የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ዕረፍት

በዝግጅት ክፍሉ

ነሐሴ ፳፫ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

ቅዱሳን ጻድቃን በሕይወተ ሥጋ እያሉ፣ ከሞቱም በኋላ (በዐጸደ ነፍስ ኾነው) በጸሎታቸው ለሚታመኑ፤ በቃል ኪዳናቸው ለሚማጸኑ ምእመናን የድኅነተ ሥጋ፣ የድኅነት ነፍስ ምክንያቶች ናቸው፡፡ ቅዱሳን ጻድቃን በመንፈሳዊ አርአያነታቸው፣ በጸሎታቸውና በትምህርታቸው ከከበቡን የነፍስ ጠላቶች፤ ከርኲሳን መናፍስትና ከጨለማው ልጆች፤ ከክፉ ሰዎች ሽንገላና ተንኰል ለመጠበቅ ከእግዚአብሔር የተቀበሉት ሥልጣን ምን ጊዜም ይሠራል፡፡ በጻድቃን መኖር አገር ከጥፋት ትድናለች፡፡ የጻድቃንን ስም ጠርቶ እግዚአብሔርን በመለመን በረከትና ረድኤት ይገኛል፡፡ ስለ ጻድቃን ብሎ እግዚአብሔር ምሕረቱን ያድላል፡፡ ጻድቃንን ማሰብ፣ ሥራቸውንም መዘከር ክርስቲያናዊ ሕይወታችንን ያጐለምስልናል፡፡ በነፍስ በሥጋም ይጠብቀናል፤ ይረባናል፤ ይጠቅመናል፡፡ ስለዚህም ነው ቤተ ክርስቲያናችን ጻድቃንን እንድናስባቸው፤ በስማቸውም ለድሆችና ለጦም አዳሮች እንድንመጸውት፤ መታሰቢያቸውንም እንድናደርግ የምትመክረን፣ የምታስተምረን፡፡ ከእነዚህ ቅዱሳን መካከል መካከል ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት አንዱ ናቸው፡፡

አቡነ ተክለ ሃይማኖት በእግዚአብሔር መልካም ፈቃድ፤ በሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ብሥራት ከአባታቸው ከካህኑ ጸጋ ዘአብ እና ከእናታቸው ከቅድስት እግዚእ ኃረያ ታኅሣሥ ፳፬ ቀን ፲፪፻፲፪ (1212) ዓ.ም በቡልጋ አውራጃ ኢቲሳ በሚባል ቦታ ተወለዱ፡፡ (ቦታው በአሁኑ ሰዓት ደብረ ጽላልሽ ኢቲሳ ተክለ ሃይማኖት ተብሎ ይጠራል)፡፡ በተወለዱ በሦስተኛው ቀን እሑድ ከጠዋቱ በሦስት ሰዓት ከእናታቸው ዕቅፍ ወርደው ‹‹አሐዱ አብ ቅዱስ አሐዱ ወልድ ቅዱስ አሐዱ ውእቱ መንፈስ ቅዱስ፤ አንዱ አብ ቅዱስ ነው፤ አንዱ ወልድ ቅዱስ ነው፤ አንዱ መንፈስ ቅዱስ ቅዱስ ነው›› በማለት ሥላሴን አመስግነዋል፡፡ በተወለዱ በ፲፭ ዓመታቸው መዓርገ ዲቊናን፤ በ፳፪ ዓመታቸው ደግሞ መዓርገ ቅስናን ከግብጻዊው ጳጳስ አባ ጌርሎስ (ቄርሎስ) ተቀብለዋል፡፡

ወላጆቻቸው ያወጡላቸው ስም ‹ፍሥሐ ጽዮን ነው፡፡ በአንድ ወቅት ሕፃኑ ፍሥሐ ጽዮን ወደ ጫካ ለአደን ሔዱ፡፡ በዚያች ዕለት ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተገልጦ ጸጋ መንፈስ ቅዱን አሳደረባቸው፡፡ ለሐዋርያዊ አገልግሎት ወንጌል ወዳልተዳረሰበት ቦታ እንደሚልካቸውም አስረዳቸው፡፡ ቅዱስ ሚካኤልም ከአውሬ አዳኝነት ሰውን ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ለመመለስ እንደ ተመረጡ፤ አጋንንትን የማውጣት፣ ተአምራትን የማድረግ ሥልጣን እንደ ተሰጣቸው፤ ስማቸውም ተክለ ሃይማኖት እንደሚባል፤ ትርጓሜውም ተክለ አብ፣ ተክለ ወልድ፣ ተክለ መንፈስ ቅዱስ ማለት እንደ ኾነ አበሠራቸው፡፡ ከዚህ በኋላ ያላቸውን ንብረት ዅሉ ለቤተ ክርስቲያንና ለነዳያን ሰጥተው ‹‹አቤቱ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ! የመንግሥተ ሰማያትን በር ትከፍትልኝ ዘንድ እነሆ ቤቴን እንደ ተከፈተ ተውኹልህ›› በማለት ቤታቸውን ትተው ወንጌልን ለማስተማር ፈጥነው ወጡ፡፡ ከዚያ ጊዜ ጀምረው በመላው ኢትዮጵያ እየተዘዋወሩ ወንጌልን በመስበክና ተአምራትን በማድረግ ብዙ አሕዛብን ከአምልኮተ ጣዖት ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር፤ ከገቢረ ኀጢአት ወደ ገቢረ ጽድቅ መልሰዋል፡፡ አብያተ ክርስቲያናትንም አሳንጸዋል፡፡

ከዚህ በኋላ በደብረ ሊባኖስ ገዳም (ገዳመ አስቦ) ዋሻ በመግባትም ሁለቱን በፊት፣ ሁለቱን በኋላ ሁለቱን በቀኝ፣ ሁለቱን በግራ ስምንት ጦሮችን ተክለው እጆቻቸውን በትእምርተ መስቀል በመዘርጋት የክርስቶስን ሕማም፣ ሞትና ነገረ መስቀል በማሰብ በተመስጦ ሌሊትና ቀን ያለ ማቋረጥ በጾም፣ በጸሎት ተወስነው ሲጋደሉ፤ ከቊመት ብዛት የተነሣ በ፺፪ኛ ዓመታቸው ጥር ፬ ቀን ፲፪፻፹፱ (1289) ዓ.ም አንዲቱ የእግራቸው አገዳ ተሰብራለች፡፡ ደቀ መዛሙርቱም የመንፈሳዊ አባታቸውን ስባረ ዐፅም (የዐፅም ስባሪ) አክብረው በሥርዓት አኑረዋታል፡፡ እግራቸው እስኪሰበር የቆዩባቸው ዓመታትም ፳፪ ናቸው፡፡ ለሰባት ዓመታት በአንድ እግራቸው ቆመው ያለ ምግብና ያለ ውኃ በትኅርምት ሌሊትና ቀን እንደ ምሰሶ ጸንተው በትጋት ለሰው ዘር ዅሉ ድኅነትን ሲለምኑ ኖረዋል፡፡ ከሰባቱ ዓመታት ውስጥ ጥቂት ውኃ የቀመሱት በአራተኛው ዓመት ብቻ እንደ ነበረ መጽሐፈ ገድላቸው ይናገራል፡፡

ጻድቁ አባታችን ምድራዊ ሕይወታቸውን በተጋድሎና በሐዋርያዊ አገልግሎት ከፈጸሙ በኋላ ከዚህ ዓለም ውጣ ውረድ የሚያልፉበት ቀን ተቃረበ፡፡ በዚህ ጊዜ መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእናቱ ከቅድስት ድንግል ማርያም፣ ከቅዱሳን መላእክት፣ ከቅዱሳን ነቢያትና ከቅዱሳን ሐዋርያት ጋር ወደ እርሳቸው በመምጣት የሚያርፉበት ዕለት መድረሱን ነገራቸው፡፡ የተጋድሏቸውን ጽናት አድንቆ በስማቸው መታሰቢያ ለሚያደርጉ፣ ለነዳያን ለሚመጸዉቱ ቤተ ክርስቲያን ለሚያሠሩ የምሕረት ቃል ኪዳን ሰጥቷቸው በክብር በምስጋና ወደ ሰማይ ዐረገ፡፡ ስለ ተጋድሏቸው ጽናትም ‹‹በሰው እጅ የማይለካውን ይህንን የመንግሥት አዳራሽ ውሰድ›› በማለት የመለኮትን ነገር የሚናገር የእሳት አንደበት ያለው የጸጋ ልብስ አልብሷቸዋል፤ በመስቀል ምልክት ያጌጡ ሰባት የሕይወት አክሊላትንም አቀዳጅቷቸዋል፡፡

አቡነ ተክለ ሃይማኖት የዕረፍታቸው ጊዜ መቃረቡን ባወቁ ጊዜ የመንፈስ ልጆቻቸውን ጠርተው ጌታችን የነገራቸውን ዅሉ አስረድተው አባታዊ ምክርና ተግሣፅ ከሰጧቸው በኋላ ነሐሴ ፳፬ ቀን ከዚህ ዓለም ድካም ዐርፈዋል፡፡ የመንፈስ ልጆቻቸውም ለአንድ ቅዱስ አባትና ካህን በሚገባ ሥርዓት በማኅሌት፣ በዝማሬና በምስጋና ቀብረዋቸዋል፡፡ ጌታችንም ከእመቤታችንና ከቅዱሳን መላእክት ጋር ተገልጾላቸዋል፤ ነፍሳቸውንም ‹‹የጠራሽ፣ ንጽሕት ነፍስ ሆይ ወደ እኔ ነዪ›› ብሎ በክብር ተቀብሏታል፡፡ በመጽሐፈ ገድላቸው እንደ ተጠቀሰው አቡነ ተክለ ሃይማኖት በዚህ ዓለም የኖሩበት ዕድሜ ዘጠና ዘጠኝ ዓመት ከዐሥር ወር ከዐሥር ቀን ነው፡፡ በእናት አባታቸው ቤት ፳፪ ዓመት፤ በከተታ ፫ ዓመት፤ በይፋት ፱ ወር፤ በዳሞት ፲፪ ዓመት፤ በአማራ ፲ ዓመት፤ በሐይቅ ፲ ዓመት፤ በደብረ ዳሞ ፲፪ ዓመት፤ በትግራይና በኢየሩሳሌም ገዳማት ፩ ዓመት፤ ዳዳ በሚባል አገር ፩ ወር፤ በደብረ አስቦ ገዳም ፳፱ ዓመት ከ፲ ቀን መቆየታቸውን መጽሐፈ ገድላቸው ይናገራል (ገ.ተ.ሃ ፶፱፥፲፬-፲፭)፡፡

በአጠቃላይ ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ሕይወታቸዉን ሙሉ ለእግዚአብሔር በመስጠት፣ እንደ በሬ ተጠምደው፣ እንደ ገበሬ ታጥቀው ይህንን ዓለም ንቀው፣ በጾም በጸሎት ተወስነው በብሕትውና ከመኖራቸው ባሻገር እንደ ቅዱሳን ሐዋርያት ወንጌልን በመላው ኢትዮጵያ እየተዘዋወሩ የሰበኩ፤ በጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ድውያነ ሥጋን በተአምራት፣ ድውያነ ነፍስን በትምህርት የፈወሱ ሐዋርያ ናቸው፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያችንም ‹‹እናንተን የሚቀበል እኔን ይቀበላል፤ እኔንም የሚቀበል የላከኝን ይቀበላል፡፡ ነቢይን በነቢይ ስም የሚቀበል የነቢይን ዋጋ ያገኛል፡፡ ጻድቅንም በጻድቅ ስም የሚቀበል የጻድቁን ዋጋ ያገኛል፡፡ ማንም ከእነዚህ ከታናናሾቹ ለአንዱ ቀዝቃዛ ጽዋ ብቻ በደቀ መዝሙር ስም የሚያጠጣ እውነት እላችኋለሁ፤ ዋጋው አይጠፋበትም›› (ማቴ. ፲፥፵-፵፪) በማለት ጌታችን የተናገረውን መለኮታዊ ቃል ኪዳን መሠረት አድርጋ መጋቢት ፳፬ ቀን የፅንሰታቸውን፤ ታኅሣሥ ፳፬ ቀን የልደታቸውን፤ ጥር ፬ ቀን የስባረ ዐፅማቸውን (እግራቸው የተሰበረበትን)፤ ግንቦት ፲፪ ቀን የፍልሰተ ዐፅማቸውን፤ ነሐሴ ፳፬ ቀን የዕረፍታቸውን በዓል በትላቅ ደስታ ታከብራለች፡፡ የጻድቁ በረከት አይለየን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ምንጭ፡-

  • መለከት መጽሔት ፲፰ኛ ዓመት፣ ቍጥር ፱፡፡
  • መጽሐፈ ስንክሳር፣ ነሐሴ ፳፬ ቀን፡፡
  • ገድለ ተክለ ሃይማኖት፡፡