«ጸልዩ በእንተ ሰላም፤ስለ ሰላም ጸልዩ» (ሥርዓተ ቅዳሴ)

ሐመር  መጽሔት   26ኛ ዓመት ቊጥር 2፤ ሰኔ 2010 ዓ.ም

                                                                                                                                              በዲ/ን ታደለ ሲሳይ

ዓለም የሚሻት፤እርሷም ለዓለም የምታስፈልገው አንዲት ነገር አለች፡፡ያለ እርሷ በዓለም መኖር አይቻልም፡፡ በዓለም መኖር ብቻም ሳይሆን ሰማያዊ ርስትን መውረስም አይቻልም፡፡ስለ ሰላም ሲነገር ቃሉ ይጣፍጣል፤ ስለ ሰላም ሲሰማ ዕዝነ ልቡና ይረካል ሰላም  የተቅበዘበዙትን ታረጋጋለች፤ያዘኑትን ታስደስታለች፤ ጦርነትን ወደ ፍቅር ትለውጣለች፡፡ሰላም በፍለጋ ብቻ የምትገኝ ሳትሆን በተግባር የምትተረጎም ናትና በሰላም የኖሩት ሰላምን በተግባር ያረጋገጡ ብቻ ናቸው፡፡ ምክንቱም ሰላም ተግባራዊ ናትና፡፡ሰላምን በተግባር ለማዋል ደግሞ ሰላምን መሻት ቅድሚያ የሚሰጠው ነው፡፡«ለምኑ ይሰጣችሁማል፤ፈልጉ ታገኙማላችሁ»እንዲል(ማቴ.7÷7፣ ሉቃ. 11÷9) ስለ ሰላም ምሁራን ጽፈዋል፤ ተርጓምያን አመሥጥረዋል፤ ባለ ቅኔዎች ቅኔ ተቀኝተዋል፤ የመዝገበ ቃላት ምሁራን ብያኔ ሰጥተዋል፡፡

ለአብነትም ኪዳነ ወልድ ክፍሌ በመዝገበ ቃላቸው ላይ ሰላም ማለት«ፍጹም፣ ጤና፣ ዕረፍት፣ ዕርቅ፣ ፍቅር፣ አንድነት፣ ደኅንነት፣ ተድላ፣ ገጽታ፣ሰላምታ፣ የቡራኬ የምርቃት ቃል፣ ሰው ሲገናኝ ሲለያይ የሚለው የሚናገረው ወይም የሚጽፈው ማለት ነው» ብለው ቃላዊ ትርጉሙን አስቀምጠውታል፡፡ (መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ ገጽ-888)

ከላይ በተዘረዘረው የመዝገበ ቃላት ትርጉም መሠረት ሰላም ማለት ሁሉም ነገር ነው፡፡ሰላም ያለው ሰው ፍቅር አለው፤ሰላም ያለው ሰው ዕረፍት አለው፤ጤና አለው፤ ደኅንነት አለው፡፡ ሰላም ያለው ሰው ሁሉም ነገር አለው፡፡ ከላይ የተዘረዘሩትን የሕይወት ቁልፍ ነገሮች ማግኘት የሚቻለው በሰላም ነው፡፡ ሰላም ከሌለ ደግሞ እነዚህ ነገሮች ሁሉ አይገኙም፡፡እነዚህ የሕይወት ቁልፍ ነገሮች ከሌሉም ጽድቅ ትሩፋት አንድነት አይኖርም፡፡ከላይ የተዘረዘሩትን ነገሮች ለማግኘት ሰላምን መሻት፣በሰላም መኖር ያስፈልጋል፡፡ ለዚህም ነው«ቢቻላችሁስ በእናንተ በኩል ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ» በማለት ቅዱስ ጳውሎስ የሚያስተምረን (ሮሜ12÷18) በሰላም መኖር ካልቻልን ሕይወታችን የክርስቶስን መስቀል ተሸክሟል ለማለት እንቸገራለንና የሐዋርያው ቃል እውነት አለው፡፡የቅዱስ ጳውሎስ መልእክት እንደሚያስረዳን የሰው ልጅ ሲኖር ከእገሌና ከእገሌ ጋር ብቻ ብሎ ሳይሆን ከማንኛውም ሰው ጋር በሰላም መኖር ክርስቲያናዊ መገለጫው፣ክርስቲናዊ ሥነ ምግባሩ ነው፡፡ሰላም ውስጣዊና ውጫዊ እንደመሆኑ፣ውስጣዊ ሰላምን የምናገኘውም ከላይ ቅዱስ ጳውሎስ እንዳለው ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም መኖር ስንችል ብቻ ነው፡፡ከሰው ጋር ሰላም ከሌለን ሰላማችንን የምናጣው ከሰዎች ጋር ባለን ማኅበራዊ ግንኙነት ብቻ አይደለም፤ከልደታችን እስከ ሞታችን ድረስ አብሮን በሚኖረው ማንነታችንም ውስጥ ነው፡፡ ከሰው ጋር ብቻ ሳይሆን ከራሱ ጋር ተጣልቶ የሚባዝን፣ለራሱ ሰላምን የነሣ ብዙ ሰው አለና ሰላምን መሻት፣ ሰላማዊ መሆን ከራስ ጋር በመታረቅ ይጀመራል፡፡

አባቶቻችን ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንም ሆኑ ቅድስት ሀገር ኢትዮጵያን እየመሩ የቆዩ ታላላቅ የሀገር መሪዎች ሃይማኖትን ጠብቀው፣ዳር ድንበርን አስከብረው፣ሃይማኖትንና ሀገርን ከዚህ ማድረስ የቻሉት በሰላም ነው፡፡ያለ ሰላም ዛሬን ውሎ ነገን መድገም አይቻልም፡፡በሰላም ግን ትናንትን ማስታወስ፣ዛሬን ማስተዋል፣ነገን ደግሞ ተስፋ ማድረግ ይቻላል፡፡ሰላም ባለበት ሞት የለም፤ሰላም በሌለበት ግን ውድቀት አለ፡፡ሰላም ያለው ለሚሠራው ለሚያደርገው ለሚኖረው ሁሉ ድፍረት አለው፤ሰላም የሌለው ሰው በፍርሀት ወጀብ ሲናወጥ ይኖራል፡፡ ለዚህም ነው በሰላም ያለ ሰው መፍራትና ሞት እንደሌለበት ቅዱስ መጽሐፍ የተናገረው፡፡ (መሳ.6÷23)

 ከሰላም የምናገኘው ጥቅም ምድራዊ ብቻ እንዳልሆነም ቅዱስ መጽሐፍ ያስረዳናል፡፡ሰማያዊ ርስታችን ገነት መንግሥተ ሰማያት የምንወርሰው በሰላም ነው፡፡ሰላም ያለው ሰው ጽድቅን ይሠራል፡፡ጽድቅን የሚሠራም ሰላም አለው፡፡ሰላም ያለው ሰው ለድሆች ይራራል፤ለድሆች የሚራራም ሰላም አለው፡፡ ሰላም ያለው ሰው በማቴ 25 ላይ እንደተጠቀሰው ለተራበ ያበላል፤ ለተጠማ ያጠጣል፤ ለታረዘ ያለብሳል፤ የታሠረ ይጠይቃል፡፡ በዚህም ሥራው በትንሣኤ ዘጉባኤ ትንሣኤ ዘለክብርን ያገኛል፡፡ሰላም የሌለው ሰው ደግሞ በተራበ ይጨክናል፤ ለተጠማ አያዝንም፤ የታመመ አይጠይቅም፤የታረዘ አያለብስም፤በዚህም ምክንያት በትንሣኤ ዘጉባኤ ትንሣኤ ዘለኀሣርን ያገኛል፡፡(ማቴ35÷42) ከዚህ ላይ እንደምንረዳው ሰላም የብፅዕና የጽድቅ መንገድ መሆኗን ነው፡፡ለዚህም ነው«ብፁዓን ገባርያነ ሰላም፤ሰላምን ዕርቅን የሚያደርጉ ብፁዓን ናቸው» ተብሎ ሰላምን ዕርቅን ማድረግ ብፅዕና መሆኑ የተገለጠልን (ማቴ.5÷9)

በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን አውታሮች እንደምንገነዘበው በተለያዩ ጊዜያት ዓለም በሰላም እጦት ስትናጥ ቆይታለች፡፡በዚህም የተነሣ ብዙ ሰው ሠራሽ ንብረቶች ከማለቃቸው በተጨማሪ እጅግ ክቡሩና በአምሳለ እግዚአብሔር የተፈጠረው የሰው ልጅ እንደ ተራ ነገር በየሜዳው ወድቆ ቀርቷል፡፡ለዚህም በአንደኛውና በሁለተኛው የዓለም ጦርነት በዓለማችን ላይ የደረሰው ኪሳራ ማሳያ ነው፡፡በሀገራችንም በተለያዩ ጊዜያት በሥልጣን፣በሃይማኖትና በተለያዩ ምክንያቶች ብዙ የሰው ሕይወት ተቀጥፏል፡፡ በጣሊያን ጦርነት፣በእንግሊዝ ወረራ፣በግራኝ አሕመድ ሃይማኖታዊ ጥቃት፣ በዮዲት ጉዲት ዐመፅ በርካታ የሰው ልጅ ተቀጥፏል፤በሰላም ተከፍተው የነበሩ በሮች በሞት ተዘግተዋል፡፡ምድራችን በደም ታጥባለች፣አረጋውያን ያለ ጧሪ ቀባሪ ቀርተዋል፤ሕፃናት ያለ አሳዳጊ ብቻቸውን ሆነዋል፡፡ 

በየቤታችን በየጓዳችን ስንመለከት እንኳን ተኳርፎ፣ተበጣብጦ፣ፍቅርን አጥቶ የሚያድረው ብዙ ነው፡፡ይህ ሁሉ አለመረጋጋትና መባዘን የሚመጣው በሰላም ማጣት ብቻ ነው፡፡ያለ ሰላም መኖር እንቅልፍ መተኛት እንኳን አይቻልም፡፡ሰላም ያለው ሰው ግን በእግዚአብሔር ተባርኮ ሰላም እንቅልፍ መተኛት ይችላል፤ በሰላም ወጥቶ በሰላም ይገባል፡፡የሰው ልጅ በእምነት ኖሮ፣ ሠርቶ የሚገባው፣አንቀላፍቶ የሚነሣው ሰላም ሲኖረው ብቻ ነው፡፡«በሰላም እተኛለሁ አንቀላፋለሁም፤አቤቱ አንተ ብቻህን በእምነት አሳድረኸኛልና» እንዲል (መዝ 4÷8)

ፍቅር በሰው ልጆች እንዲሠርጽ፣ መግባባት እንዲኖር፣መረዳዳትና መከባበር እንዲመጣ በመንፈሳዊ ተቋማት በሓላፊነት የሚገኙ ሰዎች ሰላምን ማስተማር አለባቸው፡፡መሪዎች የሰላም አክባሪ ሲሆኑ ተመሪው ሕዝብ ሰላምን ይከተላል፡፡የሃይማኖትና የቤተ እምነቶች መሪዎችና አባቶች የሰላም ሰባኪ ሲሆኑ ምእመናን(የእያንዳንዱ ቤተ እምነት ተከታይ)የሰላም ባለቤት ይሆናሉ፡፡ተመሪ ሁልጊዜም ቢሆን መሪውን ያያል፡፡ ሰላማዊ መሪ እንደ ሙሴ ባሕር ከፍሎ ሕዝቡን ያሻግራል፡፡ሰላም የሌለው መሪ ደግሞ እንደ ፈርዖን እስከ ሠራዊቱ ይሰጥማል፡፡ሕፃን የእናት የአባቱን የታላላቆቹን አርአያ ይዞ እንደሚያድግ ሕዝብም መሪዎቹን፣አባቶቹን ይከተላል፡፡የሃይማኖት አባቶች የሰላም ሰባኪ ሳይሆኑ ሰላማዊ ምእመናንን አፍርቶ ማለፍ ቀላል አይደለም፡፡ የተከፋፈለ መሪ የተከፋፈለ ሕዝብን ያፈራልና፡፡

ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ደግሞ ሁልጊዜም ቢሆን «ጸልዩ በእንተ ሰላም፤ስለ ሰላም ጸልዩ» እያለች ለሁሉም ሰላም እንደሚያስፈልግ ከሰበከች በኋላ፣ለቅድስት ቤተ ክርስቲንም ሰላም እንደሚሻት ስታስተምር«ጸልዩ በእንተ ሰላመ ቤተ ክርስቲያን ስለ ቤተ ክርስቲያን ሰላም ጸልዩ» እያለች ልጆቿን ትመክራለች (ሥርዓተ ቅዳሴ) ይሁን እንጂ በሰላም ማጣት ምክንያት እንደ እናት ቤተ ክርስቲያን የችግር ገፈት ስንቀምስ መቆየታችን የቅርብ ጊዜ ትዝታ ብቻ ሳይሆን አሁን ያለው እውነታ ነው፡፡

ሰላምን የምታስተምር ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ኵላዊት ናትና ለዓለም ሁሉ የሰላም አርአያ ልትሆን እንደሚገባ ሁሉንም አካል የሚያስማማ ነው፡፡የቤተ ክርስቲያን ሰላም የሚታየው ደግሞ በእኛ በልጆቿ ነው፡፡ነገር ግን በውስጣዊም ይሁን በውጫዊ ምክንያት የእኛ የልጆቿ ሰላም ሲደፍርስ የቅድስት ቤተ ክርስቲያንም ሰላም ይደፈርሳል፡፡

ቅድስት ቤተ ክርስቲናችን ሓላፊነትን የሰጠቻቸው ብፁዓን አበው በጸሎታቸው ለቅድስት ቤተ ክርስቲንና ለሀገር፣በአስተዳደራቸውና በትህርምትነታቸው ደግሞ ለእኛ ለልጆቻቸው አርአያ የሚሆኑን፣ቡራኬን የሚሰጡን የምንባረክባቸው የእግዚአብሔር ስጦታዎቻችን ናቸው፡፡

እግዚአብሔር እነርሱን የሰጠንም ፈጥሮ ስለማይተወን፣እንድንበዛ መንግሥቱን እንድንወርስ፣ እንዳንጠፋ፣እንዳንናወጽ፣እንድንረጋጋ፣በሰላም እንድንኖር፣ በመጨረሻም መንግሥቱን እንድንወርስ ስለሚፈልግ ነው፡፡«ኢየኀድጋ ለሀገር ዘእንበለ አሐዱ ሔር፤ያለ አንዳች ቸር ደግ አስተማሪ ሰው ሀገርን እንዲሁ አይተዋትም»እንዲል መጽሐፍ፡፡ከዚህ በተጨማሪም ለምድራችንና ለሕዝባችን አባቶቻችን እንደሚያስፈልጉን«ኢኀደጋ ለምድር እምቅድመ ዓለም ወእስከ ለዓለም ዘእንበለ ካህናት ወዲያቆናት፤ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ እስከ መጨረሻው ድረስ ምድርን ያለ ካህናትና ዲያቆናት አይተዋትም»በማለት ይናገራል (ኅዳር ጽዮን ዋዜማ) ይሁን እንጂ ኢየሱስ ክርስቶስን በገዳመ ቆሮንቶስ በሦስቱ አርእስተ ኃጣውእ ለመፈተን ኀፍረት ያልተሰማው ጠላት ዲያብሎስ አባቶቻችንንም የተለያዩ ምክንያቶችን መሠረት በማድረግ ለመፈተን ሞክሯል፡በመረጃ የተወገዙ መናፍቃንም ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን እንደ መጠለያ በመጠቀም  ሕዝቡን አውከዋል፤ ቤተ ክርስቲያንንም እየበጠበጡ ይገኛሉ፡፡

በተለያዩ ጊዜያት አባቶቻችንን አንድ ለማድረግና ቅድስት ቤተ ክርስቲያንንም ከመከፋፈል ለመታደግ በተደረገው ጥረት እንኳን ድብቅ ዓላማቸው እንዳይሰናከል ለማድረግ የዕርቁን ሂደት ሲያሰናክሉ መቆየታቸው የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡ለእነርሱ የዓላማ መሳካትም ሆነ ለምእመናን መበታተን የዕርቀ ሰላሙ አለመሳካት ወሳኝ ነውና በሁለቱም (በሀገር ውስጥም  በውጭም)  በሚገኙ መካከል  ዕርቀ ሰላሙን የማይደግፉ አካላት መኖራቸው የማይካድ ነው፡፡የእነዚህን አካላት ዓላማ ተረድቶ ቅድሚያ ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን አንድነትና ልዕልና መቆም ከብፁዓን አበው ጀምሮ የእያንዳንዳችን ምእመናን ድርሻ ነው፡፡

ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በቅዳሴዋ በወንጌሏ፣ በእያንዳንዱ የወንበር ትምህርቷ ሰላምን ታስተምራለች፤ልጆቿን«ጸልዩ በእንተ ሰላመ ቤተ ክርስቲያን አሐቲ ቅድስት ጉባኤ እንተ ሐዋርያት ርትዕት በኀበ እግዚአብሔር፤ የሐዋርያት  ጉባኤ ስለሆነችው በእግዚአብሔር ዘንድም ርትዕት ስለሆነችው አንዲት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ጸልዩ» እያለች ማስተማሯ ማዘዟ ለሰላም ያላትን አቋም ያመለክታል (ሥርዓተ ቅዳሴ) ስለ ቤተ ክርስቲያን ሰላም መጸለይ ስለ ምእመናን ስለ ሕዝብ መጸለይ ነው፡፡ስለ ሕዝብ መጸለይ ደግሞ ስለ ሀገር መጸለይ ነው፡፡የቤተ ክርስቲያንን ሰላም መሻት የአንድን ምእመን ሰላም መሻት ነው፤ቤተ ክርስቲያን ማለት የምእመናን ኅብረትና እያንዳንዱን አማኝ የሚመለከት ነውና፡፡ለዚህም ነው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ለሁሉም ድኅነትና ሰላም የምትጸልየው፡፡ሌላው ይቅርና ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ስለ እናት ሀገራቸው ሲሉ በየበረሃው ያሉ ሀገር ጠባቂዎችን የማትዘነጋ ርኅሩኅ እናት ናት፡፡ለዚህም ነው«ዕቀብ ሕዝባ ወሠራዊታ ለሀገሪትነ ኢትዮጵያ፤የኢትዮጵያ ሀገራችንን ሕዝቦቿንና ሠራዊቷን ጠብቅላት» እያለች በዘወትር የቅዳሴ ሥርዓቷ የምትጸልየው፡፡

እግዚአብሔር አምላክ ቅድስት ቤተ ክርስቲንን በደሙ ሲመሠርታት ጠብን ጥልን ክርክርን በሞቱ ገድሎ፣በደሙ አንጽቶ ነው፡፡ይህ ለዓለም ሰላም የተከፈለ ዋጋ፣ለድኅነታችን የተሰጠ ሥጦታ፣ ለሰላም የተጠራንበት መንገድ ነው፡፡ አይሁድ ክርስቶስን በጥላቻ ቢሰቅሉትም እርሱ ግን የተሰቀለው ለሰላም ነው፡፡አይሁድ ክርስቶስን በጥላቻ ቢገርፉትም እርሱ ግን በትሕትና የተገረፈው ሰላምን ለማምጣት ነው፡፡የተቅበዘበዘው፣ሰላም ያጣው፣በሞት ጥላ ሥር የነበረው ዓለም፤መዳንንና ሰላምን የሚያገኘው በክርስቶስ ሞት በክርስቶስ መስቀል ነበርና፡፡ለዚህም ነው የቤተ ክርስቲያን ብርሃን የሆነው ቅዱስ ያሬድ«ገብረ ሰላመ በመስቀሉ፤በመስቀሉ ሰላምን አደረገ» በማለት የተናገረው (መጽሐፈ ድጓ)

ይህ ሁሉ ዋጋ የተከፈለለትን ሰላም በተግባር አለመኖር ዋጋ ያስከፍላል፡፡ በክርስቶስ ሞት የተሰጠንን ሰላም በከንቱ መጣል የክርስቶስን ዋጋ እንደ ማቃለል ይቆጠራል፡፡ ክርስቶስ በመስቀሉ ለዓለም የሰጠውን ሰላም ገንዘብ አለማድረግ የመስቀሉን ስጦታ አለመቀበል ነው፡፡ በቅዱስ መጽሐፍ እንደተገለጠው የተጠራነው በፍቅር በሰላም ልንኖር ነውና ሰላም ገንዘባችን ሊሆን ይገባል (1ኛቆሮ7÷15)

«ወንድሞች ሆይ በመካከላችሁ የሚደክሙትን በጌታም የሚገዟችሁን የሚገሥጿችሁንም ታውቁ ዘንድ ስለ ሥራቸውም በፍቅር ከመጠን ይልቅ ታከብሯቸው ዘንድ እንለምናችኋለን፡፡ እርስ በርሳችሁ በሰላም ኑሩ»እንዳለው ሰዎችን በሥራቸው እያከበርን፣ ግሣጼንና ምክርን እየተቀበልን፣ከጥፋታችን እየታረምን በሰላምና በፍቅር መኖር ይጠበቅብናል(1ኛተሰ.5÷12) ይህንን ስናደርግ በሰላም መኖራችን ዕረፍት ያሳጣቸው አካላት ቢኖሩ እንኳን እኛ የሰላምን ጥሪ ማዳመጥ፣ የሰላምን ደወል መስማት፣መንገዷንም መከተል ይገባናል፡፡ይህ ሲሆን ነው ራሳችን ወድደን ዓለምንም በፍቅር ልናሸንፍ የምንችለው፡፡

በሰላም የማይኖር ሰው ዓለምን ማሸነፉ ይቅርና አባቱን ሊያከብር እናቱንም ሊወድ አይችልም፡፡ ሰላም የሌለው ሰው ወንድሙን ሊወድ  እኅቱንም ሊያስደስት አይችልም፡፡ ሰላም የሌለው ሰው ቤተሰብ መሥርቶ ሊያስተዳድር፣ ሀገርንም ሊመራ አይችልም፡፡ሌላው ይቅርና ሰላም የሌለው ሰው ራሱን ይወድ ዘንድ ከራሱ ጋርም በሰላም ይኖር ዘንድ አይቻለውም፡፡ሰላም የፍቅር እናት፣ የአብሮነት ምሰሶ፣የጽድቅ መንገድ፣ የመከባበር ምዕራፍ ናትና፡፡

በመሆኑም ከሕፃን እስከ ዐዋቂ፣ከሊቅ እስከ ደቂቅ፣ ከመምህሩ እስከ ደቀ መዝሙሩ ስለ ሰላም ማሰብ ማስተማርና መኖርን ገንዘብ ማድረግ ይገባል፡፡ቤተ ክርስቲያንን እንዲመሩ ሥልጣኑን ከእግዚአብሔር የተረከቡ አበው፣ካህናት፣ዲያቆናትም ሰላምን ለምእመናን እየሰበኩ እያስተማሩ፣ በሰላም መኖርን ለሚሻው ሕዝባቸው ሰላምን ማብሠር አለባቸው፡፡ባለፉት ጊዜያት በጠላት ዲያብሎስ ሴራ የነበረውና ብዙዎቻችንን አንገት ያስደፋው ሰላም ማጣት ሊጠፋ የሚችለው ሰላምን በተግባር በመተርጎም ብቻ ነውና ይቅር መባባል፣ጥፋትን ማመን፣ባለፈው ጥፋት መጸጸት፣ስለ ቀጣዩ ሰላም ማሰብ፣ አንድነትን መናፈቅ፣ስለ አንድነት መቆም፣የቤተ ክርስቲያንን ልዕልና መጠበቅ ይገባል፡፡ ይህ የሰላም ጉዳይም ለእገሌ ብቻ ተብሎ የሚተው ሳይሆን በተለያዩ አካላትና መዋቅሮች ከሚገኙ ሰዎች ሁሉ የሚጠበቅና ሊተገበር የሚገባው ነው፡፡

    ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የሰላም እመቤት የሰላም ተምሳሌት ናት፡፡የራሷን ሰላም አስከብራ ለሌሎችም አርአያ በመሆን ዘመናትን አሳልፋለች፡፡ነገር ግን ዘመናትን ባሳለፈች ቊጥር በሰላም ፈላጊነቷ የማይደሰተው ጠላት ዲያብሎስ ሁልጊዜም ቢሆን ሰላሟን ለመንሳት ተኝቶ አያውቅም «የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በየዘመኑ የተለያዩ ፈተናዎች የተፈራረቁባት ሲሆን ቤተ ክርስቲያኒቱ የእግዚአብሔር ማደሪያ ናትና የመጣውን የፈተና ጎርፍና ነፋስ ሁሉ ተቋቁማ  አሁን ላለንበት ዘመን ደርሳለች፡፡ የዐላውያን ገዥዎችን ሰይፍ፤ ከውስጥም ከውጭም የነበሩ መናፍቃንን ቅሰጣ ተሻግራ እስከ አሁን የሐዋርያት፣የቅዱሳን ሊቃውንትን የአትናቴዎስን ፣የቄርሎስን ሃይማኖት ይዛ ተገኝታለች» ተብሎ የተጻፈውም ለዚህ ነው (ሐመር 25ኛ ዓመት ቊጥር5) ይህ የሚያሳየው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በተለያዩ የፈተና ወጀቦች ስትታመስ ብትኖርም የሰላም መርከብ ናትና አለመውደቋን ነው፡፡

እንደሚታወቀው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በግብጽ ቤተ ክርስቲያን ሥር ሆና ለበርካታ ዓመታት የራሷ መንበረ ፓትርያርክ ሳይኖራት፣የራሷን ፓትርያርክ፣የራሷን ኤጲስ ቆጶሳት ሳትሾም ቆይታለች፡፡ነገር ግን ከአንድ ሺህ ስድስት መቶ ዓመታት በኋላ በአባቶቻችን ጥረት ፈቃደ እግዚአብሔር ተጨምሮበት ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን የራሷን መንበረ ፓትርያርክ አቋቁማ የራሷን ኢትዮጵያዊ ፓትርያርክ መርጣ፣ ከራሷ ልጆች ኤጲስ ቆጶሳትን ሾማ መገልገል ጀመረች፡፡ይሁን እንጂ፣በ1983 ዓ.ም የገጠማት የመከፋፈል አደጋ ለአገልግሎቷ እጅግ እንቅፋት ሆኖ ቆይቷል፡

  ይህ መከፋፈል አገልግሎቱን በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ለማዳረስ ትልቅ እንቅፋት የሆነ ከመሆኑም ባሻገር የቤተ ክርስቲያንን ተሰሚነትም እጅግ የተፈታተነ ነበር፡፡ከዚህም አልፎ በካህናትና በካህናት መካከል፣እንዲሁም በምእመናን መካከል አለመግባባትን፣ጥላቻን ፈጥሯል፡፡ ይህንን ችግር ለመቅረፍ በተለያዩ ጊዜያት ለቤተ ክርስቲያን ሰላም የሚቆረቆሩ አካላት ዕርቅ ለመፍጠርና አንድ ለማድረግ ቢጥሩም፣የቤተ ክርስቲያንን አንድነት የማይፈልጉ አካላት ለእነዚህ ዕርቅ ፈላጊዎች ከግብራቸው ጋር የማይስማማ ስም በመስጠት፣በማሸማቀቅ፣ጉዳዩን ከፖለቲካ ጋር በማያያዝ የታሰበው እንዳይሳካ ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡

አሁን ደግሞ እንደ እግዚብሔር ፈቃድ በአባቶች  ይሁኝታን አግኝቶ የተቋቋመው የሰላምና የአንድነት ጉባኤ ሥራውን በአግባቡ እየተወጣ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡በሀገር ውስጥም በውጭም በሚኖሩ አባቶች መካከልም ጥሩ ተቀባይነትና ፍላጎት እንዳገኘም«…ከአንድ ዓመት በላይ ባደረገው ጥረት ከወትሮው በተለየ ሁኔታ በኹለቱም ወገን አባቶች ዘንድ ለዕርቁ ተፈጻሚነት ከፍተኛ መነሣሣትና አበረታች ምላሽ እየታየ ሲኾን ሒደቱም በጥሩ ኹኔታ ላይ ይገኛል»በማለት በመግለጫው ላይ አሳውቋል (የሰላምና የአንድነት ጉባኤው መግለጫ ሰኔ 1 ቀን፣2010 ዓ.ም)

ይህ ሒደት የቤተ ክርስቲያንን አንድነት ለሚናፍቁ ሰዎች እጅግ የሚያስደስትና ተስፋ ሰጭም ነው፡፡ይሁን እንጂ አሁንም ቢሆን ይህ ዕርቅና ሰላም የማያስደስታቸው አካላት መኖራቸውን መዘንጋት ሞኝነት ነው፡፡ በተቃራኒው ቆመው ዕርቁን ለማደናቀፍ ደፋ ቀና የሚሉ አካላት በውስጥም በውጭም መኖራቸው እሙን ነውና ይህ መልካም ጅምር ከፍጻሜ እንዲደርስ የሁላችንም ጸሎትና ልመና ያስፈልጋል፡፡በውስጥም በውጭም ላሉ አባቶቻችን ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን ያላቸው ቅንነትና ተቆርቋሪነት የማይካድ ሐቅ ቢሆንም፣ይህንን ተቆርቋሪነታቸውን ደግሞ በዕርቅና በአንድነት እንዲያጠነክሩት የሁሉም ምእመናን ፍላጎትና ምኞት ነው፡፡

ዕርቁንና ሰላሙን በጉጉት እየጠበቀ ያለው ሕዝበ ክርስቲያን ስጋቱም በዚያው ልክ ነውና ሰርጎ ገቦች ገብተው እንዳይበጠብጡ ከሁለቱም ወገን ጥንቃቄን ይሻል፡፡ ይህ ስጋት የሕዝበ ክርስቲያኑ ብቻ ሳይሆን ዕርቀ ሰላሙን እያካሄደ ባለው አካልም ያለ እውነታ ነው፡፡ የሰላምና የአንድነት ጉባኤውም «በሁለቱም ወገን ያላችሁ አባቶች የዕርቀ ሰላሙን ሒደት በተመለከተ የምትሰጡት መግለጫ ሓላፊነት በተሞላበትና በጥንቃቄ እንዲኾን አበክረን እንማጸናለን፡፡ ምክንያቱም የተለያዩ አካላት ቃላትን በቅንነት ከማየት ይልቅ ከጭብጡ ውጭ በመተርጎም የተዛባ አመለካከት እንዲፈጠር ማድረግ ላይ የሚያተኩሩ ስለሆነ የቃላት አገላለጹ በራሱ ለድርድሩ እንቅፋት እንዳይሆን በመስጋት ነው»በማለት አባቶች እጅግ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ተማጽኗል (የሰላምና የአንድነት ጉባኤው መግለጫ፣ሰኔ 1፣ 2010 ዓ.ም)

በመሆኑም ብፁዓን አበው የማንንም ወገን የመከፋፈል ሥራ ወደ ጎን ትተው ለዕርቁ ቅድሚያ በመስጠት ቤተ ክርስቲንንና ልጆቻቸውን አንድ ማድረግ፣ምእመናን በጉጉት የሚጠብቁትን ዕርቅ በተግባር ማሳየት፣የጠላት ዲያብሎስን የጥፋት ወጥመድ መሰባበርና ለቆሙላት ቤተ ክርስቲያን ቀኝ እጅ በመሆን ፍጻሜውን እንዲያሳዩን ምኞታችን ነው!

በሁለቱም ወገን የምንገኝ ምእመናንም ዓላማችን አንድ ብቻ እንደሆነ መዘንጋት የለብንም፡፡ የክርስቲያን ዓላማው ሁከትና ብጥብጥ፣ምድራዊ ድሎትና ምድራዊ ምቾት አይደለም፡፡ ሁላችንንም አንድ የምታደርገን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ደግሞ የተመሠረተችው በክርስቶስ ደም ነው፡፡የምታስተምረንም ዘለዓለማዊ መንግሥትን እንጂ ይህንን ኀላፊውን ዓለም እንድንወርስ አይደለም፡፡በመሆኑም የሁላችንም ዓላማ ሰማያዊ መንግሥትን ወርሰን መኖር መሆኑን ለአፍታ እንኳን መዘንጋት የለብንም፡፡

በትንሣኤ ዘጉባኤም የምንጠየቀው ምን ሠራችሁ እንጂ የማን ደጋፊ ነበራችሁ የሚል አይደለም፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን ልኮ በደሙ አንድ አድርጎናልና እግዚአብሔር ለሰጠን አንድነት መቆም መጽናት አለብን፡፡ለአባቶቻችን ቅርበት ያለን አካላትም ለዕርቁ እንቅፋት ከመሆን ይልቅ በታየንና በተገለጸልን መጠን ከአባቶቻችን እግር ሥር ቁጭ ብለን መልካሙን መንገድ መጠቆም ይጠበቅብናል፡፡ዛሬ መሠረት የምንጥልለት አንድነት ለልጆቻችን ሕይወትና ለነገዋ ቤተ ክርስቲያን ጥንካሬ ወሳኝ ነው፡፡በመሆኑም በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የክፍፍሉ ቀጥተኛም ሆነ ኢ-ቀጥተኛ ተሳታፊ የሆን ምእመናን ሁሉ ያለፈው ይበቃል ብለን አንድነቱ እንዲፈጠር በሐሳብ፣በጸሎት ልንተጋ ይገባል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

                                                        ምንጭ፤ሐመር  መጽሔት 26ኛ ዓመት ቊጥር 2፤ ሰኔ 2010 ዓ.ም