‹‹በመንገድ ላይ እንዳላጠፋህ በፊትህ መልአክ እሰዳለሁ፤›› (ዘፀ. ፴፫፥፫)፡፡

በመምህር ኢዮብ ይመኑ 

ኅዳር ፲፪ ቀን ፳፻፲ ዓ.

በረኃብ ምክንያት ከከነዓን ወደ ግብጽ የተሰደዱት የያዕቆብ ቤተሰቦች፣ በአባታቸው በያዕቆብ ምርቃት በግብጽ ምድር ቍጥራቸውም እጅግ እየበዛ መጣ፡፡ መብዛታቸውም ከ፲፪፻፹ – ፲፬፻፵፭ ቅድመ ልደተ ክርስቶስ የተነሣውን፣ ዮሴፍን የማያውቀውን ንጉሥ አስፈራው (ዘፀ. ፩፥፰)፡፡ ንጉሡም ጠላት ይኾኑብናል ያም ባይኾን ጠላት ቢነሣብን አብረው ይወጉናል በሚል ፍርኃት፣ አገዛዙን አጸናባቸው፡፡ በከባድ ሥራ እየጠመደ በጭካኔ ጡብ እያስገነባ ፊቶም፣ ራምሴ፣ ዖን የተባሉ ታላላቅ ከተሞችን አሠራቸው፡፡ ኖራ እያስወቀጠ፣ ጭቃ እያስረገጠ በሥራ ደክመው ልጅ እንዳይወልዱ ጉልበታቸውን አደከማቸው፡፡ በጅራፍ እየገረፈ መከራ አጸናባቸው፡፡ ይህን ቢያደርግም ጉልበታቸው እየበረታ፣ ከእርሱ መከራ የአባቶቻቸው ምርቃትና ቃል ኪዳን እየረታ አሁንም በዙ፡፡ ንጉሡም ወንድ ሲወለድ በመግደል እስራኤልን ለመቆጣጠር ሞከረ፡፡ ነገር ግን የመከራው ብዛት የሕዝቡም ጩኸት የራሔልም ዕንባ የሕዝቡን መከራ ቅድመ እግዚአብሔር እንዲደርስ አደረገው፡፡

በግብጽ ምድር በመከራ የኖሩት እስራኤላውያን፣ በፈርዖንና በሠራዊቱ ላይ ከደረሱ ፱ መቅሠፍቶች፣ ፲ኛ ሞተ በኵር እና ፲፩ኛ ስጥመተ ባሕር በኋላ በእግዚአብሔር ፈቃድ፣ በቅዱስ ሚካኤል ተራዳኢነትና በሙሴ ጸሎት በተአምራት ከግብጽ ምድር ወጥተው ወደ ርስታቸው ከነዓን ገብተዋል፡፡ ‹‹በመንገድ ላይ እንዳላጠፋህ በፊትህ መልአክ እሰዳለሁ፤›› (ዘፀ. ፴፫፥፩-፫) ተብሎ እንደ ተጻፈው፤ ከመከራ የወጡትን እስራኤል በጉዟቸው ከሚገጥማቸው መሰናከል እየጠበቀ፣ በመንገድ ላይ እንዳይጠፉ እያማለደ፣ በምሕረት እየታደገ፣ ከጠላት ጋር ሲዋጉም አብሮ እየቀደመ፣ ከዲያብሎስ ተንኮል እየሰወረ እግዚአብሔር ወዳዘጋጀላቸው ሥፍራ ያስገባቸው የእግዚአብሔር መልአክ የቅዱስ ሚካኤል መታሰቢያ በዓል በየዓመቱ ኅዳር ፲፪ ቀን በቤተ ክርስቲያናችን ይከበራል፡፡

እግዚአብሔር የሰው ልጆችን ድካም የሚያውቅ አምላክ ነው፡፡ የሰው ልጅ ደግሞ የእግዚአብሔርን ውለታ የሚዘነጋ፣ የተደረገለትንም የሚረሳ፣ ፊቱ ባለ ነገር ላይ ብቻ የሚጨነቅ፣ ነገ በሚመጣው ብቻ የሚጠበብ እንጂ የትናንትና ታሪኩን አስቦ እግዚአብሔርን የሚያመሰግን ባለመኾኑ፣ የተደረገለትን ውለታ እንዳይረሳ ይልቁን እግዚአብሔርን እንዲያመሰግን እንደዚሁም ያለፉት ሥራዎቹ እንዳይረሱ መታሰቢያን ሰጥቶናል፡፡ የቅዱሳን በመታሰቢያ በዓላት እኛን እንድንድን ለመርዳትና ለማገዝ የተሠሩ ሥርዓቶች ናቸው፡፡ መጽሐፍ ‹‹መታሰቢያህም ለልጅ ልጅ ነው … ይህ ለሚመጣ ትውልድ ይጻፍ፡፡ የሚፈጠርም ሕዝብ ለእግዚአብሔር ዕልል ይላል›› (መዝ. ፻፩፥፲፪) እንዳለ የቅዱሳን በዓል መታሰቢያነቱ የእግዚአብሔርን ሥራ ለማድነቅ ለማመስገን ነው፡፡ ተጠቃሚዎቹ ደግሞ እኛ ምእመናን ነን፡፡ ከዚህም ባሻገር መጪውን ትውልድ ወደ እግዚአብሔር ማቅረቢያ፣ ለነገ መንፈሳዊ ሕይወት ማዘጋጃ፣ የበረከትም ማግኛ ይኾናል – መታሰቢያ፡፡

በመጽሐፍ ቅዱስ እንደ ተመዘገበው የዮርዳኖስን የሞላ ውኃ በእግዚአብሔር ተአምራት ተቋርጦ በደረቅ መሻገራቸው ለማሰብ ኢያሱ እስራኤላውያንን ‹‹በአምላካችሁ በእግዚአብሔር ታቦት ፊት ወደ ዮርዳኖስ መካከል እለፉ፡፡ ከእናንተም ሰው ዅሉ በእስራኤል ልጆች ነገድ ቍጥር በጫንቃው ላይ አንድ አንድ ድንጋይ ከዚያ ይሸከም፡፡ ይህም በመካከላችሁ ምልክት ይኾናል ልጆቻችሁም በሚመጣ ዘመን ‹የእነዚህ ድንጋዮች ነገር ምንድር ነው?› ብለው ሲጠይቁአችሁ እናንተበእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ታቦት ፊት የዮርዳኖስ ውኃ ስለ ተቋረጠ ነው፤ እነዚህ ድንጋዮች ለእስራኤል ልጆች ለዘለዓለም መታሰቢያ ይኾናሉ› ትሏቸዋላችሁ፤›› ብሏቸዋል (ኢያሱ ፬፥፬-፯)፡፡ ይህም መታሰቢያ ዕለታት ወይም በዓላት ወይም ምልክቶች ጥቅም እንዳላቸው ያስረዳናል፡፡ በእነዚህ ዕለታት፣ ሰው እግዚአብሔርን አመስግኖ፣ ከቅዱሳኑ በረከት አግኝቶ፣ ራሱን በቅድስና ሥፍራ አውሎ፣ ቅድስናን ተምሮ ለቅድስና የሚያበቃውን በረከት ያገኛል፡፡  እግዚአብሔር አምላካችን ሥራ የሠራበት፣ በጽኑ ተአምራት ሕዝቡን የታደገበት መንገድ እንደ ቀላል በዝምታ የሚታለፍ ሳይኾን መታሰቢያ የሚደረግለት በዓል ነው፡፡ ‹‹ተዝካረ ገብረ ለስብሐቲሁ፤ ለተአምራቱ መታሰቢያአደረገ፤›› (መዝ. ፻፲፥፬) ተብሎ እንደ ተጻፈ፡፡

ስለዚህም ኅዳር ፲፪ ቀን እግዚአብሔር በታላላቅ ተአምራት ሕዝቡን ነጻ ያወጣበት ዕለት በመኾኑ የመታሰቢያ በዓል ኾኗል፡፡ እግዚአብሔር በባሕርዩ የእርሱ ለኾኑት ቅዱሳን ክብርና ሞገስ የሚሰጥ አምላክ ነው፡፡ ሰዎች የእርሱ የኾኑትን እንዲያከብሩለት የሚፈልግ አምላክም ነው፡፡ ለዚህም ነው ‹‹እነሆም መጥተው በእግሮችህ ፊት ይሰግዱ ዘንድ እኔም እንደወደድኹህ ያውቁ ዘንድ አደርጋቸዋለሁ፤›› በማለት የተናገረው (ራዕ. ፫፥፱)፡፡ ወዳጆቹን ማክበር እግዚአብሔርን ማክበር ነው፡፡ እነርሱን ማሰብም እርሱን ማሰብ ነውና ነው፡፡ ‹‹የእግዚአብሔርን ቃል የተናገሯችሁን ዋኖቻችሁን አስቡ፡፡ የኑሮአቸውንም ፍሬ እየተመለከታችሁ በእምነት ምሰሏቸው›› ተብሎ እንደ ተጽፏልና (ዕብ. ፲፫፥፯)፡፡

ቅዱሳኑን መመልከት እግዚአብሔርን መመልከት ነው፡፡ ስለዚህም ይህ የከበረ ዕለት፣ እስራኤል በመንገድ ላይ እንዳይጠፉ በቅዱስ ሚካኤል ተራዳኢነት፣ ጥበቃና መሪነት ወዳዘጋጀላቸው ሥፍራ መግባታቸውን የምናስብበት በዓል ነው፡፡ ቤቱ የእርሱ ቢኾንም መታሰቢያነቱን ለወዳጆቹ፣ ደስ ላሰኙት ቅዱሳኑ እግዚአብሔር ይሰጣል (ኢሳ. ፶፮፥፬)፡፡ ልዩ ከኾነው ስሙ ጋር ስማቸው አብሮ እንዲነሣ ያደርጋል፡፡ አድሮባቸው ሥራ ሠርቷልና እንዲሁ አይተዋቸውም፤ እንዲታሰቡለት ያደርጋል እንጂ፡፡ በቤቱም በፊቱም እነርሱ ሲታሰቡና ሲከብሩ ደስ ይሰኛል፡፡ ምንጩም ፈቃጁም እርሱ ራሱ ነውና፡፡ ‹‹እግዚአብሔርን ለሚፈሩ፣ ስሙንም ለሚያስቡ የመታሰቢያ መጽሐፍ በፊቱ ተጻፈ፤›› እንዳለ ነቢዩ (ሚል. ፫፥፲፮)፡፡ ቅዱሳኑ ስሙን በፍጹም አስበዋልና እግዚአብሔር ደግሞ ስማቸው በሌሎች (በእኛ) እንዲታሰብ ፈቅዷል፡፡ ከዚህ አኳያ ከእስራኤል ዘሥጋ ነጻ መውጣት ጋር ‹‹ስሜ በእርሱ ስለ ኾነ›› (ዘፀ. ፳፫፥፳) የተባለለት ቅዱስ ሚካኤል፣ በየዓመቱ ኅዳር ፲፪ ቀን መታሰቢያው ይከበራል፡፡

‹‹የእግዚአብሔር ሠራዊት አለቃ ኾኜ አሁን መጥቼአለሁ›› (ኢያሱ ፭፥፲፬) በማለት መልአኩ እንደ ተናገረው ኢያሱና እስራኤላውያንን የረዳቸው፣ ያጸናቸው እርሱ ቅዱስ ሚካኤል ነው፡፡ ዲያብሎስ በተንኮል የሙሴን መቃብር አሳይቶ ሕዝቡን በአምልኮ ጣዖት ሊጥል ሲያደባ በጣዖት ወድቀው እግዚአብሔርን በድለው እንዳይጠፉ ከፊታቸው ቀድሞ ከዲያብሎስ ስውር ሤራ የጠበቃቸው ቅዱስ ሚካኤል ነው፡፡ ‹‹የመላእክት አለቃ ሚካኤል ግን ከዲያብሎስ ጋር በተከራከረ ጊዜ ስለ ሙሴ ሥጋ ሲነጋገር ‹ጌታ ይገሥፅህ› አለው እንጂ የስድብን ፍርድ ሊናገረው አልደፈረም፤›› እንዲል (ይሁዳ፣ ቍ. ፱)፡፡ ዳግመኛም ቀኑን በደመና ዓምድ ከበረኃው ዋዕይ እየጋረደ፣ ሌሊቱን በብርሃን ዓምድ ጨለማውን እያስወገደ፣ ከመሰናክል እያዳነ ከመከራ እየጠበቀ እስራኤልን ነጻ አውጥቷቸዋልና ለቅዱስ ሚካኤል መታሰቢያ በዓል ተደርጎለታል (ዘፀ. ፳፫፥፳፤ መዝ. ፴፫፥፯)፡፡

በዘመነ ኦሪት የሶምሶንን አባት እና እናት ልጅ እንደሚወልዱ ባበሠራቸው ጊዜ ማኑሄ፣ ‹‹ነገርህ በደረሰ ጊዜ እንድናከብርህ ስምህ ማን ነው?›› (መሣ. ፲፫፥፲፯) በማለት የእግዚአብሔርን መልአክ መጠየቁ በምስጋና፣ በደስታ ቀናቸው ይህን ተአምራት ያሳያቸውን መልአክ ለማክበርና መታሰቢያ ለማድረግ ነበር፡፡ ይህም የቅዱሳንን በዓል የማበክበር ትውፊት ከጥንት ጊዜ ጀምሮ መኖሩን በሚገባ ያሳያል፡፡ የደስታ፣ የምስጋና ቃል የሚሰማበት ቀን ደግሞ ‹በዓል› ይባላል፡፡ መጽሐፍ ‹‹በዓል የሚያደርጉ ሰዎች የደስታ የምስጋና ቃል አሰሙ›› ይላልና (መዝ. ፵፩፥፭)፡፡ እግዚአብሔር በላያቸው ላይ አድሮ ሥራ የሠራባቸውን፣ ተአምራቱን የገለጸባቸውን ቅዱሳን መላእክት፣ ጻድቃንና ሰማዕታትን የመታሰቢያ በዓል እኛም በዚህ ዘመን በደስታና በምስጋና ማክበራንም ፍጹም አምላካዊና መንፈሳዊ መንገድ መኾኑን አምነን እንመሰክራለን፡፡ ‹‹ቀንን የሚያከብር ለጌታ ብሎ ያከብራል›› ተብሎ እንደ ተጻፈ (ሮሜ. ፲፬፥፮)፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡