ማኅበሩ የደብረ ጽጌ ገዳም የአብነት ትምህርት ቤትን በ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር ለማደስና ለማስፋፋት ስምምነት ተፈራረመ

በሰሜን ሸዋ ሰላሌ ፍቺ ሀገረ ስብከት የሚገኘው ደብር ቅዱስ ደብረ ጽጌ ማርያም አንድነት ገዳም የአብነት ትምህርት ቤትን ለማጠናከር በማኅበረ ቅዱሳንና በሀገር ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ የአንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ብር የፕሮጀክት ስምምነት ተፈራረመ፡፡
ጥቅምት 1 ቀን 2002 ዓ.ም ወደ ስፈራው በተደረገው ሐዋርያዊ ጉዞ ወቅት በማኅበረ ቅዱሳን የፍቺ ማዕከልና የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቆስጦስ የተከናወነው ይኸው የፕሮጀክት ስምምነት አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ብር የሚፈጅ ሲሆን፤ ፕሮጀክቱ ከ3-4 ዓመታት ባለው ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል፡፡

በፊርማ ሥነ ሥርዓቱ ወቅት በማኅበረ ቅዱሳን የማኅበራዊ አገልግሎት ልማት ዋና ክፍል የቅስቀሳና ገቢ አሰባሰብ ሓላፊ ወ/ሮ ዓለም ፀሐይ መሠረት እንደገለጹት፤ ይኸው የስምምነት ሰነድ የተዘጋጀው ማኅበሩ በነዚህ ዓመታት በአቅም እጥረትና በእርጅና ምክንያት ሳይታደስ በመፈራረስ ላይ የሚገኘውን የአብነት ትምህርት ቤት ለማጠናከር፣ ሦስት አዲስ ቤት ለመገንባት እና ሰባት የጥገና ማስፋፋት ለማካሄድ ነው፡፡

የፕሮጀክቱ አጠቃላይ ወጪ የማኅበሩን የሞያ አገልግሎት እንደማያካትት የገለጹት ወ/ሮ ዓለምፀሐይ፤ እግዚአብሔር ፈቅዶ ፕሮጀክቱን በወቅቱ ለማጠናቀቅ ጥረት እንደሚደረግ አስታወቀዋል፡፡

የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቆስጦስ በዚህ ወቅት እንደ ተናገሩት የቤተክርስቲያኒቱ የነገ ተስፋ የሚፈሩበት ይህ የአብነት ት/ቤት ፈርሶ ቢቀር ከፍተኛ ሐዘን ይሰማቸው እንደነበር ጠቅሰው፤ ማኅበሩ ይህን በማሰብ ያከናወነው ተግባር የሚያሰመሰግነው መሆኑን ተናግርዋል፡፡

ለፕሮጀክቱ ተግባራዊነት በዋናነት በሓላፊነት እንደሚንቀሳቀሱና ለግንባታውም ባላቸው አቅም በገንዘብ እንደሚራዱ የጠቀሱት ብፁዕነታቸው፤ ምእመናን በሥራው እገዛ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን ወደ ማኅበረ ምእመናን እያደገ እንደሚገኝም ገልጸዋል ከፕሮጀክቱ ስምምነቱ በተጨማሪም ማኅበሩ ከምእመናን ያሰባሰበውን 13 ሺሕ 200 ብር ግምት ያላቸው 108 መንፈሳ ውያን መጻሕፍት፣ መጽሔትና ጋዜጦች ለገዳሙ  የአብነት ት/ቤት በስ ጦታ አበርክተዋል፡፡

ከዛሬ 50 ዓመታት በፊት የተቋቋሙ ይኸው የአብነት ት/ቤት የተመሠረተው በብፁዕ አቡነ ባስልዮስ መሆኑ በፕሮጀክት ስምምነቱ ወቅት ተጠቁሟል፡፡

በእንግድነት የተገኙት የታዕካ ነገሥት ባዕታ ለማርያም ገዳም እና የመንበረ መንግሥት ቅዱስ ገብርኤል የበላይ ጠባቂ ብፁዕ አቡነ ስምኦን እና የመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም የበላይ ጠባቂ ብፁዕ አቡነ ኤርምያስ በበኩላቸው ባስተላለፉት መልእክት፣ ነገ የቅድስት ቤተክርስቲያንን አገልጋይ መፍለቂያ የሚሆኑት የአብነት ት/ቤቶ ችን ለማጠናከር እየተደረገ ያለው ጥረት የሚበረታታ መሆኑን ጠቅሰው፤ ለፕሮጀክቱ ማስፈጸሚያ እነርሱም በየግላቸው የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንደሚያደረጉ ቃል ገብተዋል፡፡

የማኅበረ ቅዱሳን ዋና ጸሐፊ አቶ ዳንኤል ተስፋዬ በበኩላቸው ማኅበሩ ገዳማትና አድባራትን በመደገፍ እንዲሁም የአብነት ት/ቤቶችን ከማጠናከር በተጨማሪ በርካታ ማኅበራዊና መንፈሳዊ አገልግሎቶችን እየሰጠ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በርካታ የአብነት ት/ቤቶች እየተዳከሙ እንደሚገኙ የገለጹት ዋና ጸሐፊው ይህን ችግር ለመቅረፍ ማኅበሩ በጎ አድራጊ ግለሰቦችንና ማኅበራትን እንዲሁም ምእመናንን በማስተባበር ፕሮጀክት ቀርጾ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

በዚህ መንፈሳዊ ጉብኝት እና የፕሮጀክት ስምምነት ወቅት ከ300 በላይ የበጎ አድራጊ ግለሰቦች እና የመንፈሳዊ ማኅበራት ተወካዮች የተገኙ ሲሆን የአብነት ት/ቤቶችን ለማጠናከር በሚደረገው ጥረት ውስጥ ከማኅበረ ቅዱሳን ጎን እንደሚቆሙ ቃል ገብተዋል፡፡