የቅዱስ ሲኖዶስ ሰማያዊና ሉዓላዊ ሥልጣን ይከበር!

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንም የሐዋርያትን ሥልጣን የያዘ የራሷ ቅዱስ ሲኖዶስ ባለቤት ከሆነች እነሆ ሃምሳ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ቅዱስ ሲኖዶሱም በሐዋርያት መንገድ አካሔዱን አጽንቶ ለመገኘት የራሱን ሕገ ቤተ ክርስቲያን አዘጋጅቶ ተቋማዊ አመራሩን ለማጠንከር ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ በዚህም ሕገ ቤተ ክርስቲያን የቅዱስ ሲኖዶሱ፣ የቅዱስ ¬ትርያርኩ፣ የቋሚ ሲኖዶስ፣ የመንበረ ¬ትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ሥራ አስኪያጅ፣ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ፣ የሊቃነ ጳጳሳትና የአስተዳደር ጉባኤው … ሥልጣንና ተግባር በሕገ ቤተ ክርስቲያኑ በግልጽ ተቀምጧል፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስም የሕግ አውጪው አካል እርሱ በመሆኑ ለጊዜው በሚያስፈልጉና ወቅቱ በሚጠይቃቸው አግባቦች የኢትዮጵያን ቤተ ክርስቲያን ጥንካሬ ለማስጠበቅና ከቤተ ክርስቲያን ጠላቶች ጠብቆ፤ ለቀጣይ ትውልድ ከመንፈስ ቅዱስ የተቀበለውን አደራ ለማስረከብ ያወጣቸውን ሕግጋት ያስጠብቃል፤ ያሻሽላልም፡፡ ለሚያወጣቸውም ሕግጋትና ለውሳኔዎቹ መነሻ የሚሆኑት ደግሞ ቅዱሳት መጻሕፍትና የመንፈስ ቅዱስ ጸጋና ረድኤት ናቸው፡፡ ያሉ ችግሮችንም አጉልተው ሊያሳዩ የሚችሉ እውነተኛ መነጽሮቻችን እነርሱ ናቸውና፡፡

ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በቅዱስ ሲኖዶስ አሠራር ውስጥ ጣልቃ የሚገቡና ካለው ሕግና ሥርዓት ውጪ የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦችና ቡድኖች እየተስተዋሉ ነው፡፡ ለዚህም ማሳያው ከግንቦት 5 እስከ 13 ባደረገው ጉባኤ ያሳለፈውን ውሳኔ ተከትሎ የተከሰተው ችግር ነው፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ በቤተ ክርስቲያኒቱ ታይቷል ያለውን «የአስተዳደር ችግሮች፣ የሙስናና፣ የቤተሰባዊ አስተዳደር» አካሔድ መኖሩን በማመን ዘመኑን የዋጀ በተጠና ዕቅድና አፈጻጸም የሚከናወን፤ ሓላፊነትና ተጠያቂነት የሰፈነበት ዘመናዊ የአስተዳደር ሥርዓት ለመዘርጋት ውሳኔ አስተላልፏል፡፡ በውይይቱም ወቅት በአሠራሮች ውስጥ የመልካም አስተዳደር፣ የፋይናንስ አጠቃቀም፣ የሰው ኃይል አደረጃጀት ችግሮች መታየታቸውንና በልማት ሥራዎችም የሚፈለገውን ያህል ለውጥ አለመኖሩ ላይ ከስምምነት ደርሷል፡፡ እነዚህን ችግሮች ለማስተካከልና ከእርሱ የሚጠበቀውን የቅድስና አሠራር ለማስፈን የሚያስችል ከብፁዓን አባቶች የተውጣጣ ኮሚቴ የሰየመ ቢሆንም ተግባሩን ለማከናወን ያደረገው ጅምር እንቅስቅሴ ግን ውዝግብ አስከትሏል፡፡ ለዚህ ችግር መፈጠር ደግሞ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረጉ ያሉት ከብፁዓን አባቶች ውጪ ያሉ ግለሰቦች መሆናቸው በተከታታይ እየሆኑ ያሉት ነገሮች ያመለክታሉ፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ ለቤተ ክርስቲያኒቱ ይጠቅማል በማለት የወሰነው ውሳኔ ገና ተግባራዊ እንቅስቅሴ ሳይጀመርበት አለመግባባት እንዲከሰት የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ማንነት ደግሞ አጠያያቂ ሆኗል፡፡ ምክንያቱም የውሳኔው አተገባበር ገና በሒደት ላይ እያለ ይህ ዓይነት ውዥንብር እንዲፈጠር መፈለጉም ማኅበራችንን ጨምሮ ለብዙ ምእመናን ያሳዘነ አካሔድ ሆኗል፡፡

ከዚህ አልፎም የቤተ ክርስቲያኒቱን አባቶች ክብርና ስም የሚያጐድፍ ተያይዞም የቤተ ክርስቲያንን እውነተኛ መንገድ የሚያሰድቡ የሕትመት ውጤቶችን በማሠራጨት የብፁዓን አባቶችን እንቅስቅሴ ለማዳከም፣ ለስምና ለክብራቸው በመሰቀቅ መልካሙን እንዳይሠሩ ለማድረግ የተለያዩ አፍራሽ እርምጃዎች ተወስደዋል፡፡ ከቅዱስ ¬ትርያርኩ ጀምሮ ብፁዓን አባቶች በሚያጠፉት ጥፋት ጠያቂ፣ ከሳሽ፣ ፈራጅ፣ መካሪ … ራሱ ቅዱስ ሲኖዶስ ሆኖ ሳለ ከዚያ አግባብ ውጪ፣ ከክርስቲያኖች በማይጠበቅ መንገድ፣ ለቤተ ክርስቲያን በመቆርቆር ስም የሚደረጉ የጥፋት ዘመቻዎች መቆም እንዳለባቸው ማኅበራችን የጸና እምነት አለው፡፡

በመሆኑም ቅዱስ ሲኖዶስ በሕገ ቤተ ክርስቲያኑ መሠረት ያለውን ሰማያዊና ሉዓላዊ ሥልጣን ራሱ የማስከበር ሓላፊነት ያለበት ሲሆን የቅዱስ ሲኖዶስ አባል የሆኑ ሁሉም ብፁዓን አባቶች የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ሁሉ ሕገ ቤተ ክርስቲያኑን ጠብቀው እየተከናወኑ መሆኑን ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል እንላለን፡፡ ችግሮችም በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የተወሰኑ ውሳኔዎችን ተግባራዊ በማድረግ ሒደት ላይ የተከሰቱ ስለሆነ የሲኖዶሱን ውሳኔ አፈጻጸም እንዲከታተል ሕገ ቤተ ክርስቲያኑ ሓላፊነት የሰጠው አካል ሓላፊነቱን እንዲወጣ ያስፈልጋል፡፡

በውሳኔ አሰጣጥ፣ ውሳኔዎችን በመተርጐም ሒደት ብፁዓን አባቶች ያላቸውን ግልጽ ድርሻ በረድኤተ መንፈስ ቅዱስ፣ በቅዱሳት መጻሕፍትና በሕሊና ምስክርነት ላይ ተደግፈው መፈጸም እንዳለባቸው የሁሉም እምነት ነው፡፡ በዚህ መንገድም አካሔዱን ካላጸና ሓላፊነት ያልተሰጣቸው ሌላ አካላት ጣልቃ ገብተው ተጽዕኖ እንዲፈጥሩ እድል ስለሚሰጥ ዘወትር አስፈላጊ የሆኑ ጥንቃቄዎች ሁሉ መደረግ እንዳለባቸው እናምናለን፡፡

የቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዳደር ጉባኤም በቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠው የማስፈጸም ሥልጣን የተወሰኑትን ደንቦች፣ መመሪያዎችና ልዩ ልዩ ውሳኔዎች ተግባራዊ ማድረግ፤ ከእያንዳንዱ የሥራ ዘርፍ በሚቀርበው ጉዳይ ላይ እየተወያየና የሥራ አፈጻጸም ስልት እያወጣ መወሰን፤ በሚመለከተው ደረጃ የአስተዳደር ችግሮች ሲፈጠሩ እያጠና መፈትሔ መስጠት፤ ከየሀገረ ስብከቱ በይግባኝ የሚመጡ ጉዳዮችን መወሰን እንደሆነ ይታወቃል፡፡ እነዚህ ተግባራት ሁሉ ግን የቅዱስ ሲኖደስን ሥልጣን ከማክበር ጋር፤ ለወሰናቸውም ውሳኔዎች ከመገዛት ጋር የሚፈጸሙ ናቸው፡፡ ከዚህ ባለፈ ግን በቅዱስ ሲኖደስ ውሳኔ ላይ ተጽዕኖ የመፍጠርና አግባብ ያልሆነ የውሳኔ አተረጓጐምን የመከተል አካሔድ እንዳይኖር ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበት እናምናለን፡፡

በአጠቃላይ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በቤተ ክህነቱ አሠራር ውስጥ ይመለከተናል የሚሉ ወገኖች ሁሉ ቅዱስ ሲኖዶስ ያለውን የሕግ አውጪነትና ተርጓሚነት ሥልጣን አምኖ መንቀሳቀስ ለቤተ ክርስቲያኒቱ ተቋማዊ አሠራር ሕልውና የግድ የሚያስፈልግ ነው፡፡ በመሆኑም እነዚሁ አካላት ለቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔዎች ተግባራዊነት እንዲተባበሩና በውሳኔዎቹ ይዘቶች ላይ ያሉ ብዥታዎችንም ራሱ ቅዱስ ሲኖዶስ ግልጽ የሚያደርግበትን የራሱን አሠራር መጠበቅና ማስጠበቅ ይገባቸዋል፡፡ ከዚህ ባለፈ ግን የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔን እየተሰበሰቡ በመቃወም ሥልጣንና ቅድስናውን የመፈታተን አካሔድ ከወዲሁ ሊገታ ይገባዋል፡፡

በሃይማኖት ተቆርቋሪነት ስም የብፁዓን አባቶችን ስም በማጉደፍ፣ ለማጉደፍም በመዛት በአባቶች መካከል መለያየትን የሚያሰፍኑ በሥልጣንም ሆነ በሓላፊነት የማይመለከታቸው ግለሰቦችም ሆኑ ቡድኖች ከድርጊቶቻቸው መቆጠብ ይኖርባቸዋል፡፡ እንዲህ ያሉ ወገኖች ከምንም በላይ ለቤተ ክርስቲያን ሰላምና አንድነት የማይጨነቁ ከሆነ፣ በመንፈስ ቅዱስ ለተሾሙ አባቶችም ክብርን የመስጠት ፍላጐት ካጡ፣ እንዲሁም አባቶች በቅዱስ ሲኖዶስ በሚኖራቸው የመወሰን ድርሻ ላይ ተጽእኖ የመፍጠር አዝማሚያ ማሳየታቸውን ከቀጠሉ ማኅበራችን ድርጊታቸውን ከማውገዝ ባለፈ በሃይማኖት ወገንተኝነታቸው ላይ ጥያቄ ይኖረዋል፡፡

በሌላም በኩል አንዳንድ የግል መገናኛ ብዙኃን በሚያቀርቡት የተዛባ መረጃ ጉዳይ በሚመለከታቸው የቤተ ክህነቱ ወገኖች ላይ ስጋትና ጥርጣሬ ከመፍጠር አልፎ ከፍተኛ ችግሮች እያስከተለ ነው፡፡ ይህ አካሔድ ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ዕድገትና ጥንካሬ ለዓመታት ሲንቀሳቀስ የቆየውን ማኅበራችንን ማኅበረ ቅዱሳንን በእጅጉ ያሳስበዋል፡፡ በመሆኑም እነዚህ የመገናኛ ብዙኀን በእውነተኛ ምንጮች ላይ ተደግፈው እውነተኛ መረጃዎችን በመስጠት ችግሩን ለመፍታት እንዲንቀሳቀሱ መጠየቅ እንወዳለን፡፡

ካህናትና ምእመናንም ቤተ ክርስቲያናችን ከእግዚአብሔር ጋር የምንገናኝባት የክርስቶስ ሙሽራ መሆኗ ተጠብቆ እንዲቀጥል የፈጣሪም ረድኤትና በረከት እንዳይለየን ለሰላሟና አንድነቷ በንቃት መቆም ይገባናል፡፡ ምእመናን ዓሥራት በኩራት አውጥተው የሚያስተዳድሯት ቤተ ክርስቲያን በመሆኗ የቅዱስ ሲኖዶስ ሰማያዊና ሉዓላዊ ሥልጣንን በሕገ ቤተ ክርስቲያኑ መሠረት የማስከበር የማይተካ ሚና አላቸውና፡፡ በመሆኑም ምእመናን ጉዳዮችን የራሳችን ጉዳይ በማድረግ ቤተ ክርስቲያን በየጊዜው ከሚያጋጥማት ፈተና እንድትድን በጾም በጸሎት እንድንበረታ መልእክታችን ነው፡፡

ምእመናንን ዕለት ዕለት በማገልገል ከምድር የሆነውን ብቻ ሳይሆን ሰማያዊውን ደመወዝ በተስፋ የሚጠባበቁ ካህናትም በጾም በጸሎት ከመትጋት ባሻገር በፈተና ጊዜ ፈተናን ለማስረግ አጋጣሚዎችን የሚጠቀሙ የቤተ ክርስቲያንን ጠላቶች መከታተልና ማስታገስ ይጠበቅባቸዋል፡፡

ከምንም በላይ ደግሞ በሕገ ቤተ ክርስቲያኑ ምዕራፍ ሁለት አንቀጽ ስድስት እንደተቀመጠው የክርስቲያን ወጣቶች እንቅስቃሴ እንዲጐለብት ቅዱስ ሲኖዶስ ዓላማው አድርጐ እየሠራ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በመሆኑም በሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መመሪያ ሥር ሆነን አገልግሎት እየሰጠን ያለን ሰንበት ት/ቤቶችና ማኅበራት የቅዱስ ሲኖዶስን ሰማያዊና ሉዓላዊ ሥልጣን ማስከበር ለሥራችን ስኬትና ለምናገለግላት ቤተ ክርስቲያን ተቋማዊ ጥንካሬ ወሳኝ መሆኑን ልንረዳ ይገባል፡፡ ስለዚህም በተለያዩ ጊዜያት ቤተ ክርስቲያናችን ከውስጥና ከውጪ የሚገጥማትን ፈተና ለመቋቋም ጥረት ማድረግ ይገባናል፡፡ ማኅበረ ቅዱሳንም ይህን ድርሻውን ተረድቶ የሚንቀሳቀስ መሆኑን እየገለጸ፤ በቀጣይም በቅዱስ ሲኖዶስ የሥልጣን የበላይነት በቤተ ክርስቲያናችን አንድነት እና በቅዱስ ¬ትርያርካችን አባትነት ላይ የጸና አቋም እንዳለው በግልጽ ማስቀመጥ ይፈልጋል፡፡ ለዚህም እውን መሆን ከሚተጉ አካላት በመተባበር ያላሠለሰ ጥረት ማድረጉን እንደሚቀጥል መልእክቱን ያስተላልፋል፡፡

                                                            ወስብሐት ለእግዚአብሔር።