ለእውነት፣ ለኅሊና ምስክርነት መገዛት አግባብ ይሆናል፡፡

 

ከዚህ በፊትም ማኅበረ ቅዱሳን እንዳስገነዘበው አባቶች ሰላሙን ለማምጣት የሚያስችሉ ቀኖናዊ ጉዳዮችም ላይ ለመወሰን ለማጽናትም መንፈሳዊ ሥልጣንን የተጎናጸፉ በመሆናቸው ዕንቅፋትን ማራቅ ይችላሉ፡፡ የዕርቅ ሒደቱ ሲፈጸምም ሃይማኖታዊ መልክ ያጡ እና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንትና ምእመናንን የማያሳምኑ ቅድመ ሁኔታዎችን ከመደርደር መታቀበ ከተቻለ በተስፋ የተሞላ ሒደት እንደሚሆን ይታመናል፡፡

 

ከማንምና ከምንም በላይ የቤተ ክርስቲያናችንን ቤተሰብ ማሳመን የማያስችሉ እርምጃዎች ውስጥ መግባት ተአማኒነትን ሊያሳጡ ይችላሉ፡፡ ለዓመታት የዘለቀውን መለያየት /ውዝግብ/ ለመፍታት በሚደረገው ጥረት ውስጥም የካህናቱ የሰንበት ትምህርት ቤቶች የአገልግሎት ማኅበራትና በአጠቃላይ የሕዝበ ክርስቲያኑ ሐሳብና አስተያየቶች ከግምት የሚገቡበት አካሔድ ሊኖር ይገባል፡፡ ሕዝበ ክርስቲያኑ ካልተሰማ በቀጣዩ ጊዜ በቤተ ክርስቲያናችን አስተዳደር አካላት ላይ የሚኖረው አመኔታ ይላላል፡፡ በመሆኑም በዚህ በዕርቁ ሒደት ክርስቲያኖች ያላቸው ሐሳብ ሊመረመር ይገባል፡፡ ስለዚህ ሁሉም የሃይማኖት ቤተሰብ ደስ የሚሰኝበት ምዕራፍ ላይ ለመድረስ መትጋት ከአባቶቻችን ይጠበቃል፡፡

 

ስለዚህም ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ለሰላሙ መስፈን አስፈላጊ የሆነ ዋጋ እንዲከፈል ግፊት በማድረግ ሊረባረቡ ይገባል፡፡ ምእመናንም ከካህናት አባቶች ጋር በጸሎት በመትጋት ለዚህ ችግር ዘላቂ መፍትሔ እግዚአብሔር እንዲሰጠን መማጸን ይገባናል፡፡ የተጀመሩትን ሒደቶች ሁሉ በእውነተኛነት በሚዛናዊነት እየተከታተሉ በጎ ተጽዕኖ ማሳደር ይገባናል፡፡ ቤተ ክርስቲያን ያሳለፈችው ያለፉት ዓመታት ኣሳዘኝ ሁኔታዎች እንዳይቀጥሉ ዛሬ ላይ ማድረግ የሚገባንን ሁሉ ማድረግ እንደሚገባን ማኅበረ ቅዱሳን ያምናል፡፡ ለዚህም ይሠራል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

 

  • ምንጭ፡- ሐመር መጽሔት 20ኛ ዓመት ቁጥር 8 ታኅሣሥ 2005 ዓ.ም.