የጋብቻ ሕይወት እና የሩካቤ ሥርዓት – ክፍል ፬

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

ሚያዝያ ፲፬ ቀን ፳፻፲ ዓ.

ለ. መባዛትና ዘርን መተካት

ሁለተኛው የጋብቻ ዓላማ ለመባዛትና ዘርን ለመተካት ነው፡፡ እግዚአብሔር አምላክ አዳምና ሔዋንን ብዙ፤ ተባዙ፡፡ ምድርንም ሙሉአት፤ ግዙአትም” በማለት ዘራቸውን እየተኩ በምድር ይበዙ ዘንድ፣ ፍጥረታትንም ይገዙ ዘንድ አዝዟቸዋል (ዘፍ. ፩፥፳፪-፳፰፤ ፱፥፯)፡፡ በዚህ ሕግ መሠረት የሰው ልጅ መሰሉን እየተካና እየተባዛ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ትውልድ ይቀጥላል፡፡ ይህ ትእዛዝ ለእንስሳትም የተሰጠ ሕግ ቢኾንም የሰው ልጅ ግን ከፍጥረት ዂሉ የከበረ ነውና እንደ እንስሳት በዘፈቀደ ሳይኾን በሕግ ተወስኖ ይባዛና ዘሩን ይተካ ዘንድ የጋብቻ ሕግ ተሠርቶለታል፡፡ ከእንደዚህ ዓይነቱ ክቡር ጋብቻ የሚወለዱ ልጆችም የተባረኩና እግዚአብሔርን የሚፈሩ ይኾናሉ፡፡ የቅኖች ትውልድ ትባረካለች” በማለት ቅዱስ ዳዊት እንደ ተናገረው (መዝ. ፻፲፪፥፪)፡፡

ሐ. ከዝሙት መጠበቅ

ሦስተኛው የጋብቻ ዓላማ ከዝሙት ፆር ለመጠበቅ ማለትም ፍትወተ ሥጋን ለመከላከል ወይም ለመቋቋም ነው፡፡ እንደሚታወቀው የሰው ልጆች መልአካዊና እንስሳዊ ባሕርያት አሉን፡፡ በመልአካዊ ባሕርያችን እንደ መላእክት ‹‹ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ›› እያልን እግዚአብሔርን ማመስገን፣ ጾም፣ ጸሎት ይስማማናል፡፡ በእንስሳዊ ባሕርያችን ደግሞ መራብ፣ መጠማት፣ ፍትወተ ሥጋ ይሠለጥንብናል፡፡ የጋብቻ ሕይወት የዝሙትን ፆር ለማሸነፍ ከእግዚአብሔር የተሰጠን መከላከያ መንገድ ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ጋብቻ የዝሙትን ጠንቅ ለመከላከል እንደሚያስችል ሲያስረዳ ስለ ዝሙት ጠንቅ ለእያንዳንዱ ለራሱ ሚስት ትኑረው፤ ለእያንዳንዲቱ ደግሞ ለራስዋ ባል ይኑራት” በማለት አስተምሯል (፩ኛ ቆሮ. ፯፥፪-፱)፡፡ ፍትሐ ነገሥትም ሕግ ወደማፍረስ የሚያደርስ የፈቲው ፆር በብዙ ሰዎች ቢጸና ጋብቻ መፈጸም እንዲገባ ይናገራል (አንቀጽ ፳፬፣ ክፍል ፩)፡፡

በአጠቃላይ ጋብቻ፣ እንከብርበትና በጋራ እንኖርበት ዘንድ፤ እንደዚሁም ራሳችንን ከኃጢአት እንጠብቅበት ዘንድ እግዚአብሔር ያዘጋጀልን መንፈሳዊ ሥርዓት ነው፡፡ ሦስቱ የጋብቻ ዓላማዎችም ከላይ የተጠቀሱት ናቸው፡፡ የጋብቻ ዓላማዎች ጠቢብ፣ ልዑል ከሚኾን ከፈጣሪ የተሰጡ ጸጋዎች፤ ከአብርሃም፣ ከይስሐቅ፣ ከያዕቆብ የተገኙ ግብራት ናቸው፡፡ ከእነዚህ የተለየ የጋብቻ ዓላማ ሊኖር አይችልም፡፡ ወኢረከብነ አሐደ እምእሉ ዘይፈቅዳ ለሕገ አውስቦ ዘእንበለ ዘርእ ባሕቲቱ፤ ከነቢያት ከሐዋርያት አንዱ ስንኳ የግቢን ሥርዓት ‹ለዝሙት ትኹን› ብሎ ያስተማረ አላገኘንም፡፡ ልጅ ለመውለድ ብቻ ነው እንጂ” ተብሎ እንደ ተጻፈ (ፍት. ነገ. አን. ፳፬፣ ቍ. ፷)፡፡

ከዚህ ላይ የጋብቻ አስፈላጊነቱ በሦስት ዓላማዎች ብቻ የተወሰነ አለመኾኑን መረዳት ተገቢ ነው፡፡ ምክንያቱም በሦስቱ ዓላማዎች ውስጥ የሚካተቱ ብዙ ቁም ነገሮች ይኖራሉና፡፡ ለምሳሌ መረዳዳት በስሜት፣ በአሳብ፣ በገንዘብ፣ በመሳሰሉትና በሌሎችም ማኅበራዊ ዘርፎች መተጋገዝን ያጠቃልላል፡፡ ዘርን በመተካት ውስጥም ወልዶ መሳም፣ ዓይንን በዓይን ማየት፣ በወሊድ ጊዜ የሚደረግ ክብካቤና ሥርዓት ያለው የልጅ አስተዳደግ ተግባራት ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ስለዚህ ጋብቻ ዓላማው በሦስት ዋና ዋና ክፍሎች ቢጠቀስም በእነዚህ ዓላማዎች ሥር ግን ሌሎች ቁም ነገሮችም ይካተታሉ፡፡

፩.፫ ሕይወት ከጋብቻ በፊት

የጋብቻ ሕይወት በዓላማ የተዘጋጀልን ሥርዓት ይኹን እንጂ ሰውነታቸውን መቈጣጠር የሚችሉ ቢኖሩ እንዲያገቡ አይገደዱም፡፡ ማግባትም አለማግትባም አንድም በእግዚአብሔር ፈቃድ አንድ በግል ፍላጎትና ስሜት ይፈጸማልና፡፡ ነገር ግን እያንዳንዱ ከእግዚአብሔር ለራሱ የጸጋ ስጦታ አለው፤ አንዱ እንደዚህ፣ ሁለተኛውም እንደዚያ … ዂሉ እንደ ተጠራ እንዲሁ ይኑር” እንዳለ ቅዱስ ጳውሎስ (፩ኛ ቆሮ. ፯፥፯-፳)፡፡ ስለዚህ አንድ ሰው የፈቲውን ፆር ማሸነፍ ከቻለ እንዲያገባ አይገደድም ማለት ነው፡፡ ወእመሰ ኮንከ ዘኢትፈቅድ ብእሲተ ኢትኅሥሥ ኪያሃ፤ ሚስት ማግባት የማትሻ ከሆነ ሚስት ላግባ አትበል” እንዲል ፍትሐ ነገሥት፡፡ ሥርዓቱ ለሴቶችም ተመሳሳይ ነው፡፡

ጋብቻ የሚከልከልባቸው ኹኔታዎችም እንዳሉ ማወቅም ይገባናል፡፡ ለምሳሌ ሩካቤ ለመፈጸም የማያስችል (የሚከለክል) ደዌ ወይም ተፈጥሯዊ ችግር፣ ምንኵስና (ለመመንኰስ ቃል መግባት) ተተቃሾች ናቸው፡፡ ከተጋቡ በኋላ ጥላቻ እንዳይመጣ እንደዚህ ዓይነት የጤና ክሎችን አስቀድሞ ማወቅና መፍትሔ ማግኘት ያስፈልጋል፡፡ ከዚሁ ዂሉ ጋርም በእምነት መለያየት፣ እስከ ሰባት ትውልድ ድረስ ዝምድናም ጋብቻን የሚከለክሉ ጉዳዮች ናቸው፡፡

ለመጋባት ከመስማማታችን በፊት በእምነት አንድ መኾናችንን፣ በዕድሜ መመጣጠናችንንና መዋደዳችንን ማረጋገጥ ይገባል፡፡ የሁለቱ ተጋቢዎች ስምምነት፣ የቤተሰቦቻቸው ወይም የአሳዳጊዎቻቸው ፈቃድ ለጋብቻ ሕይወት አንደኛው ቅድመ ኹኔታ ነው፡፡ እንደዚሁም የሚያምኑ ከማያምኑ ጋር መጋባት የለባቸውም፡፡ ቢዋደዱም እንኳን ከመጋባት በፊት ያላመነውን (ችውን) ወደ ክርስትና ሃይማኖት መመለስና ማስጠመቅ ይኖርባቸዋል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ ለጋብቻ የተዘጋጁ ጥንዶች ዕድሜም ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ ነው፡፡ ይህም በልጅነት መንፈስ ቃል ከተጋቡ በኋላ ቃላቸውን እንዳያፈርሱ ሲባል ነው፡፡ ቃላቸውን ቢጠብቁም እንኳን ልጅ ለማሳደግና ቤተሰብን ለመምራት ሊከብዳቸው ይችላልና ነው፡፡

በዚህም ምክንያት ተገቢ ወዳልኾነ እርምጃ ማለትም ፅንስን ወደማስወረድ ዓይነት ተግባር ሊገቡ ይችላሉና የሚጋቡ ጥንዶች ለአካለ መጠን የደረሱ መኾን ይገባቸዋል፡፡ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ለወደፊቱ በትዳር ተወስነን ለመኖር የምናስብ ከኾነም ጊዜው ደርሶ አጋራችንን እስክናገኝ ድረስ በትሕትና፣ በንጽሕናና በክርስቲያናዊ ሥነ ምጋባር ጸንተን ልንኖር ይገባናል፡፡ ይህንን ለማድረግም ኾነ ዕቅዳችንን ለማሳካት እንዲቻለን ቅዱሳት መጻሕፍትን ማንበብ፣ መጾም፣ መጸለይ፣ መማር፣ ቅዳሴ ማስቀደስና ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን መቀበል ያስፈልጋል፡፡

ከዚህ ውጪ ትዳር የመመሥረት ፍላጎትና አቅም ኖሯቸው ዕድሜያቸው ከፍ በማለቱ ምክንያት አፍረው ወይም ‹‹ሰው ምን ይለኝ›› በሚል ሥጋት ተይዘው ትዳር ያልመሠረቱ ሰዎች ካሉ በጋብቻ የመኖር ዕቅድ እስካላቸው ድረስ በመዘግየታቸው ምክንያት ሳይሳቀቁ ትዳር ሊመሠርቱ ይገባል፡፡ “‹ሲያረጁ አምባር ይዋጁ› ይሉኛል” ብሎ በመሳቀቅ ጋብቻን መሸሸ ተገቢ አይደለም፡፡ ስለዚህ ጉዳይ ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ሲል ያስተምራል፤ ዳሩ ግን ማግባት ወደሚገባው ዕድሜ በደረሰ ጊዜ ስለ ድንግልናው ያፈረ ሰው ቢኖር የወደደውን ያድርግ፤ ቢያገባም ኀጢአት የለበትም፤ የወደደውን እንዲያደርግ ተፈቅዶለታል” (፩ኛ ቆሮ. ፯፥፴፮)፡፡

፩.፬ የእጮኝነት ጊዜ

ጋብቻ ለመመሥረትና የትዳር አጋር ለመምረጥ የሚያስችል ዕድሜ ላይ የደረሱ ሰዎች ለጋብቻ ከተፈቃቀዱና ከተስማሙ በኋላ በቅድሚያ ለመምህረ ንስሓቸው ይነግራሉ፡፡ ከዚያም ለወላጆቻቸው (ለአሳዳጊዎቻቸው) ያሳውቃሉ፡፡ ጋብቻ የሚመሠረተው ከዚህ በኋላ ነው፡፡ እስከዚያው ድረስ ግን ግንኙታቸው ወደ ኀጢአት እንዳይወስዳቸውና ከመጋባታቸው በፊት በሩካቤ ሥጋ እንዳይወድቁ መጠንቀቅ ይገባቸዋል፡፡ ምክንያቱም እጮኛ መምረጥ ማለት መጋባት ማለት አይደለምና፡፡ የመተጫጨት ባህልና ሥርዓትን መጠበቅም ይገባል፡፡ ይህም ፈቃድና ስምምነትን፣ ዕድሜን፣ ዝምድናን፣ እንደዚሁም ሃይማኖትን ያገናዘበ መኾን ይኖርበታል፡፡

በመተጫጨት ጊዜ ሊታሰብበት የሚገባው ሌላኛው ጉዳይ የሚጋቡት ጥንዶች የዕድሜ ደረጃ ነው፡፡ የመተጫጫና የመጋቢያ ዕድሜም የወንዶች ከሃያ ወይም ከሃያ አምስት፤ የሴቶች ደግሞ ከዐሥራ አምስት ወይም ከዐሥራ ስምንት ዓመት በላይ ሊኾን እንደሚገባው በሕገ ቤተ ክርስቲያን ተደንግጓል (ፍት. ነገ. አን. ፳፬፣ ምዕ. ፫፣ ክፍ. ፪)፡፡ ተጋቢዎቹ በዕድሜ ብዙ የተራራቁ ከኾነ በጋብቻቸው ላይ ችግር ሊያስከትል ይችላል፡፡ በተጋቢዎች መካከል ምንም ዓይነት ዝምድና እንዳይኖርም መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ በቤተ ክርስቲያን ሥርዓት መሠረት ሥጋዊና መንፈሳዊ ዝምድናን ለማስጠበቅ ሲባል እስከ ሰባት ትውልድ ድረስ መጋባት አይፈቀድም፡፡

የእጮኝነት ጊዜ፣ ጋብቻ ከምንመሠረትበት ጊዜ በፊት ማለት ከቤተሰብ ወይም ከአሳዳጊ ጋር ከምናሳልፈው ጊዜ ጀምሮ ለዓቅመ አዳም (ሔዋን) እስከምንደርስበት ያለውን የወጣትነት የዕድሜ ክልል ያጠቃልላል፡፡ ከነጠላነት እስከ እጮኝነት ያለውን ይህን ወቅት ሕገ እግዚአብሔርንና ክብራችንን በመጠበቅ በንጽሕና ማሳለፍ ይኖርብናል፡፡ እንዲህ ካደረግን የወደፊቱ የጋብቻ ሕይወታችን የሠመረ፣ ፍቅር የሞላበትና በረከት የበዛበት ይኾንልናል፡፡ ይህን የዕድሜ ክልል ክርስቲያናዊ ባልኾነ፣ ሥርዓት በሌለው መንገድ ካሳለፍነው ግን ቀጣዩ ሕይወታችንም ፈተና የበዛበት ሊኾን ይችላል፡፡ ስለዚህ በኋላ እንዳንሰናከል አስቀድመን በጠንካራ መሠረት ላይ ልንታነጽ ይገባናል፡፡

ይቆየን