ዳግም ምጽአት(ለሕፃናት)

መጋቢት 26 ቀን 2005 ዓ.ም.

ቤካ ፋንታ

ልጆች እንደምን ሰነበታችሁ፡፡ በእኩለ ጾም /በጾሙ አጋማሽ/ ለምናከብረው ለደብረ ዘይት በዓል እንኳን በሰላም አደረሳችሁ፡፡ ልጆች ዛሬ የምንማረው ስለ ደብረ ዘይት በዓል ሲሆን ትምህርቱ በዋናነት ስለ ዳግም ምጽዓት ያስረዳል፡፡

 

ዳግም ምጽአት ማለት ለሁለተኛ ጊዜ መምጣት ማለት ነው፡፡ ይህም ማለት አምላካችን ፈጣሪያችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደገና ወደ እኛ የሚመጣበትን ቀን ያመለክታል፡፡ ልጆችዬ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰማያት ሰማያት ወርዶ ከእናታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም በተወለደ ጊዜ ለፍጥረታት ሁሉ ለመጀመሪያ ጊዜ በግልጽ ታይቷል፡፡ በዳግም ምጽአት ጊዜ ደግሞ ሁሉም ሰዎች እያዩት እንደገና ስለሚመጣ ያቺ ቀን ዳግም ወደ እኛ የሚመጣበት ስለሆነች ዳግም ምጽአት ተባለች፡፡

ከታላቁ የመለከት ድምጽ በኋላ ቅዱሳን መላእክት በሙሉ ከቅዱሳን ሰዎች ጋራ ከእነ ቅዱስ አባታችን አብርሃም፣ ቅዱስ ዳዊት፣ ከቅዱሳን ሐዋርያት፣ ከእነ ቅዱስ ያሬድ፣ ከአባታችን አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ጋራ ሁሉም ቅዱሳን ሆነው እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም በመካከል ሆና ፈጣሪያችንን እግዚአብሔርን በመዝሙር እያመሰገኑት ከበሮን እየመቱ፣ መለኮቱን እየነፉ፣ እልል እያሉ ከሰማይ ውስጥ ይመጣሉ፡፡ ያን ጊዜ ሁላችንም አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ፊት ለፊት በዓይናችን እንመለከተዋለን፡፡

 

ከዚያ በኋላ አንድ ታላቅ ቅዱስ መልአክ ከምድር ጫፍ እስከ ምድር ጫፍ ድረስ የሚሰማውን የመጨረሻውን የመለከት ድምፅ ሲያሰማ የሞቱት ሰዎች ሁሉ ከተቀበሩበት ይነሣሉ፡፡ ተነሥተውም በእግዚአብሔር ፊት ይቆማሉ፡፡ መልካም የሠሩትና እግዚአብሔርን የሚወዱት ሰዎች ነጭ ለብሰው በቀኙ ይቆማሉ፡፡ በምድር ላይ ሲኖሩ ጨካኞችና ክፉ ሥራን በመሥራት የኖሩት ደግሞ ጥቁር ለብሰው በግራ በኩል ይቆማሉ፡፡

 

እግዚአብሔር አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስም በስተቀኝ በኩል ለቆሙት “በምድር ላይ ስትኖሩ እኔን አምናችኋል፡፡ ኀጢአት አልሠራችሁም ልጆቼ ሆይ እኔ እንዳዘዝኳችሁ እናት አባቶቻችሁን አክብራችኋል፣ ለተቸገሩ ሰዎችም የሚበሉትን ምግብ፣ የሚጠጡትን መጠጥ፣ የሚለብሱትንም ልብስ ሰጥታችኋል፡፡ ቤተ ክርስቲያን እንዳስተማረቻችሁ አሥርቱ ትእዛዛትን፣ ስድስቱ ቃላተ ወንጌልን በመጠበቅ መልካምና ደግ ልጆቼ ስለሆናችሁ ታላቅ ሽልማት እሸልማችኋለሁ፡፡ ሽልማታችሁም መንግሥተ ሰማያት ነች፡፡” በማለት በቀኙ የሚቆሙትን ቅዱሳኑን እና ደጋጋ ክርስቲያኖችን ደስ ያሰኛቸዋል፡፡

 

እግዚአብሔር ለደጋግ ሰዎች ያዘጋጃት መኖሪያ መንግሥተ ሰማያት እጅግ የተዋበች በውስጧም በጣም ባማረና በከበረ እንቁ የተጌጠች ነች፡፡ በዚያች ሰማይ ሁል ጊዜ ብርሃን ያለማቋረጥ ይበራባታል፤ ጨለማም ከቶ የለም፣ የሚያስፈራ ነገር የለም፣ ድካም የለም፣ ራብ የለም በመንግሥተ ሰማያት ዘወትር ደስታ፣ ዝማሬ እልልታ ይሆናል፡፡ መንግሥተ ሰማያት በታላቅ ረጅም ቅጥር የታጠረች ናት፡፡ አሥራ ሁለት በሮች አሏት፡፡ በውስጧ የሚገቡ ሰዎች ክፉ ነገርን የማያደርጉ፣ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ የጠበቁ እና ዕለት ዕለት እግዚአብሔርን ለማመስገን ወደ ቤተ ክርስቲያን የሚሄዱ ክርስቲያኖች ናቸው፡፡ በዚያ ሲኖሩ ሁል ጊዜ ደስ እያላቸው እግዚአብሔርን ፊት ለፊት እያዩት ከእርሱ ጋር ይኖራሉ፡፡ በዚያ እጅግ የምንወዳት እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከሁሉም ቅዱሳን ጋር አለች፡፡

 

በመጨረሻም አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በግራ በኩል ለቆሙት ሰዎች “በምድር ላይ ስትኖሩ ያዘዝኳችሁን ትእዛዝ አልጠበቃችሁም፣ እናት አባታችሁን አላከበራችሁም፣ የኀጢአትን ሥራ ሠርታችችኋልና ወደ መንግሥተ ሰማያት አትገቡም፡፡ የእናንተ መኖሪያ ገሃነመ እሳት ነው ከፊቴ ሂዱ፡፡” በማለት ይናገራቸዋል፡፡ እነርሱም ወደ ዘለዓለማዊ እሳት ይጣላሉ፡፡

 

ልጆች ዳግም ምጽአት ምን ማለት እንደሆነ አሁን በደንብ ተረዳችሁ አይደል፡፡ እንግዲህ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግመኛ በሚመጣበት ጊዜ በቀኙ እንድንቆምና መንግሥተ ሰማያትን እንድንወርስ ሁላችንም እግዚአበሔር እንዳዘዘን መልካምና፣ ደግ ሰዎች ልንሆን እና በቤተ ክርስቲያን የእግዚአብሔርን ቃል እየተማርን ልናድግ ይገባል፡፡

 

እግዚአብሔር አምላካችን ዳግም በሚመጣበት ጊዜ ከቅዱሳኑ ሁሉ ጋራ መንግሥተ ሰማያትን ያወርሰን ዘንድ ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንልን፡፡