ፍልሰተ ዐፅሙ ለአቡነ ተክለ ሃይማኖት

በዝግጅት ክፍሉ

ግንቦት ፲፩ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

ቅዱሳን ጻድቃን በሕይወተ ሥጋ ሳሉም ኾነ ካረፉ በኋላ (በዐጸደ ሥጋም ኾነ በዐጸደ ነፍስ) በጸሎታቸው ለሚታመኑ፣ በቃል ኪዳናቸው ለሚማጸኑ ምእመናን በመጸለይና ወደ እግዚአብሔር በማማለድ ድኅነተ ሥጋ፣ ድኅነተ ነፍስን የሚያስገኙልን የችግር ጊዜ አማላጆቻችንና አስታራቂዎቻችን ናቸው፡፡ ቅዱሳን በጸሎታቸውና በትምህርታቸው ከከበቡን የነፍስ ጠላቶች፤ ከርኲሳን መናፍስትና ከጨለማው ልጆች፤ ከክፉ ሰዎች ሽንገላና ተንኰል ለመሰወርና ለመጠበቅ ከእግዚአብሔር የተቀበሉት ሥልጣን ምን ጊዜም ሲሠራ ይኖራል፡፡ በጻድቃን መኖር አገር ከጥፋት ትድናለች፡፡

የጻድቃንን ስም ጠርቶ እግዚአብሔርን በመለመን በረከትና ረድኤት ይገኛል፡፡ ስለ ጻድቃን ብሎ እግዚአብሔርም ምሕረቱን ያድላል፡፡ እነርሱን ማሰብና ማክበር፣ ሥራቸውንም መዘከር ክርስቲያናዊ ሕይወታችንን ያጐለምሳል፡፡ ለድኅነተ ሥጋ፣ ለድኅነተ ነፍስ ይረባል፤ ይጠቅማል፡፡ ስለዚህም ነው ቅዱስ ወንጌል ቅዱሳን ጻድቃንን እንድናስባቸው፣ በስማቸውም ለድሆችና ለጦም አዳሮች እንድንመጸውት፣ መታሰቢያቸውን እንድናደርግ የሚመክረን፤ የሚያስተምረን (ማቴ.፲፥፵፩-፵፪)፡፡ ከእነዚህ ቅዱሳን መካከልም ኢትዮጵያዊው ጻድቅ አቡነ ተክለ ሃይማኖት አንደኛው ናቸው፡፡

በየዓመቱ ግንቦት ፲፪ ቀን ቅዱስ ሚካኤል ሊቀ መላእክት፣ ኢትዮጵያዊው ንጉሥ እስክንድር፣ ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ፣ ቅዱስ መስቀል፣ ቅዱስ እስጢፋኖስ፣ ቅዱስ ሚናስ፣ የመላልዔል ልጅ ያሬድ እና ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት በቤተ ክርስቲያናችን ይታሰባሉ፡፡ በዛሬው ዝግጅታችን የጻድቁ አባታችንን የፍልሰተ ዐፅም ታሪክ የስማቸውን ትርጕም በማስቀደም እንደሚከተለው በአጭሩ አቅርበነዋል፤

‹ተክል› ማለት ፍሬያማ ዕንጨት፣ ዛፍ፣ ቅመም፣ ቅጠላ ቅጠል፣ የሚበላ፣ የሚሸተት፣ ገነታዊ ዕፅ፣ እንዲሁም ሕግ ሥርዓት ማለት ነው (ኪዳነ ወልድ ክፍሌ፤ ማቴ.፲፭፥፲፫)፡፡ ‹ሃይማኖት› ማለት ደግሞ በሀልዎተ እግዚአብሔር፣ በእግዚአብሔር አምላክነት፣ በሥላሴ አንድነትና ሦስትነት፣ በቅዱሳን ተራዳኢነት ማመን፤ አምኖም መመስከር ማለት ነው፡፡ ‹ተክለ ሃይማኖት› የሚለው ሐረግም የሃይማኖት ተክል፣ ይኸውም የጽድቅ ፍሬን ያፈራና ከኃጢአት ሐሩር ማምለጫ ዛፍ፤ ምእመናንን በቃለ ወንጌል ያጣፈጠ ቅመም፤ መዓዛ ሕይወቱ የሚማርክ፣ ቢመገቡት ረኃበ ነፍስን የሚያስወግድ ቅጠል፤ የጻድቃን መጠለያ ዕፅ የሚል አለው፡፡ መጽሐፈ ገድላቸውም ‹‹ተክለ ሃይማኖት ማለት የአብ፣ የወልድ፣ የመንፈስ ቅዱስ ተክል ማለት ነው›› በማለት የስማቸውን ትርጕም ያትታል፡፡ ጻድቁ አባታችን ተክለ ሃይማኖት በአሚነ ሥላሴ ጸንተው ሌሎችንም እንዲጸኑና እንዲያምኑ አድርገዋልና፡፡

‹‹… ስምዑ ወለብዉ ፍቁራንየ መጽሐፈ ዜናሁ ለክቡር ወቅዱስ ወለብፁዕ ፍቁረ እግዚአብሔር ዘይትነበብ በዕለተ ፍልሰተ ሥጋሁ አመ ፲ወ፪ ለግንቦት ውእቱ ድሙር ምስለ በዓለ ትንሣኤሁ ለእግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ ወበዓለ ሚካኤል ሊቀ መላእክት ፍቁሩ ለተክለ ሃይማኖት፤ ወዳጆቼ ሆይ፣ የከበረ፣ የተቀደሰ፣ የተደነቀ፣ የእግዚአብሔር ወዳጅ የሚኾን የአባታችን የተክለ ሃይማኖትን ክብሩን፣ ገናንቱን የሚናገረውን፤ ዐፅሙ በፈለሰበት ግንቦት ፲፪ ቀን የሚነበበውን መጽሐፍ አስተውላችሁ ስሙ፡፡ ይኸውም ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ የትንሣኤ በዓል እና ከተክለ ሃይማኖት ወዳጅ ከሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል በዓል ጋር የተባበረ ነው …፤›› (ገድለ ተክለ ሃይማኖት ምዕ.፷፪፥፭-፰)፡፡

አቡነ ተክለ ሃይማኖት በ፲፫ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጀመሪያ አካባቢ በአገራችን ኢትዮጵያ ምድር በሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት ኢቲሳ (ደብረ ጽላልሽ) ከአባታቸው ካህኑ ጸጋ ዘአብ እና ከእናታቸው እግዚእ ኀረያ አብራክ የተገኙ ቅዱስ አባት ናቸው፡፡ አባታችን ሕይወታቸዉን ሙሉ ለእግዚአብሔር በመስጠት፣ እንደ በሬ ተጠምደው፣ እንደ ገበሬ ታጥቀው ይህንን ዓለም ንቀው፣ በጾም በጸሎት ተወስነው፣ በብሕትውና ከመኖራቸው ባሻገር እንደ ቅዱሳን ሐዋርያት ወንጌልን በመላው ኢትዮጵያ እየተዘዋወሩ የሰበኩ፣ በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ድውያነ ሥጋን በተአምራት፣ ድውያነ ነፍስን በትምህርት የፈወሱ ሐዋርያ ናቸው፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንም ይህንን ውለታቸውን በማሰብና ከእግዚአብሔር ዘንድ የተሰጣቸውን ቅድስና መሠረት አድርጋ በስማቸው ጽላት ቀርፃ ስታከብራቸው ትኖራለች፡፡

አቡነ ተክለ ሃይማኖት በዚህ ዓለም የኖሩበት ዕድሜ ዘጠና ዘጠኝ ዓመት ከዐሥር ወር ከዐሥር ቀን ነው፡፡ በእናት አባታቸው ቤት ፳፪ ዓመት፤ በከተታ ፫ ዓመት፤ በዊፋት ፱ ወር፤ በዳሞት ፲፪ ዓመት፤ በአማራ ፲ ዓመት፤ በሐይቅ ፲ ዓመት፤ በደብረ ዳሞ ፲፪ ዓመት፤ በትግራይ ገዳማት በመዘዋወርና ወደ ኢየሩሳሌም በመመላለስ ፩ ዓመት፤ ዳዳ በሚባል አገር ፩ ወር፤ በአሰቦ ገዳም ፳፱ ዓመት ከ፲ ቀን መቆየታቸውን መጽሐፈ ገድላቸው ይናገራል (ገ.ተ.ሃ ፶፱፥፲፬-፲፭)፡፡

ጻድቁ አባታችን ምድራዊ ሕይወታቸውን በተጋድሎና በሐዋርያዊ አገልግሎት ከፈጸሙ በኋላ ከዚህ ዓለም ውጣ ውረድ የሚያልፉበት ቀን በተቃረበ ጊዜ ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእናቱ ከቅድስት ድንግል ማርያም፣ ከቅዱሳን መላእክት፣ ከቅዱሳን ነቢያትና ከቅዱሳን ሐዋርያት ጋር ወደ እርሳቸው በመምጣት የሚያርፉበት ዕለት መድረሱን ነግሯቸው፣ የተጋድሏቸውን ጽናት አድንቆላቸው በስማቸው መታሰቢያ ለሚያደርጉ፣ ለነዳያን ለሚመጸዉቱ ቤተ ክርስቲያን ለሚያሠሩ የምሕረት ቃል ኪዳን ሰጥቷቸው በክብር በምስጋና ወደ ሰማይ ዐረገ፡፡

አቡነ ተክለ ሃይማኖትም የዕረፍት ጊዜያቸው መቃረቡን ባወቁ ጊዜም የመንፈስ ልጆቻቸውን ጠርተው ጌታችን የነገራቸውን ዅሉ አስረድተው አባታዊ ምክርና ተግሣፅ ከሰጧቸው በኋላ ነሐሴ ፳፬ ቀን ከዚህ ዓለም ድካም ዐረፉ፡፡ የመንፈስ ልጆቻቸውም ለአንድ ቅዱስ አባትና ካህን በሚገባ ሥርዓት በማኅሌት፣ በዝማሬና በምስጋና ቀበሯቸው፡፡ ጌታችንም ከእመቤታችንና ከቅዱሳን መላእክት ጋር ተገልጾ ታያቸው፤ ነፍሳቸውንም ‹‹የጠራሽ፣ ንጽሕት ነፍስ ሆይ! ወደ እኔ ነዪ›› ብሎ በክብር ተቀበላት፡፡

ወደ ፍልሰተ ዐፅማቸው ታሪክ ስንመለስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ከዚህ ዓለም ውጣ ውረድ ከተለዩ በ፶፯ኛው ዓመት የካቲት ፲፱ ቀን ለመንፈስ ልጃቸው ለአባ ሕዝቅያስ ብርሃን ለብሰው በሕልም ተገለጡላቸውና ‹‹ወዳጄ ሕዝቅያስ ሆይሰላም ለአንተ ይኹን! ጌታዬበኋለኛው ዘመን ከዚህ ሥፍራ ልጆችህ ሥጋህን ያፈልሳሉያለኝ ዘመን ደርሷልና ሳትዘገይ ልጆቼን ዅሉ ቅጠራቸውና እስከምፈልስበት ቀን ድረስ ግንቦት ፲፪ ቀን ይሰብሰቡ፡፡ እናንተም በምስጋና በጸሎት መንፈሳዊ በዓልን አድርጉ፡፡አባቴ ተክለ ሃይማኖትየሚለኝ ዅሉ በዚህች በፍልሰተ ዐፅሜ ቀን ይምጣ፤ መንፈሳዊ በዓልንም ያድርግ፡፡ እኔና ቅዱስ ሚካኤል ከወዳጄ አባ ፊልጶስ ጋር ስለ እኔ ፍቅር የተሰበሰበውን ሕዝብ ልንባርክ እንመጣለን፤›› ከአሏቸው በኋላ ተሠወሯቸው፡፡

አባ ሕዝቅያስም እንደ ታዘዙት ‹‹የአባታችሁን ዐፅም ከዋሻው ወደ ታላቁ ቤተ ክርስቲያን ታፈልሱ ዘንድ ኑ፤ ተሰብሰቡ›› ብለው የአባታችን ወዳጆች ባሉባቸው አገሮች ዅሉ መልእክት ላኩ፡፡ ምእመናንም ጥሪውን ተቀብለው በዓሉን ለማክበር ከአራቱም አቅጣጫ ተሰበሰቡ፡፡ ዐሥራ ሁለቱ መምህራንም መጡ፤ እነዚህም፡- የወረብ አገሩ አባ አኖሬዎስ፣ የፈጠጋሩ አባ ማትያስ፣ የእርናቱ አባ ዮሴፍ፣ የሞረቱ አባ አኖሬዎስ፣ የመርሐ ቤቴው አባ መርቆሬዎስ፣ የጽላልሹ አባ ታዴዎስ፣ የወገጉ አባ ሳሙኤል፣ የወንጁ አባ ገብረ ክርስቶስ፣ የድንቢው አባ መድኃኒነ እግዚእ፣ የዳሞቱ አባ አድኃኒ፣ የክልአቱ አባ ኢዮስያስ እና የመሐግሉ አባ ቀውስጦስ ናቸው፡፡

እነዚህ መምህራን ከአባ ሕዝቅያስ ጋር በመኾን የአቡነ ተክለ ሃይማኖትን ዐፅም ከዐረፈበት ዋሻ ባወጡት ጊዜ ዐፅማቸው ዕለት የተገነዘ በድን ይመስል ነበር፤ መዓዛውም ሽቱ፣ ሽቱ ይሸት ነበር፡፡ በአባታችን ዐፅም ቀኝና ግራም መስቀል ተተክሎ ነበር፡፡ በዐፅማቸውም ብዙ ድንቅ ተአምራት ተደርገዋል፡፡ ይህንን የአባታችንን ዐፅም አባ ሕዝቅያስና ዐሥራ ሁለቱ መምህራን በሣጥን አክብረው ወደ ቤተ ክርስቲያኑ ወስደው በመንበሩ ፊት ሦስት ጊዜ አዞሩት፡፡

በዚህች ዕለት አስቀድመው የካቲት ፲፱ ቀን ለአባ ሕዝቅያስ በሕልም እንደ ነገሯቸው ብፁዕ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ከቅዱስ ሚካኤልና ከአባ ፊልጶስ ጋር ወደ ቤተ ክርስቲያኑ መጥተው ዐፅማቸው እስኪያረፍ ድረስ ከመንበሩ ተቀምጠው ቆይተው ዐፅማቸው ካረፈ በኋላ የተሰበሰበውን ሕዝብ ባርከው በክብር ወደ ሰማይ ዐረጉ፡፡ መምህራኑና ምእመናኑም በዓሉን በታላቅ ደስታ አክብረው በሰላም ወደየቤታቸው ተመለሱ፡፡ በዘመኑ የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ፍልሰተ ዐፅም በዋለበት ዕለት ርክበ ካህናትም አብሮ መከበሩ በዓሉን ልዩ ድምቀት ሰጥቶት እንደ ነበር በመጽሐፈ ገድላቸው ተገልጿል፡፡ ከዚያን ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በታላቁ ገዳም በደብረ ሊባኖስ ቅዱሳን ፓትርያሪኮች፣ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳትና በርካታ ምእመናን እየተሰበሰቡ በዓሉን በድምቀት ያከብራሉ (ገ.ተ.ሃ ፷፭፥፩-፳፬)፡፡

የብፁዕ አባታችን ዐፅም በፈለሰበት ዕለት ዐሥራ ሁለቱ መምህራን እና በርካታ ምእመናንን እንደ ተሰበሰቡ ዅሉ እኛንም እግዚአብሔር አምላካችን በኢየሩሳሌም ሰማያዊት ይሰብስበን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ምንጭ፡

  • መጽሐፈ ስንክሳር፣ ግንቦት ፲፪ ቀን፡፡
  • ገድለ ተክለ ሃይማኖት፣ ፲፱፻፹፱ .ም፤ አዲስ አበባ፡፡