“የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሚና በአየር ንብረት ለውጥ” በሚል መሪ ቃል ጥናታዊ የውይይት መድረክ ተካሄደ

ዲ/ን ቴዎድሮስ ኃይሉ
 
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን ጥናትና ምርምር ማዕከል “የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሚና በአየር ንብረት ለውጥ“ በሚል መሪ ቃል ሰኔ 18 ቀን 2003 ዓ.ም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዝየም መሰብሰቢያ አዳራሽ ጥናታዊ የውይይት መድረክ ተካሄደ፡፡
 
በዕለቱ አምስት ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡ ከነዚህም ጥናታዊ ጽሑፎች በጠዋቱ ክፍለ ጊዜ “የዓባይ ወንዝና የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን” የሚል ጥናታዊ ጽሑፍ በአቶ ዘሪሁን አበበ ቀርቧል፡፡ አቶ ዘሪሁን በጥናታቸው በዋናነት የውኃ ፖለቲካ ከምሥራቅ አባይ ተፋሰስ/ናይል/ አንጻር፣ በዚህም መሠረት ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምን ዓይነት ቁርኝት አላት? የውሃው ፖለቲካ እንዴት ነው ተጽዕኖ ሊፈጥርባት የሚችለው? ምን ዓይነት የራሷ የሆነ ጥቅም አላት?  የሚለውን በማሳየት ሰፋ ያለ የጥናት ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በመቀጠል በአቶ ወንድወሰን ሚቻጎ “የአየር ንብረት ለውጥና ሃይማኖታዊ እሳቤ” በሚል ጥናታዊ ጽሑፍ ቀርቧል፡፡ አቶ ወንድወሰን በጥናታቸው የኢትዮጵያ ኦርቶዶከስ ቤተ ክርስቲያን በአየር ለውጥ ላይ ምን ዓይነት ሚና አላት? ዕውቀት በአየር ንብረት ለውጥ ላይ ያለው አስተዋጽኦና የሃይማኖት እሳቤ በአየር ንብረት ለውጥ ላይ አስተዋጽኦ የሚያመጣው ምንድን ነው? በሚል ሰፋ ያለ የጥናታዊ ጽሑፍ መነሻቸውን አቅርበው ጥያቄዎችና አስተያየቶች ከተሰጡ በኋላ የጠዋቱ ክፍለ ጊዜ ተጠናቋል፡፡

ከሰዓት በኋላ በነበረው ክፍለ ጊዜ ሦስት ጥናታዊ ጽሑፎች የቀረቡ ሲሆን በመጀመሪያው ክፍለ ጊዜ “የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን አስተዋጽኦ የካርቦን ልቀትን ለመከላከል “በሚል በዲያቆን ቱሉ ቶላ ቀርቧል፡፡ ዲያቆን ቱሉ በአዲስ አበባ በሚገኙ ሰባት ቀደምት አድባራትና ገዳማት ላይ ተመርኩዘው የሠሩትን ጥናት አቅርበዋል፤ በመቀጠል በአቶ ተስፋዬ አራጌ “የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሚና ለተፈጥሮ ደን ጥበቃና እንክብካቤ” በሚል በደቡብ ጎንደር በሚገኝ ሦስት በተመረጡ ወረዳዎች ባሉ አስር አብያተ ክርስቲያናት ስለ ደንና አጠባበቅ የተደረገ ጥናት አቅርበዋል፣ በመጨረሻም በአቶ ብርሃኑ በላይ “የቅብዓ ሜሮን ዕፅዋት የዳሰሳ ጥናት” በሚል ጥናት፣ ሜሮንን ለማዘጋጀት የምንጠቀምባቸው ዕፅዋት እነማን ናቸው? በቀጣይስ እነዚህ ዕፅዋቶች እንዴት ነው? ማሳደግና መንከባከብ የምንችለው? በሚል መነሻ ጥናታቸውን አቅርበዋል፡፡

ከጥናታዊ ጽሑፎች ጋር ተያያዥነት ካላቸው ከአዲስ አባባ ዩኒቨርሲቲ፣ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማት እንዲሁም በግል የተጋበዙ ከ300 በላይ እንግዶች የተገኘበት ሲሆን፣ በመጨረሻም የጥናትና ምርምር ማዕከሉ አማካሪ፣ የሰቲት ሁመራ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በብፁዕ አቡነ ሉቃስ “ጊዜ ገቢር ለእግዚአብሔር” በሚል ርዕስ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ ተሰጥቶ የመርሐ ግብሩ ፍጻሜ ሆኗል፡፡

የማኅበረ ቅዱሳን ጥናትና ምርምር ማዕከል ከተመሠረተ ጀምሮ በርካታ ጥናታዊ የውይይት መድረኮችን ያካሄደ ሲሆን ባለፈው ዓመትም የመጀመሪያውን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ጥናት መጽሔት አሳትሞ አበርክቷል፡፡