የወደቁትን እናንሣ

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

ነሐሴ ፲ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

‹‹እናንተ የአባቴ ቡሩካን፣ ዓለም ሳይፈጠር የተዘጋጀላችሁን መንግሥት ትወርሱ ዘንድ ኑ፡፡ ተርቤ አብልታችሁኛልና፤ ተጠምቼ አጠጥታችሁኛልና፤ እንግዳም ኾኜ ተቀብላችሁልና፡፡ ታርዤ አልብሳችሁኛልና፤ ታምሜም ጐብኝታችሁኛልና፤ ታስሬም ወደ እኔ መጥታችሁ ጠይቃችሁኛልና፤›› (ማቴ. ፳፭፥፴፬-፴፯) ተብሎ በቅዱስ ወንጌል እንደ ተጻፈው፣ ክርስቲያኖች የእግዚአብሔርን መንግሥት ለመውረስ ከምንበቃባቸው ትእዛዛት መካከል አንደኛው ሰዎችን መርዳት ነው፡፡ ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰዎችን መርዳት የሚያስገኘውን ሰማያዊ ዋጋ ሲገልጽም ‹‹በእኔ ካመኑ ከእነዚህ ከታናናሾች ወንድሞቼ ለአንዱ ያደረጋችሁትን ዅሉ ለእኔ አደረጋችሁት፤›› በማለት ቃል ኪዳን ሰጥቷል (ማቴ. ፳፭፥፵)፡፡

ይህን ቃል ባለማስተዋልና በሥጋዊ ስንፍና በመያዝ ለራሳችን ድሎት ብቻ የምንሽቀዳደም ራስ ወዳዶች ብዙዎች ብንኾንም፣ በአንጻሩ ቃሉን ተስፋ በማድረግ በገዛ ፈቃዳቸው ተነሣሥተው፣ በማኅበር ተሰባስበው ሰዎችን በመርዳት ክርስቲያናዊ ተግባር የሚፈጽሙ በጎ አድራጊ ምእመናን በየአገሩ አሉ፡፡ ጧሪ ቀባሪ ያጡ ሕሙማንንና አረጋውያንን የማሳከም፣ የመከባከብና ራሳቸውን እንዲችሉ የማገዝ ዓላማና ርእይ ሰንቀው በአዲስ አበባ ከተማ ከተቋቋሙ የበጎ አድራጎት ማኅበራት መካከል የወደቁትን አንሡ የነዳያን መርጃ ማኅበር አንዱ ነው፡፡ የማኅበሩ ተቋማዊ ጠባይዕና አሠራር ምን ዓይነት ነው? የገቢ ምንጩ ምንድን ነው? ሒሳብ አያያዙስ እንዴት ነው? ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን ሰዎች የሚያሰባስበው በምን ዓይነት መሥፈርት ነው? የሚሉና ሌሎች ጥያቄዎችን አንሥተንላቸው፣ የማኅበሩ መሥራች አቶ ስንታየሁ አበጀ ማብራርያ ሰጥተውናል፡፡ የተወደዳችሁ የድረ ገጻችን ተከታታዮች! በዛሬው ዝግጅታችን፣ መሥራቹ የሰጡንን ቃለ ምልልስ እና ማኅበሩ ባሳተመው ብሮሸር ላይ የተጠቀሱ ተግባራቱን መነሻ በማድረግ የማኅበሩን አገልግሎት እናስቃኛችኋለን፡፡ መልካም ንባብ!

አቶ ስንታየሁ አበጀ፣ የማኅበሩ መሥራች

የወደቁትን አንሡ የነዳያን መርጃ ማኅበር ከዐሥራ ዘጠኝ ዓመታት በፊት በአቶ ስንታየሁ አበጀ አስተባባሪነት ተመሠረተ፡፡ እኒህ ምእመን በደረሰባቸው ሥጋዊ ችግር ምክንያት ጠያቂ አጥተው በየጎዳናውና በየመቃብር ቤቱ ሲንገላቱ ኖረው ከዓመታት በኋላ ቆመው መሔድ ስለ ተቻላቸው ‹‹እግዚአብሔር በልዩ ጥበቡ እኔን ከወደቅሁበት ያነሣኝ ለትምህርት ነው፡፡ ስለዚህ እንደኔ የሚጠይቃቸው ያጡ ሰዎችን ከየወደቁበት ማንሣት አለብኝ›› የሚል መልካም ርእይ ሰንቀው፣ ከበጎ ፈቃደኞች ጋር ኾነው መስከረም ፩ ቀን ፲፱፻፺ ዓ.ም ‹‹የወደቁትን አንሡ›› በሚል ስያሜ የነዳያን መርጃ ማኅበር አቋቋሙ፡፡ ማኅበሩ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ነዳያንን የመደገፍ፣ አረጋውያንን የመንከባከብና ጧሪ ቀባሪ ያጡ ወገኖችን የመርዳት ተልእኮውን ቀጥሏል፡፡

መሥራቹ እንደ ገለጹልን ማኅበሩ ለዓላማው ማስፈጸሚያ የሚውለውን የገቢ ምንጭ የሚያገኘው ከአባላቱ ወርኃዊ መዋጮ፣ እንደዚሁም በአገር ውስጥና በውጭ አገር ከሚኖሩ በጎ አድራጊዎች ነው፡፡ በሒሳብ አያያዝም ዘመናዊና ሕጋዊ አሠራርን በመከተል ገቢውንና ወጪውን በደረሰኝ ይቈጣጠራል፤ ኦዲትም ያስደርጋል፡፡ የሚተዳደረውም በቦርድ አወቃቀር ሲኾን፣ ሕጋዊ ፈቃድና እውቅና አግኝቶ በበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት ኤጀንሲ ተመዝግቧል፡፡ የራሱ መተዳደርያ ደንብና ስልታዊ ዕቅድም አዘጋጅቷል፡፡ ወደፊት ለሚያከናውናቸው ተግባራትም ከፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ፣ ከሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ጋር የፕሮጀክት ስምምነት ተፈራርሟል፡፡ ማኅበሩ ዘር፣ ሃይማኖት፣ ፆታ ሳይለይ ልዩ ርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች ከሠላሳ በላይ በሚኾኑ ሠራተኞቹ አማካይነት ድጋና ክብካቤ ያደርጋል፡፡ በዚህ ተግባሩ ባበረከተው አገራዊ አስተዋጽዖም በየጊዜው ከመንግሥትና ከሌሎች ልዩ ልዩ ተቋማት የምስጋና ገጸ በረከትና የሜዳልያ ሽልማት ተበርክቶለታል፡፡

የማኅበሩ ማእከል ውጫዊና ውስጣዊ ገጽታ በከፊል

ከጽ/ቤቱ ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው ማኅበሩ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ እስከ ፳፻፰ ዓ.ም ድረስ ለስድስት መቶ ሃያ ሦስት ሰዎች የምግብ፣ የመጠለያና የሕክምና ድጋፍ አድርጓል፡፡ ከእነዚህ መካከል ሁለት መቶ አንዱ በማኅበሩ በተደረገላቸው ርዳታ ከሕመማቸው ተፈውሰዋል፡፡ አራቱ በማኅበሩ ውስጥ ተቀጥረው በማገልገል ላይ ሲኾኑ፣ ቀሪዎቹ ደግሞ በልዩ ልዩ የሥራ መስክ ተሰማርተው ራሳቸውን እያስተዳደሩ ነው፡፡ ሦስት መቶ ዐሥራ ሁለቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡ ማኅበሩ ካሁን በፊት ቤት ተከራይቶ አገልግሎት ሲሰጥ የቆየ ሲኾን፣ በአሁኑ ሰዓት ደግሞ በጉለሌ ክፍለ ከተማ ፈረንሳይ ለጋስዮን አንቀጸ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን አካባቢ ከመንግሥት በተሰጠው ቦታ ባስገነባው የአረጋውያን መጦርያና መንከባከቢያ በርካታ ሕሙማንንና አረጋውያንን አሰባስቦ የምግብ፣ የልብስ፣ የመጠለያና የሕክምና አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡ ከዚህ ዓለም በሞት የሚለዩትንም በክብር እንዲሸኙ ያደርጋል፡፡ በዚህ ዓመትም አገልግሎቱን በይበልጥ አጠናክሮ በከፍተኛ ባለሙያዎች በመታገዝ ከሦስት መቶ በላይ አረጋውያንን በማእከሉ በማሰባሰብ፤ ለሦስት መቶ አረጋውያን የተመላላሽና የቤት ለቤት ድጋፍ በማድረግ፤ እንደዚሁም ለአረጋውያኑና ለተንከባካቢዎቻቸው ልዩ ልዩ ሥልጠናዎችን በመስጠት የበጎ አድራጎት ተልእኮውን ሲወጣ ቆይቷል፤ ወደፊትም ይቀጥላል፡፡

ጕብኝት ባደረግንበት ወቅት እንዳስተዋልነው በማኅበሩ እየተጦሩ ከሚገኙ ወገኖች መካከል አንዳንዶቹ የአብነት መምህራን፣ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች፣ በመንግሥትና በግል ድርጅቶች ሓላፊነት የነበራቸው ሰዎች ናቸው፡፡ እነዚህ የቤተ ክርስቲያንና የአገር ባለውለታዎች በሕመም፣ በጤና እና በእርጅና ምክንያት የአልጋ ቁራኛ፣ የደዌ ዳኛ ኾነው ጎዳና ላይ በወደቁበት ወቅት ይህ ማኅበር ደርሶላቸው አስፈላጊውን ዅሉ ድጋፍ እያደረገላቸው ይገኛል፡፡ በተለይ የአእምሮ ሕሙማንና ከአንድ በላይ በኾነ የጤና እክል የተጠቁ ማለትም የማየትም የመስማትም የመንቀሳቀስም ችግር ያለባቸውና ሰውነታቸውን መቈጣጠር የማይችሉ አባቶች፣ እናቶች፣ ወንድሞችና እኅቶች ኹኔታ ልብን ይነካል፡፡ እነዚህ ወገኖች የሚንቀሳቀሱትም፣ የሚመገቡትም፣ የሚለብሱትም፣ የሚጸዳዱትም በሰው ርዳታ ነው፡፡ እነርሱን ያየ ሰው የማኅበሩን ዓላማ በግልጽ ይረዳዋል የሚል እምነት አለን፡፡ የማኅበሩ መሥራች እንደ ነገሩን የሠራተኞችን ደመወዝ ሳይጨምር ለሕሙማኑ የዳይፐር መግዣ ብቻ በየቀኑ ከአንድ ሺሕ አራት መቶ ስልሳ አምስት ብር በላይ ወጪ ይደረጋል፡፡ ይህም ማኅበሩ ሰውን ለመርዳት ሲል የሚከፍለውን መሥዋዕትነትና የሚያሳልፈውን ውጣ ውረድ የሚያመለክት ነው፡፡

በማእከሉ ድጋፍ ከሚደረግላቸው ሕሙማንና አረጋውያን ጥቂቶቹ

በአጠቃላይ ‹‹መልካም ሥራ የክፉ ቀን ስንቅ ነው›› በሚለው መሪ ቃሉ የሚታወቀው የወደቁትን አንሡ የነዳያን መርጃ ማኅበር በጤና፣ በእርጅና ወይም በሌላ ልዩ ልዩ ምክንያት በየመንገዱ ወድቀው የሚለምኑ ወገኖችን በማሰባሰብ፤ እንደዚሁም በያሉበት ቦታ ባለሙያዎችን በመላክ የሕክምና፣ የምግብ እና የልብስ ድጋፍ እንዲያገኙ ያደርጋል፡፡ ለወደፊትም ይህን ተግባሩን በስፋት አጠናክሮ ለመቀጠል ዕቅድ አውጥቶ በመተግበር ላይ ነው፡፡ የማእከሉ ክሊኒክ በአካባቢው ለሚገኙ ድጋፍ ፈላጊ የኅብረተሰብ ክፍሎች የሕክምና አገልግሎት እንዲሰጥ ማድረግ፤ ተጨማሪ የመጠለያና የሆስፒታል ተቋማትን መገንባት፤ የጎዳና ላይ ምጽዋትን ተቋማዊ በማድረግ ነዳያን ወጥ በኾነ መንገድ ርዳታ እንዲያገኙ ማመቻቸት፤ ከርዳታ ድርጅቶችና በጎ አድራጎት ማኅበራት ጋር በጥምረት በመሥራት የአረጋውያንን ችግር በጋራ መፍታት ከማኅበሩ ዕቅዶች መካከል የሚጠቀሱ ተግባራት ናቸው፡፡

‹‹ስድስቱ ቃላተ ወንጌል በወደቁትን አንሡ የነዳያን መርጃ ማኅበር ውስጥ ይፈጸማሉ፤›› የሚሉት የማኅበሩ መሥራች አቶ ስንታየሁ አበጀ የየተቋማት ሠራተኞች፣ የድርጅት ባለቤቶች በጥቅሉ በጎ አድራጊ ወገኖች መጥተው ሕሙማኑን በመጠየቅና ቦታውን በመጐብኘት፣ የሚቻላቸው ደግሞ በምግብ፣ በቁሳቁስ (ልብስ፣ ፍራሽ፣ አልጋ፣ ወዘተ.) አቅርቦት እንደዚሁም የገንዘብ፣ የጉልበትና የሐሳብ ድጋፍ በማድረግ ቢተባበሩ የወደቁ ወገኖችን በማንሣት፣ ነዳያንን በመደገፍ፣ የታመሙትን በማሳከምና አረጋውያንን በመከንከባከብ ማኅበሩ ከዚህ ቀደሙ በበለጠ ሓላፊነቱን በአግባቡ ለመወጣት እንደሚቻለው አስረድተዋል፡፡ መሥራቹ እንደ ነገሩን ክርስትና፣ ሰርግ፣ ምረቃ፣ ተዝካርና የመሳሰሉ መርሐ ግብሮችን ማኅበሩ በሚያከራያቸው አዳራሾች ማዘጋጀት ደግሞ ሌላው የርዳታ ማድረጊያ መንገድ ነው፡፡ በመጨረሻም ላለፉት ዓመታት በልዩ ልዩ መንገድ ማኅበሩን በመደገፍ፤ እንደዚሁም ለትውልድ እንዲተላለፍ ኾኖ በታነጸው የአረጋውያን መጦርያ ማእከልና ክሊኒክ ግንባታ በመሳተፍ ላበረከተው አስተዋጽዖ አቶ ስንታየሁ ኅብረተሰቡን በእግዚአብሔር ስም አመስግነው፣ ‹‹ወደፊትም ማኅበሩ በሚያከናውናቸው ዘርፈ ብዙ ተግባራት ዓቅሙ በሚፈቅደው ዅሉ በመሳተፍ ኅብረተሰቡ ታሪካዊ አሻራውን እንዲያኖርና ወገናዊ ግዴታውን እንዲወጣ ይኹን›› ሲሉ በአረጋውያንና በዓቅመ ደካሞች ስም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

አምላካችን በመንግሥቱ ያስበን ዘንድ ዅላችንም ከማኅበሩ ጋር በመኾን የወደቁትን እናንሣ የዝግጅት ክፍላችን መልእክት ነው፡፡ ማኅበሩን መደገፍ፣ በአባልነት መሳተፍ ወይም በመጦርያ ማእከሉ የሚገኙ ሕሙማንንና አረጋውያንን መጠየቅ ለምትፈልጉ የማእከሉ አድራሻ፡- አዲስ አበባ ከተማ የካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 01 ፈረንሳይ ለጋስዮን ከገነተ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን 600 ሜትር ገባ ብሎ ራስ ካሣ በሚባለው ሰፈር ከአንቀጸ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን አጠገብ ነው፡፡ ስለ ማኅበሩ አገልግሎት የበለጠ መረጃ ለማግኘትም በሚከተሉት አድራሻዎች መጠየቅ ይቻላል፡፡

የቢሮ ስልክ ቍጥር፡- +251-111-243-401

አቶ ስንታየሁ አበጀ፡- 09 12 01 70 32 /09 35 99 92 92

ወ/ሮ ዓይናለም ኃይሌ፡- 09 11 23 91 59 /09 35 40 17 17

የፓስታ ሳጥን ቍጥር፡- 25404

E-mail፡- yewodekutnansu@gmail.com

aynalemamit@yahoo.com

Web site፡- www.yewedekutnansu.org

ገንዘብ በባንክ ገቢ ማድረግ የምትፈልጉ፣ የወደቁትን አንሡ የነዳያን መርጃ ማኅበር፡-

  1. በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መሐል ከተማ ቅርንጫፍ፣ የተንቀሳቃሽ ሒሳብ ቍጥር፡- 10000 0454 4513 ወይም 10000 2418 3959
  2. ኅብረት ባንክ ሒሳብ ቍጥር፡- 1141 1161 0272 1018 አዲስ አበባ ኢትዮጵያ

ብላችሁ እንድትልኩ ማኅበሩ ይጠይቃል፡፡ ገንዘቡ ወደ ባንክ ከገባ በኋላም ለሒሳብ ቍጥጥር ያመች ዘንድ በሦስት ኮፒ አሠርታችሁ አንዱን ኮፒ ለማኅበሩ እንድታደርሱ በአክብሮት ያሳስባል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡