የዓለም ከተማ ወረዳ ማዕከል ያሠራውን ጽሕፈት ቤት አስመረቀ።

በተስፋዬ አእምሮ
 የካቲት 29፣2003 ዓ.ም

በሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት የዓለም ከተማ ወረዳ ማዕከል ያስገነባውን ጽሕፈት ቤት የካቲት 13 ቀን 2003 ዓ.ም  አስመረቀ፡፡ 

የወረዳ ማዕከሉ ሰብሳቢ ወ/ሪት ሰላማዊት ፍስሐ በምረቃ መርሃ ግብሩ ላይ እንደገለጹት ወረዳ ማእከሉ ከተቋቋመበት ከ1992 ዓ.ም ጀምሮ የራሱ የሆነ ጽሐፈት ቤት አልነበረውም። የተለያዩ መረጃዎችም በአባላት እጅ ይቀመጡና ለጥፋት ይጋለጡ እንደነበር አስታውሰው ይኸን ችግር ለመቅረፍ የማእከሉ ጽሕፈት ቤት የሚገነባበት ቦታ ለማግኘት ለቅዱስ አማኑኤል ቤተ ክርስቲያን ሰበካ ጉባኤ ጥያቄ ቀርቦ በሰበካ ጉባኤው መልካም ፈቃድ ከ2001 ዓ.ም ጀምሮ የገንዘብ ማሰባሰብና የግንባታ ሥራው ተጀምሮ አሁን ለምረቃ በቅቷል ብለዋል፡፡

የጽሕፈት ቤቱ መገንባት የማዕከሉን አገልግሎት ለማፋጠን ከፍተኛ ድርሻ የሚኖረው ሲሆን ለጽሕፈት ቤቱ ሥራ የወጣው ወጪ ፣ ዘጠኝ ሺ ስድስት መቶ አርባ ስምንት ብር ከበጎ አድራጊዎች፣ አርባ ሦስት ሺ ሰባት መቶ ሰላሳ ስድስት ብር ከአባላት እንዲሁም ሁለት ሺ ብር ከእድር የተገኘ ሲሆን በድምሩ 55,384.00 ብር /በሃምሳ አምስት ሺህ ሦስት መቶ ሰማንያ አራት ብር/ መሆኑንና በአጠቃላይ 95 ከመቶ ግንባታው በአባላት፣ በምዕመናንና በግቢ ጉባኤያት ተሳትፎ እንደተከናወነ የደብረ ብርሃን ወረዳ ማዕከል ያደረሰን መረጃ ይጠቁማል፡፡

በዕለቱ ጥሪ የተደረገላቸው የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች፣ የወረዳ ማዕከሉ አባላት፣ የደብረ ብርሃን ማዕከልና የዋና ማዕከል ተወካዮች ተገኝተዋል፡፡