የማኅበረ ቅዱሳን ወቅታዊ የአዘክሮ መልእክት

ጥቅምት ፭ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም

‹‹ወንድሜ ሆይ፥ በጎ አድራጊ እንጂ ክፉ አድራጊ አትኹን፤›› (፫ኛ ዮሐ. ቍ. ፲፩)::

በጌታችን ላይ በአይሁድ የተፈጸመውን ዂሉ ለድኅነተ ሰብእ እንደ ተፈጸመ ተቀብለን ሐተታ ላለማብዛት ብንተወው እንኳን መልካም የሚሠሩትን ክፉ ስም እየሰጡ ቤተ ክርስቲያንን የሚከፋፍል ሥራ መሥራት የተጀመረው በዚያው በሐዋርያት ዘመን እንደ ኾነ ቅዱስ መጽሐፍ ይመሰክራል፡፡ ‹‹ከእነርሱ አንዳንዶች በቅናታቸውና በክርክራቸው፥ ሌሎችም በበጎ ፈቃድ ስለ ክርስቶስ ሊሰብኩና ሊያስተምሩ የወደዱ አሉ፡፡ በፍቅር የሚያስተምሩም አሉ፤ ወንጌልን ለማስተማር እንደ ተሾምኹ ያውቃሉና፡፡ በኵራት ስለ ክርስቶስ የሚያስተምሩ ግን፥ ይህን አደርገው በእስራቴ ላይ መከራ ሊጨምሩብኝ መስሏቸው ነው እንጂ በእውነት አይደለም፤ በቅንነትም አይደለም፡፡ ነገር ግን ምን አለ? በየምክንያቱ በእውነትም ቢኾን፥ በሐሰትም ቢኾን ስለ ክርስቶስ ይናገራሉ፤ ሰዉን ዂሉ ወደ እርሱ ይጠራሉ፡፡ በዚህም ደስ ብሎኛል፤ ወደ ፊትም ደስ ይለኛል፤› (ፊልጵ. ፩፥፲፭-፲፰) በማለት የክርስትና ተቃዋሚዎች ቅዱስ ጳውሎስን ለማሳሰርና በእርሱ ላይ ከባድ መከራ ለማምጣት ሲሉ ራሱ የሚሰብከውን ቅዱስ ወንጌል ለመጠቀም መጣራቸውን ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ገልጾልናል፡፡ ከመልእክቱ እንደምንረዳው ታላቁ ሐዋርያ በቅንዓትና በክፋትም ቢኾን ‹‹እሰይ! እንኳን ወንጌል ተሰበከ!›› ሲል ለበጎ አድርጎ ይወስደዋል፡፡ ድርጊታቸው ለበጎ ባይኾንም ሰማዕያንን ስለሚያዘጋጅለትና የበለጠ እንዲረዱ ስለሚጋብዝለት እንደ መልካም ዕድል ወስዶታል፤ ኾኖለታልም፡፡

እጅግ የሚያስደንቀው ደግሞ የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት እንቅፋት ይገጥመው የነበረው ቤተ ክርስቲያንን በሓላፊነት ሊያገለግሉ በተለያየ መዓርግ ከተሾሙት ወገኖች ጭምር መኾኑ ነበር፡፡ ይህም የተከሠተው ልክ እንደ ቀደመው ዂሉ ራሳቸው ሐዋርያት በነበሩበትና ከራሱ ከመድኃኔ ዓለም ክርስቶስ የሰሙትን የድኅነት ወንጌል በሚመሰክሩበት ዘመን ነበር፡፡ ከዚህም የተነሣ እንደ ፍቁረ እግዚእ ቅዱስ ዮሐንስ ያሉ ሐዋርያት ይሰሙናል ብለው ለሚያስቧቸው አገልጋዮች የሁለቱንም ዓይነት አገልጋዮች ጠቅሰው በጎውን እንዲመስሉና ክፉውን ግን እንዳይከተሉት ያሳስቡ እንደ ነበረ ለርእስነት ከተጠቀምንበት ኃይለ ቃል ለመረዳት ይቻላል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ ይህችን ሦስተኛዪቱን መልእክቱን የላካት ለደቀ መዝሙሩ ለጋይዮስ ሲኾን መልእክቱንና አደራውን የሚሰጠው በዘመኑ የነበሩትን ሁለቱንም ዓይነት አገልጋዮች በንጽጽር ካቀረበለት በኋላ ነበር፡፡ አንድ ምዕራፍ ብቻ ባላት፣ በይዘት አነስተኛ በኾነች፣ በጭብጥና በፍሬ ነገር ግን ከሌሎቹ መልእክታተ ሐዋርያት በማታንሰው በዚህች መልእክቱ ያነጻጸራቸው ሁለቱ አገልጋዮች ደግሞ ዲዮጥራጢስ እና ድሜጥሮስ ነበሩ፡፡

ሐዋርያው በዚህ መልእክቱ ቍጥር ዘጠኝ ላይ እንደ ገለጸው ዲዮጥራጢስ ፍቁረ እግዚእ የተባለ ቅዱስ ዮሐንስ ለቤተ ክርስቲያን የላከውን መልእክት እንኳን የማይቀበል፤ እንዲያገለግሉ የተፈቀደላቸውን አገልጋዮች የሚያንገላታና የሚቀበሏቸውን ሳይቀር ከቤተ ክርስቲያን ለማባረር ጥረት የሚያደርግ ክፉ አገልጋይ ነበረ፡፡ በአንጻሩ ድሜጥሮስ ደግሞ የቤተ ክርስቲያኒቱ የኾኑትን፣ ለዕድገቷና ለጥንካሬዋ የሚላላኩትን ዂሉ የሚቀበል፤ በመልካም የሚያስተናግድና ከበጎዎቹ ጋር ዂሉ አብሮ የሚሠራ፤ የልቡናውን ሳይኾን የቤተ ክርስቲያንን፤ የራሱን ብቻ ሳይኾን የአባቶቹን ድምፅ፣ ምክርና ዐሳብ ተቀብሎ የሚያስተናግድ ቅን አገልጋይ ነበር፡፡ ይህንንም ቅዱስ ዮሐንስ ‹‹ስለ ድሜጥሮስ ዂሉ ይመሰክሩለታል፤ እውነት ራሷም ትመሰክርለታለች፤ እኛም መስክረንለታል፤ ምስክርነታችንም እውነት እንደ ኾነች ታውቃላችሁ፤›› ሲል ይመሰክርታል (ቍ. ፲፪)፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ እነዚህን ሁለቱን አገልግዮች ያነጻጸረውም መልእክቱን የሚልክለት ሌላው ረድዕ ቅዱስ ጋይዮስ አብነት ሊያደርገው የሚገባው ዲዮጥራጢስን ሳይኾን ድሜጥሮስን መኾን እንዳለበት ለማሳየት ነው፡፡ ‹‹ወንድሜ ሆይ፥ በጎ አድራጊ እንጂ ክፉ አድራጊ አትኹን፤›› ማለቱም ስለዚህ ነው (ቍ. ፲፩)፡፡

በዘመናችን ያለው የማኅበረ ቅዱሳን አገልግሎት የገጠመው ኹኔታም ከዚህ ኹኔታ ጋር በእጅጉ እንደሚመሳሰል ስለምናምን፤ ማኅበሩም ለአባላቱና ለወዳጆቹ ብቻ ሳይኾን በቤተ ክርስቲያን ላሉ አገልጋዮች ዂሉ የሚያቀርበው ወቅታዊ የአዘክሮ መልእክት ይኼው ‹‹ወንድሜ ሆይ፥ በጎ አድራጊ እንጂ ክፉ አድራጊ አትኹን፤›› የሚለው የቅዱስ ዮሐንስን ምክር ነው፡፡ የሐዋርያት ዘመን አገልግሎት በሁለቱ ዓይነት ሰዎች የተያዘ ከነበር የእኛ ዘመን አገልግሎት ከዚያ የተሻለ ነገር እንዴት ሊገጥመው ይችላል? ፍቁረ እግዚእ (ጌታ የሚወደው) የተባለው፤ በክርስቶስ ዕለተ ስቅለት እንኳን ከእግረ መስቀሉ ሳይርቅ ከመከራ መስቀሉ ያልሸሸው፤ እስከ ዕለተ ሞቱ ድረስም ሞተ ወልደ እግዚአብሔርን እያሰበ ፊቱን ለቅጽበትም ሳይፈታና ፈገግ ሳይል በፍጹም ዂለንተናው ያገለገለው፤ እኔ እስክመጣ ቢኖርስ ብሎ ጌታችን በቅርብ ሞትን እንደማያይ ቃል ኪዳን የገባለት፤ ንጽሕት ቅድስት ድንግል ማርያምን ‹‹እነኋት እናትህ›› ተብሎ ከእግረ መስቀል የተቀበለው ቅዱስ ዮሐንስ እስኪቸገር ድረስ ቤተ ክርስቲያንን ለፍላጎታቸው ብቻ የሚጠቀሙባት አገልጋዮች በዚያ ዘመን ከነበሩ ‹‹በእኛ ዘመን ለምን እንዲህ ያለ ነገር ኾነ?›› ብለን ልንደነቅበት የማይገባ እንደ ኾነ ለመረዳት የሚያስቸግር አይኾንም፡፡ በዚያው አንጻር ደግሞ እንደ ድሜጥሮስ እውነት ራሷ የምትመሰክርላቸው አገልጋዮች መኖራቸውን መዘንጋት ተገቢ አይደለም፡፡ ይልቁንስ ዋናውና ለእኛ ለዂላችን የሚያስፈልገው ነገር ‹‹እኛ ልንመስለውና አብነት ልናደርገው የሚገባው የትኛውን ነው?›› የሚለው ሊኾን ይገባል፡፡

የቍጥር መለያየትና የፍሬ ነገሩ መለዋወጥ ካልኾነ በቀር ዛሬም እንደ ጥንቱ ወይም በየዘመናቱ ዂሉ በታሪክ እንደ ተመዘገበው በቤተ ክርስቲያን ሁለቱም ዓይነት አገልጋዮች ይኖራሉ፡፡ ጌታችንም በወንጌል ‹‹ያን ጊዜ ሁለት ሰዎች በአንድ እርሻ ላይ ይኖራሉ፤ አንዱን ይወስዳሉ፤ ሁለተኛዉንም ይተዋሉ፡፡ ሁለት ሴቶች በአንድ ወፍጮ ይፈጫሉ፤ አንዲቱን ይወስዳሉ፤ ሁለተኛዪቱንም ይተዋሉ፡፡ ሁለት ሰዎች በአንድ አልጋ ላይ ይተኛሉ፤ አንዱን ይወስዳሉ፤ ሁለተኛዉንም ይተዋሉ፡፡ እንግዲህ ትጉ፤ ጌታችሁ በምን ሰዓት እንደሚመጣ አታውቁምና፤›› (ማቴ. ፳፬፥፵-፵፪) በማለት እስከ ዕለተ ምጽአት ድረስ ሁለቱም በእግዚአብሔር ቤት በአንድነት በአንድ የአገልግሎት መድረክ ላይ አንድ ዓይነት አገልግሎት እየፈጸሙ ለመኖራቸውና ለእግዚአብሔር የሚኾነውንና የማይኾነውን የሚለየውም እርሱ ራሱ በረቂቅ ፍርዱ እንደ ኾነ ገልጾልናል፡፡ ስለዚህም በአንዱ የወንጌል እርሻ ላይ እግዚአብሔር የሚወስደውና የሚተወው እንዳለ የሚያውቅ ባለቤቱ ስለ ገለጸልን የተጻፈውን ተረድተን፣ የጌታችንን ቃል ተቀብለን፣ በመኖሩ ከመደነቅ ወጥተን ልናደርገው ስለሚገባን ብቻ ማሰቡ ተገቢ ይኾናል፡፡ ቃሉ ዂላችንንም የሚመለከት የእውነትና የፍርድ ማስጠንቀቂያ ቃል ነውና፡፡

ስለዚህም በመግቢያው አንቀጽ ላይ እንደ ገለጽነው፣ ቅዱስ ጳውሎስን እንደ ገጠመው ዂሉ፣ በአሁኑ ጊዜም ወንጌልን ወይም ነገረ ቤተ ክርስቲያንን ለዓላማና ለጽድቅ የሚላላኩለት አሉ፤ በአንጻሩ ደግሞ እውነተኞቹን አጥፍቶ ፍላጎትን አንግሦ የራስን አጀንዳ ለማራመድ የሚሯሯጡትም አሉ፡፡ እነዚህም ቅዱስ ጳውሎስ እንደ ገለጸው የንጹሐኑን አግልግሎት ሳይቀር አገልጋዮቹን ለመክሰስና ለመወንጀል በየዘመናቱ ከሚኖሩ የጥፋት አካላት ጋር ወዳጅነትን ለመግዛትና ለመሳሰሉት ይጠቀሙበታል፤ ሕዝብንም ለመቀስቀስና ከራሳቸው ጋር ለማሰለፍ ይሠሩበታል፤ መልካሙን ነገር ለክፉና ለጥፋት እየተረጐሙ ያቀርቡበታል ማለት ነው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስን እንደ ገጠመውም ከቤተ ክርስቲያን ፍላጎት፣ ከሐዋርያት እና ከተላውያነ ሐዋርያት (ከሐዋርያት ተከታዮች) በጎ ምክር ይልቅ የራሳቸውን እና የእኔ የሚሉትን አካል ጥቅም ለማስጠበቅ ብቻ ሊጠቀሙበት ይደክማሉ፡፡ ይህ የየዘመኑ ክሥተት እንደ ኾነው ዂሉ የእኛም ዘመን ትንሽና ደካማ አገልግሎት እንኳን ከዚህ ልታመልጥ አልቻለችም፡፡ ምንም እንኳን ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ክርስቲያኖች ‹‹የእነርሱ ጥፋት፥ የእናንተም ሕይወት ይታወቅ ዘንድ የሚቃወሙን ሰዎች በማናቸውም አያስደንግጧችሁ፡፡ ይህንም ጸጋ እግዚአብሔር ሰጥቷችኋል፤ ነገር ግን ስለ እርሱ መከራ ልትቀበሉም ነው እንጂ ልታምኑበት ብቻ አይደለም፤›› (ፊልጵ. ፩፥፳፰-፳፱) ሲል እንደ ገለጸው የማይቀርና ዂሉም ነገር ልንቀበለው የሚገባ ቢኾንም አንዳንድ ጊዜ ግን ነገሩን ከሃይማኖት አንጻር ከማየት ወጥተን እንዳንገኝ ራስን መመርመሩ በእጅጉ የተገባ ነው፡፡

ምንም እንኳን ግብሩና ስሙ ብዙ የተራራቁ እንደ ኾኑ ጥናቶች ቢያመለክቱም የእኛ ዘመን የመረጃ ዘመን ነው ስለሚባል ኢንተርኔትን ተጠቅሞ በዋና መገናኛ ብዙኃንም ኾነ በየማኅበራዊ ሚዲያው የሚሠራጨውን ዂሉ አምኖና ተቀብሎ መሔድ ሳናውቀውም ቢኾን ወሬ ፈጣሪዎቹንና የጥፋት መልእክት አሠራጮችን ከመምሰል የሚያድን አይደለም፡፡ በማኅበራችን በማኅበረ ቅዱሳን ስም የሚሠራጩ አስመስለው ለሚከስሱና ቅዱስ ጳውሎስ እንደ ተናገረው ለተንኮልና መከራ ለመጎተት ኾነ ብለው የሚሠሩትን ከመተባበርም፣ ለይቶ ለማየትም አስቸጋሪ ደረጃ ላይ እንደ ደረሰ ለብዙዎች አያዳግትም፡፡ ማኅበሩ አቋሙን፣ መልእክቶቹንና ለሕዝበ ክርስቲያን ሊደርሱ ይገባቸዋል የሚላቸውን መረጃዎች ዂሉ በራሱ ይፋዊ ሚዲያዎች ወይም ደግሞ ማኅበሩን በሕግ በሚወክሉ አካላት የሚዲያ መግለጫዎች ብቻ የሚገልጽ ቢኾንም አንዳንዶች ግን እነዚህን ዂሉ ሳያጠሩና ሳይመረምሩ በማኅበሩ ስም ለክስ የሚያመቹ አድርገው የሚጽፉ አካላትን መረጃዎች በማኅበራዊ ሚዲያ ሳይቀር እንደሚቀባበሉ፤ የማኅበሩን አገልግሎትና አሠራር ከሚረዱት ምእመናን የሚደርሱት ጥቆማዎች ያመለክታሉ፡፡

ስለዚህም ኾነ ብላችሁና በተንኮልም ባይኾን የማኅበሩ መልእክቶችና አቋሞች መኾናቸውን ከማኅበሩ አካላት ሳትጠይቁና ሳትረዱ፤ ነገሩንም ሳትመረምሩ በችኮላና በስሜት ምን አልባትም ከዚህ በፊት በነበራችሁ የተሳሳተ መረጃና ግምት ምክንያት ለተጻፉና በማኅበራዊ ሚዲያው በሚናፈሱት ዂሉ ማኅበሩን ለምትወቅሱ፣ ለምትተቹና ለምትሰድቡም ዂሉ ወደ ማኅበሩ ቀርባችሁ ኹኔታዎቹን ሳታጣሩና መረጃ ሳትቀበሉ መዘገባችሁን እንድታቆሙ ለማሳሰብ እንወዳለን፡፡ ቢያንስ ቢያንስ የሙያ ሥነ ምግባሩ የሚጠይቀውን ያህል እንኳ ሳትጓዙ ለመፈረጅ መቻኮላችሁ የሚያስገርም ኾኖም አግኝተነዋል፤ በሌላው ላይ የማታደርጉትን ማደረጋችሁን በግልጽ ያመለክታልና፡፡ አውቃችሁና ወዳጅ መስላችሁ ለራሳችሁ የተንኮልና የክስ ዓላማ እንዲጠቅማችሁ በማሰብ ይህን በማኅበሩ፣ በአባላቱና በወዳጆቹ ስም ስማቸው በይፋ በማይታወቁ አካላት ስም ይህን የምታደርጉትንም ቢኾን አይጠቅማችሁምና ከዚህ ድርጊታችሁ እንድትታቀቡ እውነትና ፍቅር በኾነው አምላካችን ስም እናሳስባችኋለን፡፡ ባለማወቅ እና ለማኅበሩ አገልግሎት የሚያግዝ እየመሰላችሁ ይህን የምታደርጉ አባላትም ኾነ ደጋፊዎች ካላችሁም እንደሚባሉት ያሉ የስድብና የጥላቻ መልእክቶች ማኅበሩን ሊጠቅሙ ቀርቶ የአገልግሎቱ አደናቃፊዎችንም ሊጎዱ ስለማይችሉ፤ ሊጎዱ እንኳ ቢችሉ በክርስትናችን የተከለከሉና የተወገዙ ስለ ኾኑ ከማድረግ እንድትቆጠቡ ለማሳሰብ፣ በሐዋርያው ቃልም  ‹‹ወንድሜ ሆይ፥ በጎ አድራጊ እንጂ ክፉ አድራጊ አትኹን፤››  ለማለት እንወዳለን፡፡

የማኅበሩ አባላትና ወዳጆቹ፣ እንዲሁም የአገልግሎት አጋሮቹና ተባባሪዎቹ ዂላችሁ በቅዱሳት መጻሕፍት የተጻፉልንን ምክሮች ከማዘከርና ዂልጊዜም ቢኾን ከክፉው ተጠብቀን መልካም የኾነውን አርአያና አብነት ከማድረግ ልንቆጠብ አይገባንም፡፡ በትንሹ እና ሕይወታችንን በሙሉ ሳይኾን ከትርፋችን የምናገለግላት ቤተ ክርስቲያናችን በምድር ላይ እንዳሉ ሌሎች ተቋማት የዚህ ዓለም አደረጃጀትና አሠራር ብቻ የሚመራት ምድራዊ ተቋም ሳትኾን ረቂቅነትን እና መንፈሳዊነትንም ገንዘብ ያደረገች አካለ ክርስቶስ እንደ መኾኗ መጠን የምንፈጽመው ዂሉ መንፈሳዊነት ከጎደለው፣ ርባና ቢስ መኾኑን ለአፍታም ቢኾን ልንዘነጋው የሚገባ ነገር አይደለም፡፡ ለድርጊቶቻችን አብነት የምናደርገውም ቅዱስ ዮሐንስ እንዳስተማረው ብልሆቹን፣  መልካሞቹንና ደጎቹን እንጂ ሞኞቹን፣ ክፉዎቹንና ተንኮለኞቹን ሊኾን አይችልም፡፡ በዚያውም ላይ ከቅዱሳት መጻሕፍት ምክር ልንወጣ አይፈቀድልንም፡፡ ራሱ ጌታችን ‹‹ብትወዱኝስ ትእዛዜን ጠብቁ›› አለን እንጂ የተቃዋሚዎቻችን ሰይፍና ጎመድ ልንይዝ አልፈቀደልንም፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ‹‹ወገኖቻችንም ፍሬ ቢሶች እንዳይኾኑ፥ በሚፈለገውም ሥራ ጸንተው እንዲገኙ በጎ ምግባርን ይማሩ፤›› (ቲቶ. ፫፥፲፬) በማለት እንደ ገለጸው ከቤተ ክርስቲያን ወገን የኾናችሁ ዂሉ፣ በውጭ እንዳሉት ወደ ፍሬ ቢስነት ከሚወስድ ማንኛውም መንገድ ልትቆጠቡ ይገባችኋል፡፡

በእርግጥ ነቢየ እግዚአብሔር ኤርምያስ ‹‹በሕዝቤ መካከል ክፉዎች ሰዎች ተገኝተዋል፤ ሰዎችንም ይዘው ይገድሉ ዘንድ ወጥመድን ይዘረጋሉ፤›› (ኤር. ፭፥፳፮) ሲል እንዳመለከተን፣ በመካከል የተዘሩ አጥማጆችና ባለ ወጥመዶች ሊያሰነካክሉን፣ ስሜታችንን ሊያደፈርሱትና ወደ ወጥመዳቸው ሊያንደርድሩን በተለያየ ዘዴ ይገፉን ይኾናል፡፡ ኾኖም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በመልእክቱ ‹‹ነገር ግን ወንድሞች ሆይ፥ ትበዙና ትጨምሩ ዘንድ እንማልዳችኋለን፡፡  የዋሃንም ትኾኑ ዘንድ፥ ሥራችሁንም ታከናውኑ ዘንድ፥ እንዳዘዝናችሁም በእጃችሁ ትሠሩ ዘንድ፥ በውጭ ባሉት ሰዎችም ዘንድ ከማንም አንዳች ሳትሹ በሚገባ ትመላለሱ ዘንድ እንለምናችኋለን፤›› (፩ኛ ተሰ. ፬፥፲-፲፪) ሲል ያዘዘንን ቃል ማስታወስ አስፈላጊ ነው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስም ‹‹ፍጹም ዋጋ እንድታገኙ እንጂ የሠራችሁበትን እንዳታጡ ራሳችሁን ዕወቁ፤›› (፪ኛ ዮሐ. ቍ. ፰) በማለት እንደዚህ ዓይነት ክፉ ተግባር የቀደመ መልካም ተግባራችንን ዋጋ ጨምሮ የሚያጠፋ መኾኑን በማስታወስ ፈጽመን እንዳናደርገው ያስጠነቅቀናል፡፡ ምንም ያህል ፈተና እና መከራ ቢመጣም እኛ ልናደርገው የሚገባን በመልካም ሥራና ልናደርገው የሚገባውን በማደረግ መጽናት ብቻ ይኾናል፡፡ ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስም ‹‹በእግዚአብሔር የሚያምኑ ሰዎች በመልካም ምግባር ዂሉ መረዳዳትን እንዲያስቡ ታጸናቸው ዘንድ እወዳለሁ፤ ሰውንም የሚጠቅመው በጎ ነገር ይህ ነው፤›› (ቲቶ ፫፥፰) ሲል ለቲቶ ያሳሰበውና ለዂላችንም የደረሰው፣ ጥቅም የሚገኘው በመንፈሳዊነትና በእውነት ኾኖ በመጽናት ብቻ ስለ ኾነ ነው፡፡

አንዳንድ ጊዜ እንዲህ ያለውን ምክር የማይቀበሉና በራሳቸው ዐሳብ ሔደው ለቤተ ክርስቲያን ጥቅምና ረብ ማስገኘት የሚችሉ አስመስለው የሚናገሩ፤ ዐሳባቸውንም በአንዳንድ ጥቅሶች አስደግፈው በተቆርቋሪነት መንፈስ የሚገዳደሩአችሁ እንኳን ቢኖሩ፣ እንዲህ ያለውንም ፈተና በትዕግሥት እንድትወጡትና አሁንም በጎውን እንድትመርጡ እናሳስባችኋለን፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹‹እግዚአብሔር ወገኖቹን ያውቃቸዋል፤ የእግዚአብሔርንም ስም የሚጠራ ዂሉ ከክፉ ነገር ይርቃል› የሚለው ይህም ማኅተም ያለበት የእግዚአብሔር መሠረት ጸንቶ ይቆማል፤›› (፪ኛ ጢሞ. ፪፥፲፱) በማለት ለቅዱስ ጢሞቴዎስ ያሳሰበውም በእግዚአብሔር እና በቤተ ክርስቲያን ስም ሰዎች ያልተገባ ድርጊት ውስጥ እንዳይገቡ ለማስጠንቀቅ ነውና፡፡ ሐዋርያው እንደዚህ ያሉትን ሰዎች ከዚህም አለፍ ብሎ ‹‹እግዚአብሔርን እንደሚያውቁት በግልጥ ይናገራሉ፤ በሥራቸው ግን ይክዱታል፤ እነርሱም ርኩሳንና የማይታዘዙ፥ በበጎ ሥራም ዂሉ የተናቁ ናቸው፤›› (ቲቶ ፩፥፲፮) በማለት ድርጊታቸውን ከክህደት ይደምረዋል እንጂ ተቆርቋሪዎች ብሎ አያመሰግናቸውም፡፡ ይህን እውነት ተረድተናል የምንል ደግሞ ‹‹አሁንም ስለዚህ እናንተ እንደምታደርጉ ወንድሞቻችሁን አጽናኑ፡፡ አንዱም አንዱም ወንድሙን ያንጸው (፩ኛ ተሰ. ፭፥፲፩) በተባለው ቃል ተጠቅመን ልንተራረም እንጂ ልንተቻች አይገባንም፡፡ ቢቻል ቢቻል ‹‹ያን ጊዜም አለቆችና መሳፍንቱ ስለ መንግሥቱ በዳንኤል ላይ ምክንያት ይፈልጉ ነበር፤ ነገር ግን የታመነ ነበርና፥ ምንም በደል አልተገኘበትምና በእርሱ ላይ ሰበብና በደል ያገኙበት ዘንድ አልቻሉም፤››  (ዳን. ፮፥፬-፭) ተብሎ እንደ ተመሰከረለት እንደ ዳንኤል ሰበብ የለሽ እስከ መኾን መድረስ፤ ካልተቻለ ደግሞ ሊያስፈርድብን ከሚገባ ስሕተትና ጥፋት መቆጠብ ለክርስቲያን ዂሉ የሚገባው ተግባር ነው፡፡

ይህ ዂሉ ግን ክሶችንና ውንጀላዎችን ያስቀራል ማለት እንዳልኾነ የተጠቀሱት ጥቅሶች ለመጻፋቸው ምክንያት ከኾኑት ታሪኮች፣ ይልቁንም ከነቢዩ ዳንኤል ታሪክ የምንረዳው ነው፡፡ ኾኖም ክርስቲያኖች ይህን ዂሉ ሊያደርጉት የሚገባቸው በሌላ በምንም ምክንያት ሳይኾን ‹‹ነገር ግን እግዚአብሔር ስለ ፈተነንና ወንጌሉን ለማስተማር የታመን ስላደረገን እንዲህ እናስተምራለን፤ ሰውን ደስ ለማሰኘት እንደሚሠራም አይደለም፤ ልቡናችንን ለመረመረው ለእግዚአብሔር ነው እንጂ፤›› (፩ኛ ተሰ. ፪፥፬) ተብሎ እንደ ተጻፈው አገልግሎታችን እናገለግልሃለን የምንለውን እግዚአብሔርን ደስ ስለማሰኘት ብቻ ነው፡፡ ማኅበሩም ቢኾን ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ ‹‹ልጆቼ በእውነት ሲሔዱ ከመስማት ይልቅ ከዚች የምትበልጥ ደስታ የለችኝም፤›› (፫ኛ ዮሐ. ቍ. ፬) ሲል እንደ ገለጸው አባላቱና ደጋፊዎቹ ብቻ ሳይኾኑ ክርስቲያኖች ዂሉ በእውነት ሲሔዱ ከማየት የተለየ ፍላጎት የለውም፡፡ ስለዚህም ይህ መልእክት የደረሳቸውንም ዂሉ ከታዘዙት በበለጠ እንዲፈጽሙት ይበረቱ ዘንድ ‹‹በመታዘዝህ ታምኜ፥ ካዘዝኹህም ይልቅ እንደምትጨምር ዐውቄ ጻፍኹልህ፤›› (ፊልሞና ፩፥፳፩) የሚለውን ቃለ ሐዋርያ እያስታወስን፤ በቃለ ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ በድጋሜ ‹‹ወንድሜ፣ ወዳጄ (አባል፣ ደጋፊ፣ ተባባሪ፣ ክርስቲያን ዂሉ) ሆይ፥ በጎ አድራጊ እንጂ ክፉ አድራጊ አትኹን›› በማለት ማኅበረ ቅዱሳን መልእክቱን ያስተላልፋል፡፡

ስብሐት ለእግዚአብሔር!

ማኅበረ ቅዱሳን