የጽዮን ምርኮ – ክፍል ሁለት

ኅዳር ፳፪ ቀን ፳፻፱ .

በመምህር ብዙነህ ሺበሺ

 የአፍኒንና ፊንሐስ ኀጢአት ….

፬ኛ የአባታቸውን ምክር አለመስማታቸው

ካህኑ ዔሊ ልጆቹ ያደረጉትን ኃጢአት ዅሉ ሰምቶ ‹‹ስለ ክፉ ሥራችሁ ከዚህ ሕዝብ ሰምቻለሁና ስለምን እንደዚህ ያለ ነገር ታደርጋላችሁ? ልጆቼ ሆይ የእግዚአብሔርን ሕዝብ ኃጢአተኛ በማድረጋችሁ ስለ እናንተ የደረሰኝ ወሬ መልካም አይደለምና ይህ አይኾንም፡፡ ሰውስ ሰውን ቢበድል እግዚአብሔር ይፈርድበታል፡፡ ሰው ግን እግዚአብሔርን ቢበድል ስለ እርሱ የሚለምን ማነው?›› በማለት ቢመክራቸውም ‹‹ልጥፋ ያለች ከተማ ነጋሪት ቢጐሰምም አትሰማም›› እንዲል የአበው ብሂል አፍኒንና ፊንሐስ የአባታቸውን ቃል አልሰሙም ነበር /፩ኛ ሳሙ. ፪፥፳፫-፳፭/፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ደዊት ‹‹ዘይሴሰይ እክልየ አንሥአ ሰኰናሁ ላዕሌየ፤ እንጀራዬን የበላ በእኔ ላይ ተረከዙን አነሣ›› /መዝ.፵፥፱/ እንዳለው ዛሬም የአባቶችን ትምህርትና ተግሣፅ የማይሰሙ፤ የቤተ ክርስቲያንን እክለ ትምህርት ተመግበው አድገው ጠላቶቿ የኾኑ ውሉደ አፍኒን ወፊንሐስ ጥቂቶች አይደሉም፡፡

ከትእዛዛተ እግዚአብሔር አንደኛው ‹‹አባትና እናትህን አክብር›› የሚለው ነው፡፡ መቼም አባት ሲባል ማን ማንን እንደሚመለከት የማያውቅ የለም፡፡ በሐዋርያት እግር የተተኩ አባቶች ሊቃነ ጳጳሳትን እያቃለሉ ‹‹በቅዱስ ሲኖዶስ አንመራም፡፡ ቤተ ክርስቲያን አርጅታለች፤ እናድሳት፤›› በማለት በክርስቶስ ደም የተመሠረተች የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ዶግማና ቀኖና የሚጥሱ ራሳቸውን ‹‹ተሐድሶ›› እያሉ የሚጠሩ ምናምንቴዎች እጣ ፈንታቸው እንደ አፍኒንና ፊንሐስ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን አረጀች ከተባለ የተመሠረተችው በክርስቶስ ደም፣ በሐዋርያት ስብከት ነውና ክርስቶስ አርጅቷል፤ የሐዋርያትም ትምህርት ጊዜው አልፏል ማለት ነዋ? ለአንዲት ቃል እንኳን ትርጕም መስጠት የማይችሉ ‹‹መጽሐፍ ቅዱስን እንተረጕማለን፤ ቤተ ክርስቲያንን እናድሳለን›› በማለት የሚያሳዩት ድፍረት ለእነርሱ ዕውቀታቸው መኾኑ ነው፡፡ ‹‹የሰነፍ ዕውቀቱ ድፍረቱ›› እንዲል የአበው ብሂል፡፡

ሊቀ ነቢያት ቅዱስ ሙሴ ‹‹ተሰአሎ ለአቡከ ወይነግረከ ወለሊቃውንቲከ ይዜንዉከ፤ አባትህን ጠይቅ፤ ያስታውቅህማል፡፡ ሽማግሌዎችህንም ጠይቅ፤ ይነግሩህማል›› /ዘዳ. ፴፪፥፯/ በማለት እንደ ተናገረው አባቶች ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የሚናገሩትን፣ ሊቃውንቱ የሚያስተምሩትን የሚሰማና በትምርታቸው የሚመራ ከስሐትት ይድናል፡፡ የዔሊ ልጆች የአባታቸውን ቃል ሰምተው ተጸጽተው ቢኾን ኖሮ በኢሎፍላውያን ሰይፍ ባልወደቁም ነበር፡፡ ቤተ ክርስቲያን እክለ ትምህርቷን ተመግበው ያደጉ ልጆቿ ሲጠፉባት ታዝናለች፡፡ ስለዚህም ‹‹አብዳነ አጥብብ፤ ሰነፎችን አለብም›› እያለች ትጸልያለች፡፡ የቤተ ክርስቲያን ዓላማዋ የራሷን ልጆች ከመጠበቅ ባገሻገር ከውጭ ያሉትንም ወደ ውስጥ ማስገባት ነውና፡፡ ‹‹ከዚህም በረት ያልኾኑ ሌሎች በጐች አሉኝ፤ እነርሱን ደግሞ ላመጣ ይገባኛል፡፡ ድምፄንም ይሰማሉ አንድም መንጋ ይኾናሉ፤ እረኛውም አንድ›› እንዳለ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ /ዮሐ. ፲፥፲፮/፡፡

የካህኑ ዔሊ አለመታዘዝ

እግዚአብሔር አምላክ ዔሊን ምስፍናን ከክህነት ጋር አስተባብሮ በእስራኤል ላይ ለዐርባ ዓመት እንዲያገለግል አክብሮት ነበር፡፡ ዔሊ ግን ከእግዚአብሔር ይልቅ ለልጆቹ አደላ፡፡ የኀጥኡን ድኅነት እንጂ ጥፋቱን የማይወደው እግዚአብሔር ዔሊን በነቢዩ ላይ አድሮ መክሮት ነበር /፩ኛ ሳሙ. ፪፥፳፯-፴፯/፡፡ ዳግመኛም ልጆቹ በእስራኤል ሕዝብ ላይ የሚያደርጉት ነውር በብላቴናው በሳሙኤል ተነግሮት ነበር፡፡ የዔሊ ትልቁ ጥፋት ልጆቹን ከሥልጣናቸው አለመሻሩ ነበር፡፡ ምክር ለማይሰማ እርምጃ መውሰድ ግድ ነውና፡፡ ስለዚሀም ካህኑ ዔሊ ‹‹ከእኔ ይልቅ ልጆችህን ለምን አከበርህ?›› ተብሎ በእግዚአብሔር ተወቀሰ /፩ኛ ሳሙ. ፪፥፳፱/፡፡ ‹‹ከእኔ ይልቅ ወንድ ልጁን ወይም ሴት ልጁን የሚወድ ለእኔ ሊኾን አይገባውም›› /ማቴ. ፲፥፴፯/ እንዳለ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቅዱስ ወንጌል፡፡

ካህኑ ዔሊ ከእግዚአብሔር ፍቅር ተለየ፡፡ ልጆቹን የማይገሥፅ እርሱ ልጆቹን አይወድምና፡፡ ‹‹በበትር ከመምታት የሚራራ ሰው ልጁን ይጠላል፤ ልጁን የሚወድ ግን ተግቶ ይገሥፀዋል›› /ምሳ. ፲፫፥፳፬/ እንዳለ ጠቢቡ ሰሎሞን፡፡ በበትር መምታት ማለት ጽኑዕ ተግሣፅ ማለት ነው፡፡ ወላጆች ልጆቻቸውን ተግተው የማይገሥፁ፣ ውሏቸውንም የማይከታተሉ ከኾነ ጉዳቱ ከራሳቸው አልፎ ለአገርም ይተርፋል፡፡ በምግባር፣ በሃይማኖት ኰትኵተው የሚያሳድጉ ወላጆች ተተኪ የቤተ ክርስቲያን ትውልድ፤ አገር ተረካቢ ዜጎችን ያፈራሉ፡፡ ዔሊ ልጆቹን ተግቶ ባለመገሠፁ ራሱንም ልጆቹንም አጥቷል፡፡ ዛሬም መንፈሳዊ ተልእኮአቸውን በአግባቡ የማይወጡ አገልጋዮችን የማይገሥፁ አባቶች ከዔሊ ውድቀት ሊማሩ ይገባቸዋል፡፡ እለእስክንድሮስ ከሐዲውን አርዮስን እንደ ገሠፀው እና ከስሕተቱ አልመለስም ባለ ጊዜም እንዳወገዘው ዅሉ ዛሬም አባቶች ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ሕገ ቤተ ክርስቲያንን የሚጥሱ ካህናትን ሊገሥፁና ሊያስተካክሏቸው ይገባል፡፡

በዔሊ ልጆች እኩይ ተግባርና ካህኑ ዔሊም ልጆቹን ተግቶ ባለመገሠፁ ልጆቹ በኢሎፍላውያን ጦር ወደቁ፤ እርሱም በታቦተ ጽዮን መማረክና በልጆቹ ሞት ደንግጦ ከወንበሩ ላይ ወድቆ ሞተ፡፡ የፊንሐስ ሚስት በድንጋጤ የወለደችውን ልጅ ‹ክብር ከእስራኤል ለቀቀ› ስትል ‹ኢካቦድ› ብላ ጠራችው፡፡ የእስራኤል ክብራቸው ሞገሳቸው የነበረችው ታቦተ ጽዮን ተማርካለችና፡፡ በዔሊ ልጆች ኃጢአት ምክንያት እግዚአብሔር ኃይልና ሞገስን ከጽዮን አነሣ፡፡ መፈራትንም ከኃያላኑ ገፈፈ፡፡ ለዚህም ነው የፊንሐስ ሚስት ልጇን ኢካቦድ በማለት የጠራችው፡፡ ታቦተ ጽዮን እግዚአብሔር ኃይሉን የሚገልጥባት የትእዛዛቱ ጽላት፤ ሕዝበ እስራኤልን ከጠላት፣ ከአባር፣ ከቸነፈር፣ ከመቅሠፍት የሚያድንባት ማደሪያው ናት፡፡ ቅዱስ ዳዊት ‹‹እስመ ኀረያ እግዚአብሔር ለጽዮን ወአብደራ ከመ ትኩኖ ማኅደሮ፤ እግዚአብሔር ጽዮንን መርጦአታልና፤ ማደሪያውም ትኾነው ዘንድ ወዶአታልና›› /መዝ. ፻፴፩፥፲፫/ በማለት የዘመረው ለጊዜው ስለ ታቦተ ጽዮን ነው፤ ፍጻሜው ግን ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም ነው፡፡

ታቦተ ጽዮን የእግዚአብሔር ትእዛዝ መቀመጫ እንደ ነበረች እመቤታችንም አማናዊትና ዘለዓለማዊት የእግዚአብሔር ማደሪያ ናትና፡፡ ‹‹ዛቲ ይእቲ ምዕራፍየ ለዓለም፤ ይህች ለዘለዓለም ማረፊያዬ ናት›› እንዲል /መዝ. ፻፴፩፥፲፬/፡፡ ታቦተ ጽዮን በዔሊ ልጆች ኀጢአት ምክንያት ተማርካ ወደ ምድረ ፍልስጥኤም ተሰዳለች፤ እመቤታችንም በክፉው ሄሮድስ ከምድረ እስራኤል ወደ ግብጽ ተሰዳለች፡፡ ከዚሁ ዅሉ ጋርም ታቦተ ጽዮን የምእመናን ምሳሌ ናት፡፡ ታቦተ ጽዮን የእግዚአብሔር ማደሪያ እንደ ኾነች ዅሉ፣ ምእመናንም የእግዚአብሔር ማደሪያዎች ናቸውና፡፡ ‹‹ሥጋችሁ ከእግዚአብሔር የተቀበላችሁት በእናንተ የሚኖረው የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንደ ኾነ አታውቁምን?›› እንዳለ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ /፩ኛ ቆሮ. ፮፥፲፱-፳/፡፡ በዔሊ ልጆች ኃጢአት ታቦተ ጽዮን እንደ ተማረከች ምእመናን ከእግዚአብሔር ፈቃድ ሲወጡ የእግዚአብሔር ጸጋ ይለያቸዋል፡፡ ታቦተ ጽዮን በኢሎፍላውያን እንደ ተማረከች፣ ምእመናንም ራሳቸውን ለዲያብሎስ ምርኮ አሳልፈው ይሰጣሉና፡፡

ይቆየን፡፡