የማቴዎስ ወንጌል

 ሐምሌ 3 ቀን 2006 ዓ.ም.

ምዕራፍ አራት

በዚህ ምዕራፍ መጀመሪያ ያለው ንባብ የሚተርክልን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከተጠመቀ በኋላ ሳይውል ሳያድር በኢያሪኮ አካባቢ ወደሚገኘው /ሣራንደርዮን/ የአርባ ቀን ተራራ ተብሎ ወደሚታወቀው ሥፍራ ወጣ፡፡ በዚያም ዐርባ መዓልትና ዐርባ ሌሊት ጾመ፣ ከዚህ በኋላ ተራበ፤ ጸላኤ ሠናይት ዲያብሎስ ሦስት ፈተናዎችን አቀረበለት፡፡

የመጀመሪያው ፈተና መራቡን አይቶ ድንጋይ በማቅረብ እነዚህን ባርከህ ወደ ዳቦነት ለውጥ አለው፡፡ ጌታችንም የሰይጣን ታዛዥ በመሆን የሚገኘውን ሲሳይ በመንቀፍ “ሰው በእግዚአብሔር ቃል እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም” አለው፡፡ በሦስት ሲፈትነው በትዕግሥት አሸነፈው፡፡

ዳግመኛው በትዕቢት ይፈትነው ዘንድ አሰበ፡፡ ጌታም ሐሳቡን ዐውቆ ወደ መቅደስ ጫፍ ሄደለት፡፡ ፈታኙም ከቤተ መቅደስ ጫፍ ዘሎ እንዲወርድ የመጽሐፍ ቅዱስን ጥቅስ ጠቅሶ ጠየቀው፡፡ ጌታም “ጌታ አምላክህን አትፈታተነው ተብሎ ተጽፎብሃል” ብሎ ጠቅሶ መዞ የመጣውን ሰይጣን ጥቅስ ጠቅሶ አፉን አስያዘው መዝ.90፡11፤ ዘዳ.6፡16፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለሚጠይቋችሁ ሁሉ መልስ ለመስጠት የተዘጋጃችሁ ሁኑ ማለቱ ይህንን ይዞ ነው፡፡ 1ኛ ጴጥ.3፡15፡፡

ፈታኝ ዲያብሎስም የቀደሙት ሁለቱ ፈተናዎቹ ጌታን እንዳልጣሉት ባየ ጊዜ ሦስተኛ ፈተናውን አቀረበ፡፡ የዓለምን ግዛት ከነክብሩ አሳየውና “ወድቀህ ብትሰግድልኝ ይህን ሁሉ እሰጥሃለሁ” አለው፡፡ ጌታም “ሂድ አንተ ሰይጣን ለጌታህ ለአምላክህ ስገድ እርሱንም ብቻ አምለክ ተብሏል” ብሎ በመመለስ በፍቅረ ንዋይ ያቀረበለትን ፈተና ገንዘብን በመጥላት አሸንፎታል፡፡

እነዚህም ጌታ የተፈተነባቸው ሦስቱ ፈተናዎች ዛሬ ሰው የሚፈተንባቸው ዋና ዋና ኃጢአቶች ናቸው፡፡ እርሱም እነዚህን መርጦ የተፈተነበት ለአርአያ ነው፡፡ ድል ማድረግ የምንችልበትን መንገድም አብነት ሆኖ አሳይቶናል፡፡ ከዚህ በኋላ የማስተማር ሥራውን በተለያዩ ቦታዎች ጀመረ፡፡ ደቀ መዛሙርቱንም ከየቦታው ጠራ፡፡

 

  • ምንጭ፡- ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ 4ኛ ዓመት ቁጥር 1 መስከረም 1989 ዓ.ም.