የጸሎት ቤት/ለሕፃናት/

መጋቢት 12 ቀን 2005 ዓ.ም.

ቤካ ፋንታ

ልጆችዬ እንኳን ለዐቢይ ጾም ሦስተኛ ሳምንት በሰላም አደረሳችሁ፡፡ ይህ ሦስተኛው ሳምንት ምኲራብ ተብሎ ይጠራል፡፡ ዛሬ የምንማረውም ትምህርት በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ ሁለት ከቁጥር 12 እስከ 17 ያለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ነው፡፡

ቤተ ክርስቲያን ማለት የክርስቲያኖች ቤት ማለት ነው፡፡ የእግዚአብሔር ልጆች በአንድነት ተሰብስበው እግዚአብሔርን የሚያመሰግኑበት፣ ከእግዚአብሔር ጋር የሚነጋገሩበት ቤት ስለሆነች የጸሎት ቤት ወይም የእግዚአብሔር ቤት እየተባለች ትጠራለች፡፡

በአንድ ወቅት ምን ሆነ መሰላችሁ፥ ጌታችን መድኀኒታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ቅዱሳን ሐዋርያትን ይዞ ወደ ምኲራብ መጣ፡፡ በድሮ ጊዜ ምኲራብ ትባል ነበር፤ አሁን ግን ቤተ ክርስቲያን ተብላ ትጠራለች፡፡ ጌታችንም ወደ ምኲራብ ሲገባ በቤቱ ዙሪያ ብዙ ነጋዴዎች፣ ሻጮች እና ለዋጮች ግቢውን ሞልተው ሲሸጡ ሲነግዱ አያቸው፡፡ አንዳንዱ በሬ ይሸጣል፣ ሌላው በግ፣ ሌላው ዶሮ፣ ሌላው ደግሞ እርግብ…. እየሸጡ የጸሎት ቤት የነበረውን የእግዚአብሔርን ቤት የገበያ ቦታ አደረጉት፡፡ የሰዎቹ ድምጽ፣ የእንስሳቱ ጩኸት ብቻ ምን ልበላችሁ ግቢው በጣም ተረብሿል፡፡ በዛ ላይ አንዳንዶቹ ይጣላሉ፣ ይሰዳደባሉ፣ በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ ሆነው ክፉ ነገርን ይነጋገራሉ፡፡

አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔርን ቤት ንቀው የጸሎት ቤት የሆነችውን መቅደስ የገበያ ቦታ እንዳደረጉት ሲመለከት ወዲያው ረጅም ጅራፍ ሠራ፡፡ በጅራፉም እየገረፈ በሬዎቹን በጎቹን ሁሉንም ከግቢ አስወጣቸው፡፡ በታላቅ ቃልም ጮኸ “ቤቴ የጸሎት ቤት ናት፥ እናንተ ግን የንግድ ቤት፣ የወንበዴዎች መደበቂያ አደረጋችሁት” ብሎ በአለንጋ እየገረፈ አባረራቸው፡፡

ኢየሱስ ክርስቶስም ሁሉንም አስወጣ ጸጥታ ሆነ ለተሰበሰቡት ሕዝብ ካሁን በኋላ እንዲህ አታድርጉ፡፡ በእግዚአብሔር ቤት መጸለይ፣ መስገድ፣ መዘመር፣ መማር እንጂ መሸጥ፣ መግዛት፣ መረበሽ፣ መሳደብ፣ መጣላት፣ ክፉ ነገር ማድረግ መጮኸ አይፈቀድም ብሎ አስተማራቸው፡፡ ሕዝቡም አጥፍተናል ይቅርታ አድርግልን ሁለተኛ ይህን ጥፋት አናጠፋም ብለው ቃል ገቡ፡፡

ከዚያም ለተሰበሰቡት የእግዚአብሔር ልጆች ያስተምራቸው ጀመረ፡፡ የሚማሩትም ሰዎች በጣም ደስ ብሎዋቸው ከእግሩ ሥር ቁጭ ብለው ተማሩ፡፡ ዐይናቸው የማያይላቸው ሰዎችም ወደ እርሱ ቀርበው አምላካችን ሆይ እባክህ አድነን ሲሉት፣ እጁን ዘርግቶ ዐይናቸውን ሲነካው ሁሉም ማየት ጀመሩ፡፡ የታመሙ ሰዎች ሁሉ ወደ እርሱ መጡ፣  ሁሉንም አዳናቸው፡፡

ልጆችዬ በእግዚአብሔር ቤት በቤተ ክርስቲያን ስንገባና ስንወጣ ተጠንቅቀን መሆን እንዳለብን አስተዋላችሁ አይደል፡፡ ምክንያቱም የእግዚአብሔር ቤት የተቀደሰና፣ ሁሌም መላእክት እግዚአብሔርን የሚያመሰግኑበት የተባረከች ንጽህት ሥፍራ ስለሆነች ነው፡፡  ልጆችዬ ወደ ቤተ ክርስቲያን ስንገባም ሆነ ስንወጣ ተጠንቅቀን ሌሎችን ሳንረብሽ፣ ሳንሮጥ፣ ሳንጮኸ መሆን አለበት፡፡ በሰንበት ትምህርት ቤትም ከወንድሞቻችንና ከእኅቶቻችን ጋራ ስለ እግዚአብሔር እየተነጋገርን፣ እየተማማርን ልናሳልፍ ይገባናል፡፡

እግዚብሔር አምላካችን በቅድስናና በንጽሕና በቤተ ክርስቲያን እንድንኖር ይርዳን አሜን፡፡