የትንሣኤ የቅዳሴ ምንባብ 2( 1ጴጥ.1፥1-13)

ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ ከጴጥሮስ፥ በጳንጦስ፥ በገላትያና በቀጰዶቅያ፥ በእስያና በቢታንያ ሀገሮች ለተበተኑ ስደተኞች፥ እግዚአብሔር አስቀድሞ እንዳወቃቸው፥ በመንፈስ ቅዱስም እንደሚቀደሱ፥ ይታዘዙና በኢየሱስ ክርስቶስ ደም ይረጩ ዘንድ፥ ለተመረጡት፥ ጸጋና ሰላም ይብዛላችሁ፡፡
ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን በመነሣቱ፥ ለሕያው ተስፋ እንደ ምሕረቱ ብዛት ሁለተኛ የወለደን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አባት እግዚአብሔር ይመስገን፡፡ የማያረጀውን፥ የማይለወጠውንና የማይጠፋውን፥ በሰማያት ለእኛና ለእናንተ ተጠብቆልን ያለውን ለመውረስ፥ በኋላ ዘመን በሃይማኖት ትገለጥ ዘንድ ለተዘጋጀችው ድኅነት በእግዚአብሔር ኀይል ለተጠበቃችሁት፥ እስከ ዘለዓለም ደስ ይላችኋል፤ ነገር ግን በሚመጣባችሁ ልዩ ልዩ መከራ አሁን ጥቂት ታዝናላችሁ፡፡ በእሳት ከአጠሩት ከጥሩ ወርቅ በሚመረጥ ሃይማኖታችሁ እንደምትቀበሉት መከራ መጠን ኢየሱስ ክርስቶስ በሚገለጥበት ጊዜ በክብር፥ በጌትነትና በምስጋና ትገኛላችሁ፡፡ እርሱም ሳታዩት የምትወዱት ነው፤ እስከ ዛሬም ድረስ አላያችሁትም፤ ነገር ግን ታምኑበታላችሁ፤ አሁንም ፍጻሜ በሌላትና በከበረች ደስታ ደስ ይላችኋል፡፡ በሃይማኖታችሁም ፍጹምነት የነፍሳችሁን ድኅነት ታገኛላችሁ፡፡
ለእናንተም ስለሚሰጠው ጸጋ ትንቢት የተናገሩ ነቢያት የመረመሩአትና የፈለጉአት መድኀኒት ናት፡፡ በእነርሱም የነበረ የክርስቶስ መንፈስ ስለ ክርስቶስ መከራ፥ ከእርሱም በኋላ ስለሚመጣው ክብር፥ አስቀድሞ እየመሰከረ በምን ወይም እንዴት ባለ ዘመን እንዳመለከተ ይመረምሩ ነበር፡፡ ለእነርሱም ከሰማይ በተላከ በመንፈስ ቅዱስ ወንጌልን የሰበኩላችሁ ሰዎች አሁን በነገሩአችሁ ነገር እናንተን እንጂ ራሳቸውን እንዳላገለገሉ ተገለጠላቸው፡፡ ይህንም ነገር መላእክቱ ሊመለከቱ ይመኛሉ፡፡ ስለዚህ የልቡናችሁን ወገብ ታጥቃችሁና ነቅታችሁ ኑሩ፤ ኢየሱስ ክርስቶስም ሲገለጥ የምታገኙትን ጸጋ ፈጽማችሁ ተስፋ አድርጉ፡፡