“አዲስ ልብና አዲስ መንፈስ ለእናንተ አድርጉ” /ሕዝ 18፥31/

በማሞ አየነው

የሰው ልጅ ለሥጋዊና መንፈሳዊ እንቅስቃሴው አመች በሆነ መልኩ እግዚአብሔር ለሚያፈራርቃቸው ዘመናት ቀመር ሲያወጣ ኖሯል፡፡ ጊዜያትንም ከደቂቃ ሽራፊ እስከ ሺህ ዘመናት ድረስ ከፋፍሎ ይጠቀማል፡፡ በዚህ የጊዜ ቀመርም ትናንትን ያስረጃል፤ ዛሬን ደግሞ አዲስ ያደርጋል፡፡ በጊዜ ዑደትም ብዙ ሺህ አዲስ ዓመታት አልፈው ብዙ ሺህ አዲስ ዓመታት መጥተዋል፡፡ የዘመናት መፈራረቅ ሰው የእግዚአብሔርን ሥራ እንዲያደንቅ፣ መግቦቱንም እንዳይረሳ ያደርጋል፡፡ እግዚአብሔር አምላክም ቃል ኪዳኑን እንዳልረሳ፣ ፍጥረቱን እንዳልዘነጋ ያመለክታል፡፡

 

 

ቅዱስ ዳዊት «የሰው ሁሉ ዓይን  አንተን ተስፋ ያደርጋል፡፡ ምግባቸውንም በየጊዜው ትሰጣቸዋለህ» እንዳለ፣ወራትን እያፈራረቀ፣ በዝናብ እያበቀለ፣በፀሐይ እያበሰለ ለፍጥረታት ምግባቸውን ይሰጣል።/መዝ 144፥15/ እግዚአብሔር አምላክ ዓመታት አያረጁበትም፣ አይለወጡበትም «አንተ ግን ያው አንተ ነህ ዓመቶችህም ከቶ አያልቁም» እንዲል /መዝ 101፥27/፡፡ ስለዚህም ዓመታት የሚቀያየሩት የሚያልቁትና የሚጀምሩትም ለሰው ልጆች ብቻ ነው፡፡ አዲስ ዓመት የክረምትን መውጣትና የመከርን መድረስ የዝናሙን ማለፍ ተከትሎ የሚከበር የአዲስ ተስፋ እና ብስራት በዓል ነው፡፡ ይህን አስመልክቶ ጠቢቡ ሰሎሞን እንዲህ ብሏል፡፡ «እነሆ ክረምት አለፈ ዝናቡም አልፎ ሄደ፡፡ አበቦች በምድር ላይ ተገለጡ፣ የዜማም ጊዜ ደረሰ፣ የቁርዬውም ቃል በምድራችን ተሰማ፣ በለሱ ጎመራ ወይኖችም አበቡ፣ መዐዛቸውንም ሰጡ» /መኃ 2፥11/፡፡ በአዲስ ዓመት ዓመታት ብቻ ሳይሆኑ ምድርም ገጽታዋን ትለውጣለች፡፡ የደረቁ ዛፎችና የደረቀችው መሬት አረንጓዴ ይለብሳሉ፤  አዝርእትና እፅዋት በአበባ ለዘር ለፍሬ ይደርሳሉ፡፡ ይህም በዓሉን እጅግ ደማቅና ተወዳጅ ያደርገዋል፡፡ መግቦቱን እንድናከብር እና ቃል ኪዳኑንም እንዳንረሳ እግዚአብሔር አምላክ አዝዞናልና፡፡

ስለዚህም ነው ቅድስት ቤተክርስቲያን በዓሉን በድምቀት የምታከብረው ምዕመናንንም እንዲያከብሩት የምታስተምረው፡፡ ነገር ግን አሁን አሁን እየታየ ባለው የአከባበር ሁኔታ የበዓሉን መንፈስ ፍፁም ሥጋዊ እንዲሆን ግብረ እግዚአብሔርን ፤ መግቦተ እግዚአብሔርን ከማሰብ ይልቅ የሥጋን ነገር ብቻ እያሰብን እንድናከብር የሚያስገድዱ ነገሮች ይስተዋላሉ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ አዲስ ዓመትን እንዴት ማክበር እንዳለብን የሚነገረን ነገር አለ፡፡ በክርስትና መስመር ያለ ሰው እነዚህን ጠቃሚ ነጥቦች በማየት ራሱን እንዴት ማስተካከል እንዳለበት፣ አዲሱን ዓመት እንዴት መቀበል እንዳለበት ይገልጻል፡፡ መጽሐፍ ከሚያስተምረን ብዙ ቁም ነገሮች የተወሰኑትን እንደሚከተለው እንመለከታለን፡፡

 

1.“አዲሱን ሰው ልበሱ” /ኤፌ 4 ፥22/


የዓመታት መቀያየር በእኛ ክርስቲያናዊ ሕይወት ውስጥ ለውጥ ካላመጣ በድሮው አሮጌ ሰውነታችን አዲሱን ዓመት ከተቀበልን ዛሬ ከትናንት በምን ይሻላል? ድሮ የነበሩንን የኃጢአት ልምዶች ዛሬ ማስወገድ ካልቻልን አዲስ ዓመት መጣ ማለት ረቡ ምንድን ነው? አዲስ ዓመት ሲመጣ በአእምሯችን ልናመላልሰው የሚገባው ነገር የመንፈሳዊ ሕይወታችን መለወጥ መሻሻልና ማደግ ነው፡፡ እነዚህን ሃሣቦች ተግባራዊ ለማድረግ አሮጌውን እኛነታችንን አውልቀን አዲሱን ሰው መልበስ ያስፈልጋል፡፡ «አሮጌውን ሰው ከሥራው ጋር ገፍፋችሁታልና፤ የፈጠረውንም ምሳሌ እንዲመስል እውቀትን ለማግኘት የሚታደሰውን አዲሱን ሰው ለብሳችሁታልና» እንዲል ቅዱስ ጳውሎስ /ቆላ 3፥10/። አሮጌውን ሰው ከነ አሮጌ ሥራው ስንገፈውና አዲሱን ሰው ስንለብስ ነው ዓመቱን አዲስ የምናደርገው አሮጌው ሰው በምክንያትና በሰበብ አስባቦች የተሞላ ነው፡፡ ጊዜ ለሰጠው አምላክ እንኳን ጊዜ የሚሰጠው በድርድርና በቅድመ ሁኔታ ነው፡፡ አሮጌው ሰው ስለንስሐ ሲነገረው “ከልጅነቴ ጀምሮ ሕግጋቱን ጠብቄያለሁ” ይላል፡፡ ስለ ሥጋወደሙ በተነገረው ጊዜ “ይህ የሚያስጨንቅ ንግግር ነው ማን ሊሰማው ይችላል»/ዮሐ 6፥60/ ይላል፡፡ ወደ እግዚአብሔር ቤት እንዳይገሰግስ «አባቴ ሞቷል እቀብር ዘንድ ፍቀድልኝ»/ሉቃ 9፥59/ ብሎ ራሱን በምክንያቶች ይከባል፡፡ ይህ ከእግዚአብሔር ጋር ያለያየን አሮጌው ሰውነታችን በአዲስ ሊቀየር ይገባዋል፡፡ አሮጌው ሰውነታችን ነፍሳችን እንድትጠማ ምክንያት ሆኗል፡፡ «እንጨትና ውኃ በሌለበት በምድረ በዳ ነፍሴ አንተን ተጠማች» እንዲል /መዝ 62፥1/ ስለዚህም ነፍሳችን ከጥሟ ትረካ ዘንድ በቃለ እግዚአብሔርም ትረሰርስ ዘንድ አዲሱን ሰው እንልበስ። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም «ፊተኛ ኑሯችሁን እያሰባችሁ እንደሚያታልል ምኞት የሚጠፋውን አሮጌውን ሰው አስወግዱ። በአእምሯችሁ መንፈስ ታደሱ፤ ለእውነትም ለሚሆኑ ጽድቅና ቅድስና እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠረውን አዲሱን ሰው ልበሱ።» እንዲል /ኤፌ 4፥22-24/፡፡

 

2.“አሮጌው እርሾ አስወግዱ” /1ቆሮ 5፥7/


ጌታችን በመዋዕለ ሥጋዌው «ጽድቃችሁ ከጻፎችና ከፈሪሳዊያን ካልበለጠ ወደ እግዚአብሔር መንግስት አትገቡም።» ብሎ አስተምሮ ነበር፡፡ ከጻፎችና ከፈሪሳዊያን እኩይ ግብር አንዱና ዋነኛው ደግሞ በሁለት ቢላዋ የመብላት ልምዳቸው ነው፡፡ የሙሴን ሕግ እንፈጽማለን እናስፈጽማለን ይላሉ፤ በሌላ በኩል ይሄንኑ ሕግ ራሳቸው ሲጥሱ እንመለከታለን፡፡ ጽድቅና ኃጢአትን በአንድ ሰውነታቸው ሊፈጸሙ የሚሞክሩ ሰዎች ነበሩ፡፡ ጽድቃችን ይህን ከመሰለ ሁኔታ እንዲለይም ጌታችን አስተምሮናል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም በመልእክቱ እንዲህ ይለናል፤ «እንግዲህ ያለ እርሾ እንዳላችሁ አዲሱን ሊጥ ትሆኑ ዘንድ አሮጌውን እርሾ አስወግዱ….። ስለዚህ በቅንነትና በእውነት ቂጣ በዓልን እናድርግ እንጂ በአሮጌ እርሾ በክፋትና በግፍ እርሾም አይደለም፡፡» /1ቆሮ 5፥7/፡፡ እርሾ ለሊጥ አስፈላጊ የሚሆነው ሊጡን እስከሚያቦካ ድረስ ብቻ፡፡ ሊጡን ካቦካ በኋላ አሮጌው እርሾ ይወገዳል፡፡ ካለያ ሊጡን ሆምጣጣና ጣዕም የለሽ ያደርገዋል፡፡ ሊጡ ቂጣ መሆን የሚችለውም አሮጌው እርሾ ከተወገደ በኋላ ነው፡፡
በክርስትና ሕይወታችንም ጽድቅና ኃጢአት እየተፈራረቁ ሊያስቸግሩን ይችላሉ፡፡ በአዲስ የንስሐ ሕይወት እንኖር ዘንድ ቀድሞ የነበረውና ከጽድቃችን ጋር የተቀላቀለው እኩይ ግብር ሊወገድ ይገባል፡፡ ይህ ካልሆነ ጽድቃችን ከፈሪሳውያን በምን ተሻለ? በዓልንም በቅንነትና በእውነት ቂጣ የምናከብረው አሮጌውን እርሾ ስናስወግድ ነው፡፡ በቂጣ የተመሰለው ክርስቲያናዊ ሕይወታችን ለሰው ምግብ መሆን የሚችለው ከአዲሱ ማንነታችን /ከአዲሱ ሊጥ/ ጋር አብሮ የተቀላቀለው አሮጌ እርሾ ማለትም ጽድቅን ከኃጢያት አደባልቆ የሚሄደው ሰውነታችን ይህን ግብሩን እርግፍ አድርጐ መተው አለበት።

 

3.“አዲስ ልብና መንፈስም ለእናንተ አድርጉ” /ሕዝ 18፥31/


በመንፈሳዊ ሕይወት ውስጥ ትልቁ ፈተና ያለንን ነገር ጠብቆ መቆየት መቻል ነው፡፡ መንፈሳዊ ዝለት የሚፈጠረውም መንፈሳዊ እንቅስቃሴያችን ተደጋጋሚና ዕድገት የሌለው መሆን ሲጀምር  ነው፡፡ መንፈሳዊ ዕድገት የሚያሳይ ሰው ለመንፈስ ዝለት አይጋለጥም፡፡ በአዲስ ልብና በአዲስ መንፈስ ሕይወቱን የሚመራ ክርስቲያን አይሰለችም፣ ለእሱ ክርስትና ሁሌም አዲስ ነው፤ አንዴ የሚፈጽሙትና የሚጨርሱት ሳይሆን የዕድሜ ልክ ሕይወት ነው፡፡ ስለዚህም ክርስትና በአዲስ ልብና በአዲስ መንፈስ የሚኖር አዲስ ሕይወት፣ የድሮውን እየረሱ ነገን ለመያዝ የሚደረግ የተስፋ ሕይወት ነው፡፡ « ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው፤ አሮጌው ነገር አልፏል፤ እነሆ ሁሉም አዲስ ሆኗል፡፡»  እንዲል ቅዱስ ጳውሎስ። /2ቆሮ 5፥17/ አዲስ ዓመትንም አዲስ የምናደርገው አዲስ ልብና አዲስ መንፈስ ስንይዝ ብቻ ነው፡፡ የለውጥ መጀመሪያ የልቦና መለወጥ ነውና፡፡ በስሜት የሚመጣ ለውጥ ዘላቂነት የለውም፡፡ ትንሽ ነፋስ ሲነፍስ መወዛወዝ ይጀምራል፡፡ ለዚህም ነው ነብዩ የድሮው እኛነታችንን እንድናስወግድ አዲስ ልብና አዲስ መንፈስም እንዲኖረን የሚመክረን «አዲስ ልብና አዲስ መንፈስም ለእናንተ አድርጉ፤ የእስራኤል ቤት ሆይ ስለምን ትሞታላችሁ? የሟቹን ሞት አልፈቅድምና´ /ሕዝ 18፥31/።

 

በአጠቃላይ አዲስ ዓመትን ለአዲስ ክርስቲያናዊ ሕይወት መነሻ አድርገን ብናከብር በዓሉን እውነተኛ የአዲስ ዓመት በዓል ያደርገዋል፡፡ «ካመንበት ጊዜ ይልቅ መዳናችን ዛሬ ወደኛ ቀርቦአል፡፡ እንግዲህ የጨለማውን ሥራ አውጥተን የብርሃንን ጋሻ ጦር እንልበስ» እንዲል ሐዋርያው ያለፉትን የባከኑ ዓመታት ለማስተካከል የብርሃን ጋሻ ጦር በመልበስ የጨለማን ሥራ ማስወገድ አስፈላጊ ነው፡፡/ሮሜ 13፥12-44/ በልብስና በቤት በመኪና ብቻ ሳይሆን በልባችን መታደስ መለወጥ የሚገባን ልዩ ጊዜ ቢኖር ይኼው አዲስ ዓመት ነው።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር