ድረ ገጾችን በስፋት ለስብከተ ወንጌል አገልግሎት መጠቀም እንደሚገባ ጥናቶች አመለከቱ

ጥቅምት ፲፰ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

ማኅበረ ቅዱሳን ባዘጋጀው አዲስ ስልታዊ ዕቅድ የስብከተ ወንጌል አገልግሎቱን የበለጠ ለማጠናከርና ከባለድርሻ አካላት ጋር እንዴት በቅንጅት ተቀራርቦ መሥራት እንደሚቻል የሚያመለክቱ ጥናታዊ ጽሑፎች መስከረም ፳፱ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም በማኅበሩ አዳራሽ ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡ በጥናቶችም ማኅበራዊ ድረ ገጾችን በስፋት ለስብከተ ወንጌል አገልግሎት መጠቀም እንደሚገባ ተጠቁሟል፡፡

dscf6211

ዲያቆን ያረጋል አበጋዝ

በዐውደ ጥናቱ ‹‹ኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮን ለማስፋፋት ፈታኝና ምቹ ኹኔታዎች›› በሚል ርእሰ ጉዳይ ጥናት ያቀረቡት ዲያቆን ያረጋል አበጋዝ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በየዘመናቱ የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ስትሰጥ ብትቆይም ከ፲፱፻፹-፲፱፻፺ ዓ.ም የነበራት ሐዋርያዊ አገልግሎት ይበልጥ የተጠናከረ እንደ ነበረ ጠቅሰው ለዚህም በወቅቱ የሰባክያነ ወንጌል ቍጥር መጨመር፣ የሰንበት ትምህርት ቤቶች አገልግሎት መስፋፋትና ምእመናን ስለ ሃይማኖታቸው ለማወቅ ያላቸው ፍላጎት ከፍተኛ መኾን የመሳሰሉት ጉዳዮች ለሐዋርያዊ አገልግሎት መፋጠን ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳበረከተ ገልጠዋል፡፡

ዲ/ን ያረጋል አያይዘውም ኦርቶዶክሳዊ መንፈስና መረዳት ያላቸውን ሰባክያነ ወንጌል በብዛት በመመደብ ኦርቶዶክሳዊ ትምህርት መስጠት የስብከተ ወንጌል አገልግሎትን ወደተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር እንደሚያስችል አስረድተዋል፡፡

dscf6257

ዲያቆን ዶ.ር ቴዎድሮስ

‹‹በስብከተ ወንጌል የአኃት አብያተ ክርስቲያናት ተሞክሮ›› በሚል ርእስ ባዘጋጁት ጥናታቸው የመጀመሪያዎቹን ሦስቱን ዓለም አቀፍ የቤተ ክርስቲያን ጉባኤያት የሚቀበሉ ኦሬንታል (አኀት) አብያተ ክርስቲያናት እንደሚባሉ ያስታወሱት ዲያቆን ዶክተር ቴዎድሮስ በለጠ ደግሞ ስብከተ ወንጌልን አጠናክሮ ለመቀጠል መልካም አጋጣሚዎችንና ተግዳሮቶችንም በጥናታቸው ዘርዝረዋል፡፡

‹‹የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ተግዳሮቶችና መልካም አጋጣሚዎች›› በሚል ርእስ ጥናት ያቀረቡት አቶ ፋንታኹን ዋቄ በበኩላቸው እምነታቸውን በሕይወት የሚገልጡ ምእመናን መበራከት፣ የምእመናን መንፈሳዊ ሕይወት መጠናከር፣ የጉባኤ ቤት መምህራን እነሱን አክለውና መስለው የሚያገለግሉ ሊቃውንትን መተካትና የአፅራረ ቤተ ክርስቲያንን እንቅስቃሴ መግታት መቻል የቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ አገልግሎት መጠናከር መገለጫዎች መኾናቸውን ገልጠዋል፡፡

dscf6302

አቶ ፋንታኹን ዋቄ

‹‹የኦርቶዶክሳዊ ምእመን ተልእኮ ራስን መጠበቅ፣ ሌሎችን መጠበቅና በሌሎች ለመጠበቅ ፈቃደኛ መኾን ነው›› ያሉት አቶ ፋንታኹን አያያይዘውም የዓለም የዕውቀት ዐውድ ኢክርስቲያናዊ በኾኑ አካላት እንደተቃኘና ቴክኖሎጂውን ለጥፋትም ኾነ ለልማት መጠቀም እንደሚቻል ጠቅሰው ጊዜውን በቍሳዊ ነገር መለካትና ለመንፈሳዊ ሕይወት ትኵረት አለመስጠት በብዙዎች ዘንድ እንደሚስተዋል ተናግረዋል፡፡ ለዚህም መፍትሔው የስብከተ ወንጌል አገልጋዮችን በብዛትም በጥራትም በማፍራት ምእመናንን ከጥፋት መጠበቅ መኾኑን በጥናታቸው ጠቁመዋል፡፡

‹‹ስብከተ ወንጌልን ከማስፋፋት አንጻር የማኅበራዊ ድረ ገጾች አስተዋጽዖ›› የሚለው ጥናታዊ ጽሑፍ አቅራቢ አቶ ነጻነት ተስፋዬም ማኅበራዊ ድረ ገጾች የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ከቦታ ቦታ ሳይንቀሳቀሱ ወንጌልን እንዲያስተምሩ፤ ምእመናንም ባሉበት ቦታ ኾነው እንዲማሩ የሚያስችሉ መሣሪያዎች መኾናቸውን አስገንዝበዋል፡፡

አቶ ነጻነት ጥንታዊቷና ታሪካዊቷ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ማኅበራዊ ድረ ገጾችን በተፈለገው መጠን እየተጠቀመች አለመኾኗን በማስታዎስ ማኅበራዊ ድረ ገጾችን በመጠቀም ለቤተ ክርስቲያን ተቆርቋሪና ለአገር አሳቢ ትውልድ ማፍራት እንደሚቻል አመላክተዋል፡፡

dscf6182

አቶ ነጻነት ተስፋዬ

በቤተ ክርስቲያን ወጥ የኾነ የድረ ገጽ አጠቃቀምና ተቋማዊ አደረጃጀት አለመኖር፣ የሃይማኖት አባቶች በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ያላቸው ግንዛቤ አነስተኛ መኾን፤ የአፅራረ ቤተ ክርስቲያን የቅሰጣ መልእክት፤ ማኅበራዊ ሚዲያውን የጥፋት መሣሪያ ብቻ አድርጎ ማሰብና የመሳሰሉት ችግሮች ማኅበራዊ ድረ ገጾችን ስንጠቀም ከሚገጥሙን መሰናክሎች መካከል እንደሚጠቀሱ አቶ ነጻነት አስገንዝበው የማኅበራዊ ድረ ገጾችን አጠቃቀም ከፍ ለማድረግም የአስተሳሰብ ለውጥ ማምጣት፤ የሌሎች አብያተ ክርስቲያናትን ልምድ መውሰድ፤ በስብከተ ወንጌል ላይ ብቻ ያተኰረ ትምህርት መስጠት፤ ሰባክያነ ወንጌል፣ የቤተ ክርስቲያን አባቶችና የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች የራሳቸው ድረ ገጽ እንዲኖራቸውና የእርስ በእርስ ግንኙነት እንዲፈጥሩ ማድረግ አስፈላጊ መኾኑን አስገንዝበዋል፡፡

በመጨረሻም ማኅበራዊ ድረ ገጾች ስብከተ ወንጌልን ለማስፋፋት ዓይነተኛ ሚና እንዳላቸው ኹሉ በአግባቡ ካልተጠቀምንባቸው ደግሞ የሚያስከትሉት ጉዳት ከፍተኛ ስለሚኾን ጉዳታቸውን ከጥቅማቸው በመለየት መጠቀም እንደሚገባ አቶ ነጻነት አስታውሰዋል፡፡

ምንጭ፡- ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ፣ ከጥቅምት ፲፮-፴ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም፤ ገጽ ፩ – ፪፡፡