የተራራው ምሥጢር (ማቴ. ፲፯፥፩-፱)

በዲያቆን ታደለ ፈንታው

ነሐሴ ፲፪ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በፊልጶስ ቂሣርያ ‹‹መነ ይብልዎ ሰብእ ለወልደ እጓለ እመሕያው፤ የሰው ልጅን ማን እንደ ኾነ ይሉታል?›› የሚል ጥያቄ ለደቀ መዛሙርቱ ባቀረበላቸው ጊዜ ‹‹አንዳንዱ መጥምቁ ዮሐንስ፣ ሌሎችም ኤልያስ፣ ሌሎችም ኤርምያስ ወይም ከነቢያት አንዱ ነው ይላሉ›› የሚል ምላሽ አቀረቡ፡፡ ‹‹እናንተስ ማን ትሉኛላችሁ?›› ብሎ በጠየቃቸው ጊዜም ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ «አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ» ብሎ ድንቅ የኾነ ምስክርነቱን ሰጠ (ማቴ. ፲፮፥፲፫-፲፬)፡፡ ጌታችን ‹‹የዮና ልጅ ስምዖን! እንደዚህ ዓይነቱን ምስክርነት ሥጋና ደም አልገለጸልህም፤ በሰማይ ያለው አባቴ እንጂ›› አለ፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ በዚህ ምስክርነቱ ‹ብፁዕ› ተብሎ ተጠርቷል፡፡ በዘመናችን ብዙዎች የሥጋና ደም ዐሳብን ይዘው አምጻኤ ዓለማትነቱ፤ ከሃሊነቱ፤ ጌትነቱ፤ ተአምራቱ፤ መግቦቱ፤ ዓይን ነሥቶ ዓይን ለሌለው ዓይን መስጠቱ አልታያቸው ብሎ ‹አማላጅ› ይሉታል፡፡ ያለ ባሕርዩ ባሕርይ ሰጥተው በየመንደሩ፤ በየዳሱ አለ ብለው ይጠሩታል፤ እርሱ ግን ‹‹እነሆ ክርስቶስ በመንደር ወይም በእልፍኝ ውስጥ አለ ቢሏችሁ አትመኑ›› በማለት አስጠንቅቋል (ማቴ. ፳፬፥፳፫)፡፡ ከራሳቸው ልቡና አንቅተው ስለ ጌታችን የተሳሳተ መረዳት ያላቸው፣ ሰውንም የሚያሳስቱ የሥጋና ደም ዐሳባቸውን ቀላቅለው ንጹሑን የወንጌል ቃል የሚበርዙ ወገኖች ብፁዓን አልተባሉም፡፡

ይህ ምስክርነት በተሰጠ ማለትም ጌታችን በቂሣርያ ‹‹የሰውን ልጅ ማን ይሉታል?›› ብሎ በጠየቃቸው በሰባተኛው ቀን ከደቀ መዛሙርቱ ሦስቱን ይዞ ወደ ረጅምና ከፍ ወዳለ ተራራ ወጣ፡፡ ተራራውንም ሐዋርያት በሲኖዶስ ታቦር ብለው ጠቅሰውታል፡፡ በከፍታው ላይ ያለ ልዑል እግዚአብሔር ረጅምና ከፍ ያለ ነገርን ይወዳል፡፡ ንጉሡ ዖዝያን በሞተበት ዓመት ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስ እግዚአብሔርን የተመለከተው በረጅምና ከፍ ባለ ዙፋን ላይ ነበር፡፡ ጌታችን ሰው ኾኖ ሥጋን ሲዋሐድም ከፍጥረታት ዅሉ ከፍ ያለውን አማናዊ ዙፋኑን የድንግል ማርያምን ማኅፀን ነበረ የመረጠው፡፡ ይኼንን ኹኔታ ሊቁ አባ ሕርያቆስ እንዲህ ብሎ በማድነቅ ይጠይቃል፤ ‹‹ድንግል ሆይ! ሰባት የእሳት መጋረጃ ከሆድሽ በስተየት በኩል ተጋረደ? በስተቀኝ ነውን? በስተግራ ነውን? ታናሽ ሙሽራ ስትኾኚ፡፡›› እግዚአብሔር ለአባታችን ያዕቆብ በራእይ የገለጸለት መሰላልም ከምድር ከፍ ያለ ነበረ፡፡ ምሳሌነቱም ከፍጥረታት ዅሉ ከፍ ላለች ለእመቤታችን ነው፡፡ ጌታችን ከፍ ያለ ነገርን መምረጡም ልዑለ ባሕርይ ነኝ ሲል ነው፡፡

በቅዱሱ ተራራ ላይ

ከሐዋርያት ሦስቱ ከነቢያት ሁለቱ በተገኙበት ልብሱ እሳት ክዳኑ እሳት የኾነ እግዚአብሔር ወልድ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በፊታቸው ተለወጠ፡፡ አካሉ ሙሉ ብርሃን ሆነ፡፡ ጽጌያት ከአዕጹቃቸው እንዲፈነዱ ፊቱም እንደ ፀሐይ ብሩህ ኾነ፡፡ ልብሱም እንደ በረዶ ነጭ ኾነ፡፡ ክብሩን ግርማውን ጌትነቱን ገለጠ፡፡ ሙሴና ኤልያስ ከእርሱ ጋር ሲነጋገሩ ተሰሙ፡፡ ከደመናውም ውስጥ ‹‹ዝንቱ ውእቱ ወልድ ዘአፈቅር ዘቦቱ ሠመርኩ ወሎቱ ስምዕዎ፤ ልመለክበት የወደድኹት፣ ለተዋሕዶ የመረጥኹት ልጄ ይህ ነው፡፡ እርሱንም ስሙት›› የሚል አስፈሪ ድምፅ መጣ፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ‹‹ከዚህ መኖር ለእኛ መልካም ነው›› አለ፡፡ አንተ የአምላክነት ሥራህን እየሠራህ ብንራብ እያበላኸን፣ ብንታመም እየፈወስከን፣ ብንሞት እያነሣኸን፤ ሙሴ የወትሮ ሥራውን እየሠራ – ደመና እየጋረደ፣ መና እያወረደ፣ ባሕር እየከፈለ፣ ጠላት እየገደለ፤ ኤልያስም እንደዚሁ ሰማይ እየለጎመ፣ እሳትን እያዘነመ፣ ዝናም እያቆመ በዚህ መኖር ለእኛ መልካም ነው፡፡ ሦስት አዳራሽ እንሥራ፤ አንዱን ለአንተ፤ አንዱን ለሙሴ፤ አንዱን ለኤልያስ አለ፡፡ ይህንን ገና እየተናገረ እንዳለ ብሩህ ደመና መጥቶ ጋረዳቸው፡፡ አብ የሰጠው ምስክርነትም ተሰማ፡፡ እመቤታችን በገሊላ ቃና ‹‹እርሱን ስሙት›› (ዮሐ. ፪፥፭)፡፡ በማለት ስለ ልጅዋ የሰጠቸው ምስክርነት ይኸው ነበረ፡፡ የተአምረ ማርያም ደራሲ ‹‹የእመቤታችን ዐሳብ እንደ እግዚአብሔር ዐሳብ ነው›› የሚለውም መንፈስ ቅዱስ የሚያናግረውን እንደዚህ ዓይነቱን ታላቅ ምስክርነት ነው፡፡

ጌታችን ግርማ መለኮቱን ስለ ምን ገለጠ?

ጸሐፍት ፈሪሳውያን የሕግ፣ ባለቤት ሠራዔ ሕግ እርሱ መኾኑን ባለመገንዘባቸው ሕግ ጥሷል በማለት በተደጋጋሚ ይከሱት ነበረ፡፡ አይሁድ ‹‹ይህ ሰው ከእግዚአብሔር አይደለም፤ ከእርሱስ ቢኾን ሰንበትን አይሽርም ነበር›› ብለዋልና ክርስቶስ ከእግዚአብሔር አብ እንደ ወጣ፣ የሰንበትም ጌታዋ እንደ ኾነ ይታወቅ ዘንድ ክብሩን መግለጥ ነበረበት፡፡ እንደ ገናም ‹‹ቃሌን የሚጠብቅ ቢኖር ለዘለዓለም ሞትን አይቀምስም›› በማለት ሲያስተምራቸው ‹‹በውኑ አንተ ከሞተው ከአባታችን ከአብርሃም ትበልጣለህን?›› ብለው ጠይቀውት እርሱም ‹‹እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ አብርሃም ሳይወለድ እኔ አለሁ›› ብሏቸው ነበርና ክብሩን መግለጥ ነበረበት፡፡ በሕይወት ካሉት ኤልያስን፣ ከሞቱት ሙሴን የማምጣቱ ምሥጢር በሞትና በሕይወት ላይ ሥልጣን ያለኝ እኔ ነኝ ሲል ነው፡፡ ሙሴን ከመቃብር፣ ኤልያስን ከብሔረ ሕያውያን ማምጣቱም የሰማይና የምድር ገዢ እኔ ነኝ ሲል ነው፡፡ እንደ ገናም በሐዋርያቱ የተሰጠውን ምስክርነት በባሕርይ አባቱ በአብ ለማስመስከር ነው፡፡ አስቀድሞ ‹‹የሁለት ወገኖች ምስክርነት እውነት እንደ ኾነ ተጽፏል፡፡ ስለ እራሴ የምመሰክር እኔ ነኝ፤ አብ ስለ እኔ ይመሰክራል›› ብሎ ነበርና (ዮሐ. ፰፥፲፯)፡፡

በመጀመሪያ ተራራ የመንግሥተ ሰማያት ምሳሌ ነው፡፡ ተራራን በብዙ ድካም እንዲወጡት መንግሥተ ሰማያትንም በብዙ መከራ ያገኟታልና፡፡ ይህንንም ቅዱስ ጳውሎስ ሲገልጥ ‹‹እስመ በብዙኅ ፃማ ሀለወነ ንባኣ ለመንግሥተ እግዚአብሔር፤ በብዙ ጭንቅ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት እንገባ ዘንድ አለን›› በማለት አስረድቷል (ሐዋ. ፲፬፥፳፩-፳፪)፡፡ የደብረ ታቦሩን ምሥጢር ሲመሰክርም ቅዱስ ጴጥሮስ እንዲህ ሲል ይናገራል፤ ‹‹የእርሱን ግርማ አይተን እንጂ በብልሃት የተፈጠረውን ተረት ሳንከተል የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ኃይልና መምጣት አስታወቅናችሁ፡፡ ከገናናው ክብር ‹በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ እርሱ ነው እርሱን ስሙት› የሚል ያ ድምፅ በመጣለት ጊዜ ከእግዚአብሔር አብ ክብርንና ምስጋናን ተቀብሎአልና፡፡ እኛም በቅዱሱ ተራራ ከእርሱ ጋር ሳለን ይህ ድምፅ ከሰማይ ሲወርድ ሰማን፤›› (፩ኛ ጴጥ. ፩፥፲፮)፡፡

ለምን ደብረ ታቦርን መረጠ?

ጌታችን ምሥጢረ መለኮቱን በታቦር ያደረገው በሌላ ተራራ ያላደረገው አስቀድሞ ታቦር ትንቢት የተነገረበት ተራራ በመኾኑ ነው፡፡ ነቢዩ ዳዊት ‹‹ታቦር ወአርሞንኤም በስመ ዚአከ ይትፌሥሑ›› ብሎ ተናግሯል፡፡ ይህም በጌታችን ሰው መኾን የነቢያት ትንቢት ፍጻሜ ማግኘቱን የሚያሳይ ነው፡፡ ዐሥራ ሁለቱንም ደቀ መዛሙርት የመረጣቸው ጌታችን ነው፡፡ በመጀመሪያ ሙሴን ለመስፍንነት፣ አሮንን ለክህነት የመረጠበት ግብር እንዳልታወቀ ከደቀ መዛሙርቱ ሦስቱን የመረጠበትን ምክንያት የሚያውቀው እርሱ ብቻ ነው፡፡ እንደ ቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ ግን ሦስቱን ወደ ተራራ ይዟቸው ስምንቱን ከእግረ ተራራው ጥሎአቸው የሔደው ምክንያት ስለ ነበራቸው ነው፡፡ የመጀመሪያው ከሌሎቹ የሚበልጡበት ምክንያት ነበራቸውና፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስን ይወደው ነበርና፡፡ ቅዱስ ዮሐንስም ‹‹ጌታ ይወደው የነበረ ደቀ መዝሙር›› ተብሎ በብዙ ቦታ ተገልጧል፡፡ ቅዱስ ያዕቆብም ‹‹አንተ የምትጠጣውን ጽዋ እኛም እንጠጣለን›› ብሏል (ማቴ. ፳፥፳፪)፡፡ ዳግመኛም ቅዱስ ጴጥሮስ ‹‹አንተ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ›› ብሎ መስክሮ ስለ ነበረ ምስክርነቱ በእርሱ ብቻ የሚቀር ሳይኾን እግዚአብሔር አብም በደመና ኾኖ ‹‹በእርሱ ደስ የሚለኝ ልጀ እርሱ ነው እርሱን ስሙት›› በማለት የሰጠው ምስክርነት ከቅዱስ ጴጥሮስ ምላሽ ጋር ያለው ድንቅ ስምምነት ይገለጥ ዘንድ ነው፡፡ በዚህም ቅዱስ ጴጥሮስ የሰጠው ምስክርነት ሥጋና ደም ያልገለጠለት መኾኑ በተረዳ ነገር ታውቋል፡፡

ሙሴና ኤልያስ ለምን በተራራው ተገኙ

ሙሴና ኤልያስ በቅዱሱ ተራራ ከጌታችን ጋር የተነጋገሩ ነቢያት ነበሩ፡፡ በቅዱሱ ተራራ በተከበበ ብርሃን ውስጥ ኾነው ስማቸውን የጠቀስናቸውን ነቢያትን እንመለከታለን፡፡ እነዚህ ጾም የሚያስገኘውን ጥቅም ያሳዩ ናቸው፤ ዐርባ፣ ዐርባ ቀናትን ጾመዋልና፡፡ በቅዱሱም ተራራ ከተገኙት ቅዱሳን መካከል ናቸው፡፡ እነዚህ ለመገኘታቸው ምክንያት ነበራቸው፡፡ ጌታችን አስቀድሞ ‹‹እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ ከዚህ ቁመው ካሉት የእግዚአብሔርን መንግሥት እስኪያዩ ድረስ የማይሞቱ አሉ›› ብሎ ተናግሮ ነበርና እግዚአብሔር ነቢዩ ኤልያስን እንዲገኝ አድርጓል፡፡ ሙሴ ደግሞ ‹‹እባክህ ፊትህን አሳየኝ›› ብሎ ለምኖት ነበር፡፡ እግዚአብሔርም ‹‹ፊቴን ማየት አይቻልህም፤ ነገር ግን ክብሬን በዓለቱ ላይ እተውልሃለሁ›› የሚል ተስፋ ለሙሴ ሰጥቶት ስለ ነበረ እግዚአብሔር የተናገረው ቃል ከሞት በኋላ እንኳን ተፈጻሚነቱ ይታወቅ ዘንድ ሙሴ በቅዱሱ ተራራ ላይ ተገኘ፡፡ ዳግመኛም ጌታችን ስለ ማንነቱ ሲጠይቃቸው ደቀ መዛሙርቱ ሰዎች ሙሴ፣ ኤልያስ፣ … እንደሚሉት ተናግረው ስለ ነበረ እርሱ አምላከ ሙሴና አምላከ ኤልያስ መኾኑ ይታወቅ ዘንድ ከነቢያት ሁለቱ ተገኙ፡፡ እንደገናም ሙሴ የሕጋውያን፤ ኤልያስ የደናግል ምሳሌ ነው፡፡ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት የተጠሩት ሁለቱም ወገኖች ናቸውና ሁለቱ ነቢያት በደብረ ታቦር ተገኙ፡፡

ከደቀ መዛሙርት ሦስቱን ብቻ ለምን ይዞ ወጣ?

ያየዕቆብ እና የዮሐንስ እናት ማርያም ባውፍልያ ጌታችን መንግሥቱ ከዚህ ዓለም መስሎሏት ‹‹በነገሥህ ጊዜ እኒህ ልጆቼ አንዱ በቀኘህ አንዱ በግራህ እንዲቀመጡ አድርግልኝ?›› የሚል ልመናን ስለ ልጆችዋ አቅርባ ነበር፡፡ ጌታችንም መንግሥቱ ሰማያዊት እንጂ ምድራዊት አለመኾኗን ይገልጥላቸው ዘንድ ይዞአቸው ወደ ተራራ ወጣ፡፡ ስምንቱን ከእግረ ደብር ትቷቸው የወጣው በይሁዳ ምክንያት ነው፡፡ ክብሩንና መንግሥቱን እንዳያይ ይሁዳ ትንቢት ተነግሮበታልና ለይቶም እንዳይተወው ‹‹ከምሥጢረ መንግሥቱ ቢለየኝ ከሞቱ ገባሁበት›› ብሎ እንዳያስብ ምክንያት ለማሳጣት ስምንቱን ትቷቸው ወጣ፡፡

በዘመነ ኦሪት ከእስራኤል ሽማግሌዎች ሕዝቡን ያስተዳድሩ ዘንድ ሰባ ሰዎችን መርጦ ወደ ቅዱሱ ተራራ እንዲያቀርባቸው፤ ከመንፈሱ ወስዶ በሽማግሌዎቹ ላይ እንዲያፈስባቸውና ሙሴን እንዲያግዙት እግዚአብሔር ሙሴን አዝዞት ነበር፡፡ ሙሴም ከእያንዳንዱ ነገድ ስድስት ሰዎችን መረጠ፡፡ ከዐሥራ ሁለቱ ነገድ የተመረጡ ሰዎችም ሰባ ሁለት ኾኑ፡፡ ሙሴም እንደ ታዘዘው ሰባዎቹን ሰዎች ይዞ የቀሩትን ሁለቱን ኤልዳድንና ሞዳድን ከእግረ ደብር ትቷቸው ወደ ተራራው ወጥቷል፡፡ በደብረ ሲና ለሰባው ሊቃናት የተገለጠው ምሥጢር ከተራራው ሥር ለነበሩ ሁለቱ ሰዎችም ተገልጧል፡፡ በተመሳሳይ ኹኔታ በርእሰ ደብር (ደብረ ታቦር) ለሦስቱ ደቀ መዛሙርት የተገለጠው ምሥጢርም በእግረ ደብር ላሉ ለስምንቱም ተገልጦላቸዋል፡፡

ከዚህ ትምህርት የምንማረው ቁም ነገር

የቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ መሠረቱን በነቢያትና ሐዋርያት ላይ ያደረገ መኾኑን በቅዱሱ ተራራ ላይ የተገኙት ነቢያትና ሐዋርያት ምስክሮች ናቸው፡፡ እኛም ‹‹በነቢያትና ሐዋያርት መሠረት ላይ ታንጻችኋል›› ተብለናል፡፡ ስለ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ማንነት የታመነ ምስክርነት አግኘተናል፡፡ አስቀድሞ ሐዋርያው ‹‹በመጀመሪያ ቃል ነበረ፤ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፡፡ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ፤›› (ዮሐ. ፩፥፩) በማለት የሰጠንን ምስክርነት፤ እንደ ገናም ‹‹ጸጋንና እውነትን ተመልቶ በእኛ ላይ አደረ›› በማለት የጠቀሰውን፤ ቅድመ ዓለም ከአብ ያለ እናት፣ በዚህ ዓለም ቅድስት ከምትኾን ከእመቤታችን ከድንግል ማርያም ያለ አባት የተወለደውን አምላክ ወልደ አምላክ በማመን የወንጌል ጋሻን ደፍተን፣ የእምነት ወንጌልን ተጫምተን በማመን እንበረታለን እንጂ ባለማመን ምክንያት አንጠፋም፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጠብቃ ካቆየቻቸው መንፈሳውያት እሴቶች መካከል በጌታችን፣ በእመቤታችንና በቅዱሳኑ ስም በዓላትን ማክበር ይገኙበታል፡፡ ከእነዚህም አንዱ የደብረ ታቦር በዓል ነው፡፡ በዓሉ ዳቦ በመድፋት፣ ጠላ በመጥመቅ በየቤቱ በደማቅ ሥርዓት ይከበራል፡፡ በተለይ የአብነት ተማሪዎች ከሕዝቡ በመለመን ስሙን ይጠራሉ፡፡ ይህም ልንጠብቀው የሚገባን መንፈሳዊ እሴታችን ነው፡፡ ጌታችን የቅዱሳኑን መታሰቢያ በተመለከተ ሲናገር ‹‹በደቀ መዝሙር ስም ቀዝቃዛ ውኃ ያጠጣ ዋጋው አይጠፋበትም›› በማለት ተናግሯል (ማቴ. ፲፥፵፪)፡፡ በቅዱሳኑ ስም የሚደረግ ምጽዋት ይህን ያህል በረከት ካስገኘ፣ በራሱ በባለቤቱ ስም የሚደረገውማ እንደምን አብዝቶ ዋጋ አያሰጥ? ክርስቲያኖች! በአጠቃላይ ምሥጢረ መለኮቱን የገለጠበትን ከጌታችን ዐበይት በዓላት አንዱ የኾነውን የደብረ ታቦርን በዓል የምናከብረው በዚህ መንፈስ ነው፡፡ አምላካችን ‹‹ለሚወዱኝ እስከ ሺሕ ትውልድ ድረስ ምሕረትን የማደርግ እኔ እግዚአብሔር ነኝ›› (ዘፀ. ፳፩፥፮) ብሏልና በዓሉን በክርስቲያናዊ ሥርዓት በማክበር የበረከቱ ተሳታፊዎች መኾን ይገባናል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር