የጌታችን መከራ በሊቃውንት አንደበት

መጋቢት ፳፯ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም 

‹‹ታመመ፤ ሞትን ከተቀበለበት ከሥጋ ተዋሕዶ በመስቀል ላይ በፈቃዱ ለሥጋውያን ሞተ፣ ባሕርየ መለኮት ሥጋን ተዋሕዶ በማኅፀን ካደረ ጀምሮ ሥጋ ገንዘቡ እንደመሆኑ በሥጋ ይኸንን ሥርዓት ፈጸመ፡፡ ለማይመረመር ለመለኮቱ ባሕርይ እንደሚገባ ደግሞ እርሱ ኅብስት አበርክቶ ዂሉን ያጠግባል፡፡ አይራብም፤ አይጠማም፤ አይደክምም፤ አያንቀላፋም፤ አይታመምም፤ አይሞትም፤ ሕይወትን ለዂሉ ይሰጣል፡፡ ዳግመኛ በዚያ በሲኦል ተገዝተው ያሉ ነፍሳትን ያድን ዘንድ በአካለ ነፍስ ወደ ሲኦል ወረደ፤ በመለኮቱም ሲኦልን በዘበዘ፤›› (የእስክንድርያው ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ ቄርሎስ)፡፡

‹‹እጆቹን፤ እግሮቹን በተቸነከረባቸው ችንካሮች መወጋቱንም እናምናለን፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስእርሱ ደዌያችንን ወሰደሕማማችንንም ተሸከመ፤ እኛን ለማዳን ኃጢአታችንንም ለማስተስረይ መከራ ተቀበለእንዳለ፤ በባሕርዩ ሕማም የሌለበት ሲኾን በሥጋ የታመመ ነው፡፡ በእርሱ ከመከራ ሥጋ ከመከራ ነፍስ ድነናል፡፡ በተገረፈና በተቸነከረም ጊዜ በመከራው መለኮትን ሕማም ተሰማው የሚል ሰው ቢኖር የተለየ የተወገዘ ይሁን፤›› (ሊቀ ጳጳስ ቅዱስ ጎርጎርዮስ)፡፡

‹‹እርሱ መቼም መች ከመለኮቱ ሳይለይ የሰውነትን ሥራ ገንዘቡ አደረገ፡፡ ይኸውም መራብ፣ መጠማት፣ መንገድ በመሔድ መድከም፣ በመስቀል ላይ መሰቀል፣ በብረት ችንካር መቸንከር ነው፡፡ በሰውነቱ መቸም መች ሰው ነው፤ በአምላክነቱም ሰውን የፈጠረ ነው፡፡ ነገር ግን ከማይከፈል ተዋሕዶ በኋላ መከፈል የለበትም፡፡ ሰው እንደ መኾኑ ስለ እኛ የታመመው፣ የሞተው እርሱ ነው፡፡ በመለኮቱ ግን መቸም መች አይታመምም፤ አይሞትም፡፡ ሕማምንና ሞትንም አይቀበልም፡፡ በሞቱ ሞትን ያጠፋው እርሱ ነው፡፡ ሲኦልንም የበዘበዘው እርሱ ነው፤›› (የአንጾኪያው ሊቀ ጳጳስ ቅዱስ ዲዮናስዮስ)፡፡

‹‹ነፍሱን ከሥጋው በለየ ጊዜ ያን ጊዜ በሲኦል ፈጥኖ ብርሃን ታየ፡፡ ጌታችን በአካለ ሥጋ ያይደለ በአካለ ነፍስ ወደ ሲኦል ሔደ፡፡ ሲኦል ተነዋወጠች፤ መሠረቶቿም እፈርስ እፈርስ አሉ፡፡ ምድርን ያለ ጊዜዋ እንዳታልፍ ክብርት ደሙን በምድር ላይ አፈሰሰ፡፡ ከኅልፈት ጠበቃት በእርሷ ያለውንም ዂሉ ጠበቀ፡፡ ስለ ፍጥረት ሥጋውን በመስቀል እንደ ተሰቀለ ተወው፡፡ ነፍሱ ግን ወደ ሲኦል ወረደች ከዚያ ተግዘው የነበሩ ነፍሳትን አዳነች፤ ሲኦልንም በዘበዘች፡፡ ፍጥረትንም ዂሉ ገንዘብ አደረገች፡፡ ሥጋውም በመቃብር ያሉ ሙታንን አስነሣ፤ ነፍሱም በሲኦል ተግዘው የነበሩ ነፍሳትን ፈታች፤›› (የእስክንድርያው ሊቀ ጳጳስ ሐዋርያው ቅዱስ አትናቴዎስ)፡፡

‹‹ከብርሃን የተገኘ ብርሃን፣ ከባሕርይ አምላክ የተገኘ የባሕርይ አምላክ፣ የተወለደ እንጂ ያልተፈጠረ፣ በባሕርዩ ከአባቱ ጋር አንድ የሚኾን፡፡ ዂሉ የተፈጠረበት፤ ያለ እርሱ ግን ምንም ምን የተፈጠረ የሌለ፤ በሰማይ በምድር ያለውም ቢኾን፡፡ እኛን ስለ ማዳን ከሰማየ ሰማያት ወርዶ በግብረ መንፈስ ቅዱስ ከቅድስት ድንግል ማርያም ፍጹም ሰው ኾነ፡፡ የሠላሳ ዘመንልማሳ ኾኖ በጲላጦስ የሹመት ዘመን ስለ እኛ ተሰቀለ፤ ስለ እኛም ታመመ፤ ሞተ፤ ተቀበረ፤›› (ሠለስቱ ምእት)፡፡

‹‹ምትሐት ያይደለ በእውነት ተራበ፤ ተጠማ፡፡ ዳግመኛም ከኃጥአን፣ ከመጸብሐን ጋር በላ፤ ጠጣ፡፡ ያቀረቡለትንም በላ፡፡ ራሱን አሳልፎ ለመስቀል ሰጠ፡፡ እጁን፣ እግሩን ተቸነከረ፤ ጐኑን በጦር ተወጋ፡፡ ከእርሱም ቅዱስ ምሥጢር የተገለጠበት ደምና ውኃ ፈሰሰ (ወጣ)›› (ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሣርያ)፡፡

‹‹የሚሠዋ በግ እርሱ ነው፤ የሚሠዋ ካህን እርሱ ነው፡፡ ከባሕርይ አባቱ ከአብ ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ ጋርም መሥዋዕት የሚቀበል እርሱ ነው፡፡ በፈቃዱ መከራን በሥጋው የተቀበለ መከራንም የታገሠ እርሱ ነው፡፡ እንደ በግ ሊሠዋ መጣ፤ በግ በሚሸልተው ሰው ፊት እንደማይናገር አልተናገረም፡፡ በአንደበቱ ሐሰት አልተገኘበትም፤›› (ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ)፡፡

‹‹በሥጋ መወለድ፣ በመስቀል መከራ መቀበል፣ መሞት፣ መነሣት፣ ገንዘቡ የኾነ እርሱ እግዚአብሔር ቃል ነው፡፡ ስለዚህ በመስቀል ላይ ሳለ ከጥንት ጀምሮ በመቃብር ያሉ ሙታንን አስነሣ፤›› (ሰማዕቱ ሊቀ ጳጳስ ቅዱስ ፊልክስ)፡፡

‹‹ሙሴም ሞትን ያጠፋ ዘንድ አልቻለም፤ እርሱንም ይዞ ገዛው እንጂ፡፡ ከእርሱም በኋላ የተነሡ ነቢያትንም ሞት ገዛቸው እንጂ፡፡ ክርስቶስ ግን በቸርነቱ ለዂሉ ሕይወትን ሰጠ፤›› (የሮማ ኤጲስ ቆጶስ ቅዱስ አቡሊዲስ)፡፡

‹‹በመስቀል በሥጋ ተሰቅሎ ሳለ ለመለኮት ከሥጋ መለየት የለበትም፡፡ አንዲት ሰዓትም ቢሆን የዐይን ጥቅሻ ያህል ስንኳ ቢሆንም መለኮት ከትስብእት አልተለየም፣ በመቃብር ውስጥ በሰላም መለኮት ከትስብእት አልተለየም (የሮሜ ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ አዮክንድዮስ)፡፡

‹‹ከአብ ጋር አንድ እንደ መኾንህ ሞት የሌለብህ አንተ ነህ፡፡ ከእኛ ጋር አንድ እንደ መኾንህ በፈቃድህ የሞትህ አንተ ነህ፡፡ በመቃብር ያደርህ አንተ ነህ፡፡ በኪሩቤል ላይ ያለህ አንተ ነህ፡፡ ከሙታን ጋር በመቃብር የነበርህ አንተ ነህ፡፡ በአንተ ሕማምና ሞትም ድኅነት ተሰጠ፡፡ ከሙታን ጋር የተቈጠርህ አንተ ነህ፡፡ ለሙታንም ትንሣኤን የምትሰጥ አንተ ነህ፡፡ ሦስት መዓልት ሦስት ሌሊት በመቃብር ያደርህ አንተ ነህ፡፡ በዘመኑ ዂሉ ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር የምትኖር አንተ ነህ፡፡ በመለኮት ሕማም ሳይኖርብህ በሥጋ የታመምህ አካላዊ የእግዚአብሔር ቃል አንተ ነህ፤›› (የኪስኪስ ኤጲስ ቆጶስ ቅዱስ ኤራቅሊስ)፡፡

‹‹ኃጢአታችንን ለማሥተስረይ በሥጋ እንዲህ ታመመ፤ እንደ ሞተ ከነፍሱም በተለየ ጊዜ ሥጋውን እንደ ገነዙ እናምናለን፤›› (የኢየሩሳሌም ኤጲስ ቆጶስ ቅዱስ ዮሐንስ እንዲህ አለ)፡፡

‹‹ነቢይ ዳዊትነፍሴን በሲኦል አትተዋትም፤ የባሕርይ ልጅህንም ሙስና መቃብርን ያይ ዘንድ አሳልፈህ አትሰጠውም› አለ፡፡ ይህም ጌታ በተዋሐደው አካል ያለውን የነፍስና የሥጋ ተዋሕዶ ያስረዳል፡፡ የቀና ልቡና ዕውቀት በእርሱ ጸንቶ ይኖር ዘንድ፡፡ ዳዊት እንደ ተናገረው እውነት ኾነ፤ ነፍስ መለኮትን ተዋሕዳ ወደ ሲኦል ወርዳለችና፡፡ ሥጋም ሦስት መዓልት ሦስት ሌሊት በመቃብር ሳለ መለኮት ከሥጋ አልተለየም፤ አምላክ ሰው የመኾኑን እውነት ያስረዳ ዘንድ፡፡ መለኮት ነፍስን ተዋሕዶ በአካለ ነፍስ የሲኦል ምሥጢርን ገልጦ ፈጽሟልና በሲኦልም በቁራኝነት አልተያዘምና፤›› (የቆጵሮስ ደሴት ኤጲስ ቆጶስ ቅዱስ ኤጲፋንዮስ)፡፡ 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ምንጭ፡- ስምዐ ተዋሕዶ፣ ሚያዝያ ፩ -፲፭ ቀን ፳፻፯ .ም፡፡