የቃለ ዓዋዲው ክለሳ በውጭ ያለውን አገልግሎት ያካትት-

ሚያዚያ 1/2004 ዓ.ም.

ሃያኛው መቶ ክፍለ ዘመን በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን በርካታ ለውጦች የተስተናገዱበት ነበር፡፡ ከለውጦቹ ውስጥ ደግሞ ዋና ዋናዎቹ ሁለት ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ የመጀመሪያው ለውጥ በውድ የመጣ ይልቁንም ለውጡ እውን ይኾን ዘንድ ከ0ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ ነገሥታትና ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት የተጋደሉለት ለውጥ ነው፡፡ ይኸውም የቤተ ክርሰቲያኗን አስተዳደር ለ1600 ዘመናት በቅብጥ ቤተ ክርስቲያን ጥላ ሥር እንዲቆይ ያደረገው ሊቃውንት መንበረ ጵጵስናውን ትንሽ ቆይቶም መንበረ ፕትርክናውን ተረክበው ዕውቀት መንፈሳዊ እየመገበች ያሳደገቻቸውን ቤተ ክርስቲያን መምራት የጀመሩበት የለውጥ ምዕራፍ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ቤተ ክርስቲያኗ ለሀገር ለሕዝብ ለምትሰጠው አገልግሎት ዋጋ ይኾናት ዘንድ ከነገሥታት ተሰጥቷት የነበረው ርስት ጉልት ተነጥቆ «ራስሽን ቻይ» የተባለችበት የግድ ለውጥ ነው፡፡

እነዚህ ሁለት ለውጦች በቤተ ክርስቲያኗ ረጅም ታሪክ ሲከሰት ያዩ በወቅቱ የነበሩ አበው፤ ቤተ ክርስቲያኗ በለውጦቹ ግራ ስትጋባ የነበረ ሐዋርያው ተልእኮዋን አጠናክራ በምትቀጥልበት ሁኔታ ላይ መምከርን ያዙ፡፡ የምስክራቸው ነጥቦች የቤተ ክርስቲያኗን አስተዳደር እንዴት ሀገራዊ መልክዕ መስጠት ይቻላል) በገቢዋ ከካህናቷና አገልጋዮቿ የዕለት ጉርስ የዓመት ልብስ አልፎ ሀገርን ትመግብ የነበረች ቤተ ክርስቲያን የነበራት የኢኮኖሚ ምንጭ ከደረቀ ዘንድ፤ አገልግሎቷ በገንዘብ ማጣት እንዳይታጐል ምን ይደረግ) የሚሉ ነበሩ፡፡ በመንፈስ ቅዱስ ገላጭነትም በርካታ የመፍትሔ አቅጣጫዎች አስቀመጡ፡፡

 

በወቅቱ ከተቀመጡ የመፍትሔ አቅጣጫዎች ውስጥ መሠረታዊው የቤተ ክርስቲያኗን አስተዳደራዊ አንድነት የሚያስጠብቅ፤ ለቤተ ክርስቲያኗ አገልግሎት የሚያስፈልገው ገንዘብም በራሷ ልጆች /ምእመናን/ የሚሸፈንበትን ሁኔታ የሚያረጋግጥ ሕገ ቤተ ክርስቲያን አርቅቆ ሥራ ላይ ማዋል ነበር፡፡ ቃለ ዓዋዲ በመኾኑም ይህ ሕግ በምክረ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ተራቅቆ፤ በትእዛዝ አዋጅ ቁጥር 83/65 ተፈቅዶ፤ ጥቅምት 15 ቀን 1965 ዓ.ም በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ ተፈርሞ ሥራ ላይ ዋለ፡፡ ካህናትና ምእመናን በያሉበት በታወቀ መልኩ እየተደራጁ የቤተ ክርስቲያኗን አስተዳደር እንዲመሩ የሚያደርገው ይህ ሕገ ቤተ ክርስቲያን ሥራ ላይ ከዋለበት ጊዜ ጀምሮ ለሕጉ እውን መኾን የተጉት አበው ያሰቡለትን ዓላማ በማስፈጸም ላይ ይገኛል፡፡ በእርግጥ በአፈጻጸሙ ሒደት ከሕጉ የመነጩ ሳይኾን ከአፈጻጸም የሚታዩ ችግሮች መኖራቸው ግልጽ ነው፡፡ የአሁኑ መልእክታችን ዓላማ እሱ ባለመኾኑ ወደዚያ አንገባም፡፡

 

ቃለ ዓዋዲ ሕጋችን በቤተ ክርስቲያኗ ሁሉን አቀፍ እንቅስቃሴ ላይ ያመጣውን አዎንታዊ ለውጥ በምንመለከትበት ጊዜ ጥንካሬውና ብቃቱ ተፈትኖ የተረጋገጠው በሀገር ቤት ባለችዋ ቤተ ክርስቲያን ላይ ብቻ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡

 

ሕጉ ተረቅቆ ሲወጣ ቤተ ክርስቲያናችን በውጪው ዓለም ያልተስፋፋችበት ወቅት በመኾኑ የተቀረጸው በሀገር ቤት ያለችዋን ቤተ ክርስቲያን አስተዳደርና አንድነት እንዲያጠናክር ሆኖ ነበር፡፡ ከአንድም ሦስት ጊዜ የተሻሻለ መሆኑ ቢታመንም በአበው ትጋትና በስዱዳን ልጆቿ ብርታት በውጭው ዓለም እየተስፋፋች ያለችዋን ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን እንቅስቃሴ እንዲያግዝ የሚያስችል አንቀጽ አልተጨመረበት፡፡ ይህም በመሆኑ ቤተ ክርስቲያናችን በውጭው ዓለም በፍጥነት የመስፋፋቷን ያህል አስተዳደራዊ ችግሮቿም እንዲበዙ ሆኗል፡፡ በተለያዩ ክፍላተ ዓለም ለሚቋቋሙ አብያተ ክርስቲያናት ያገለግሉ ዘንድ አባቶች ሲላኩም የሹመት ደብዳቤያቸውን አስይዞ ከመላክ ያለፈ ቤተ ክህነታችን ለአገልጋዩ መመሪያ የሚሆን ወጥ ሰነድ ሲሰጥ አልታየም፡፡ የለምና፡፡ በዚህም የተነሣ በውጭ ያለችው ቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ዥንጉርጉር እንዲሆን ሆኗል ማለት ይቻላል፡፡

 

ጠቢቡ «ቦ ጊዜ ለኲሉ» እንዳለው፤ ይህ ችግር ለረጅም ጊዜያት ሲንከባለል ኖሮ፤ በችግሩም ልጆቻቸውን ተከትለው በመሰደድ የሚያገለግሉ አበውም ግራ ሲጋቡ ቢቆዩም ጉዳዩ የቤተ ክርስቲያንኗ ከፍተኛ አመራር አካል /አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ/ አጀንዳ ወደ መሆን የተሸጋገረው ግን በያዝነው ዓመት መጀመሪያ ነበር፡፡ ባለፈው ጥቅምት ወር ፳)፬ ዓ.ም በተካሔደው የአጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ፤ እሱን ተከትሎም የተደረገው የቅዱስ ሲኖዶስ መደበኛ ምልአተ ጉባኤ ተወያይቶ ውሳኔ ካሳለፈባቸው ነጥቦች አንዱ ቃለ ዓዋዲው ወቅታዊውን የአገልግሎት ስፋት ባገናዘበ መልኩ እንዲከለስ፤ በክለሳውም በውጭ ያለችውን ቤተ ክርስቲያን አስተዳደርም ከግንዛቤ ውስጥ የከተተ የሚል ነበር፡፡ ያንን ውሳኔ ተቀብሎ የሚያስፈጽመው አካል /የሰበካ ጉባኤ መምሪያ/ ይህ አንገብጋቢ ጉዳይ በአስቸኳይ ወደ ተግባር እንዲለወጥ በመትጋት ላይ ይገኛል፡፡ እናም መምሪያው በሚያስተባብረው የቃለ ዓዋዲ ክለሳ ሂደት በውጭው ዓለም የምትገኘዋን ቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ ችግሮች ከግንዛቤ ውስጥ በሚገቡበት ሁኔታ ላይ ቢደረጉ የምንላቸውን ጥቂት ሐሳቦች እንሰነዝራለን፡፡

 

የመጀመሪያው ይሁንታ ለጉዳዩ ቀጥተኛ ባለቤቶች ዕድል በሚሰጥበት ሁኔታ ላይ ያጠነጠነ ነው፡፡ በውጭ ላለችው ቤተ ክርስቲያን የሚመች ሕግ ባለመኖሩ ሲቸገሩ የኖሩትና የሚኖሩት በውጭ ባለችዋ ቤተ ክርስቲያን የሚያገለግሉ ካህናትና ምእመናን ናቸው፡፡ የችግሩን ስፋት የሚያውቁት፣ የመሰላቸውንም መፍትሔ ለመስጠት ሲሞክሩ የኖሩት አሁንም ቢሆን የሚሉት ሐሳብ ያላቸው እነሱ ናቸውና፡፡ በመሆኑም ቃለ ዓዋዲውን በውጭ ላለችዋ ቤተ ክርስቲያን በሚመች መልኩ በመከለሱ ሒደት በውጭው ዓለም የሚኖሩ ካህናትና ምእመናን ጉልህ ድርሻ እንዲኖራቸው ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ለዚህም ሐሳባቸውን በየደረጃው /በአጥቢያ፣ በሀገር በአህጉርና በአህጉራት/ የሚያብላሉበትንና ይሁንታቸውን የሚያዋቅሩበትን መንገድ ዘርግቶ ተግባራዊ ማድረግ ይገባል፡፡ በዚህ ዓይነት የሕግ ረቀቁ ከታች ወደ ላይ እየዳበረ ከመጣ በኋላ አዲስ አበባ ላይ በሚካሔደው መደበኛ አጠቃላይ መንፈሳዊ ሰበካ ጉባኤ ቀርቦ የማጠቃለያ ውይይት ተደርጎበት በቅዱስ ሲኖዶስ ሕግ ሆኖ እንዲወጣ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ይህ መሆኑ አሁን በውጭው ዓለም የሚታየው አስተዳደራዊ ዥንጉርጉርነትና እሱ የወለዳቸውንም በርካታ ችግሮች ይቀርፋል፡፡

 

በውጭ ያለችዋን ቤተ ክርስቲያን አንድነት የሚያጠናክር ማእከላዊ ሕግ ወጥቶ ሥራ ላይ አልዋለም ብንልም፤ በውጭው ዓለም የሚያገለግሉ ካህናትና ምእመናን እንደ የአካባቢያቸው ነባራዊ ሁኔታና ችግሮቻቸው ይዘት መፍትሔ ይሆኑናል ያሏቸውን ሕግጋት እያረቀቁ ተግባር ላይ ሲያውሉ ቆይተዋል፡፡ በመሆኑም በውጭው ዓለም ልዩ ልዩ ይዘት ያላቸው የአብያተ ክርስቲያናት ሕገ ደንቦች አሉ፡፡ ቃለ ዓዋዲውን በመከለስ በተለይ በውጭ ያለችዋን ቤተ ክርስቲያን ችግር የሚያቃልሉ አንቀጾችን በማካተት  ሒደት እነዚህን ሕገ ደንቦች ሰብስቦ ማጥናቱ ተገቢ ነው፡፡ ደንቦቹ ምንም እንኳን በዚያ ያለችዋ ቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ ዥንጉርጉርነት መገለጫዎች ሆነው ቢቆዩም አልፎ አልፎ ለክለሳው ግብኣት የሚሆነ ጠቃሚ ሐሳቦች ይኖሯቸዋልና፡፡

 

ከላይ እንዳልነው በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሌለችበት ክፍለ ዓለም የለም ማለት ይቻላል፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን በስደት ከሄዱ ኢትዮጵያውያን አልፋ፤ በተሰደደችባቸው ሀገራት ጭምርም በጥምቀት ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ እየወለደች ወደ ጉያዋ የምትሰበስባቸው ሕዝቦች እየበዙ ይገኛሉ፡፡ በመሆኑም የቃለ ዓዋዲው ክለሳ ቤተ ክርስቲያኗ እምነት በቀዘቀዘችበት ዓለም ሙቀትና የክርስትና ተስፋ በመሆን የሰበሰበቻቸውን እነዚህን ሕዝቦች በአጥጋቢ ሁኔታ እንድታገለግል የሚያስችላት መሆን ይኖርበታል፡፡

 

ቃለ ዓዋዲውን በውጭ ላለችዋ ቤተ ክርስቲያን በሚመች መልኩ የመከለሱ ውሳኔ የዘገየ ቢሆንም፤ ዛሬ ቤተ ክርስቲያናችን በውጭው ዓለም እያደረገችው ካለው ፈጣን መስፋፋት አንጻር በእጅጉ አስፈላጊና በአስቸኳይ ተግባራዊ መሆን ያለበት ነው፡፡ በመሆኑም ለዚህ ውሳኔ ተግባራዊነት ሁላችንም የበኩላችንን እናድርግ፤ ከዚህም ጋር ዐቅሙና ለጉዳዩ ቅርበት ያለን አካላት ለሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያው ሞያዊ ድጋፍ ልናደርግ ይገባል እንላለን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር