‹ትውልድ ሁሉ የእግዚአብሔርን ቃል ተመልከቱ› /ኤር 2፥31/

ዲ/ን ብርሃኑ አድማ
‹አንድ ምድራዊ ንጉሥ ወይም ጠቅላይ ሚኒስቴር ወይም ሌላ ታላቅ ባለሥልጣን ደብዳቤ ቢጽፍልን በደስታ አናነበውምን? በእርግጠኝነት በታላቅ ደስታ የማያነበውና በልዩ ትኩረት የማይመለከተው አይኖርም፡፡ ይሁን እንጂ ከምድራዊ ባለሥልጣን እንዲህ ያለ ደብዳቤ የተጻፈለት ሰው የለም፤/ለሥራ፣ ለሹመት፣…ካልሆነ በቀር/ ከሰማያዊው ንጉሥ ግን ያልተጻፈለት የለም፣ በምድራዊ ዋጋ የማይታመን ለሕይወት መድኃኒት የሆነ ደብዳቤ ተጽፎልን ነበር። ይሁን እንጂ ለአንድ ምድራዊ ንጉሥ ደብዳቤ የምንሰጠውን ያህል ክብርና ትኩረት እንኳን አልሰጠነውም፡፡
 
መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ምን ማለት እንደሆነ አልገባንምና፡፡ ወንጌልን ስናነብ እኮ ክርስቶስ ራሱ እያነጋገረን እኛም ከእርሱ ጋር እየተነጋገርንና ወደ እርሱ እየጸለይን ነበር፡፡ አንድ አባት መጽሐፍ ቅዱስን አስመልክተው የተናገሩት ነበር፡፡ በርግጥም መጽሐፍ ቅዱስ ለእያንዳንዳችን የተጻፈና የተነገረ የእግዚአብሔር ቃል ነበር፡፡ ነገር ግን እንደ ሳሙኤል ‹ባሪያህ ይሰማልና ተናገር›እንደ ኢሳይያስም ‹እኔ አለሁ› የሚል እግዚአብሔርን ሰምቶ ለመታዘዝ የተዘጋጀ ብዙም ያለ አይመስለኝም፡፡ /1ኛ ሳሙ 3፥10፣ ኢሳ 6፥8/

የእግዚአብሔር ቃል /መጽሐፍ ቅዱስ/
በመጽሐፍ ቅዱስ የተመዘገበው የእግዚአብሔር ቃል ፍጹም እውነትና ከእርሱ የተገኘ ቃል ነው፡፡ ይህም ማለት በጸሐፊዎቹ ሥጋዊ ዕውቀት ወይም አመለካከት ተጽእኖ ሥር የወደቀ አይደለም፡፡ የተጻፈው በመንፈስ     ቅዱስ መሪነት ወይም መንፈስ ቅዱስ በአደረባቸው አበው ብቻ ነውና ፡፡ «ትንቢት ከቶ በሰው ፈቃድ አልመጣምና..ዳሩ ግን በእግዚአብሔር ተልከው ቅዱሳን ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው ተናገሩ» ተብሎ እንደጻፈ። ጸሐፊዎቹ በመንፈስ ቅዱስ የተመረጡ  /መንፈስ ቅዱስ ያደረባቸው/ ሰዎች ብቻ ናቸው፡፡ /2ኛ ጴጥ 1፥21/ ቅዱስ ጳውሎስም ‹የእግዚአብሔር መንፈስ ያለባቸው መጻሕፍት› በማለት ይጠራቸዋል፡፡ /2ኛ ጢሞ 3፥16/ ስለዚህ መቼም ቢሆን ትክክል ናቸው፡፡

 
ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት ‹በምድር ላይ እንደተፈተነ ሰባት ጊዜ እንደተጣራ ብር የእግዚአብሔር ቃላት የነጹ ቃላት ናቸው› /መዝ1፥16/ ሲል እንደተናገረው ልንጠራጠረው ወይም ስህተት ሊኖርበት ይችላል ተብሎ የሚገመት ቃል የለም፡፡ የእግዚአብሔር ቃል ፍጹም፣ ጽሩይ ፣ንጹሕ ፣እውነተኛ ቃል ነውና፡፡ እግዚአብሔር ለሙሴ ‹ከወንድሞቻቸው መካከል እንደ አንተ ያለ ነቢይ አስነሣላቸዋለሁ፤ ቃሌንም በአፉ አደርጋለሁ፤ ያዘዝሁትንም ቃል ሁሉ ይነግራቸዋል፤ በስሜም  የሚናገረውን ቃሌን የማይሰማውን ሰው እኔ እበቀልለታለሁ› ሲል የተናገረው ቃል የነቢያቱ ወይም የሐዋርያቱ ሳይሆን የእግዚአብሔር ቃል ብቻ ስለሆነ ነው፡፡ /ዘዳ18፥18-19/ ስለዚህም በመጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈው ሁሉ የእግዚአብሔር ቃል ብቻ ነው፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ‹ቃሌን ሰምቶ የማይጠብቀው ቢኖር የምፈርድበት እኔ አይደለሁም!…እኔ ተናገርሁት ቃል እርሱ በመጨረሻው ቀን ይፈርድበታል፡፡› ያለን ቃሉ ንጹሕ የራሱ ብቻ ስለሆነ ነው፡፡ /ዮሐ 12፥47-48/ የሰው ቃል ቢሆን ሊፈርድብን አይችልምና፡፡
ቃለ እግዚአብሔር ለሕይወታችን
ያለምንም ቅድመ ሁኔታና ያለ ተጨማሪ ዓላማ የእግዚአብሔርን ቃል የምንሰማው ለነፍሳችን ድኅነት ነው፡፡ ይህም ማለት ሰማዕያኑ /ሰሚዎቹ ወይም አንባቢዎች/ የእግዚአብሔርን ቃል የምናነብበት፣ የምንሰማበት ተቀዳሚ ዓላማ ድኅነት ብቻ መሆን አለበት ለማለት ነው፡፡ ‹አስቀድማችሁ ጽድቁንና መንግሥቱን ፈልጉ፤ ሌላው ሁሉ ይጨመርላችኋል› /ማቴ 6፥33/ መባላችንን መዘንጋት የለብንም፡፡ እኛ ለነፍሳችን ድኅነት ስንሰማው ከእግዚአብሔር የምንቀበለው እጅግ ይበዛል፡፡ ‹ይጨመርለችኋል› ያለን አምላካችን ይጨምርልን ዘንድ የታመነ ነው፡፡ በዚህም መሠረት ጥቂቶቹን ጥቅሞች እንመልከትና እንዴት ማንበብና መማር እንዳለብን እንመልከት፡፡
ሀ/ ለሕይወተ ነፍስ፡- ‹ሲሳያ ለነፍስ ቃለ እግዚአብሔር ውእቱ፤ የነፍስ ምግቧ የእግዚአብሔር ቃል ነው› እንደተባለ ያለ እግዚአብሔር ቃል ለድኅነት የምትበቃ ነፍስ የለችም፡፡ ጌታ በወንጌል ‹እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ ቃሌን የሚጠብቅ ቢኖር ለዘለዓለም ሞትን  አያይም/ ዮሐ8፥51/ ያለው ድኅነት ነፍስን የሚያስገኝ ስለሆነ ነው፡፡ በዚሁ ምዕራፍ ላይ ‹ከእግዚአብሔር የሆነ የእግዚአብሔርን ቃል ይሰማል› ያለውም ያለ ቃለ እግዚአብሔር የእግዚአብሔር መሆን ስለማይቻል ነው፡፡ / ዮሐ 8፥47/ ቃሉን የሚሰሙ፤ እንደሰሙም የሚኖሩት ግን በሰላምና በሕይወት ይኖራሉ፡፡ ራሱ ጌታም ‹እኔ የነገርኋችሁ ቃል መንፈስ ነው፤ ሕይወትም ነው፡፡› ብሏልና፡፡ /ዮሐ 6፥63/ ቅዱስ ጳውሎስም ቅዱሳት መጻሕፍት ሰውን ለፍፁምነት የሚያበቁ፣ በጎ የሚያደርጉ፣ በተግሣጽ ልብን የሚያጸኑና በትምህርት እያነጹ በጽድቅ ላለው ምክር እንደሚጠቅሙ አስረግጦ ያስተምራል፡፡ /2ኛ ጢሞ 3፥16-17 ፣ ሮሜ 15፥3-4/ ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊትም ሕጉን /መጻሕፍትን/ በቀንም በሌሊትም የሚያነብ ሰው ቢኖር ቅጠሎቿ እንደማይረግፉና ፍሬዋን በየጊዜው እንደምትሰጥ በወንዝ ዳር እንደተተከለች ዛፍ ይሆናል፤ ይላል፡፡ /መዝ 1፥2-3/
ለ/ ለሕይወተ ሥጋ፡- ጌታችን በወንጌል ‹ሰው በእንጀራ ብቻ አይኖርም፤ በእግዚአብሔር ቃልም ጭምር ነው እንጂ› እንዳለ ቃለ እግዚአብሔር ለሥጋዊ ሕይወታችንም ይጠቅመናል፤ /ማቴ 4፥4/፡፡ ነቢየ እገዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት ‹ቃልህ (ሕግህ) ለእግሬ መብራት ለመንገዴም ብርሃን ነው› እንዳለ ቅዱሳት መጻሕፍትን የሚያነቡ ሰዎች መንገዳቸው ሁሉ የተቃና ይሆንላቸዋል፡፡ /መዝ118፥105/ ሳምራዊቷ በእርሷ ተሰውሮ አምስት ባሎቿን ከገደለባት መንፈስ ርኩስ ነጻ የወጣችው የእግዚአብሔርን ቃል በመስማት ነው፡፡ /ዮሐ4፥7-40/  መቶ አለቃው ‹ቃል ብቻ ተናገር ብላቴናዬም ይፈወሳል› በማለቱ እንደ እምነቱ ተደርጎለታል፡፡ ይህም ብቻ አይደለም ዓለሙ ሁሉ የተፈጠረው በእግዚአብሔር ቃል ነውና የእግዚአብሔር ቃል የጎደለብንን ሁሉ ይሞላል፡፡ ቅዱስ ዳዊት «የቃልህ ፍቺ ያበራል ፤ሕጻናትንም ጠቢባን /አስተዋዮች/ ያደርጋል፤ አፌን ከፈትሁ አለከለክሁም፤ ወደ ትእዛዝህ ናፍቄአለሁና» እያለ ናፍቆቱን የሚናገረው ከቃለ እግዚአብሔር የማይገኝ ዕውቀትና ጥበብ ስለሌለ ነው፡፡ /መዝ 118፥129-131/

እግዚአብሔር ይነግሮሙ ለሕዝቡ በመጽሐፍ /መዝ 86፥6/

ቅዱስ ዳዊት ‹እግዚአብሔር ለሕዝቡ በመጽሐፍ ይነግራቸዋል› ይላል፡፡ ስለዚህም እግዚአብሔር እንዲነግረው የፈለገ ሁሉ ቅዱሳት መጻሕፍትን ማንበብ ይጠበቅበታል፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ኤርምያስም ‹ትውልድ ሁሉ የእግዚአብሔርን ቃል ተመልከቱ› የሚለን ቅዱሳት መጻሕፍትን በማንበብና በማድመጥ እንድንጠቀም ነው፡፡ ለመሆኑ አንድ ሰው መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብ አስቀድሞ መገንዘብ ያለበት ጉዳይ ምንድ ነው?  የሚለውን መረዳት ያፈልጋል፡፡

ሀ/ መጽሐፍ ቅዱስን በቤተ ክርስቲያን መንፈስ መረዳት

በመጀመሪያ ደረጃ መጽሐፍ ቅዱስን ከቤተ ክርስቲያን እንደተቀበልነው ወይም እነዳገኘነው መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ቤተክርስቲያን ስንልም ክርስቶስ መሠረቷ ጉልላቷ የሆነላት /1ኛ ቆሮ 3፥6፣ ዕብ 6፥1፣ ኤፌ 5፥22/ በምድርም፣ በገነትም፣ በብሔረ ብፁአንና በብሔረ ሕያዋን ያሉት የቅዱሳን ሰዎችና የማኅበረ መላእክት አንድነት ማለታችን ነው፡፡ ቅዱስ የሆነው ትውፊት ወይም ቅብብል እስከ ዘመነ ሊቃውን ካደረሳቸው በኋላ በቤተ ክርስቲያን ቀኖና ተወስነዋል፡፡ ስለዚህ አንድ አማኝ መጽሐፍ ቅዱስን እንደሌላ የፍልስፍና መጽሐፍ በፈለገው መንገድ ሊተነትነው አይችልምም፣ አይገባምም፡፡ ከቤተ ክርስቲን የተቀበለው ከሆነ በቤተ ክርስቲያን /በኅብረቱ በአንደነቱ መንፈስ/ ሆኖ መረዳት ይገባዋል፡፡ ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ «የሚተረጉምልኝ ሳይኖር ይህ እንዴት ይቻለኛል?» /ሐዋ 8፥31/ ያለው ራሱን በኅብረቱ ውስጥ አድርጎ ስለሚያኖርና የእነርሱንም ርዳታ ስለሚሻ ነበር፤ አገኘም፡፡ ሉቃስና ቀልዮጳ ‹በመንገድ ሲናገረን መጻሕፍትንም ሲከፍትልን /ሲተረጉምልን/ ልባችን ይቃጠል አልነበረምን?› የተባባሉት መጻሕፍትን መረዳት የሚቻለው በቤተ ክርስቲያን መንፈስ /ትምህርት፣ ትርጓሜና ሥርዓት መሠረት /ማንበብና ማጥናት ስንችል ብቻ ስለሆነ ነው፡፡ /ሉቃ 24፥32/ ቅዱስ ጴጥሮስም «በመጽሐፍ ያለውን ትንቢት ሁሉ ማንም ለገዛ ራሱ ሊተረጉም አልተፈቀደው….» የሚለው ለዚህ ነው፡፡ /2ኛ ጴጥ 1፥20/ ያለ ትርጓሜ መንፈስ የምናነብ ከሆነ ከቤተ ክርስቲያን የመውጣት ዕድላችን ሰፊ ነውና እንጠበቅ፡፡

ለ/ በመታዘዝ ማንበብ፡-

መጻሕፍቱ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ተጽፈዋል ብሎ የሚያምን ሰው ሲማር የሚሰማው፤ ሲያነብም የሚያዳምጠው በመታዘዝ መንፈስ ነው፤ ቃሉ በሰው ቋንቋ  የተጻፈ የእግዚአብሔር ድምጽ ነውና፡፡ ስለዚህ አንድ አማኝ በሚያነብበት ጊዜ ራሱን አስገብቶ ከመጻሕፍቱ ባለቤት ከእግዚአብሔር በትሕትና መንፈስ በማድመጥ ያነብባል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ‹ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዓይነትና ጎዳና ለአባቶቻችን በነቢያት ተናግሮ….›› ስለሚል መንገዱ ቢለያይም ነገሩ ሁልጊዜም ለእኛ ሁሉ ነው፡፡ /ዕብ1፥1/ ስለዚህ በመታዘዝ ማንበብ ማለት አንደኛ በማድነቅ/በተመስጦ/ ሁለተኘ ለራስ በማድመጥ ማንበብ ነው፡፡ ይህም ቅድስት ድንግል ማርያም ‹‹ይኩነኒ በከመ ትሌበኒ፣ እነደ ቃልህ ይሁንልኝ ›› እንዳለችው ቃሉን በእምነት በመቀበልና በመታዘዝ ማንበብ ነው፡፡

ሐ/ ለእኔ ብሎ ማንበብ፦

እውነት የመጽሐፍ ቅዱስ አንባቢ ለራሱ ብሎ ያነባል፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰው በዝሙት የተከሰሰችውን ሴት ታሪክ ቢያነብ ያን ጊዜ እርሷን ወክሎ መናዘዝ፣ራሱን መክሰስ ይገባዋል፡፡ ‹‹በሰላም ሒጂ›› የሚለው ቃል ላይ ሲደርስም ክርስቶስ ለራሱ እንደተናገረው እየሰማ ሥርየተ ኃጢአት ማግኘትን እየተቀበለ ያነባል፡፡ /ንስሐ አያስፈልግም ማለት አይደለም/፡፡ ይህንኑ አለፍ ብሎም ‹‹ዳግመኛም ኃጢአት አትሥሪ›› የሚለውን አድምጦ ዳግም ኃጢአት ላለመሥራት እየታዘዘ ማንበብ አለበት፡፡ በዚህ መንገድ ካልሆነ የሌሎች ሰዎች ታሪክን የሚያነብ ይመስለውና ሳይጠቀም ይቀራል፡፡ ስለዚህ የአዳምን ታሪክ ሲያነብ የወደቀው፤ የእግዚአብሔርንም ድምጽ ለራሱ አድርጎ ይሰማል፡፡ ‹‹አዳም አዳም ወዴት ነህ›› የሚለውን ‹‹ እኔ ወዴት ነኝ›› እያለ ያነበዋል፡፡ እግዚአብሔር ለቃየል ‹‹ወንድምህ አቤል ወዴት ነው?›› ሲል የጠየቀው የእኔ ወንድሞች /ክርስቲያኖች፣ ደቂቀ አዳም…/ ወዴት ናቸው? እያለ ያነባል እንጂ አርቆ አያነብም፡፡ በዚህም የእግዚአብሔርን የምሕረት ድምጽ ይሰማል፡፡ ስለጠፋው በግ፣ ስለጠፋው ልጅ፣ ስለፈሪሳውያን ፣….. ስለሌሎችም ሲያነብ የሚያስበው ራሱን ነው፣ወይም እራሱን ከእነዚያ እንደ አንዱ በመቁጠር ያነባል፤ ያን ጊዜ በትክክል እግዚአብሔር ለእርሱ የሚለውን ይሰማል፡፡

ማጠቃለያ

በሊቃውንት ዘንድ ቅዱሳት መጻሕፍት ለማንበብ ከዚህ በላይ ግንዛቤና ዝግጅት የሚያስፈልገው ቢሆንም እኛ ለመጀመር ያህል እንኳን መጽሐፍ ቅዱሳችንን በዚህ መንገድ እንቅረበው፡፡ በዚያን ጊዜ ‹‹እኔ ስጸልይ ለእግዚአብሔር እየተናገርኩ ነው፡፡ መጻሕፍትን ሳነብ ደግሞ እግዚአብሔር ለእኔ የሚናገረውን እሰማለሁ›› ያሉት ሊቅ ሕይወትን ገንዘብ ማድረግ እንችላለን፡፡የአሁን ዘመን የእግዚአብሔርን ቃል የምንራብበትም ዘመን ነው፡፡ ‹‹ እነሆ በምድር ላይ ራብን የምሰድበት ዘመን ይመጣል? ይላል ጌታ እግዚአብሔር፡፡ እርሱም የእግዚአብሔር ቃል ከመስማት እንጂ እንጀራን ከመራብና ውኃን ከመጠማት አይደለም፡፡ ከባሕርም እስከ ባሕር ድረስ፤ ከሰሜንም እስከ ምሥራቅ ድረስ ይቅበዘበዛሉ፤ የእግዚአብሔርን ቃል ለመሻት ይሯሯጣሉ፤ አያገኙትምም፡፡ በዚያ ቀን መልካሞች ደናግል ጎበዛዝትም በጥም ይዝላሉ››ተብሎ እንደተጻፈ ነፍሳት በርግጥም ተጠምተዋል፡፡/አሞ 8፥11-14/
ረሀብ የተፈጠረው ግን በመጻሕፍት ወይም በመምህራን አለመኖር አይደለም፡፡ በሰው ወይም በሰማዕያንና በአንባብያን አለመዘጋጀት ነው ማለት ይቻላል፡፡ ምእመናን ስንሰማም ሆነ ስናነብ መንፈሳችንን ከሥጋዊ ዓላማ ‹‹ የእግዚአብሔር ልጅስ ከሆንክ ይህንን ድንጋይ ዳቦ አድርግ›› በማለት ሰይጣን ከሚያቀርበው ፈተና ማለትም መንፈሳዊ ነገርን ለምድራዊ ጥቅም ከማዋል ርቀን በቤተ ክርስቲያን መንፈስ፣ ለእኔ እግዚአብሔር ምን ይለኛል? ቤተ ክርስቲያን ምን ትላለች? በማለት በመታዘዝ መንፈስ ተዘጋጅተን ከመጣን እግዚአብሔር ይናገረናል፡፡ ‹‹ የልብ መዘጋጀት ከሰው ነው የምላስ /የጸሎትና የዝግጅት/ መልስ ግን ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው›› ተብሎ ተጽፎአልና /ምሳ 16፥1/
ስለዚህ ከስሜት፣ ከእልህ፣ ከመብለጥና ከመፎካከር ስሜት ወጥተን እናንብበው፤ ያን ጊዜ በግጥም ‹‹ የእግዚአብሔርን ቃል ተመልከቱ›› የሚለውን ትእዛዝ እንፈጽማለን፤ እግዚአብሔርም ምስጢሩን ይገልጽልናል፤ ለድኅነትም ያበቃናል፡፡
                                                
ወስብሐት ለእግዚአብሔር