የብርሃናተ ዓለም ጴጥሮስና ጳውሎስ ዕረፍት

ሐምሌ ፮ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

ሐምሌ ፭ ቀን በአንድ በኩል የብርሃናተ ዓለም ቅዱስ ጴጥሮስና ቅዱስ ጳውሎስ በዓለ ዕረፍት የሚዘከርበት ዕለት ሲኾን፣ በሌላ በኩል ደግሞ የጾመ ሐዋርያት ፋሲካ የሚከበረውም በዚሁ ዕለት ነው፡፡ በዛሬው ዝግጅታችን የእነዚህን ቅዱሳን ታሪክ በአጭሩ ይዘንላችሁ ቀርበናል፤

ቅዱስ ጴጥሮስ

ጴጥሮስ ማለት በግሪክ ቋንቋ ዓለት (መሠረት) ማለት ነው፡፡ ወላጆቹ ስምዖን ይሉት ነበር፡፡ በአባቱ የሮቤል፣ በእናቱ የስምዖን ነገድ ሲኾን፣ የተወለደውም በገሊላ አውራጃ በቤተ ሳይዳ ነው፡፡ ሰዎችን በወንጌል መረብ እያጠመደ ወደ ክርስትና ሕይወት ይመልስ ዘንድ ጌታችን ከዓሣ አጥማጅነት ለሐዋርያነት ጠርቶታል /ሉቃ.፭፥፲፤ ማር.፩፥፲፮/፡፡ በመንፈሳዊ ቅንዓቱና ለጌታችን በነበረው ፍቅር የሐዋርያት አለቃ ኾኖ ተሹሟል፡፡ ለአገልግሎት ከተጠራበት ጊዜ ጀምሮም በእስያ፣ በሮም፣ በሰማርያ፣ በልዳ፣ በኢዮጴ፣ በአንጾኪያ፣ በገላትያና በሌሎችም አገሮች እየተዘዋወረ ወንጌልን ሰብኳል፡፡ በስብከቱ ምክንያትም ልዩ ልዩ መከራን ተቀብሏል፡፡ በቃል ካስተማረው ትምህርት በተጨማሪ በመጽሐፍ ቅዱስ በስሙ የተመዘገቡ ሁለት መልእክታትን ጽፏል፡፡

በመጨረሻም የክርስቲያኖች ጠላት የነበረው የሮም ንጉሥ ወደ አካይያ ዘምቶ ድል አድርጎ በደስታ ወደ ሮሜ ሲመለስ መኳንንቱን ለማስደሰት፤ ጣዖታቱንም ለማክበር ሲል በቅዱስ ጴጥሮስና በሌሎችም ክርስቲያኖች ላይ የሞት ፍርድ ዐወጀ፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ በሮም ሲያስተምር ቆይቶ የሮም መኳንንት እንዳይገድሉት ትጥቁን ለውጦ ከሮም ሲወጣ ጌታችን መስቀል ተሸክሞ ተገለጸለት፤ በዚህ ጊዜ *አቤቱ ጌታ ሆይ ወዴት ትሔዳለህ? ሲል ቢጠይቀው ጌታችንም *ልሰቀል ወደ ሮም እሔዳለሁ* አለው፡፡ *ዳግመኛ ትሰቀላለህን?* ባለው ጊዜም *አንተ ሰትፈራ ጊዜ ነው እንጂ* አለው፡፡ ያን ጊዜም *ጐልማሳ ሳለህ ወገብህን ታጥቀህ ወደ ወደድኸው ትሔድ ነበር፡፡ ስትሸመግል ግን እጅህን ታነሣና ሌላ ሰው ያስታጥቅሃል፤ ወደማትወደውም ይወስድሃል፤* /ዮሐ.፳፩፥፲፰/ በማለት ጌታችን የነገረው ቃል ትዝ አለውና አሟሟቱን የሚያመለክት መኾኑን አስታውሶ ወደ ሮም ተመልሶ ወንጌልን መስበኩን ቀጠለ፡፡

በሮማውያን ሕግ ቅጣት የተፈረደበት ወንጀለኛ የሮም አገር ተወላጅ ከኾነ የወንጀሉ ክብደትና ቅለት እየታየ ግርፋት ወይም ሞት ይፈረድበት ነበር እንጂ በአንድ ወንጀል ሁለት ቅጣት አይቀጣም ነበር፡፡ ወንጀለኛው የውጪ አገር ዜጋ (ከሮም ውጪ) ከኾነ ግን ለምሳሌ ቅጣቱ ግርፋት ከኾነ ከተገረፈ በኋላ እስራት ይጨመርበታል፤ ቅጣቱ ሞት ከኾነም ከገረፉት በኋላ በመስቀል ወይም በሌላ መሣሪያ ይገድሉት ነበር፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ዜግነቱ ሮማዊ አልነበረምና በግርፋትም፣ በእስራትም በሞትም እንዲቀጣ ተፈረደበት፡፡

እንደ ሥርዓታቸውም አስቀድመው ከገረፉት በኋላ ሊሰቅሉት ሲሉ ወታደሮቹን *እንደ ክብር ንጉሥ እንደ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ አቁማችሁ ሳይኾን፣ ዘቅዝቃችሁ ስቀሉኝ* አላቸው፡፡ እነርሱም እንዳላቸው አድርገው ሐምሌ ፭ ቀን ዘቅዝቀው ሰቅለውታል፡፡ በመስቀል ላይ ሳለም ተከታዮቹን በሃይማኖታቸው እንዲጸኑ ካዘዛቸው በኋላ ነፍሱን ለእግዚአብሔር ሰጠ፡፡ ሥጋውንም ደቀ መዝሙሩ መርቄሎስ ሽቱ ቀብቶ፣ በነጭ ሐር ገንዞ ዛሬ ቫቲካን በምትባለዋ ስፍራ በክብር ቀብሮታል፡፡

ቅዱስ ጳውሎስ

ቅዱስ ጳውሎስ ለአገልግሎት ከመጠራቱ በፊት ሳውል ይባል ነበር፡፡ ከኦሪቱ ምሁር ከገማልያል ሕገ ኦሪትንና መጻሕፍተ ነቢያትን ተምሯል፡፡ ለሕገ ኦሪት ቀናኢ ከመኾኑ የተነሣም የክርስቶስ ተከታዮችን ኹሉ ያሳድድ ነበር፡፡ ቅዱስ እስጢፋኖስ በድንጋይ ተደብድቦ ሲገደልም የገዳዮቹ ልብስ ጠባቂ ነበር /ሐዋ.፯፥፶፰፤ ፳፪፥፳/፡፡ ክርስቲያኖችን ለማሳደድ ወደ ደማስቆ ሲሔድ ለሐዋርያነት ተጠርቷል /ሐዋ.፱፥፩-፴፩፤ ፳፪፥፩-፳፩/፡፡ ለሐዋርያነት ከተጠራበት ጊዜ ጀምሮ በመላው ዓለም እየተዘዋወረ ወንጌልን በመስበክ ብዙዎችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አሳምኗል፡፡

ሲሰብክም ጣዖት አምላኪ፣ ሕመምተኛ፣ ችግረኛ፣ አረማዊና አይሁዳዊ እየመሰለ ብዙዎችን አስተምሮ ለእግዚአብሔር መንግሥት አቅርቧል /፩ኛቆሮ.፱፥፲፱-፳፫/፡፡ ወንጌልን በመስበኩ ምክንያትም ከአይሁድና ከአረማውያን ዘንድ ብዙ መከራና ስቃይ ደርሶበታል፡፡ ዐረብ፣ አንጾኪያ፣ እልዋሪቆን፣ ሊቃኦንያ፣ ሦርያ፣ ግሪክና ልስጥራን ካስተማረባቸው አገሮች ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ በቃል ካስተማረው ሌላ በመጽሐፍ ቅዱስ በስሙ የተመዘገቡ ፲፬ መልእክታት አሉት፡፡

አገልግሎቱን ሊፈጽም ሲልም የሮም ንጉሥ ኔሮን ቄሣር የክርስቲያኖች ቍጥር እየጨመረ የመጣው በቅዱስ ጳውሎስ ትምህርት በመማረካቸው ምክንያት መኾኑን ተረድቶ፤ ይልቁንም የቤተ መንግሥቱ ሰዎች ሳይቀር በቅዱስ ጳውሎስ በመማረካቸው ተቈጥቶ ቅዱስ ጳውሎስን ወደ ፍርድ ሸንጎው አስቀረበው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም በቀኝ እጁ ከሰንሰለቱ ጋር መስቀሉን ይዞ ንጉሡንና ወታሮቹን ሳይፋራ የኢየሱስ ክርስቶስን የእግዚአብሔር ልጅነትና አምላካዊ ሥልጣኑን ይመሰክር ነበር፡፡ ንጉሡም በቍጣ ይሙት በቃ ፈረደበት፡፡

ከላይ እንደ ተገለጸው ሮማውያን የሞት ፍርድ ሲፈርዱ የሚቀጣው ሰው የሌላ አገር ዜጋ ከኾነ ከፍርዱ ውጪ ተጨማሪ ቅጣት ይቀጡትና ይገድሉት ነበር፡፡

ቅዱስ ጳውሎስ ግን የሮም ዜግነት ስለ ነበረው ሳይገርፉ በአንድ ቅጣት ብቻ በሰይፍ እንዲገደል ወስነውበታል፡፡ ወደሚገደልበት ስፍራ ሲወስዱትም በንግግሩና በአስተያየቱ ኹሉ ምንም ፍርኀት አይታይበትም ነበር፡፡ እንዲያውም በጦርነት ድል አድርጎና ማርኮ እንደ ተመለሰ ወታደር ይደሰት ነበር እንጂ፡፡ ለሚገድሉትም ይቅርታን ይለምን ነበር፡፡ በገዳዮቹና በተከታዮቹ ፊትም የክርስትና ሽልማቱ የእግዚአብሔር መንግሥት መኾኑን የሚያስገነዝብ ቃል እያስተማረ እግዚአብሔር የሚሰጠውን የጽድቅ አክሊል ለመቀበል ይቻኮል ነበር /፪ኛቆሮ.፬፥፮-፲፰/፡፡

ሊገድሉት ሲወስዱትም ከንጉሥ ኔሮን ወገን የኾነችውን የአንዲት ብላቴና መጐናጸፊያ *ዛሬ እመልስልሻለሁ* ብሎ ከተቀበላት በኋላ *መልካሙን ገድል ተጋድያለሁ፤ ሩጫዬን ጨርሻለሁ፡፡ ሃይማኖቴን ጠብቄአለሁ፤ ወደፊትም የጽድቅ አክሊል ተዘጋጅቶልኛል፤* በማለት በመልእክቱ እንደ ተናገረው /፪ኞጢሞ.፬፥፯-፰/፣ ፊቱን በንጉሡ ልጅ መጐናጸፊያ ተሸፍኖ አንገቱን በሰይፍ ተቀልቶ አገልግሎቱን በሰማዕትነት ፈጽሟል፡፡ ደቀ መዛሙርቱም ራሱን ከአንገቱ ጋር ቢያደርጉት እንደ ቀድሞው ደኅና ኾኖላቸው በክብር ገንዘው ቀብረውታል፡፡

ሰያፊው ቅዱስ ጳውሎስን እንደ ገደለው ለመናገር ወደ ንጉሡ ሲመለስም ያቺ መጐናጸፊያዋን የሰጠችው ብላቴና *ጳውሎስ ወዴት አለ?* አለችው፡፡ እርሱም *ራሱን ተቈርጦ በመጐናጸፊያሽ ተሸፍኖ ወድቋል* ሲላት *ዋሽተሃል፤ እነሆ ጴጥሮስና ጳውሎስ በእኔ በኩል አልፈው ሔዱ፡፡ እነርሱም የመንግሥት ልብስ ለብሰዋል፡፡ በራሳቸውም በዕንቍ ያጌጡ አክሊላትን አድርገዋል፡፡ መጐናጸፊያዬንም ሰጡኝ፡፡ ይህችውም እነኋት፤ ተመልከታት* ብላ ሰጠቸው፡፡ ከእርሱ ጋራ ለነበሩትም አሳየቻቸው፡፡ አይተውም አደነቁ፤ ስለዚህም በጌታቻን በኢየሱስ ክርስቶስ አመኑ፡፡

እኛም ቅዱሳን ሐዋርያት ያቆዩልንን የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ጠብቀን፣ በክርስቲያናዊ ምግባር ጸንተን እንድንኖርና በመጨረሻም የእግዚአብሔርን መንግሥት ለመውረስ እንድንበቃ የቅዱሳኑ ጸሎት ይርዳን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ምንጭ፡-

መጽሐፈ ስንክሳር፣ ሐምሌ ፭ ቀን፤

ዜና ሐዋርያት፡፡