የጽዮን ምርኮ – ክፍል ሦስት

ኅዳር ፳፫ ቀን ፳፻፱ .

በመምህር ብዙነህ ሺበሺ

ታቦተ ጽዮን ዳጎንን እንደ ሰባበረችው /፩ኛ ሳሙ. ፭፥፩-፭/

ፍልስጥኤማውያን እስራኤልን ድል አድርገው ታቦተ ጽዮንን ወደ አዛጦን ወሰዱአት፡፡ በዚያም ከቤተ ጣዖታቸው አስገብተው ዳጎን የተባለውን ጣዖት ከፍ ባለ መቀመጫ አድርገው እርሷን ግን ከታች አስቀመጧት፡፡ ሲነጋም የአዛጦን ሰዎች ማልደው ለጣዖቱ ሊሰግዱ ቢሔዱ ዳጎንን በግምባሩ ወድቆ አገኙት፡፡ አንሥተው ወደ ቦታው መለሱት፤ በነጋ ጊዜ እንደልማዳቸው ቢሔዱም እነሆ ዳጎን በታቦተ ጽዮን ፊት በምድር ላይ ወድቆ ነበር፡፡ ራሱ፣ እጆቹም ተቈራርጠው በመድረኩ ላይ ወድቀው ደረቱ ብቻውን ቀርቶ ነበር፡፡ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ‹‹ንጉሥ በመንግሥቱ ገበሬ በርስቱ እንደማይታገሥ እግዚአብሔርም በአምላክነቱ ከገቡበት አይታገሥም›› እንዲሉ ፍልስጥኤማውያን የእግዚአብሔር ማደሪያ ታቦተ ጽዮንን በጣዖት ቤት ከጣዖት እግር ሥር በማስቀመጣቸው እግዚአብሔር በቍጣ ተነሣባቸው፡፡ ኃይሉንም በታቦቱ ላይ አሳረፈ፤ ታቦተ ጽዮንም ዳጎንን ቀጠቀጠችው፤ ሰባበረችው፡፡

ይህ ታሪክ የሐዲስ ኪዳን የማዳን ሥራ ምሳሌነት አለው፡፡ ቀደም ብሎ እንዳየነው ታቦተ ጽዮን የወላዲተ አምላክ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ምሳሌ ናት፡፡ ታቦተ ጽዮን ዳጎንን እንደ ሰባበረችው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም ልጇን አዝላ ወደ ግብጽ በምታደርገው የስደት ጕዞ በምታቋርጣቸው መንገዶችና መንደሮች ዅሉ ያሉ ጣዖታት ይሰባበሩ ነበር፡፡ በግብጽ ያሉ ጣዖታት ማንም ሳይነካቸው ተሰባብረዋል፤ በውስጣቸው አድረው ሲመለኩ የነበሩ አጋንንትም በአምሳለ ሆባይ (ዝንጀሮ) እየወጡ ሲሔዱ ይታዩ ነበር /ነገረ ማርያም/፡፡ ዳጎን በታቦተ ጸዮን ፊት በግምባሩ እንደ ተደፋ እመቤታችንም በስደቷ በሲና በረሃ ስትጓዝ ያገኟት ሽፍቶች መዝረፋቸውን ትተው በፊቷ ሰግደው ሸኝተዋታል፡፡ ዳግመኛም በዕለተ ዕረፍቷ አስከሬኗን አቃጥላለሁ ብሎ የአልጋውን ሸንኮር የያዘው ታውፋንያ የተባለው አይሁዳዊ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል እጁን በሰይፍ በቀጣው ጊዜ እመቤታችን ይቅር ትለውና ትፈውሰው ዘንድ ግምባሩን መሬት አስነክቶ ሰግዶላታል፡፡

እንደዚሁም ጌታችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በታቦተ ጽዮን ይመሰላል፡፡ ዳጎን በታቦተ ጽዮን ፊት በግምባሩ ተደፍቶ እንደ ተገኘ ጌታችን በሥጋ ሰብእ ተገልጦ ወንጌለ መንግሥት በሚያስተምርበት ዘመንም አጋንንት ‹‹ቅዱሱ የእግዚአብሔር ልጅ ያለ ጊዜያችን አታጥፋን›› እያሉ ይሰግዱለት እንደ ነበር በቅዱስ ወንጌል በሰፊው ተመዝግቦ ይገኛል፡፡ ሐዋርያው ያዕቆብም ‹‹አጋንንትኒ የአምኑ ቦቱ ወይደነግፁ፤ አጋንንት ደግሞ ያምናሉ፤ ይንቀጠቀጡማል፤›› በማለት ተናግሯል /ያዕ. ፪፥፲፱/፡፡ ታቦተ ጽዮን ዳጎንን እንደ ቀጠቀጠችው (እንደ ሰባበረችው) ዅሉ ጌታችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ዲያብሎስንና ሠራዊቱን ቀጥቅጧቸዋል፡፡ ታቦተ ጸዮን የወርቅ ካሣ ተሰጥቷት ከምድረ ፍልስጥኤም እንደ ወጣች ጌታችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በወርቀ ደሙ ካሣነት የሲዖልን ነፍሳት ከሲዖል አውጥቷል፡፡

ጌታችን ለድኅነተ ዓለም በመስቀል ተሰቅሎ አዳምን ወክሎ ‹‹ኤሎሄ ኤሎሄ ላማ ሰበቅታኒ (አምላኪየ አምላኪየ ለምንት ኀደገኒ)፤ አምላኬ አምላኬ ለምን ተውከኝ›› በማለት ሲጣራ ሰምቶ ዲያብሎስ ‹‹ሥጋውን ወደ መቃብር፣ ነፍሱን ወደ ሲዖል ላውርድ›› ብሎ ቀረበ፡፡ የጌታ ጩኸትም አንድም ለአቅርቦተ ሰይጣን ነውና ሰይጣንን በአውታረ ነፋስ /ሥልጣነ መለኮት/ ወጥሮ ያዘው፤ ያን ጊዜ ዲያብሎስ ‹‹መኑ ውእቱ መኑ ውእቱ፤ ማነው ማነው›› እያለ መለፍለፍ ጀመረ /ትምህርተ ኅቡአት/፡፡ ከብዙ መቀባጠር በኋላም ‹‹አቤቱ ጌታዬ በድዬሃለሁ፤ ነገረ ልደትህን የተናገሩትን ነቢያት እነ ኢሳይያስን በምናሴ አድሬ በመጋዝ አስተርትሬአለሁ፤ ለበደሌ የሚኾን ካሣ የለኝም፤ የሲዖልን ነፍሳት በሙሉ እንደ ካሣ አድርገህ ውሰድ፡፡ እኔንም ያለ ጊዜዬ አታጥፋኝ›› በማለት አጥብቆ ለመነው፡፡ ጌታችንም ዲያብሎስን አስሮ ከአዳም ጀምሮ በሲዖል ተግዘው የነበሩ ነፍሳትን አወጣ፡፡ በዚህ ጊዜ የሲዖል ኃይላት ተሰባበሩ፤ ከመለኮቱ ብርሃን የተነሣም የሲዖል ጨለማ ተወገደ፡፡

እግዚአብሔር አምላካችን መርገመ ሥጋ መርገመ ነፍስን፣ ሊቃነ አጋንንትን፣ ሠራዊተ አጋንንትን፣ የሲዖልን ኃይላትን አጥፍቶልናልና ቅዱስ ዳዊት ከአንድ ሺሕ ዓመት በፊት ‹‹እስመ ሰበረ ኆኃተ ብርት ወቀጥቀጠ መናሥግተ ዘኀፂን፤ የናሱን ደጆች ሰብሯልና፡፡ የብረቱንም መወርወሪያ ቀጥቅጧል፤›› በማለት ዘመረ /መዝ. ፻፮፥፲፮/፡፡ ነቢዩ አጋንንትን ኆኀተ ብርት (የነሐስ ደጆች) ብሎአቸዋል፡፡ የነሐስ መዝጊያ ጠንካራ እንደ ኾነ አጋንንትም በአዳምና ልጆቹ ላይ መከራ አንጽተውባቸው ነበር፡፡ የአጋንንት ክንድ በሰው ልጆች ላይ ከብዶ ነበርና ሊቃነ አጋንንትን መናሥግተ ኀፂን (የብርት መወርወሪያ ወይም ቍልፍ) ብሏቸዋል፡፡ ቤት በብርት መወርወሪያ (ቍልፍ) ከተዘጋ እንደማይከፈት ሲዖልም ለ፶፭፻ (አምስት ሺሕ ከአምስት መቶ) ዘመን ተዘግታ የነፍሳት ወኅኒ ቤት ኾና ኖራለችና አዳሪውን በማደሪያው ጠራው፡፡ ከመዝጊያው መወርወሪያው (ቍልፉ) እንዲጠነክር ወይም መዝጊያ በቍልፍ እንዲጠነክር ከአጋንንት አለቆች (ሊቃነ አጋንንት) ይበረታሉና መናሥግተ ኀፂን (የብረት መወርወሪያ) አላቸው፡፡ አምስቱ የፍልስጥኤም ነገሥታት ሲሰግዱለት የነበረውን ዳጎንን ታቦተ ጽዮን እንደ ቀጠቀጠችው ዅሉ መድኀኒታችን ክርስቶስም ለ፶፭፻ (አምስት ሺሕ ከአምስት መቶ) ዘመን የተደራጀውን የአጋንንት ኃይል በሥልጣኑ ሰባብሮታል፡፡

ለታቦተ ጽዮን ካሣ እንደ ተሰጣት /፩ኛ ሳሙ. ፮፥፩-፱/

የእግዚአብሔር እጅ በአዛጦን ሰዎች ላይ በረታችባው፤ ሰዎቹንም በእባጭ ቍስልም መታቻቸው፤ አጠፋቻቸው፡፡ ታቦተ ጽዮንን ወደ አስቀሎና በወሰዷት ጊዜም አስቀሎናውያንንም በእባጭ መታቻቸው፡፡ ምድራቸውም በአይጦች መንጋ ተወረረ፡፡ እጅግ ዋይታና ጩኸት ኾነ፣ ታቦተ ጽዮን በፍልጥኤማውያን ላይ መቅሠፍት እንዳበዛችባቸው ባዩ ጊዜ የእግዚአብሔር ቍጣ በኀይል ወርዶባቸዋልና አምስቱ የፍልስጥኤም ነገሥታት (አዛጦን፣ አስቀሎና፣ አቃሮን፣ ጌትና ጋዛ) ከካህናተ ጣዖትና ከሟርተኞች ጋር እንዲህ በማለት ተማከሩ፤ ‹‹የእስራኤልን አምላክ ታቦት ብትሰዱ የበደል መሥዋዕት መልሱ እንጂ ባዶውን አትስደዱት፡፡ በዚያን ጊዜም ትፈወሳላችሁ፡፡ እጁም ከእናንተ አለመራቁ ስለ ምን እንደኾነ ታውቃላችሁ፤›› /፩ኛ ሳሙ. ፮፥፫/፡፡

በዚህ ተስማምተው በአምስቱ የፍልስጥኤም ግዛቶች ቍጥር አምስት የወርቅ አይጦችንና አምስት የወርቅ እባጮችን ቅርፅ አዘጋጁ፡፡ ቀንበር ያልተጫነባቸው ሁለት የሚያጠቡ ላሞንም ጠምደው በሠረገላ ከተዘጋጀው ወርቅ ጋር ታቦተ ጽዮንን ጫኑ፡፡ ሠረገላውን እየጐተቱ ከፍልስጥኤም ወጥተው ወደ ቤትሳሚስ ሔዱ፡፡ ሠረገላውም ወደ ቤትሳምሳዊው ወደ ኢያሱ እርሻ በደረሰ ጊዜ በዚያ ቆመ፡፡ የዚያ አገር ሰዎችም ታቦቱና ወርቁ የተጫነበትን ሣጥን ሲያወርዱ ወደ እግዚአብሔር ታቦት የተመለከቱ ሰባ ሰዎች በመቀሠፋቸው ምክንያት ቤትሳምሳውያን በፍርሃት ተዋጡ፡፡ የቂርያትይዓሪ ሰዎችም ታቦተ ጽዮንን በአሚናዳብ ቤት አኖሯት፤ አልዓዛር ወልደ አሚናዳብም ታቦቷን እንዲያገለግል ተደረገ፡፡ በዚያም ታቦተ ጽዮን ለሃያ ዓመት ኖረች፡፡ ከዚህ ታሪክ ለሐዲስ ኪዳን ምሳሌዎች የሚኾኑ ትምህርቶችን እናገኛለን፡፡

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በቤተ ዮሐንስ በነበረችበት ዘመን ወደ ቀራንዮ እየወጣች በልጇ መቃብር ላይ ትጸልይ ነበር፡፡ ጸሎቷም በሲዖል ያሉ ነፍሳትንና በሕይወተ ሥጋ ያሉ ኃጥአንን ማርልኝ በማለት ነበር እንጂ ስለራሷ ተድላ ደስታ አልነበረም፡፡ ‹‹ወእምአሜሃ ነበረት እግዝእትነ ቅድስት ድንግል ማርያም ወላዲተ አምላክ እንዘ ተኀዝን ወትስእል በእንተ ኵሎሙ ኃጥአን ዘከመ ዛቲ ዕለት አመ ፲ወ፮ ለየካቲት በከመ ልማዳ ቆመት መካነ ቀራንዮ ወሰአለቶ ለወልዳ፤ አምላክን የወለደች በድንጋሌ ሥጋ በድንጋሌ ነፍስ የጸናች ክብርት እመቤታችን በዚያች በየካቲት ፲፮ ቀን ቀራንዮ በሚባል ቦታ ቆማ ልጅዋን እንደ ልማዷ ስትለምን ኖረች›› እንዲል ተአምረ ማርያም፡፡

እንኳን የእናቱን ልመና የኀጥኡን ጸሎት የሚሰማ ጌታችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እልፍ አእላፋት መላእክትን፣ ቅዱሳን አበውን አስከትሎ ወረደና ‹‹ይኩን በከመ ትቤሊ እፌጽም ለኪ ኲሎ መፍቅደኪ አኮኑ ተሰባእኩ በእንተ ዝንቱ፤ የለመንሽው ዅሉ ይደረግልሽ፤ የምትወጂውን ዅሉ እፈጽምልሻለሁ፡፡ የለመንሽውን ዅሉ ላደርግልሽ ሰው ኾኛለሁና›› በማለት ታላቅ የምሕረት ኪዳን ሰጣት፡፡ በዚህ የምሕረት ኪዳንም እጅግ ብዙ ነፍሳት ከሲዖል ወጥተዋል፡፡ እስከ ምጽአትም ድረስ በቃል ኪዳኗ የሚታመኑ ምእመናን ከሲዖል ይወጣሉ፡፡ ታቦተ ጽዮን ከምድረ ፍልስጥኤም የወርቅ አይጦችና እባጮች ካሣ ተሰጥቷት እንደ ወጣች እመቤታችንም ሞተ ሥጋን የተቀበለችው በሞቷ ብዙ ነፍሳት ከሲዖል እንደሚወጡ ቃል ኪዳን ተሰጥቷት ነበርና በዕለተ ዕረፍቷ ብዙ ነፍሳት ከሲዖል ወጥተዋል፡፡ ለእመቤታችን የሞት ካሣ ኾነው የኀጥአን ነፍሳት ተሰጥተዋታል፡፡ ማለትም በሞቷ የኀጥአን ነፍሳት ከሲዖል ወጥተዋል፡፡

ይቆየን፡፡