2 (2)

የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የድኅረ ምረቃ መርሐ ግብር ጀመረ

ጥቅምት 29 ቀን 2005 ዓ.ም.

በዲ/ን ዮሴፍ ይኲኖ አምላክ


2 (2)ቅዳሜ ጥቅምት 24 ቀን 2005 ዓ.ም በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የመሰብሰቢያ አዳራሽ፤ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የኮሌጁ የቦርድ አባላት፣ የአስተዳደር ሠራተኞች፣ መምህራንና ተማሪዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በጸሎት በተከፈተው ጉባኤ፥ ኮሌጁ የሁለተኛ ዲግሪ መርሐ ግብር መጀመሩ በይፋ ተበስሯል፡፡

 

የእንኳን ደህና መጣችሁና የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ የቅድሰት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የበላይ ሓላፊና፥ የቅዱስ5 ሲኖዶስ አባል፤ ኮሌጁ፥ ከጊዜ ወደ ጊዜ በእግዚአብሔር ፈቃድ እያደገ ከፍተኛ የነገረ መለኮት ኮሌጅ ለመሆን መብቃቱን አውስተው፥በተለይ አፄ ኀ/ሥላሴ ለኮሌጁ ያበረከቱትን አስተዋጽኦ ሲናገሩ፡- “አሁን ኮሌጁ የሚገኙበትን ቦታ፥ የቤተ ክርስቲያንና የሀገሪቱ አባት የነበሩት ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኀይለ ሥላሴ ለመንፈሳዊ ትምህርት ከነበራቸው ቅን አስተሳሰብ በመነጨ ቦታውን ‘የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት’ ተብሎ እንዲሰየምና አገልግሎት እንዲሰጥ አበርክተዋል፡፡ ግርማዊነታቸው ለቤተ ክርስቲያኒቱ በሠሯቸው በጎ ሥራቸው ሲታሰቡ ይኖራሉ፡፡ ”በማለት ገልጸው፥ኮሌጁ የመክፈቻ ንግግራቸውን ያደረጉት ከጥቅምት 24 ቀን 2005 ዓ.ም. ጀምሮ በሲስተማቲክ ቲዎሎጂ የሁለተኛ ዲግሪ መርሐ ግብር ለመጀመር እንደተቻለ አስታውቀዋል፡፡

 

ከብፁዕነታቸው የመክፈቻ ንግግር ተከትሎ ስለኮሌጁ ታሪካዊ ዳሰሳ ያቀረቡት ዶ/ር አባ ኀይለ ማርያም መለሰ የኮሌጁ 4 (2)ምክትል ዋና ዲ/ን፡- “የትምህርት መድረክ የጥበብ መደብር ነው፡፡ ለአያሌ ዘመናት ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ብቸኛዋ የእውቀት ቀንዲል አብሪ ሆና ቆይታለች፡፡ ይህ የተቀደሰ ተልዕኮዋም እየሰፋና እያዳበረ ሄዶ ለዛሬ በቅተናል፡፡ ለዚህም አንዱ ዓይነተኛ መሣሪያ ይህ ከፍተኛ የትምህርት ማእከል ነው፡፡ በእግዚአብሔር ስም የተመሠረተ እውቀት መንፈሳዊ እየተስፋፋ በሄደ ቁጥር፥ የቤተ ክርስቲያናችን ክብር፣ የሃይማኖታችን ጽናት፣ የሀገራችን ፍቅር፣ ሰላምና አንድነት ይጠበቃል ይጠነክራል ይልቁንም ትውልዱ እግዚአብሔርን የሚፈራ ግብረ ገብነት ያለው ይሆናል፡፡

 

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከአንድ ሺህ አምስት መቶ ዘመን በላይ በሀገራችን በኢትዮጵያ የትምህርት ማዕከል ሆኖ ቆይታለች ይኸንኑ ለረጅም ዘመን በበላይነትና በብቸኝነት የቆየ መንፈሳዊ ትምህርት በዘመናዊው የማስተማር ስልት (ዘይቤ)  ማከናወን ይቻል ዘንድ በ1934 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ግርማዊ ቀዳማዊ ዓፄ ኃይለ ሥላሴ፥ የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅን ‘የካህናት ፎረም’ በሚል ስያሜ በቤተ መንግሥታቸው መሠረቱት፣” በማለት ስለ ታሪካዊ አመሠራረቱ ካወሱ በኋላ በ1935 ዓ.ም. የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የተመሠረተበት የገነት ልዑል ቤተ መንግሥት አሁን ወዳለበት ቦታ ተዛወሮ በዚሁ ዘመን ግርማዊነታቸው የቅድስት ሥላሴን መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ሕንፃ የመሠረት ድንጊያ እንዳስቀመጡ ገልጸዋል፡፡

 

በስተመጨረሻም በዛሬው እለት ለተሰባሰብንበት የድኅረ ምረቃ መርሐ ግብር ኮሌጁ ለዚህ መብቃቱ ለመላው የቤተ ክርስቲያን አማኞችና2 (1) ወዳጆቿ ታላቅ የምሥራችና ደስታ ነው፡፡ ይህን መርሐ ግብር ለመጀመር ከፍተኛ አባታዊ አመራር የሰጡንን የኮሌጃችንን ኃላፊ ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስን፣ እንዲሁም የአመራር ቦርዱን፣ መምህራንና የቢሮ ሠራተኞችን ለዚህ ስኬት በመሥራታቸው ልባዊ ምስጋናዬን አቀርባለሁ” በማለት ንግግራቸውን አጠናቀዋል፡፡

 

ከዶክተር አባ ኀይለማርያም ንግግር ቀጥሎ በመምህር ፍስሐጽዮን ደሞዝ የኮሌጁ ምክትል አካዳሚክ ዲን ስለኮሌጁ አካዳሚክ እድገትና ስለድህረ ምረቃ መርሐ ግብር አጀማማር ሪፖርት ቀርቧል፡፡

 

6‘‘ኮሌጁ ከተከፈተ ጊዜ ጀምሮ ለረጅም ዓመታት ደቀመዛሙርትን ያሰለጥን የነበረው በዲፕሎማ እና በዲግሪ መርሐ ግብሮች ሲሆን ከ2002 ዓ.ም ጀምሮ ግን በልሳነ ግእዝ ዲፕሎማ፣ በርቀት ሰርተፍኬት፣ በድህረ ምረቃ ዲፕሎማ(PGD) እና በዘንድሮው የትምህርት ዘመን ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ የድህረ ምረቃ የሁለተኛ ዲግሪ መርሐ ግብሮችን ሊጀምር ችሏል፡፡ ከነዚህ ፕግራሞች በተጨማሪ በቀጣይ በርቀት ትምህርት ዲፕሎማ መርሐ ግብርን ለማስጀመር አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት አጠናቅቋል፡፡’’በማለት የተናገሩት  ምክትል አካዳሚክ ዲኑ የሁለተኛ ዲግሪ መርሐ ግብር ለመጀመር ያስፈለገበትን ምክንያት ሲያብራሩ አራት ነጥቦችን ጠቅሰዋል፡፡ እነርሱም

 

1ኛ. የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ዶግማዋን፣ ቀኖናዋን፣ ሥርአቷን፣ ትውፊቷን እና ባሕሏን እንዲሁም አንድነቷን ጠብቃ ወደፊት እንድትራመድ የሚያስችላት ትውልድ ተሻጋሪ የሆነ ከፍተኛ የጥናትና ምርምር ተቋም እንዲኖራት ለማስቻል፣

 

2ኛ ቤተ ክርስቲያናችን ከፊቷ ከተጋረጡባት ተግዳሮቶች ማለትም ከዘመናዊነትና ከሉላዊነት (globalization) ራሷን የምትከላከልበት በነገረ መለኮት ትምህርት የበሰሉ መምህራንና ደቀ መዛሙርትን ለማፍራት፡

 

3ኛ. ቤተ ክርስቲያናችን በሀገር ውስጥ እና ከሀገር ውጪ ካሉዋት ተከታዮች አንፃር ሲታይ ያልዋት ከፍተኛ የነገረ መለኮት ተቋማት እጅግ በጣም አነስተኛ ስለሆኑ በዚህ በድኅረ ምረቃ ፕሮግራሙ በቂ የሰው ኀይልን እና ምሁራንን በማፍራት እንደሌሎቹ አኅት አብያተ ክርስቲያናት ተጨማሪ የነገረ መለኮት ኮሌጆች ለመክፈት የሚያስችላትን አዲስ ዕድል ስለሚፈጥር፣

 

4ኛ. የድኅረ ምረቃ ፕሮግራሙ ከፍተኛ ጥናት እና ምርምር የሚደረግበት ስለሆነ ቤተ ክርስቲያናችን በሀገር ውስጥ እና በውጪ ሀገር አንድነቷ ተጠብቆ እንዲቆይ የሚያስችሏትን የመጻሕፍት ትርጉም ሥራዎች፣ የወንጌል አገልግሎትን ለማስፋፋት የምትከተላቸውን ስልቶችና ዘዴዎችን እንዲሁም በተለያዩ የቤተ ክርስቲያናችን ጉዳዮች የሚያጠነጥኑ ጥናቶችን እና ምርምሮችን በማድረግ ችግር ፈቺ እና የመፍትሔ አቅጣጫዎችን ጠቋሚ የሆኑ መረጃዎችን ለማግኘት ይህ ፕሮግራም እንደ ምንጭ ሆኖ ያገለግላል፡፡ ’’ በማለት ተናግረዋል፡፡

 

ከምክትል አካዳሚክ ዲኑ ሪፖርት ለመረዳት እንደተቻለው ኮሌጁ በ2005 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን ለመጀመሪያ ጊዜ በመደበኛው መርሐ 4 (1)ግብር 33 ደቀ መዛሙርትን ተቀብሎ የመማር ማስተማሩን ሂደት ጀምሯል፡፡

 

በመርሐ ግብሩ ማጠናቀቂያ ላይ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክና የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የሁለተኛ ዲግሪ የማስትሬት መርሐ ግብሩ  መጀመሩን በይፋ አብስረዋል፡፡