የእመቤታችንን ስደት ስናስብ የተሰደዱትን በማሰብ ይሁን

ለክርስቲያን ዓመታት፣ ወራትና ቀናት በሙሉ የተቀደሱ ናቸው፡፡ እያንዳንዱ ቀን በእግዚአብሔር ቸርነት፣ በቅዱሳን መልካም ምግባር ተቀድሷል፡፡ ለዚህም ነው ቤተክርስቲያን በአንድ ዓመት ውስጥ የሚገኙ 365 ቀናት በቅዱሳን ስም ተሰይመው የሚዘከሩት፡፡
ምእመናን ቤተክርስቲያናቸው በሠራችላቸው ሥርዓት መሠረት በፍቅር በደስታ ከሚዘከሩት ዕለታት ደግሞ ከመስከረም 26 እስከ ኅዳር 6 ቀን የሚዘከረው የእመቤታትን ቅድስት ድንግል ማርያምና የልጇ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ስደት አንዱ ነው፡፡

የእመቤታችን ስደት የመጀመሪያው የአዲስ ኪዳን ስደት ነው፡፡ ወንጌላዊው ማቴዎስ እንደሚለው፤ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተወለደበት ጊዜ ሰብአ ሰገል የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ወዴት ነው? እያሉ በመጠየቅ ወደ ኢየሩሳሌም ሔደው ነበር፡፡ በዚያ ዘመን ምድረ እስራኤልን ይገዛ የነበረው ሄሮድስ የአይሁድ ንጉሥ ወዴት አለ የሚለውን ቃል ሰምቶ፤ ከኔ ሌላ ንጉሥ ማን አለ? በማለት በአማካሪዎቹ ግፊት ከአንድ ዓመት ተኩል እስከ ሁለት ዓመት የሚሆን ዕድሜ ያላቸውን ሕፃናት እንዲገደሉ አደረገ፡፡
 
በዚያን ጊዜ «እነሆ የጌታ መልአክ በሕልም ለዮሴፍ ታይቶ ሄሮድስ ሕፃኑን ሊገድለው ይፈልገዋልና ተነሣ፤ እናቱንና ሕፃኑን ይዘህ ወደ ግብጽ ሽሽ፤ እስክነግርህም ድረስ በዚያ ተቀመጥ አለው»፤ እርሱም ተነሥቶ ሕፃኑንና እናቱን በሌሊት ያዘና ከጌታ ዘንድ በነቢይ ልጄን ከግብጽ ጠራሁት የተባለው እንዲፈጸም ወደ ግብጽ ሔደ፡፡ ሄሮድስ እስኪሞት ድረስም በዚያ ኖረ፡፡ /ማቴ 2-13-15/ ተብሎ እንደተጻፈ ሁሉ፤ እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ይዛ፣ ዮሴፍና ሰሎሜን አስከትላ ሦስት ዓመት ከስድስት ወር በግብጽ አውራጃዎች ስደተኛ በመሆን ኖራለች፡፡

ነቢያት ስለጌታ ትንቢት በመናገራቸው፣ እመቤታችን የጌታ እናት በመሆኗ፣ ሐዋርያት ስለጌታ በማስተማራቸው ተሰደዋል፡፡

የጌታ አገልጋይም እናትም የሆነችው የእመቤታችን ስደት ግን. . . ከሁሉ የሚለይ ነው፡፡ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስና የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያምን ስደት ልዩ የሚያደርገው: –

1.    ሕግን በመተላፉ ከገነት ተሰዶ የነበረውን አዳምን ለመካስ የተደረገ በመሆኑ
2.    በግብጽ ነግሦ የነበረውን አምልኮት ጣኦት ለማሳደድ የተደረገ ስለሆነ የጌታችንና የእናቱ ስደት ልዩ ነው፡፡

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከናዝሬት ወደ ግብጽ ስትሰደድ የቀን ሐሩር የሌሊት ቁር አግኝቷታል፡፡ እሾህ እየወጋት እንቀፋት እየመታት ተጉዛለች /ተሰዳለች/፤ በስደቷም ረሃብና ጥም፣ ችግርና መከራ ደርሶባታል፡፡ በበረሃው ወንበዴዎችን ባየች ጊዜም በስደት ከሄሮድስ ጭካኔ ከሀገር ያወጣሁትን ልጄን ይገድልብኛል ብላ መሪር እንባ አልቅሳለች፡፡

በስደቷ ወቅት በደረሰባት ረሐብና ጥም የተነሣ ወደ መንደር ገብታ ብትለምን በችግር ምክንያት የሰው ፊት ማየት ከእሳት የበለጠ ወላፈኑ ስለሚያቃጥል የሰው ፊት ገርፏታል፡፡ የትእማን ቤተሰቦች ዘብተውባታል፡፡

«ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ዓለም የመጣው ሸክማችንን ሊሸከም ነውና ውኃውን ለፍጥረታት የሚሰጥ እርሱ እየጠማው፤ እንስሳትን የሚመግብ እየራበው ምድርን በልምላሜ የሚያለብስ፣ ተራቁቶ የኛን ከገነት መሰደድ የመጣብንን ዕዳ ሊክስልን ከእናቱ ጋር ተሰደደ፤ ድንግል ማርያምም የአምላክ እናት ሆና መከራን ቀመሰች፡፡ ጌታን አዝላ በረሐብ አለንጋ ተገረፈች፡፡

በመጨረሻ ግን ያ ሁሉ የመከራና የስቃይ ስደት ሲያበቃ «አንቺ ሱላማጢስ ሆይ ተመለሽ» ሲል በመኃልየ ማኀልይ ዘሰሎሞን ተነግሮ የነበረው ትንቢት ይፈጸም ዘንድ ከዚያ ሁሉ መከራና ስደት ልጇን ይዛ ወደ ናዝሬት ተመልሳለች፡፡

የእመቤታችንን ስደት ስናስብ «ሲነቅፏችሁና ሲያሳድዷችሁ በእኔም ምክንያት ክፉውን ሁሉ በውሸት ሲነግሩባችሁ ብፁዓን ናችሁ፡፡ ዋጋችሁ በሰማያት ታላቅ ነውና ደስ ይበላችሁ ሐሴትም አድርጉ፡፡ ከእናንተም በፊት የነበሩትን ነብያት እንዲሁ አሳድደዋቸዋልና» /ማቴ 5-11/ የሚለውን የስደት ዋጋ ጭምር እያሰብን መሆን ይገባል፡፡

ይህንንም የእመቤታችንን ስደት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ከመስከረም 26 እስከ ኅዳር 6 ድረስ በማኅሌትና በመዝሙር ትዘክራለች፡፡ ካህናቱም በዕለተ ሰንበት ከምሽት ጀምረው በማኅሌትና በመዝሙር ምስለ ፍቁር ወልዳን /የልጇ እና የእርሷ/ ሥዕል ይዘው ቤተክርስቲያኑን ይዞራሉ፡፡

ይህም የእመቤታችንን ስደት ለማጠየቅ ነው፡፡ ሌሎችም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የደረሰባቸውን መከራ ለማስታወስ የፍቃድ ጾም ይጾማሉ፡፡

እኛ ክርስቲያኖች በቅድስት ቤተክርስቲያን ተገኝተን በመንፈስ የሩቁን አቅርበን የእመቤታችንን ስደት በእምነት እያየን በማኅሌተ ጽጌ ድርሰታችን በዜማ «መልካሟ ርግብ ማርያም ሆይ ንጹሕ፣ ፀአዳ ፣ቀይህና ብሩህ የሚሆን ልጅሽን ታቅፈሽ ርኅሩኅ የሆነ ቅዱስ ሚካኤልና ቅዱስ ገብርኤልን አስከትለሽ ከሐዘናችንና ከችግራችን ታረጋጊን ዘንድ ፈጥነሽ ድረሽልን» ልንላት ያስፈልጋል፡፡

በቅዳሴያችንም «ድንግል ሆይ ርጉም በሆነ ሄሮድስ ዘመን ከልጅሽ ጋር ከሀገር ሀገር ስትሸሺ ከአንቺ ጋር መሰደዱን አሳስቢ፤ ድንግል ሆይ ከዓይንሸ የፈሰሰውንና በተወደደ ልጅሽ ፊት የወረደውን መሪር እንባ አሳስቢ፡፡ ድንግል ሆይ ረሐቡንና ጥሙን፣ ችግሩንና ሐዘኑን፣ ከእርሱ ጋር የደረሰብሽንም ጭንቅ ሁሉ አሳስቢ እንላለን፡፡

በዚህ መታሰቢያ ወቅት እመቤታችን ከልጇ ጋር መሰደዷን ማስታወስ ብቻ ሳይሆን እኛም በመንፈስ አብረን ከእመቤታችን ጋር መሰደድ ይገባናል፡፡ የመሰደድ ዋጋው ብፅእና ነውና፡፡ ነገር ግን ወዴት እንደምንሰደድ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ ዛሬ ብዙዎች ከጽድቅ ወደ ኃጢአት፣ ከብርሃን ወደ ጨለማ፣ ከእውነት ወደ ሐሰት፣ ከፍቅር ወደ ጸብ ተሰደዋል፡፡ የኛ ስደት ግን መሆን ያለበት ከኃጢአት ወደ ጽድቅ፣ ከጨለማ ወደ ብርሃን፣ ከሞተ ወደ ሕይወት፣ ከሐሰት ወደ እውነት፣ ከጥላቻና ክስ ወደ ፍቅርና መተሳሰብ፣ ከክህደት ወደ እምነት መሰደድ ያስፈልጋል፡፡ ከማሳደድ ይልቅ መሰደድ ይሻላልና፡፡

ዛሬ ብዙዎች ለሥጋ ተድላ በኃጢአት እየተሰደዱ ነው፡፡ እነዚህን ወገኖቻችን ከኃጢአት ስደት እንዲመለሱ በማስተ ማር፣ በመምከርና በመገሰጽ ጭምር ልንመልሳቸው ያስፈለጋል፡፡ መምህራንም ለኃጢአት የተሰደዱትን ወገኖች የንስሐ ፍሬ እንዲያፈሩ ሕይወት የሆነውን ወንጌል ሊያስተምሯቸው ይገባል፡፡

በተለያዩ የዓለም ክፍላት በችግርና በተለያዩ ምክንያቶች ከሀገር የተሰደዱትን በጸሎት ማሰብ በሚያስፈልጉ ድጋፎች ሁሉ መርዳት የክርስቲያን የዘወትር ምግባሩ ቢሆንም በተለይ በዚህ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ስደት መታሰቢያ ጊዜ በልዩ ሁኔታ በችግር የተሰደዱትን ልናስባቸው ያስፈልጋል፡፡

የእመቤታችንን ስደት ስናስብ በኃጢአትና በመከራ የተሰደዱትን በማሰብ ይሁን፡፡

 
ወስብሐት ለእግዚአብሔ