የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ መጠናከር የቤተ ክርስቲያንን ሐዋርያዊ አገልግሎት ለማስፋፋት መሠረት ነው

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስተያንን ሐዋርያዊ አገልግሎት ለማስፋፋት፣ አገልጋዮቿን መዝግባ ይዛ ሥምሪት እና ምደባ ለመስጠት፣ ችሎታቸውንና ኑሮአቸውን ለማሻሻል፣ ምእመናንን ለማብዛትና በመንፈሳዊ እውቀት ጎልምሰው፣ በምግባርና በሃይማኖት ጸንተው እንዲኖሩ ለማድረግ፣ የቤተ ክርስቲያንን አስተዳደር ለማሻሻልና በሚያስፈልጋት ማንኛውም ጉዳይ ራሷን ለማስቻል ከአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ጀምሮ እስከ መንበረ ፓትርያርክ ድረስ በየደረጃው የሚቋቋም የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ መዋቅርና አሠራር በቃለ ዓዋዲው መሠረት ዘርግታ ትገኛለች፡፡
የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤዎች በሕዝብ በሚመረጡ ካህናት፣ ምእመናን እና የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች ተሳትፎ የቤተ ክርስቲያንን ሐዋርያዊ አገልግሎት ለማስፋፋትና አስፈላጊ የሆነውን አቅም ለማጐልበት የሚመክርባቸው፣ የሥራ ክንዋኔዎችና ችግሮች እየቀረቡ የሚገመገሙባቸውና ልምዶች የሚወስዱባቸው፣ ቀጣይ አቅጣጫዎችም እግዚአብሔር ቢፈቅድ በሚል የሚታይባቸው በመሆናቸው፤ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ መዋቅር ለቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ አገልግሎት መስፋፋት ወሳኝነት ያለው ነው፡፡

ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ብቻ ሳይሆን በዓለም ላይ በሚገኙ በአኀት አብያተ ክርስቲያናትም በእንግሊዘኛው አጠራር /ሪሽ ካውንስል/ በሚል ስያሜ እየተሠራበት የሚገኝ ዘመናዊ የቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ መዋቅር ነው፡፡

የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ /ሪሽ ካውንስል/ መዋቅርና አሠራር ሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጦች በምእመናን ላይ የሚያስከትሉትን ተጽዕኖና መልካም አጋጣሚ ባገናዘበ ሁኔታ የቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ አገልግሎት ማስፋፋትና ለዚህም የሚያስፈልገውን ዐቅም መፍጠርና ማጠናከር፣ የምእመናን ችግር መፍቻ እንዲሆኑ ለማድረግ አብያተ ክርስቲያናት፡- አካባቢያዊ እና የምእመናንን አኗኗር ሁኔታዎች እንዲሁም ቤተ ክርስቲያን ማድረግ የሚገባትን ዘመኑን የዋጀ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ /ሪሽ ካውንስል/ መዋቅርና አሠራር ለመዘርጋት ተጨባጭና ነባራዊ ሁኔታዎችን የተከተሉ የሕግና የመዋቅር ማሻሻያዎችን ያደርጋሉ፡፡ የአሠራር ስልቶችን በየጊዜው ያዳብራሉ፡፡

ከዚህ አኳያም በ1991 ዓ.ም ለሦስተኛ ጊዜ ተሻሽሎ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰበካ መንፈሳዊ ደንብ /ቃለ ዓዋዲ/ አንቀጽ 61  /2/ /ሀ/ ላይ የሰበካ ጉባኤ የሚኖረውን የምእመናን ድርሻ በተመለከተ፡- «የሰበካ ምእመናን በገንዘብ አስተዋጽኦ፣ በአስተዳደር፣ በትምህርት፣ በልማትና በማኅበራዊ ኑሮ አገልግሎት በጠቅላላው በሀብት፣ በዕውቀትና በጉልበት በመረዳት በሰበካው ልዩ ልዩ የክፍል ሥራዎች ውስጥ በመሳተፍ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ማገልገል ክርስቲያናዊ ግዴታቸው ነው፡፡» በማለት በተደነገገው መሠረት ምእመናን ለቤተ ክርስቲያናቸው የሚጠበቅባቸውን አገልግሎት ሲሰጡ ለሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ዓላማ መሳካት ትልቅ ድርሻ ያለው ነው፡፡

በቤተ ክርስቲያናችን ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ደንብ /ቃለ ዓዋዲ/ መሠረት በአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን የሚከተሉት ክፍሎች ይኖራሉ፡-

ሀ/ የስብከተ ወንጌል ክፍል
ለ/ የመንፈሳዊ ትምህርት ክፍል
ሐ/ የካህናት አገልግሎት ክፍል
መ/ የሰንበት ት/ቤት ክፍል
ሠ/ የእቅድና ልማት ክፍል
ረ/ የምግባረ ሠናይ /በጐ አድራገት/ ክፍል
ሰ/ የሕግና ሥነ ሥርዓት ክፍል
ሸ/ የንብረት፣ የዕቃ ግምጃ ቤትና የታሪካዊ ቅርስ ክፍል
ቀ/ የሒሳብ ክፍል
በ/ የገንዘብ ቤት
ተ/ የቁጥጥር ክፍል
ቸ/ የሕንፃ ሥራ፣ እድሳትና ጥገና ክፍል
ኀ/ የስታቲስቲክስ ክፍል

በሚል የተዋቀሩ የሥራ ክፍሎች ያሉት ሆኖ ምእመናን በችሎታቸው በቤተ ክርስቲያን አስተዳደር መሳተፍ እንዲችሉ የሚያደርግ ሲሆን ዳር ቁመን የምንመለከተው ወይም እገሌ ይሠራዋል፤ በሚል ልንሸሸው የማይገባ፣ ተሳታፊ በመሆን በረከት የምናገኝበት እና የቤተ ክርስቲያን ችግር የሚቀረፍበት መዋቅር ነው፡፡

በመሆኑም በሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ደንብ መሠረት የሚጠበቅብንን  የድርሻችንን ካልተወጣንና ለቤተ ክርስቲያን የሚጠቅመውን በወቅቱ ካላደረግን ደንቡና መዋቅሩ ብቻውን ትርጉም ሊኖረው ስለማይችል በተሰጠን ጸጋ ልናገለግል ይገባል፡፡ እግዚአብሔርም ከእኛ ብዙ ይጠብቃል፡፡ የተቀበልነው መክሊት ነውና በተሰጠን መጠን ይፈለግብናል /ማቴ. 25-14-30/፡፡

በጉባኤ ደረጃ ያለውን ኃላፊነት ስንመለከት የአጥቢያ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ፤ የአጥቢያው ካህናት፣ ምእመናን እና የሰንበት ት/ቤት ተማሪዎች የሚሳተፉበት በዓመት ሁለት ጊዜ የሚካሄድ ጠቅላላ ጉባኤ ያለው ሲሆን፤ የወረዳ፣ የሀገረ ስብከት እና የመንበረ ¬ፓትርያርክ ሰበካ ጉባኤዎችም በየደረጃቸው በዓመት አንድ ጊዜ በመሰብሰብ አፈጻጸማቸውን በማቅረብ ውይይት የሚያደርጉባቸው የሰበካ መንፈሳዊ ጠቅላላ ጉባኤዎች የሏቸው ስለሆነ፤ እኒህ በተለያየ ደረጃ የሚደረጉት ጠቅላላ ጉባኤዎች የበለጠ ውጤታማ እንዲሆኑ ለማድረግ ቅድመ ዝግጅት እና ከጉባኤዎቹ በኋላም ቢሆን ክትትል ማድረግን የሚሹ ናቸው፡፡

በዚህም መሠረት የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤዎችን በማጠናከር የቤተ ክርስቲያንን ሐዋርያዊ አገልግሎት ለማስፋፋት ከቀደምት ተሞክሮዎች አንፃር

ምእመናን፣ የቤተ ክርስቲያንን ሐዋርያዊ አገልግሎት ለማገዝ በሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ድርሻ ስላላቸው፡- በሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ በመምረጥና በመመረጥ ቢሳተፉና የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤያቸውን በገንዘባቸው፤ በሙያቸው እና በጉልበታቸው ቢያገለግሉና ሌሎች ምዕመናንን የቤተ ክርስተያንን ችግር ለመቅረፍ የሰበካ ጉባኤ ተሳትፎ ወሳኝ እንደሆነ አጽንኦት ቢሰጡ፤

በቃለ ዓዋዲው የተገለጸው እንደተጠበቀ ሆኖ በየደረጃው ለሚገኙ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤዎች ችግር ፈቺ  የሆነ፣ ዘመኑን የሚዋጅ ስትራተጂክ እቅድ እንዲወጣላቸው እና ከጉባኤዎቹ ስብሰባ በፊትና በኋላ አፈጻጸሙ ጽኑ ክትትል የሚደረግበት ሁኔታ ቢጠናከር፤

የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤያት የእስካሁን አፈጻጸም ምን እንደሚመስል እና በቀጣይ መሻሻል የሚገባቸው አሠራሮች ምን እንደሆኑ የሚያወያዩ ጥናት በየደረጃው እንዲቀርብ ቢደረግ፤

የሰበካ መንፈሳዊ አጠቃላይ ጉባኤያት የበለጠ ውጤታማ እንዲሆኑ ለማድረግ ጉባኤዎቹ ሪፖርቶች ማዳመጥ ብቻ ሳይሆን ችግር ፈቺ በሆኑ ጉዳዮች ላይ የጠነከረ ውይይት ሊያደርጉ ስለሚችሉበት ሁኔታ በሁሉም ደረጃዎች ወጥነት እንዲኖረው ቢደረግ፤

በሰበካ መንፈሳዊ ጠቅላላ ጉባያት የሚወሰኑ ጉዳዮች ጊዜ በማይወሰድ ሁኔታ ታች በየደረጃው ለሚገኙ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤያት ለአፈጻጸም እና ለግንዛቤ እንዲደርሱ አሠራሩ የተጠናከረ እንዲሆን ቢደረግ፤ እና በአንዳንድ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤዎች የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን አጣርቶ የመፍትሔ እና የውሳኔ ሐሳብ የሚያቀርብ ትጉህ እና ለችግሮች ገለልተኛ የሆነ ምእመናን የሚሳተፉበት አሠራር መዋቅራዊ እንዲሆን ቢደረግ፤

የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤን ዓላማና ተግባር ለማሳካት አስተዋጽኦ ስለሚኖረው፤ ያልፈጸምነውን አጉልተን በማየት፣ ቅድመ ዝግጅት እና ተሳትፎ በማድረግ የሚጠበቅብንን ልንወጣ ይገባል፡