kidstmaryamtimket5.jpg

የጌታችን የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ጥምቀት በጃንሜዳ።

በፈትለወርቅ
 
በከተራ ዕለት
kidstmaryamtimket5.jpgየ2003 ዓ.ም የጌታችን የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ጥምቀት ዋዜማ የከተራ በዓል በታላቅ ድምቀት ተከብሯል። በዋናው በዓል ዋዜማ፥ ከሥርዓተ ቅዳሴው ፍጻሜ በኋላ ታቦታተ ሕጉ ከመንበረ ክብራቸው ተነስተው በየምዕራፉ በሊቃውንት አባቶች ስብሐተ እግዚአብሔር እየተደረሰ በሰንበት ት/ቤት አባላትና ምዕመናን መዝሙር እየተዘመረ ወደ ባሕረ ጥምቀቱ አምርተዋል።
 
የበዓሉ አከባበርም ከዓመት ዓመት ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን እየጠበቀ፣ እየደመቀና እያሸበረቀ እየሔደ እንደሆነ በግልጽ ይታያል። መንገዱ ሁሉ ጽዱ፥ በሰንደቅ ዓላማና በዓሉን በሚመለከቱ ጥቅሶች አሸብርቋል። ከታቦታቱ ፊት መስቀልና ቅዱሳት ሥዕላት ጥላናkidstmaryamtimket3.jpg መረዋሕ የያዙ ዲያቆናት፥ በሰልፍ ሆነው የሚዘምሩ ጥንግ ድርብና ካባ የለበሱ መዘምራን፥ የደንብ ልብስ የለበሱ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች፥ ፀአዳ የለበሱ የማኅበረ ቅዱሳን መዘምራን የጌታችን ጥምቀት የሚመለከቱ መዝሙሮችን በመዘመር፥  ወጣቶች ግራና ቀኝ እጅ ለእጅ በመያያዝ ሕዝበ ክርስቲያኑን ወደ ቀኝና ወደ ግራ ከፊትና ከኋላ በማድረግ ያለ ምንም ትርምስና ግርግር የተለያዩ ጥምቀትን የሚመለከቱ መዝሙሮችን በመዘመር፣ ወጣቶችም ፊት በመቅደም ለታቦታቱ ክብር ያዘጋጁትን ምንጣፍ በማንጠፍና ቄጠማ በመጎዝጎዝ የእግዚአብሔር ማደሪያ ለሆኑት ታቦታተ ሕጉና ለአባቶቻችን ካህናት ልዩ ክብር በማሳየት ወደ ባሕረ ጥምቀት/ጃንሜዳ/  ደርሰዋል። 
 
kidstmaryamtimket10.jpg
በጃንሜዳ ባሕረ ጥምቀተ፥ ከየአቅጣጫው የሚመጡ ታቦታት የሚያድሩ ሲሆን፣ ከደቡብ መንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም፣ መንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ፣ ታዕካ ነገሥት በአታ ለማርያምና መንበረ መንግሥት ቅዱስ ገብርኤል፥ ከምሥራቅ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ደብረ ነጎድጓድ ቅዱስ ዮሐንስ፣ ቀጨኔ ደብረ ስላም መድኀኔዓለምና መንበረ ልዑል ቅዱስ ማርቆስ፥ ከሰሜን ገነተ ኢየሱስና አንቀጸ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል እንዲሁም ከምዕራብ መካነ ሕይወት ገብረ መንፈስ ቅዱስ ናቸው።
ታቦታተ ሕጉ ቦታቸውን ይዘው ከቆሙ በኋላ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ በዓሉን አስመልክተው ሲገልፁ« በዓሉ በመላው ኢትዮጵያ እንደሚከበርና በዓሉን የምናከብር ሁሉ የክርስቶስን ሥራ ሰላምን ለመስበክ እንጅ ሌላ እንዳልሆነ በማሳየትም ጭምር መሆኑን ገልፀው አክለውም ቱሪስቶች ወደዚች አገር የሚመጡት የተሻለውን ለመውሰድና ለመረዳት ተረድቶም ለመፈጸም ነው። ስለሆነም ቤተ ክርስቲያን በዓሉን ስታከብር የቱሪስትን ዐይን ለመማረክ ብላ ሳይሆን፥ የእምነትን ትክክለኛ አቋም ይዛ ነው። ይህ ደግሞ የቀደሙ አባቶች ያቆዩልን ሥርዓት የየዘመኑን ትውልድ ሁሉ ያካተተ ነው። ቱሪስቶች የሚመጡት የአገሪቱን ቱሪዝም ገቢ ለመጨመር አስበው ሳይሆን የቤተ ክርስቲያንና የምዕመናኑ ልባዊ ፍቅር ስቧቸው ነው። ስለዚህ ፍቅራችሁ የተስማማ ይሁን፥ እናንተን እያዩ የሰማዩ አባታችሁን እንዲያመሰግኑት የሚለውን ይዘን በዓሉ በሰላምና በመፈቃቀር እንዲከበር አሳስበዋል።

በዓሉን አስመልክቶ ያነጋገርናቸው ዶ/ር አባ ኀ/ማርያም በጠቅላይ ቤተ ክህነት የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልዕኮ መምሪያ ሓላፊ «የዛሬው በዓል የከተራ በዓል ነው። ከተራ ስንል በዋዜማው ምዕመናን ተሰብስበው በአንድነት የሚሆኑበት ነው። ከተራ ማለት መሰብሰብ ክብ ሰርቶ በአንድ ላይ ምስጋና ማቅረብን የሚያመለክት ቃል ነው። በአራቱም ማዕዘን ምዕመናን በአንድ ላይ ሆነው በዓሉን ያከብራሉkidstmaryamtimket6.jpg ይህም በዓል መገለጥ/epiphany/ ይባላል። በዕለቱ ደግሞ ነገ ጌታችን በተጠመቀ ጊዜ መገለጥ ሆኗል። የአብ የወልድ የመንፈስ ቅዱስ አንድነትና ሦስትነት ተገልጿል። ክርስቲያኖችም ይህንን በዓል የምናከብረው ለበረከትና ለረድኤት ነው። ምዕመኑ በተለየ ሁኔታ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ማራኪና አስደናቂ ነገር ለቤተ ክርስቲያኒቱ እያበረከተ መሆኑንና ይህ ደግሞ የቤተ ክርስቲያኒቱንም የአገሪቱንም መልካም ገፅታ የሚያንፀባርቅ ይሆናል። አገራዊና ዓለም አቀፋዊ ገጽታውም በጣም ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጠው መሆኑንና በዓሉ በነገው ዕለትም በከፍተኛ ድምቀት እንደሚከበር ገልጸዋል።

ከቅዱስነታቸው ጸሎተ ቡራኬ በኋላ የዕለቱ ተረኛ ደብር የታዕካ ነገሥት በአታ ለማርያም ገዳም ሊቃውንት «ሃሌ ሉያ ወረደ ወልድ…» የሚለውን ያሬዳዊ ዜማ አቅርበዋል።

በብፁዕ አቡነ ፊሊጶስ የዕለቱ መልዕክትና በዓሉን አስመልክቶ ትምህርተ ወንጌል ተሰጥቷል። በመጨረሻም ቅዱስነታችው ቃለ ቡራኬና ምዕዳን ሰጥተው ታቦታተ ህጉ ወደ ተዘጋጀላቸው ድንኳን ገብተዋል።

አገልጋዮች ካህናትና ምዕመናንም ሌሊቱን በትምህርተ ወንጌል፣ በማሕሌትና በዝማሬ አሳልፈዋል። የቅዳሴ ሥርዓቱም ከሌሊቱ 6፡00 ጀምሮ እስከ 9፡00 ሰዓት ድረስ በታዕካ ነገሥት በአታ ለማርያም ገዳም ካህናት ተከናውኗል። በዕለቱ ብዙ ምዕመናን ቅዱስ ቁርባን ተቀብለዋል።

በዓለ ጥምቀት
ቅዱስነታቸው ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ፣ የአድባራትና የገዳማት አስተዳዳሪዎች፣ መነኮሳት፣ ካህናት ልብሰ ተክህኗቸውን ለብሰው ቅዱሳት መጻሕፍትን ይዘው፥ በአራቱም ማዕዘን ከበው የጥምቀተ ባሕሩን የቡራኬ ሥርዓት ያደርሳሉ፡፡ በቅዳሴና በማሕሌት ከታቦታተ ሕጉ ጋር ያደሩት ምዕመናን እንዲሁም ከየቤታቸው በሌሊት ተነስተው የመጡት፥ ባሕረ ጥምቀቱን ከበው ቆመው ሥርዓቱን እየተከታተሉ ምሥጋና ያቀርባሉ፡፡

በቅዱስነታቸው፣ በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትና በካህናት በዕለቱ የሚደርሰው ጸሎተ አኮቴት በንባብና በዜማ ተደርሶ ባሕረ ጥምቀቱ በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ተባርኮ ምዕመናን ፀበል ተረጭተዋል፡፡

በመቀጠልም የታዕካ ነገሥት በአታ ለማርያም ገዳም ሊቃውንት መዘምራን ዕለቱን በተመለከተ በያሬዳዊ ጣዕመ ዜማ ‹‹ሃሌ ሉያ ተሣሃልከ እግዚኦ በእንተ ልደቱ ወጥምቀቱ ለክርስቶስ ማዕከለ ባሕር ገብአ ወወጽአ በሰላም›› በማለት ወርበዋል፡፡ መዘምራኑ እንደጨረሱ የእነሱን ፈለግ ተከትለው የወጡት የገዳሙ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶችም ‹‹አጥመቆ ዮሐንስ ለኢየሱስ ወገሠሦ እንተ ኢትትገሠሥ ርእሶ›› የሚለውን ወረብ ካቀረቡ በኋላ የአጫብር ወረብ ቀርቧል።

ከዚህ በኋላ ለቃና ዘገሊላ ከሚመለሱት ሁለቱ የቅዱስ ሚካኤል ታቦታት በቀር ሌሎቹ ታቦታት መስቀል በያዙ ዲያቆናትና ጽንሐሕ በያዙ ካህናት ታጅበው በታላቅ ክብር በእልልታና በዝማሬ በተዘጋጀላቸው መድረክ ቆሙ፡፡ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ መልካም ፈቃድ ብፁዕ አቡነ ገሪማ የድሬዳዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና በጠቅላይ ቤተ ክህነት የውጭ ግንኙነት ኃላፊ በዓሉን በተመለከተ ሰፋ ያለ ትምህርትና መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

kidstmaryamtimket12.jpg

በመጨረሻም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ዕለቱን በተመለከተ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከምታከብራቸው ታላላቅ በዓላት ውስጥ አንዱ የሆነውን የጥምቀት በዓል ስታከብር በሚማርክና ለሌሎች አርአያ በሚሆን መልኩ እንደሆነና፥ ይህ መተሳሰብ፣ አርአያነትና ፍቅር ሌሎችን እየሳበ የበዓሉን አከባበር ሥርዓት ሊያዩና ሊካፈሉ ከአገር ውጭ የሚመጡት እንግዶቻችን ከዓመት ዓመት ቁጥራቸው እየጨመረ ነው። ለእንግዶችም ባስተላለፉት መልዕክት ወደዚህች አገር መጥተው ይህንን በዓል አብረው ማክበራቸው እድለኞች እንደሆኑና ሌሎችም ያላዩት እንዲያዩ እንዲያደርጉ አሳስበዋል፡፡ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ወጣቶችንም የአባቶቻቸውን ፈለግ ተከትለው የአባቶቻቸውን ሥርዓትና ሕግ ሳይለቁ የበለጠ እንዲሠሩ ሃይማኖታቸውን እንዲጠብቁ አሳስበዋል፡፡ ቃለ ቡራኬና ምዕዳን ከሰጡ በኋላ ታቦታተ ሕጉ በመጡበት አኳኋን ወደ መንበረ ክብራቸው በካህናት በሰንበት ት/ቤት ወጣቶችና በምዕመናን መዝሙር እየተዘመረ ተጉዘዋል፡፡

kidstmaryam.jpgበመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም የተገኙት የጠቅላይ ቤተ ክህነት ምክትል ሥራ አስኪያጅ ንቡረ እድ ኤልያስ አብርሃ በሰጡት ትምህርት «ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ማን አጠመቀው ብንባል ማን እንላለን? ዮሐንስ አጠመቀው እንበል? እኔ ግን ቅዱስ ዮሐንስ አምላክን በማጥመቁ የሰዎች ልጆች ሁላችን ነው ያጥመቅነው ብየ አምናለሁ። ኃይሌ ገ/ሥላሴ ሩጫ ቢያሸንፍ ኢትዮጵያ አሸነፈች እንደሚባለው፣ ሁሉም እንደሚደሰተው። «ተጠምቀ ሰማያዊ በእደ መሬታዊ» እንደተባለው ሰማያዊው አምላክ እግዚአብሔር ወልድ በመሬታዊው በዮሐንስ እጅ ተጠመቀ። ፈጣሪን የምናጠምቅ ሆነን አይደለም ምን ያህል እንደወደደን ያሳያል እንጂ። ብዙ ሰማያውያን ሠራዊት ነበሩ፣ በእነርሱ እጅ መጠመቅ ይችል ነበር፤ በባሕርይ አባቱ መጠመቅ ይችል ነበር፤ በባሕርይ ሕይወቱም መጠመቅ ይችል ነበር። ፈጣሪ አምላካችን በሰው እጅ ተጠመቀ እኮ? በእውነት ምን አይነት ፍቅር ነው? ምንስ አይነት መውደድ ነው? እኛም ፈጣሪ አምላክን ለማጥመቅ በቃን እኮ!» ብለዋል።

ታቦት እንተ ውስቴታ ኦሪት እንተ ውስቴታ….እልልልልልልልkidstmaryamtimket4.jpg