የጋብቻ ሕይወት እና የሩካቤ ሥርዓት – የመጨረሻ ክፍል

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

ሚያዝያ   ቀን ፳፻፲ .

ማጠቃለያ

የጋብቻ ሕይወት፣ የሰው ልጅ ፈቃደ ሥጋዉን እንዲፈጽምበት፣ ዘሩን እንዲተካበትና እንዲረዳዳበት እግዚአብሔር አምላካችን ያዘጋጀው ሥርዓት ነው፡፡ በስእለት ወይም በሌላ ምክንያት ለመመንኰስ ከወሰኑ አባቶችና እናቶች በቀር ለሰብአዊ ፍጡር ዂሉ ጋብቻ አስፈላጊ ነው፡፡ ስለዚህ ወይ በጋብቻ አለዚያም በድንግልና መጽናት እንጂ እንዲሁ እየዘሞቱ መኖር ኀጢአት ነው፡፡ ትዳር ለመመሥረት ወስነን ዝግጅት ላይ የምንገኝ ምእመናንም የጋብቻ መሥፈርታችን ሃይማኖትን፣ ክርስቲያናዊ ምግባርንና መልካም ሰብእናን መሠረት ያደረገ ሊኾን ይገባዋል፡፡ ሀብትን፣ ዝናንና ውበትን ምክንያት አድርጎ መተጫጨት መጨረሻው አያምርምና፡፡ እነዚህ ቁሳውያን መሥፈርቶች ከጊዜ በኋላ ሲጠፉ ጋብቻም አብሮ ሊፈርስ ይችላል፡፡ ስለዚህም መሥፈርታችን ከሃይማኖትና ከምግባር ጋር የተገናኘ መኾን ይኖርበታል፡፡ እነዚህ ከተሟሉ ሀብቱና ሌላው ጉዳይ በጊዜ ሒደትና በጥረት የሚመጣ ነውና፡፡

ጋብቻ፣ የመለኮትና የትስብእት ምሳሌ ነው፡፡ ‹‹እፎ ቤተ ነዳይ ኀደረ ከመ ምስኪን፤ እንደ ምስኪን እንዴት ከደሃ ቤት አደረ?›› እንደ ተባለው እግዚአብሔር አምላካችን ለተዋሕዶ የመረጠው የድሆችን ሥጋ ነው፡፡ የተዋሕዶ ምሳሌ የኾነዉን ጋብቻ የምንመሠርት ምእመናንም ሰዎችን ገንዘብ፣ መልክ፣ ዝና የላቸውም ብለን ልንንቃቸውና ከምርጫ ውጪ ልናደርጋቸው አይገባም፡፡ ጋብቻ፣ አንደኛው የሌላኛውን ድክመት እየሸፈነ የሚኖርበት እንጂ በሁለት ፍጹማን ሰዎች የሚመሠረት ሕይወት አይደለም፡፡ ፍጹም አመለካከት ያለዉን ሰው ማግኘት ይከብዳልና፡፡ በመኾኑም ጥንካሬያችንን በመጋራት፣ ድክመታችንን በማስተካከልና በመተራረም ለመኖር መዘጋጀት ይኖርብናል፡፡

በሥራ፣ በአመለካከት ወይም በሞትና በልዩ ልዩ ምክንያት መለያየት ሲመጣ ሕይወታችንን እንዴት እንደምንቀጥልና ሌሎች የመሳሰሉ ጉዳዮችንም መጻሕፍትን በማንበብ፣ ሥልጠና በመውሰድ፣ የልምድ ተሞክሮ ያላቸውን ሰዎች በመጠየቅ ከመተጫጨት በፊት ስለ ጋብቻ ሕይወት ትምህርት ብንቀስም መልካም ነው፡፡ ይህም ለወደፊቱ ሕይወታችን ደስታና ስኬት ይጠቅመናል፡፡ ከዂሉም በላይ እግዚአብሔር አምላካችን መልካምና ታማኝ የትዳር አጋር ይሰጠን ዘንድ በጸሎት መትጋት ይጠበቅብናል፡፡ ከዚሁ ዂሉ ጋርም ጋብቻ የሚከለከልባቸው መንገዶች እንዳሉም መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ እነዚህም ሩካቤን የሚከለክል ደዌ ወይም ተፈጥሯዊ ችግር፣ ምንኵስና (ለመመንኰስ ቃል መግባት)፣ በእምነት መለያየት፣ እንደዚሁም ሥጋዊ፣ መንፈሳዊና የጋብቻ ዝምድናዎች ናቸው፡፡

በሥጋዊ ዝምድና እስከ ሰባት ትውልድ ድረስ መጋባት የተከለከለ ነው፡፡ ስለዚህም በጋብቻ ዝምድና ወደ ላይ፡- ወንድ የአባቱን፣ የአያቱን የቅድመ አያቱን ሚስት፣ ልጅ፣ እኅት፣ እናት አያገባም፡፡ ወደ ታች፡- የልጁን፣ የልጅ ልጁን ልጅ ሚስት፣ ልጅ፣ እኅት፣ እናትና አያት ማግባት ክልክል ነው (ዘሌ. ፲፰፥፮-፳፩፤ ፪፥፩-፳፩)፡፡ ወደ ጎን፡- ወንዱ የወንድሞቹንና የልጆቻቸውን ሚስት ልጅ፣ እኅት፣ እናትና አያት ማግባት አይችልም፡፡ እንደዚሁም የሚስቱን አያት፣ እናት፣ አክስት፣ እኅት፣ ልጅ፣ የልጅ ልጅና በዚህ የዝምድና ሐረግ የሚገኙትን ማግባት አይፈቀድለትም፡፡ መንፈሳዊ ዝምድናን ስንመለከት ደግሞ ወደ ላይ፡- ወንዱ የክርስትና አባቱን ልጅ፣ ሚስት፣ የልጅ ልጅና እኅት፤ ወደ ታች፡- የክርስትና አባት የክርስትና ልጁን እናት፣ እኅት፣ የእኅቱንና የወንድሙን ልጅ ማግባት አይፈቀድለትም (ፍት. ነገ. ፳፬፣ ቍ. ፰፻፵፪-፰፻፶፮)፡፡

እንደዚሁም በእምነት ከማይመስለን ሰው ጋር መጋባት ክልክል ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ እንዳስተማረው ጋብቻ የኢየሱስ ክርስቶስና የቤተ ክርስቲያን ምሳሌ ነው፡፡ ጋብቻ፣ በሚያምኑና በማያምኑ ሰዎች መካከል ከተፈጸመ ምሥጢሩ ከክርስቶስና ከቤተ ክርስቲያን ተዋሕዶ ጋር አይስማማም፡፡ ስለዚህም በሃይማኖት ከማይመስሉን ጋር መጋባት እንደሌለብን እናስተውል፡፡ በእርግጥ ከአሕዛብ ወይም ከመናፍቃን ወገን የትዳር አጋር የመረጥን ካለን ትምህርተ ሃይማኖትን እንዲማሩና የክርስትና ጥምቀትን እንዲጠመቁ በማድረግ ማግባት እንችላለን (፩ኛ ቆሮ.፯፥፲፪-፲፯፤ ፍት. አን. ፳፬፣ ቍ. ፱፻፲፪-፱፻፲፭)፡፡

ጠቢቡ ሰሎሞን እንደ ቀለበት በልብህ አኑረኝ  በማለት እንደ ተናገረው (መኃ. ፰፥፮)፣ ጋብቻ ለሚጠብቁትና ለሚያከብሩት ሰማያዊ ዋጋ የሚያስገኝ የፍቅርና የአንድነት ሕይወት ነው፡፡ ለቃል ኪዳን የሚታሰረው ክብ ቀለበትም የጋብቻ ሕይወት የማይቋረጥ አንድነት መኾኑን የሚያመላክት ምሥጢር አለው፡፡ በመተጫጨትና በቃል ኪዳን ቀለበት የተመሠረተው ጋብቻ በሥርዓተ ተክሊል ይፈጸማል፡፡ ጋብቻ ምሥጢራዊነቱና ትክክለኛነቱ የሚታወቀው በሥርዓተ ተክሊል ወይም በሥርዓተ ቍርባን ሲፈጸም ብቻ ነው፡፡ ከሥርዓተ ተክሊል ወይም ከቍርባን ውጪ ጋብቻን መፈጸም በሕገ ቤተ ክርስቲያን የተከለከለ ነው (ፍት. ነገ. ፳፬፣ ምዕ. ፳፭፣ ክፍል ፪)፡፡ በድንግልና ጸንተው የቆዩ ምእመናን ጋብቻ በሥርዓተ ተክሊል፤ የመዓስባን (ሁለተኛ የሚያገቡ) ጥንዶች ደግሞ በሥርዓተ ቍርባን ይፈጸማል፡፡ ከሚጋቡት አንዳቸው በድንግልና የቆየ (የቆየች) ከኾነ ለብቻው (ለብቻዋ) ትባረክ ዘንድ ሥርዓት ተሠርቷል (ፍት. ነገ. አን. ፳፬፣ ቍ. ፱፻፮)፡፡

ክርስቲያናዊ ጋብቻ፣ በቃል ኪዳንና በቡራኬ፣ በጸሎተ ተክሊልና በቅዱስ ቍርባን መፈጸሙ ምሥጢርነት አለው፡፡ አንድነቱ ወይም ተዋሕዶው የክርስቶስና የቤተ ክርስቲያን ምሳሌ ነውና (ኤፌ. ፭፥፴፪)፡፡ በሥርዓተ ተክሊል ሙሽሮቹ የሚያደርጉት ቀለበት፣ የሚለብሱት ነጭ ልብስ፣ የሚቀቡት ቅብዓ ቅዱስ፣ የሚቀዳጁት አክሊል፣ እንደዚሁም የካህናቱ ጸሎትና ቡራኬ ሙሽሪትና ሙሽራው ከመንፈስ ቅዱስ ለሚቀበሉት በዓይን ለማይታይ ጸጋ ምክንያቶች ናቸው፡፡ ጸሎቱ ከደረሰ በኋላ ሥርዓተ ቅዳሴ ተደርጎ ሙሽሮቹ ሥጋውንና ደሙን ይቀበላሉ፡፡ ሥጋውና ደሙ የምሥጢራት ዂሉ ማኅተም ነውና፡፡ ያለ ሥጋውና ደሙ ሥርዓተ ተክሊልም ሥርዓተ ቍርባንም አይፈጸምም (ፍት. ነገ. ፳፬፣ መጅ ፩)፡፡ ከሥርዓተ ተክሊልና ከሥርዓተ ቍርባን ሥርዓት ውጪ ጋብቻን መመሥረት በፍጹም ሊለመድ አይገባም፡፡

ክርስቲያን ነን እያልን በሕገ ቤተ ክርስቲያን ካልተመራን ሰው ኾነን ተፈጥረን ሳለን እንደ እንስሳ መኖር ይኾንብናልና በትዳር ያልተወሰንን ወገኖችም የቤተ ክርስቲያናችንን መመሪያ ተቀብለን በሥርዓተ ተክሊል፣ ካልኾነም በሥርዓተ ቍርባን ለመጋባት እንዘጋጅ መልእክታችን ነው፡፡ ከዚህ በፊት በዓለማዊ መንገድ ትዳር የመሠረትን ምእመናንም ንስሐ ገብተን ሥጋዉን ደሙን እየተቀበልን ኑሯችንን ብንቀጥል፣ ለልጆቻችንም ለሌሎች ወገኖችም አብነት መኾን እንችላለን፡፡

ከዚህ በተለየ በሚስት ላይ ሚስት፤ በባል ላይ ባል መደረብ አስጸያፊና በእግዚአብሔር ዘንድ የሚያስጠይቅ ድርጊት መኾኑን ማስተዋል ተገቢ ነው፡፡ ከጋብቻ በፊትም እንኳንስ ከማያገቡት ሰው ጋር ከእጮኛ ጋርም ቢኾን ሩካቤ ሥጋ መፈጸም ኀጢአትም ነውርም ነው፡፡ ከዝሙት እንድትርቁ እግዚአብሔርን እንደማያውቁ አሕዛብ በፍትወት ድል አትነሡ፤ ከእናንተ እያንዳንዱ የራሱን ዕቃ በቅድስና እና በክብር ያገኝ ዘንድ እንዲያውቅ፤” በማለት ቅዱስ ጳውሎስ እንዳስተማረው ሰውነታችንን በቅድስና መያዝ ይገባናልና (፩ኛ ተሰ. ፬፥፭)፡፡ ይህን በመረዳት በዚህ ዓይነት ኀጢአት የምኖር ምእመናን ከዚህ ክፉ ተግባር መውጣትና ንስሓ መግባት ይኖርብናል፡፡ በንጽሕና የምንኖርም ንጽሕናችንን በመጠበቅ ከሚኾነን ሰው ጋር ጋብቻ መመሥረት፤ ትዳር የመሠረትንም አንድነታችንን ማጥበቅ ይገባናል፡፡ እንደዚህ ብናደርግ በምድርም በሰማይም እንጠቀማለን፡፡

ፍቺን በተመለከተ የጋብቻ ሕይወት ሃይማኖትን፣ ንጽሕናን እንደዚሁም መንፈሳዊ ሕይወትን የሚፈታተን እንደ ዝሙትና ሃይማኖትን መለወጥ ዓይነት ኀጢአት ወይም ሞት ካልመጣ በቀር በአንድነት እንደ ጸና ይኖራል እንጂ በቀላሉ አይፈርስም፡፡ ስለዚህም በጋብቻ አንድነት ውስጥ መለያየት (ፍቺ) እንዳይኖር በቀኖና ቤተ ክርስቲያን ተደንግጓል፡፡ በመኾኑም ችግሮችን በውይይት በመፍታት፣ በመመካከርና በመፈቃቀር ተስማምቶ እስከ ሞት ድረስ መኖር ተገቢ ነው፡፡ አብሮ ለመኖርና ለሃይማኖት እንቅፋት የሚኾኑ፣ የጋብቻን ክብር የሚያቃልሉ ለምሳሌ ሩካቤ ሥጋ ለመፈጸም አለመቻል፣ ሃይማኖትን መለወጥ፣ በትዳር ላይ መሴሰንና የመሳሰሉ እንቅፋቶች ካጋጠሙ እንደዚሁም ሞት ከመጣ ግን መፋታት ይፈቀዳል፡፡ ቢኾንም በቀኖና ቤተ ክርስቲያን ከተደነገገው ምክንያት በቀር መፋታት አይገባም (ፍት. ነገ. አን. ፳፬፣ ቍ. ፲፩-፲፯)፡፡

የጋብቻን ሕይወት ከሚፈታተኑ፣ የሩካቤ ሥጋ ሥርዓትን ከሚያዛቡ ተግባራት መካከል ዝሙት ዋነኛው ነው፡፡ ከፍተኛ የኾነ የሩካቤ ሥጋ ጥማት ወይም ሴሰኝነት ዝሙት ይባላል፡፡ ይኸውም ከጋብቻ ውጪ ሩካቤ ማድረግን፣ ግብረ ሰዶምንና በገዛ ሰውነት ላይ ፍትወተ ሥጋን መፈጸምን ያጠቃልላል፡፡ በሥልጣኔና በሌሎችም ሰይጣናዊ ተፅዕኖዎች የተነሣ በዓለማችን እየተለመደ የመጣው የዝሙት ኀጢአት ማለትም የተመሳሳይ ፆታ ጋብቻ፤ የወንዶች ከአንድ በላይ ሴት፣ የሴቶች ደግሞ ከአንድ በላይ ወንድ የማግባት ልማድ፣ ካገኙት ዂሉ ጋር በሩካቤ የመተዋወቅና የመሳሰለው አስነዋሪ ድርጊት ሊወገዝ ይገባል፡፡

ባለፉት ክፍሎች ለመዳሰስ እንደ ሞከርነው ሩካቤ ሥጋ፣ በጥንቃቄና በሥርዓት የሚፈጸም ግንኙነት ነው፡፡ በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን መሠረት ጋብቻቸውን የፈጸሙ ሕጋውያን ሩካቤ የሚያደርጉበት ቀንና ሥርዓት ተወስኖላቸዋል፡፡ ለባለ ትዳሮቹ የሩካቤ ሥርዓት ከተሠራ ያለ ጋብቻ ከተገኘው ዂሉ ጋር መተኛት ምን ያህል የእግዚአብሔርን ሕግ መተላለፍ እንደ ኾነ ለመረዳት አያዳግትም፡፡ ከተመሳሳይ ፆታ ጋር ስለሚደረገው ግንኙነትስ (ግብረ ሰዶም) ይህ ነው ብሎ ለመናገር ይከብዳል፡፡ ምክንያቱም እንደ አስፈላጊነቱ እንጠቀምበት ዘንድ የተሰጠንን የተፈጥሮ ሕግ መጣስ፤ የሰውነት ክፍሎቻችንንም ማርከስ ነውና፡፡

እያንዳንዱ የሰውነት ክፍል የሥራ ድርሻ አለው፤ አንዱ ሕዋስ የሌላዉን ሥራ ማከናወን አይችልም፡፡ በፆታ ደረጃ ለወንድና ለሴት ለተመሳሳይ አገልግሎት የተሰጡን ሕዋሳት እንዳሉን ዂሉ ለወንዶች ብቻ ወይም ለሴቶች ብቻ የተሰጡ የአካል ክፍሎችም አሉ፡፡ ለሩካቤ ሥጋም ራሱን የቻለ ሕዋስ ተሰጥቶናል፡፡ ይህን የሰውነት ክፍል በጋብቻ ተወስነን ፈቃዳችንን በሥርዓት እንፈጽምበታለን፡፡ ነገር ግን ከዚህ በተለየ ዂኔታ ከተመሳሳይ ፆታ ጋር መገናኘት የእግዚአብሔርን ሥራ ከማንቋሸሽ ባለፈ ርኵሰትም ነው፡፡ ደግሞም ከእንስሳት ማነስ ነው፡፡ ማሰብና ማመዛዘን የማይችሉ እንስሳት እንኳን ከየትኛው ፆታ ጋር መገናኘት እንደሚገባቸው ይገነዘባሉ፡፡ እንስሳት የማያደርጉትን ይህን የረከሰ ተግባር መፈጸም ነባቢት፣ ሕያዊትና ለባዊት ነፍስ ካለችው፤ በዚያውም ላይ በእግዚአብሔር አርአያና ምሳሌ ከተፈጠረ የሰው ልጅ የማይጠበቅ አስነዋሪ ድርጊት ነው፡፡

ግብረ ሰዶም ከኀጢአት ዂሉ የከፋ ኀጢአት ነው፡፡ የኀጢአት ደመወዙ ደግሞ ሞት ነው፡፡ በምድር የነፍስና የሥጋ መለየት፣ በሰማይ ደግሞ በሲዖል (በገሃነመ እሳት) መጣል ሞት ይባላል፡፡ ግብረ ሰዶምን የሚፈጽሙ ሰዎችም ከተፈጥሮ ሥርዓት ውጪ በመጓዝ ከእንስሳት በታች ኾነዋልና ፍጻሜያቸው ሞት፤ የሞት ሞት ነው፡፡ ወይስ ዓመፀኞች የእግዚአብሔርን መንግሥት እንዳይወርሱ አታውቁምን? አትሳቱ፤ ሴሰኞች ቢኾን ወይም ጣዖትን የሚያመልኩ ወይም አመንዝሮች ወይም ቀላጮች ወይም ከወንድ ጋር ዝሙት የሚሠሩ፣ ወይም ሌቦች ወይም ገንዘብን የሚመኙ ወይም ሰካሮች ወይም ተሳዳቢዎች ወይም ነጣቂዎች የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም፤ እንዳለ ቅዱስ ጳውሎስ (፩ኛ ቆሮ. ፮፥፱-፲)፡፡

በብሉይ ኪዳን ከተመሳሳይ ፆታ ጋር ግንኙነት ሲፈጽሙ የነበሩ ሰዶማውያን ንስሓ ባለመግባታቸው ምክንያት በእሳትና በዲን ተቀጥተዋል፡፡ በዚህ ዘመን የተነሡ ሰዶማውያንም በምድር በመቅሠፍት፤ በሰማይም በገሃነመ እሳት መቀጣታቸው አይቀርም፡፡ ምክንያቱም ቅዱሱን የእግዚአብሔር ሰውነት አርክሰዋልና፡፡ በዚህ የርኵሰት ኀጢአት የሚገኙ ወገኖቻችን ከመጥፋታቸው በፊት በመምከርና በማስተማር ክርስቲያኖች ከኾኑ ለንስሓ እንዲበቁ፤ ሃይማኖት ከሌላቸውም ብንችል አስተምረን ማስጠመቅ፤ ባንችል ደግሞ የሚሠሩት ሥራ ከሰው የማይጠበቅ ተግባር መኾኑን ማስገንዝብ ይገባል፡፡ ሐዋርያው ይሁዳ እንዲሁም እንደ እነርሱ ዝሙትን ያደረጉና ሌላን ሥጋ የተከተሉ ሰዶምና ገሞራ በዙሪያቸውም የነበሩ ከተማዎች በዘላለም እሳት እየተቀጡ ምሳሌ ኾነዋል፤  በማለት ሰዶምና ገሞራ መጥፋታቸውን መጥቀሱ ግብረ ሰዶም የሚያመጣውን  መሪር ቅጣት በመገንዘብ ይህን ኀጢአት እንድንጸየፈውና እንድንርቀው ለማስተማር ነው (ይሁዳ. ፩፥፯)፡፡

የጽድቅ ሥራ እና የኀጢአት ተግባር በአንድ ልብ አመንጪነት ይፈጸማሉ፡፡ ልዩነቱ ጻድቃን ልቡናቸውን መልካም ነገርን ሲያሳስቡት፤  ኃጥኣን ደግሞ ለክፉ ነገር ማዋላችን ነው፡፡ “ደግ ሰው ከመልካም ልቡ መዝገብ መልካም ነገርን ያወጣል፤ ክፉ ሰው ግን ከክፉ ልቡ መዝብ ክፉ ነገርን ያወጣል፤” እንዲል (ማቴ. ፲፪፥፴፭)፡፡ በዚህ ዓለም እግዚአብሔርን የሚያስረሱን ሥጋውያን ተግባራት ብዙ ቢኾኑም፣ በአንጻሩ ደግሞ ፈቃደ ሥጋችንን በማሸነፍ ሕግጋቱን ጠብቀን ለመኖር የምንችልባቸው አጋጣሚዎችም አሉ፡፡ ጣዖት በሚመለክበት አካባቢ ቤተ ክርስቲያን እናገኛለን፤ ዓለማዊ ጫጫታ በሚበዛበት ቦታ ቅዳሴ እንሰማለን፡፡ እንግዲህ ለሥጋችን ነጻነት፣ ለነፍሳችን ድኅነት የሚጠቅመንን መምረጥ የእኛ ድርሻ ነው፡፡ ስለኾነም እሺ ብትሉ፣ ለእኔም ብትታዘዙ የምድርን በረከት ትበላላችሁ እንደ ተባልነው (ኢሳ. ፩፥፲፱) እንደ ዝሙት ያሉ አስነዋሪ ተግባራትን ከሚያስፈጽመን ሰይጣን ሸሽተን ቅዱሱን የእግዚአብሔርን መንፈስ ልንከተል ይገባናል፡፡

በአጠቃላይ መላው ምእመናን በተለይ እሳታዊ ባሕርይ የሚበረታብን ወጣቶች በምድር በልዩ ልዩ ደዌያት እንዳንያዝ፣ በሰማይም በገሃነመ እሳት እንዳንጣል ከዝሙት ሥራ ዂሉ ራሳችንን በመጠበቅ በተቀደሰው ጋብቻ ልንወሰን ያስፈልገናል፡፡ ከዝሙት ኀጢአት ነጻ ለመኾንም ፈሪሃ እግዚአብሔርን ገንዘብ ማድረግ፤ ሥጋን በጸሎት፣ በጾምና በስግደት እንደዚሁም በሥራ ማድከም፤ በስሜት አለመነዳት፤ ራስን ከስሜታዊነት መጠበቅ፤ ከዚህም ባሻገር ሞተ ወልደ እግዚአብሔርንና የቅዱሳንን ተጋድሎ ማስታወስ ዋነኛ መፍትሔዎች ናቸው፡፡

ስናውቅ በድፍረት፣ ሳናውቅ በስሕተት በሠራነው ኃጢአት እግዚአብሔር ይቅር እንዲለን ንስሓ ልንገባ ያስፈልጋል፡፡ እንደዚሁም እስመ ፍትወት ይእቲ እሞን ለኃሣራት ወለድካማት ወፃማት ወኃሣር ወበአማን ወላዲተ ሕማም ይእቲ ለሥጋውያን ወለመንፈሳውያን እስመ ይእቲ ታተልዎን ለመፍቅዳት ብዙኃት እለ ኢይትፈቀዳ ወትሬስዮን ከመ ዘይትፈቀዳ፤ የፈቲው ፆር የኃሣረ ሥጋ፣ የኃሣረ ነፍስ፣ የድካመ ሥጋ፣ የድካመ ነፍስ፣ የፃማ ሥጋ፣ የፃማ ነፍስ መገኛ ናት፡፡ ለሥጋውያንም ለመንፈሳውያንም መከራ ሥጋ መከራ ነፍስን የምታመጣ ናት፡፡ የማይወደዱ ብዙዎችን ፈቃዳት እንደሚወደዱ አድርጋ ታሳያለችና  እንደ ተባለው አምላካችን በዝሙት ከመውደቅ እንዲጠብቀን በጾም በጸሎት ልንተጋ ይገባናል፡፡

… ወንስአሎ ለእግዚአብሔር ተሰናዕዎ ወረድኤተ ወኃይለ ወምሕረተ …፤ የፈቲው ፆር የሚጸናብን አራቱ ባሕርያት ባይስማሙልን፤ አለመስማማታቸውም እግዚአብሔር ባይረዳን፤ አለመርዳቱም ኃይሉን ባያሳድርብን፤ ኃይሉን አለማሳደሩም ይቅር ባይለን ነውናይቅር በለን፤ ኃይልህን አሳድርብን፤ ርዳን፤ አራቱን ባሕርያት አስማማልንብለን እግዚአብሔርን ዘወትር እንለምነው” ተብሎ እንደ ተጻፈው በጸሎት ኃይል የሠለጠነብንን ዝሙት ድል ማድረግ ይቻለናልና (ፍት. ነገ. አን. ፳፬፣ ቍ. ፹፯-፹፰)፡፡

አምላከ ቅዱሳን እግዚአብሔር፣ በስሕተት ወይም በድፍረት የሠራነውን ዂሉ ኀጢአት ይቅር ብሎ፣ ለወደፊቱም ከኀጢአት ጠብቆ ዂላችንንም የመንግሥቱ ወራሾች ለመኾን ያብቃን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡