የአባቴ ተረቶች

ሕይወት ቦጋለ

ሐምሌ 16/2003 ዓ.ም.

 
ሌሊቱን ለረጅም ሰዓታት የዘነበው ዝናብ አባርቶ ቦታውን ለንጋት አብሳሪዋ ፀሐይ ከለቀቀ ቆየት ብሏል፡፡
ከመኝታዬ የተነሣሁት አረፋፍጄ ቢሆንም አሁንም የመኝታ ቤቴን መስኮት ከፍቼ አውራ መንገዱን እየቃኘሁ ነው፡፡ ለምን እንደሆነ ባላውቅም ዘወትር ከእንቅልፌ ስነሣ ሰፈራችን ሰላም ለመሆኗ ማረጋገጫዬ የመኝታ ቤቴ መስኮት ናት፡፡
ሁሉም ወደየ ጉዳዩ እንደየ ሐሳቡ መለስ ቀለስ ይለዋል፡፡ የቸኮለ ይሮጣል፣ ቀደም ብሎ የተነሣው ዘና ብሎ ይራመዳል፡፡ ሥራ ፈቱ ይንገላወድበታል ብቻ መንገዱ ለሁሉም ያው መንገድ ነው፡፡ እንደ እኔ ላጤነው ከቁም ነገር ቆጥሮ ላየው ደግሞ ለዓይን ወይም ለአእምሮ የሚሆን አንድ ጉዳይ አይታጣበትም፡፡ ያባቴን ተረቶች ናፋቂ ነኝና ወደሳሎን ወጣሁ፡፡

“አቤቱ ቃሌን አድምጥ፣
ጩኸቴንም አስተውል፣
የልመናዬን ቃል አድምጥ፣
ንጉሤና አምላኬ ሆይ
አቤቱ ወደ አንተ እጸልያለሁና
በማለዳ ቃሌን ስማኝ፤
በማለዳ ፊትህ እቆማለሁ…”

አባቴ አሁንም የጠዋት ጸሎቱን አልጨረሰም እናቴ ደግሞ እንደወትሮዋ ቁርስ ለማዘጋጀት ተፍ… ተፍ እያለች ነው፡፡ ከእናቴ ፈጣንና ፍልቅልቅነት ጋር ያባቴ የእርጋታና የዝምተኝነት ባህሪ ተስማምቶ መኖሩ የሚገርመኝ ነገር ነው፡፡ ለነገሩ “ዓለም የተቃራኒ ነገሮች ድምር ውጤት ናት” ይላል አንድ ስሙ የጠፋኝ ፈላስፋ፡፡
አባቴ ጸሎቱን ጨርሶ ወደ ቤት ዘልቆ አሮጌው ሶፋ ላይ ተቀምጧል፡፡

“እንደምን አደርክ አባባ”
እግዚአብሔር ይመስገን ልጄ አንቺስ እንዴት አደርሽ?”

እናቴ ቁርስ አቅርባለች እኔም ዘወትር እንደማደርገው ከአባቴ እግር ስር ቁጭ ብዬ ጉርሻውን እየተቀበልኩ ቁርሴን እየበላሁ ነው፡፡
በአባቴ የሚነገሩ ታሪኮችና ተረቶች ከኋላቸው የሚያስከትሉትን ምክሮችና ቁም ነገሮችን ሳስብ እነዚህ ቱባ እውቀቶች ለሁሉም ቢደርሱ እንዴት ይጠቅሙ ነበር አያልኩ አስባለሁ፡፡
ዘወትር ከአባቴ የምከትባቸውን ተረቶች መጽሐፍ ለማድረግ ድንገት ሐሳቡ በአእምሮዬ ሽው ያለ እንደሆን ከእጅ ወደ አፍ የሆነውን የኛን ቤት ኑሮ አስታውሼ ተስፋ እቆርጣለሁ፡፡

“ጎሽ ልጄ የሚጠጣ ውሃ በጠርሙስ ሞልተሽ አምጭልኝ” የሚለው ያባቴ ትእዛዝ ከገባሁበት የሐሳብ ማዕበል መንጥቆ አወጣኝ፡፡
“የሚሚዬ አባት ለሚካኤል የጠመኩት ጠላ እኮ አላለቀም.. ከሱ ይጠጡ” እናቴ ነበረች፡፡
“ከዘንድሮስ ጠላ ውሃው ይሻለኛል ተይው” የሚለውን ያባቴን ምላሽ ስሰማ አባቴ በዘንድሮ ላይ ያለው ምሬት የተለየ መሆኑ እየገረመኝ ውሃውን አቀረብኩለት፡፡
“እሰይ እሰይ! እሰይ!” እያለ ጥሙን ይቆርጣል፡፡

“በአባቶቻችን ጊዜ ብዙ ሠርቶ እንዳልሠራ የሚሆን ሰው ማግኘት ቀላል ነበር፡፡ ስለ ብቁና ጎበዝ ሰው ምስክሩ ሥራው ብቻ ነበር ልጄ፡፡ ቢሆንም የዝና ናፋቂዎች ጥቂቶች አልነበሩም፡፡ ብዙኃኑ ግን ያለ አግባብ ሙገሳን እንደ ስድብ እንቆጥር ነበር፡፡ እከሌ እኮ ጀግና ነው ቢሉን ስለ ጀግንነቱ ማረጋገጫ ከእርሱው እንጂ በዝናው አናምንም ነበር፡፡

“ልጄ ዘንድሮ በዓይን የሚታይ በጎ ሥራ ጠፋ፤ እስቲ ከዓይን ተርፎ ልብን የሚሞላ ተግባር የሠራውን ሰው አሳይኝ?”  ድንገተኛው ያባቴ ጥያቄ አስደነገጠኝ፡፡ አባቴ የከበደኝን ጥያቄ ከኔ ምላሽ ሳይጠብቅ መንገሩን ቀጠለ፡፡

“ዘንድሮ ጥቂት ተሠርቶ ለስምና ለዝና የሚሮጥበት ጊዜ ነው፡፡ ከተግባር ስም የቀደመበት የውዳሴ ከንቱ ዘመን፡፡” እያለ አባቴ መናገሩን ቀጠለ፡፡ “ልጄ ስላንቺ ተግባርሽ እንጂ ዝናሽ አይመስክር” የምትለዋን የዘወትር ንግግሩን አስተውያት ባላውቅም ዘወትር መስማቴን አስታውሳለሁ የዛሬው አባቴ ገፅታ ከወትሮው በተለየ መልኩ ትካዜና ደስታ አልባ ሆኗል፡፡

ምን ሊመክረኝ ይሆን እያልኩ ወደ ጉልበቱ ተጠጋሁ

“ከአባቶቻችን ሐዋርያት ትሕትናን፣ ባለብዙ ዕውቀት ሆነው እንዳላወቁ፤ ባለጸጋ ሆነው እንዳልሆኑ መምሰልን መማር ይገባናል ልጄ ስም ከሥራ መቅደም የለበትም ልጄ…”

ቀበሮ ሥጋ በአፏ የያዘች ቁራ ትመለከትና ከመሬት ሆና “እሜት ቁራ ከአእዋፍ መካከል እንዳንቺ ያለ ውብና ቆንጆ፤ አስተዋይና ባለ አእምሮ የለም” እያለች ታሞግሳት ጀመር፡፡የቁራን ዝምታ ያልወደደችው እሜት ቀበሮ ውዳሴዋን ግን አላቆመችም

“እሜት ቁራ ሆይ በምድር ለሚገ አእዋፍ ሁሉ ንግሥት የምትሆን ፈለግን፤ በምድር ሁሉ ዞርን ግን አላገኘንም ድንገት አንቺን አየን፡፡ በዚህ ውበትሽ ላይ ድምፅሽ ቢያምር አንቺን ለንግሥትነት እንመርጥሻለንና እስቲ ድምፅሽን አሰሚኝ አለች ቀበሮ”

ንግሥት ለመሆን የተመኘችው ቁራ በቀበሮ ሙገሳ ተታላ “ቁኢኢ..” ብላ ብትጮኸ የነከሰችው ሥጋ ወደቀ፡፡ ያሰበችው የተሳካላት እመት ቀበሮ “በዚህ ድምፅና ውበት ላይ ማስተዋል ቢጨመርበት ኖሮ እንዳንቺ ያለ የአእዋፍ ንግሥት እግር እስኪነቃ ቢኬድ አይገኝም ነበር” ብላ ተመጻደቀችባት ይባላል፡፡

ልጄ ስንቱ በውዳሴ ከንቱ ጸጋውን ተነጥቆ ከክብር ተዋርዶ ይሆን? የሰው ስስ ብልት ዝና ናፋቂ መሆኑን የተገነዘበው ዲያብሎስም እንደ ልቡ እየተጫወተብን ነው፡፡ ስንት የት ይደርሳሉ የተባሉ ሰዎች ካቅማቸው በላይ ባገኙት ዝና ተልፈስፍሰው ከእርምጃው ተገተው ይሆን?

ውሃ የሞላ ብርጭቆውን አነሣና ተጎነጨለት

እሰይ! ይኸውልሽ ልጄ ለሰው ውድቀቱ ውዳሴ ከንቱ ነው፡፡ ምእመናን ጥቂት መንፈሳዊ አገልግሎት ሠርተው የበቁ የሚመስላቸው፤ አገልግለው የማንጠቅም ባሪያዎች ነን የሚሉ እንዳልነበሩ፤ ትንሽ አስተምረው /አገልግለው/ ታይታን የሚፈልጉ አገልጋዮች በቤተ ክርስቲያናችን ሞሉ፡፡ ታዲያ ትውልድ ምን ይማር ልጄ?

ለእናት ሀገሩ በቅንነት ከመሥራት ይልቅ ሀብቷን የሚቀራመታት ለድሆች ከቆመው ይልቅ ያለ አግባብ ኪሱን በጉቦ ያደለበው ስሙ ሲገን ከማየት የደለበ ምን የሚያሳዝን ነገር አለ?

ከአባቴ አንደበት የሚወጡት ቃላት ፍላጻቸው ለልቤ ደርሰው አእምሮዬን ሲሞሉት ራሴን ዘወትር ብወቅስም ያለመለወጤ አናደደኝ፡፡

“ብዙ መሥራት የሚችለው ወጣት ተጧሪ ሆነ ለኔ የሚገባኝ ከመሥራት ይልቅ መዝናናትና በሱስ መጠመድ ብቻ ነው ብሎ የሚያስብ ነው የበዛው ልጄ..”

ከአባቴ ተረት ውስጥ ራሴን መመልከት ጀመርኩ ሁሌም አንድ ተጨባጭ ነገር ላይ መድረስ ሲያቅተኝ ልኬቴ እዚህ ድረስ ነው ብዬ ሳምን፤ በራሴ መጠራጠር ጀምሬ ነበር፡፡ ትእግስት በስሜቴ ውስጥ ሲገረጅፍ ደግሞ ግን ለምን የሚለኝ አእምሮዬ ውድቀቴን ያለ ሥራና ያለ መልካም ምግባር ዛሬም በአባቴ  ቤት ተጧሪ መሆኔን አከበደብኝ፡፡

ለስማቸው የሚጨነቁት ጥቂት ሠርተው ብዙ ስም ፈለጉ እኔ ግን ያለ ሥራ ቁጭ ብያለሁ፡፡ እስከ ዛሬ የአባቴ ተረቶች እውነታቸው ከማስበው በተለየ ዘልቆ ሲታወቀኝ፣ ጠልቆ ሲዳሰሰኝ፣ ርቆም ሲታየኝ፣ ቀርቤም ሆኖ ብዥ ሲልብኝ ኖሬያለሁ፡፡ ዛሬ ግን ራሴን ተመለከትኩ፡፡

ከአባቴ ተረቶች መሠረት ዛሬ ላይ ሆኖ ትናነትን ከመናፈቅ ይልቅ የዛሬን የተግባር ሰው መሆን እንደሚገባኝ ተገነዘብኩ፡፡ የአባቴ ቃላት ተራ ተረቶች መስለውኝ ቢኖሩም ዛሬ ግን ተጨባጭ በሆነው ዓለም ውስጥ እንዴት መኖር እንደሚገባኝ ሲጠቁሙኝ የኖሩ የተዋቡ ምክሮች ናቸው፡፡ አባቴ በኋሊት መነጽር ትናንትን የሚያሰቃኘኝ የተግባር ሰው በውዳሴ ከንቱ ያልተበገረች ጠንካራ ሠራተኛ ጥሩ መንፈሳዊ ሰው እንድሆን ነው፡፡

አሁን አባቴ ካጠገቤ ተነሥቶ በረንዳ ላይ ተቀምጧል ዓይኖቹን ቡዝዝ አድርሀጎ የፊት ለፊቱን ያያል፡፡ እኔ ግን ዓይኖቹ በትውስታ ፈረስ ትናንትን፤ የሱን ዘመን እያሰቃኙት ይመስለኛል፡፡

የሱ በትናንት ዘመን መኖርና የድሮ ተረቶቹ ከተዘፈቅሁበት ከንቱነት ከግድ የለሽነትና ከተመጻዳቂነት የሚያወጡኝ የማንቂያ ደውሎች ናቸው ለካ!! አልኩ፡፡

ለወትሮው ሠርቼ ራሱን ከመለወጥ ይልቅ ሀብታም የትዳር ጓደኛና ዝና ፈላጊነቴ ገዝፎ አእምሮዬን የሞላኝ ነበርኩ፡፡ ለዚህ ነው ከሁሉም ነገር ውስጥ ሳልሆን ጠባቂ ሆኜ መኖሬ እስከ አሁን ከልብ ሳልሆን በማስታወሻ ደብተሬ ላይ የከተብኳቸውን በርካታ ያባቴን ተረቶች መልሼ ማንበብ እንደሚጠቅመኝ አሰብኩ፡፡

“ልጄ?”

አቤት አባባ

አሁን እንግዲህ 34 ዓመት ሞላሽ አይደል?

አዎን አባባ

አባቴ ከዚህ በላይ አልጠየቀኝም መልእክቱ ገብቶኛል ትንሽ ለሀገርሽና ለቤተ ክርስቲያንሽ የሚሆን በጎ ሥራ ሳትሠሪ ጊዜ ቀድሞሻል ማለቱ ነው፡፡

አባዬ?

“አቤት ልጄ”

ለካ እስካሁን ከኖሩት ተርታ አልተመደብኩም?

“እንደሱ ነው ልጄ እንደሱ!!

/ምንጭ፡- ሐመር 18ኛ ዓመት ቁጥር 5