ዳግመኛ መወለድ(ለሕፃናት)

ሚያዚያ 10 ቀን 2005 ዓ.ም.

በቤካ ፋንታ

እንደምን ሰነበታችሁ ልጆች፡፡ ዛሬ የምንማረው የእግዚአብሔር ልጆች ሁሉ ለሁለተኛ ጊዜ እንደሚወለዱ ነው፡፡

አንድ መምህር በኢየሩሳሌም ነበረ፣ ስሙም ኒቆዲሞስ ይባላል፡፡ ቀን ቀን ተማሪዎቹን ሲያስተምር ይውልና ማታ ፀሐይዋ ስትጠልቅ በጨለማ ወደ አምላካችን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ ይመጣል፡፡ ከዚያ እግሩ ሥር ቁጭ ብሎ ይማራል፡፡ ያልገባውን እየጠየቀ በደንብ ስለሚከታተል ጌታችንም እስኪገባው ድረስ ግልጽ አድርጎ ያስረዳውና የጠየቀውን ይመልስለታል፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን ኒቆዲሞስ የእግዚአብሔርን ቃል ለመማር ከቤቱ ተነሥቶ በሌሊት ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ መጣ፡፡ አምላካችንም በዚያ ሌሊት ለኒቆዲሞስ ያስተማረው ትምህርት እንዲህ የሚል ነበር፡፡ “ኒቆዲሞስ ሆይ፥ እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ወደ መንግሥተ ሰማያት አይገባም፡፡”

ኒቆዲሞስም በጣም ደንግጦ “ዳግመኛ? መወለድ እንዴት ይቻላል? ሰው ደግሞ የሚወለደው አንዴ አይደለም እንዴ? ደግሞስ አንድ ሰው ካደገ ትልቅ ከሆነ በኋላ እንደገና ወደ እናቱ ማኅፀን ገብቶ ሊወለድ እንዴት ይችላል?” እያለ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ጠየቀው፡፡ ጌታችንም የጠየቀውን ጥያቄ በደንብ አድርጎ መለሰለት፡፡

ልጆች አሁን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ መለሰለት መልስ ከመሄዳችን በፊት ኒቆዲሞስ የጠየቀውን ጥያቄ ደግሜ ልጠይቃችሁ፡-

  1. የሰው ልጆች የምንወለደው ስንት ጊዜ ነው?

  2. ሁለተኛ ጊዜ የምንወለደው እንዴት ነው?

  3. ዳግመኛ የምንወለደው የት ነው?   

 

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእግሩ ሥር ቁጭ ብለው ከሚማሩት ተማሪዎች መካከል ይህንን ጥያቄ ለጠየቀው ለኒቆዲሞስ “ዳግመኛ ልትወለዱ ያስፈልጋችኋል ስላልኩ እታድንቅ፡፡ የእኔ ልጆች እንድትሆኑ ዳግመኛ የምትወለዱት እንዴት፣ መቼ እና የት እንደሆነ አስረዳሃለሁ” ብሎ ድምፁን ከፍ አድርጎ ያስተማራቸው ትምህርት እንዲህ የሚል ነው፡-

ተማሪዎቼ ሆይ የሰው ልጆች በእናታቸው ማኅፀን ዘጠኝ ወር ከ5 ቀን ከቆዩ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ይወለዳሉ፡፡ ዳግመኛ የሚወለዱት ደግሞ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም በመጠመቅ ነው፡፡ ሕፃናት ወንዶች እና ሴቶች ከተወለዱ በኋላ ወንድ ከሆነ በ40 ቀን ሴት ከሆነች 80 ቀን ሲሞላት እናትና አባታቸው አቅፈዋቸው ቅድስትና ንጽሕት ወደ ሆነች ወደ እግዚአብሔር ቤት ወደ ቤተ ክርስቲያን ይሄዳል፡፡ ከዚያ ሲደርሱ የእግዚአብሔር አገልጋዮች ቀሳውስትና ዲያቆናቱ ደስ ብሏቸው ሕፃናቱን ተቀብለው ወደ መጠመቂያው ቤት ይዘዋቸው ይገባሉ፡፡

በመጠመቂያው ቤት ቄሶቹ ልብሰ ተክህኖ ለብሰው፣ ትልቅ መስቀል ይዘው፣ ወንጌሉን ዘርግተው ቅዱሱን ወንጌል ካነበቡ በኋላ ቄሱ በትልቁ መስቀል ሕፃናቱ የሚጠመቁበትን በገንዳ ውስጥ ያለውን ውኃ “በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም የተባረከ ይሁን” እያሉ ሲያማትቡበት ውኃው ተለውጦ ጸበል ይሆናል፡፡ ከዚህ በኋላ ሕፃናቱን በገንዳው ጸበል ውስጥ ሦስት ጊዜ ብቅ ጥልቅ፣ ብቅ ጥልቅ፣ ብቅ ጥልቅ እያደረጉ “በአብ ስም በወልድ ስም በመንፈስ ቅዱስ ስም አጠምቅሃለሁ” እያሉ ካህኑ ሲያጠምቋቸው ሕፃናቱ ለሁለተኛ ጊዜ ዳግመኛ ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ ይወለዳሉ፡፡

ከጸበሉ ሲወጡ ዲያቆኑ ሕፃናቱን ከፍ አድርጎ ሲይዝ ቄሱ በነጭ፣ በጥቁርና በቀይ ክሮች የተገመደውን ማኅተብ በመስቀል ከባረኩት በኋላ በሕፃኑ አንገት ላይ ያስሩለታል፡፡ መላ ሰውነቱንም ቅባ ሜሬን በተባለው ቅዱስ ቅባት እየቀቡት የልጁን ሰውነት ይባርኩታል፡፡ በመጨረሻም በእናት እና በአባታቸው እቅፍ ሆነው ወደ ቤተ መቅደስ ገብተው የአምላካችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን ይቀበላሉ፡፡

ይህንንም የተቀደሰ ሥርዓት በመፈጸም ዳግመኛ በመወለድ የእግዚአብሔር ልጅ የሆነ ሰው ወደ መንግሥተ ሰማያት ይገባል፡፡ በማለት አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሚያስተምራቸውና ጥያቄውን ለጠየቀው ለኒቆዲሞስ አስተማራቸው፡፡

ጌታችን ኢየሱሱ ክርስቶስ እንዳስተማረን ትምህርት ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ሁል ጊዜ ይህን ታላቅና ቅዱስ ሥርዓት ለልጆችዋ እየፈጸመች ዳግመኛ ተወልደን የሥላሴ ልጆች እንድንሆን ታደርገናለች፡፡ ይህም ድንቅ ሥርዓት ለአንድ ሰው አንድ ጊዜ ብቻ የሚፈጸም ነው፡፡ ሥርዓቱም ምሥጢረ ጥምቀት በመባል ይጠራል፡፡

ልጆቹ እንድንሆን ዳግመኛ በጥምቀት የወለደን እግዚአብሔር ስሙ የተመሰገነ ይሁን አሜን፡፡