የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ከምእመናን ጋር ተወያዩ።

በተ/ሥላሴ ጸጋ ኪሮስ

በሐዋሳ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን የተነሳው አለመግባባት አሁንም ቀጥሎ ማክሰኞ በ08/06/03 ዓ.ም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በተፈጠረው ግጭት ወጣቶችና ምእመናን ጉዳት ደርሶባቸዋል። እርሱን ተከትሎ ያለመግባባቱን ተዋናዮች ሰብስበው ያናገሩት የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ክቡር አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ተቃውሞን ሰላማዊ በሆነ መልኩ ብቻ መግለጥ እንደሚቻል አሳስበዋል።
 
በግጭቱ ወቅት በስፍራው እንደተገኙ የተናገሩ የዐይን ምስክር “በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በሁለት ጎራ ተለይቶ ጉባኤ ከተጀመረ ቆይቷል።” ብለው፤ ስለ ዕለቱ ክስተት ሲናገሩ “በአንደኛው ወገን የተወሰኑ ሰዎች ለጸሎት ተሰብስበው እያሉ ከቀኑ 9፡30 ሲሆን፥ ከሌላኛው ወገን በትር ይዘው በመምጣት ሁለት ልጆችን በተደጋጋሚ ሲደበድቧቸው፤ ሌላ አንዲት ምእመን ግንባሯ ላይ ተፈንክታ እንደተመለከቱ ገልጸዋል።

ከዚህ አለመግባባትና ግጭት በኋላ ከሁለቱም ወገን የተወከሉ ሃምሳ ሃምሳ ሰዎችና የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ገብርኤል በተገኙበት ከክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ክቡር አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ጋር ውይይት ተካሂዷል። በውይይቱ ወቅት ሁለቱም ያላቸው ሃሳብና ቅሬታ አቅርበዋል።

በአንደኛው ወገን የአለመግባባቶቹ መነሻና ሂደቶቹ የቀረቡ ሲሆን፥ በሌላኛው በኩል በአብዛኛው ሲነገሩ የነበሩት የማኅበረ ቅዱሳንን ጣልቃ ገብነት፥ እንዲሁም ማኅበሩን የመክሰስ ሁኔታዎች እንደነበር ምንጮቻችን ገልጸዋል።

ክቡር ርዕሰ መስተዳድሩ በውይይቱ ወቅት አጽንኦት ሠጥተው የገለጹት ነገር፥ ከእንግዲህ አንዲት ጠጠር በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንደማትወረወርና ማንኛውንም ተቃውሞ ሰላማዊ በሆነ መልኩ መግለጥ እንደሚቻል ነው።

አቶ ሽፈራው አያይዘውም “ሊቀ ጳጳሱ እዚህ ቦታ እስከተቀመጡ ድረስ በሀገረ ስብከታቸው የሊቀ ጳጳሱ ወሳኔ የቤተ ክርስቲያኒቱ የመጨረሻ ውሳኔ ነው፤ እርሱን ተቀብለን እንሄዳለን” በማለት አብራርተዋል።  

መነሻው ከ9 ወር በፊት አካባቢ እንደሆነ የሚነገርለት አለመግባባት፥ ቀኖና ቤተ ክርስቲያን ይጠበቅ፣ የቃለ ዓዋዲው መመሪያ ይከበር፣ የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ተግባራዊ ሊሆን ይገባል፤ በሚሉና ይህንን በሚቃወሙ መካከል እንደሆነ የሲዳማ፣ አማሮና ቡርጅ ልዩ ዞኖችና ወረዳዎች ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ኅሩያን ዓለም እሸት ገ/ጻድቅ ከማኅበረ ቅዱሳን የአማርኛ መካነ ድር ጋር ባደረጉት ቆይታ መግለጻቸው ይታወሳል።