የግቢ ጉባኤያትን ተማሪዎች መንፈሳዊ ሕይወት ለማሳደግ የሚያስችል የንሰሐ አባቶች ሴሚናር ተካሔደ

በእንዳለ ደጀኔ

ሰኔ 10 ቀን 2003 ዓ.ም 

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በሰንበት ት/ቤቶች ማ/መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን የግቢ ጉባኤያት ተማሪዎችን መንፈሳዊ ህይወት ለማሳደግ የሚያስችል የግቢ ጉባኤያት ተማሪዎች የንስሐ አባቶች ሴሚናር ተካሔደ፡፡
ከግንቦት 24 እስከ ግንቦት 26 ቀን 2003 ዓ.ም አዲስ አበባ ላይ በተካሔደው የግቢ ጉባኤያት ተማሪዎች የንሰሐ አባቶች ሴሚናር በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ ግቢ ጉባኤያት ተማሪዎች የንስሐ አባቶች ተወካዮች የተሳተፉ ሲሆን፥ በሴሚናሩም በቤተክርስቲያን ወቅታዊ ሁኔታ የንስሐ አባቶች ሚና፣ ለግቢ ጉባኤያት ተማሪዎች መንፈሳዊ እድገት የንስሐ አባቶች ሚና፣ ሉአላዊነት ዘመናዊነት በተለይ ከአንቀጸ ንስሐ አንፃር፣ የግብጽ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ተሞክሮ ወጣቶችን ለቤተክርስቲያን አገልግሎት ከማዘጋጀት አንፃር እና የማኅበረ ቅዱሳን አገልግሎት ግቢ ጉባኤያትን ለቤተክርስቲያን አገልግሎት ከማዘጋጀት አንፃር የሚሉ ርዕሰ ጉዳዮችን መሠረት ያደረገ ነበር፡፡

ለመጀመሪያ ጊዜ በተዘጋጀው በዚህ የግቢ ጉባኤያት የንስሐ አባቶች ሴሚናር ቁጥራቸው 50 የሚደርሱ አባቶች መሳተፋቸው ታውቋል፡፡

በካህናቱ አቀባበል ላይ የተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የማኅበሩ ሰብሳቢ ቀሲስ ዶ/ር ሙሉጌታ ስዩም «እናንተን አባቶች እዚህ ድረስ እንድትመጡ ያስቸገርነው በግቢ ጉባኤያት ተማሪዎች አገልግሎት ያላችሁ ድርሻ ታላቅ በመሆኑ ነው» ብለዋል፡፡

በሴሚናሩ ላይም ብፁዕ አቡነ ዮናስ የአፋር ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ተገኝተው ቡራኬና ቃል ምዕዳን የሰጡ ሲሆን «ማኅበሩ የሚያደርገው የልጅነት ድርሻውን በማገዝ እናንተ ካህናት ትልቁን ድርሻ ትይዛላችሁ» ብለዋል፡፡

ለ3 ቀናት በተካሔደው በዚህ ሴሚናር «እጅግ በጣም ተደስተናል» ያሉት ተሳታፊ ካህናቱ «ቀጣዩን ትውልዱ በመቅረጽና ለሀገርና ለቤተክርስቲያን ብቁና በሥነ-ምግባር የታነፁ ለማድረግ የምንችልበትን ግንዛቤ አግኝተናል። ይህም ካህናት ባገኘነው ግንዛቤና ልምድ ተነሳስተን ውጤታማ ሥራዎችን እንሰራለን» ብለዋል፡፡

ሴሚናሩም ሊቃውንቱን እርስ በእርስ ያስተዋወቀና በመረጃም ረገድ ልምድ ለመለዋወጥ መነሳሳትን እንደፈጠረላቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡