methehaf awalede

“የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ ለትምህርትና ለተግሣጽ. . . ይጠቅማል” 2ኛ ጢሞ.3፤16-17

 ግንቦት 12 ቀን 2006 ዓ.ም.

በዲ/ን ዮሴፍ ይኲኖአምላክ

methehaf awalede“መንፈሰ እግዚአብሔር ያለበት፣ ሰውን ከክፋት፣ ከኃጢአት፣ ከበደል የሚመልስ፤ ይልቁንም ሃይማኖቱን የሚያጸናለት መጽሐፍ ከእግዚአብሔር ነውና ይጠቅማል” በማለት ቅዱስ ጳውሎስ የተናገረው ቃል ነው፡፡ ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ይህንን ቃል ያስተላለፈው ለጊዜው በሃይማኖት ትምህርት ወልዶ ላሳደገው ለደቀመዝሙሩ ጢሞቴዎስ ቢኾንም ፍጻሜው ግን እስከ ሕልፈተ ዓለም ለሚነሡ ክርስቲያኖች ሁሉ የተናገረው ነው፡፡ “የእግዚአብሔር ሰው ፍጹምና ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ፥ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ ይጠቅማል።” (፪ኛ. ጢሞ.፫፥፲፮-፲፯)

 

መንፈሰ እግዚአብሔር ያለባቸው መጻሕፍት ሁሉ እንደሚጠቅሙና እንደሚያስፈልጉ ሐዋርያው በመልእክቱ ያስተላለፈውን ቃል መመሪያ አድርጋ ቅድስት ቤተክርስቲያንየአሥራው መጻሕፍት ልጆች የምንላቸውን አዋልድ መጻሕፍትን አዘጋጅታልናለች፡፡
አዋልድ መጻሕፍት፡-

“አዋልድ መጻሕፍት” የሁለት ቃላት ጥምር ሐረግ ሲሆን ቀጥተኛ ትርጉሙ የመጻሕፍት ልጆች ማለት ነው፡፡ መጻሕፍት የተባሉትም በቀኖና ቤተ ክርስቲያን ተለይተውና ተቆጥረው የምናውቃቸው ሰማንያ አንዱ መጻሕፍተ ብሉያትና ሐዲሳት ናቸው፡፡

አዋልድ መጻሕፍት የአሥራው መጻሕፍት ምሥጢር ትርጓሜ ተብራርቶ የሚገኝባቸው መጻሕፍት ናቸው፡፡ ቅዱሳን ነብያት እንዲሁም ሐዋርያት፤ በየዘመናቱ የተነሡ መምህራንና ሊቃውንት አዋልድ መጻሕፍት መጠቀማቸው መጽሐፍ ቅዱስ ያስረዳል፡፡ /ኢያሱ 10፤13, 2ኛ ሳሙ.1፤18/ መጽሐፍ ቅዱስን ለማብራራት አዋልድ መጻሕፍት አስፈላጊ ናቸው፡፡

ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአንድ ወቅት ‹ሕግን አውቃለሁ›ለሚል ሰው ወንበዴዎች ደብድበው በሞትና በሕይወት መካከል ጥለውት ስለሄዱ አንድ መንገደኛ በምሳሌ አስተምሮታል፡፡ ይህን ቁስለኛ አንድ ሩኅሩኅ ሳምራዊ ወደ እንግዳ ማረፊያ ቤት ወስዶ ከጠበቀው በኋላ ለእንግዶች ማደረፊያ ቤት ጠባቂውሁለት ዲናር አውጥቶሰጠውና፤ “ጠብቀው፥ ከዚህ በላይ የምትከስረውን ሁሉ እኔ ስመለስ እከፍልሃለሁ አለው፡፡(ሉቃ.፲፥፴-፴፭) ይህ ምሳሌ ነው፡፡ በወንበዴዎች የቆሰለው ቁስለኛ፤ በኃጢአት መርዝ የተለከፈና የቆሰለ የሰው ልጅ ሁሉ ሲሆን፤ ወንበዴው ደግሞ ዲያብሎስ ነው፡፡

የአዳምን ቁስል የፈወሰው ርኁሩኁ ሳምራዊ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲሆን፤ ይህን ቁስለኛ ያሳደረበት የእንግዶች ማረፊያ ቤት የተባለች ቤተ ክርስቲያን ናት (መዝ.፴፰፥፲፪፣ዘፍ.፵፯፥፱)፡፡ የእንግዶች ማረፊያ ቤት (የቤተ ክርስቲያን) ጠባቂዎች የተባሉት ደግሞ አባቶቻችን መምህራን ናቸው፡፡ (የሐዋ.፳፥፳፰) ራሱን በሩኅሩኁ ሳምራዊ የመሰለው ጌታችን ለቤተ ክርስቲያን መምህራን የሰጣቸው ሁለት ዲናር የተባሉት መጻሕፍተ ብሉያትና መጻሕፍተ ሐዲሳት ናቸው፡፡ ሁለቱን ዲናር ከሰጠ በኋላበነዚያ ብቻ ሳይወሰን “ከዚህም በላይ የምትከስረውን ሁሉ እኔ ስመለስ እከፍልሃለሁ” አለው፡፡ ይህ ቃል የሚያመለክተው በሁለቱ ዲናሮች (በብሉያትና ሐዲሳት) ተመሥርተው የረቀቀውን አጉልተው፣ የተሠወረውን ምሥጢር ገልጠው ምእመናንን የሚያስረዱ ልዩ ልዩ የትርጓሜ፣ የምክር፣ የተግሳጽ፣ የታሪክና የመሳሰሉትን መጻሕፍትን ጽፈው እንዲያስተምሩና እነዚህም ተጨማሪ መጻሕፍት በመጻፋቸው የድካማቸው ዋጋ እንደማይጠፋባቸው ሲገልጽ ነው፡፡ “እኔ ስመለስ እከፍልሃለሁ” ማለቱ በዳግም ምጽአቱ የድካማቸውን ዋጋ እንደሚከፍላቸው ያሳያል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ነገር ግን እንደምታውቁት በፊልጵስዮስ አስቀድመን መከራ ተቀበልን ተንገላታንም፥ በብዙ ገድል የእግዚአብሔርን ወንጌል ለእናንተ እንናገር ዘንድ በአምላካችን ደፈርን፡፡” (፩ኛ.ተሰ.፪፥፲፪) ብሏል፡፡ ገድል ያለው መከራውን ነው፡፡

የአዋልድ መጻሕፍት አስፈላጊነት፡-

ፍቁረ እግዚእ የተባለ ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ በወንጌሉ “ኢየሱስም በዚህ መጽሐፍ ያልተጻፈ ሌላ ብዙ ምልክት በደቀ መዛሙርቱ ፊት አደረገ፤” ካለ በኋላ “ኢየሱስም ያደረገው ብዙ ሌላ ነገር ደግሞ አለ፤ ሁሉ በእያንዳንዱ ቢጻፍ ለተጻፉት መጻሕፍት ዓለም ባልበቃቸው ይመስለኛል” (ዮሐ.፳፥፴፤፳፩፥፳፭) በማለት ተናግሯል፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ዓለም በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ ሠላሳ ሦስት ዓመት ከሦስት ወር ሲመላለስ ያደረጋቸው ተአምራት እያንዳንዳቸው እንዳልተመዘገቡ ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ በአጽንዖት አስረድቷል፡፡

በሌላ በኩል ቅዱስ ጳውሎስ “የእግዚአብሔር ሰው ፍጹምና ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ፥ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ ይጠቅማል።”በማለት የአዋልድ መጻሕፍት አስፈላጊነት ምን እንደሆነ ገልጦ ተናግሯል፡፡

በዚህ የተነሣ በእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ እየተመሩ ቅዱሳን ነቢያትና ሐዋርያት በልዩ ልዩ ጊዜና ቦታ ሆነው መጽሐፍ ቅዱስን ሲጽፉ አዋልድ መጻሕፍትን ለትርጓሜ፣ ለምክር፣ ለተግሳጽ፣ ለታሪክ አስረጂነት እንደተጠቀሙባቸው አስረድተዋል፡፡ (ኢያ. ፲፥፲፫፤ ፩ኛ.ሳሙ .፩፥፲፰፤ ይሁ.፱)

እንግዲህ በነቢያትና በሐዋርያት መሠረት ላይ ከታነጽን በእነርሱ መንገድ መመራት ያሻናል፡፡ አዋልድ መጽሐፍቱ ከትምህርት ሰጪነት ባሻገርበእለት እለት ሕይወታችንለጸሎት የምንጠቀምባቸው ናቸው፡፡ በገመድ ያለ የኤሌክትሪክ ኃይል የሚፈካውና የሚታየው በአምፖል ሲበራ እንደሆነ ሁሉ በአሥራው መጻሕፍት የሚገኝ ጥበብ፣ ትምህርትና ምሥጢርም የሚረዳው የሚገለጠው በአዋልድ መጻሕፍት ተብራርቶ ሲታይ ነው፡፡

ይቆየን