በቤተ ክርስቲያናችን ከመስከረም 1 እስከ 7 ያለው ጊዜ  ዘመነ ዮሐንስ ይባላል፤ ሳምንቱ የቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ ሕይወቱ፣ትምህርቱና ምስክርነቱ የሚታሰቡበት ነው ፡፡

                                                           የቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ ልደትና ዕድገት

ቅዱስ ሉቃስ በወንጌሉ ምዕራፍ አንድ ላይ «በይሁዳ ንጉሥ በሄሮድስ ዘመን ከአብያ የክህነት ምድብ የሆነ ዘካርያስ የሚባል አንድ ካህን ነበረ፤ ሚስቱ ኤልሳቤጥም ከአሮን ነገድ ነበረች፡፡ ሁለቱም የጌታን ትእዛዝና ሥርዓት ሁሉ ጠብቀው ያለ ነቀፋ የሚኖሩ፣ በእግዚአብሔር ፊት ጻድቃን ነበሩ፤ ይሁን እንጂ ኤልሳቤጥ መካን በመሆኗ ልጅ አልነበራቸውም፡፡» በማለት የቅዱስ ዮሐንስን እናትና አባት ያስተዋውቀናል /ሉቃ.1÷5-7/፡፡

                                                                   የአብያ ምድብ

በመጽሐፈ ዜና መዋዕል ምዕራፍ 23 እና 24 ላይ ንጉሠ እስራኤል ዳዊት ሸምግሎ መንግሥቱን ለልጁ ለሰሎሞን ሲያስረክብ በዘመኑ የነበሩትን ካህናት /ሌዋውያን እና የአሮን ልጆች/ አስቆጥሮ በዕጣ በተለያዩ የአገልግሎት ምደቦች በየነገዳቸው መድቦ በዕጣ የአገልግሎት መርሃ ግብር አውጥቶላቸው ነበር፡፡ የአብያ የካህናት ምድብ ከእነዚህ አንዱ ነበር፡፡

ብሥራተ ልደቱ ለቅዱስ ዮሐንስ


ካህኑ ዘካርያስና ቅድስት ኤልሳቤጥ ልጅ እንዲሰጣቸው እግዚአብሔርን ዘወትር በጸሎት ይጠይቁ ነበር፡፡ አንድ ቀን ዘካርያስ እንደ ብሉይ ኪዳኑ ሥርዓት /ዘጸ.3ዐ÷6-8/ ወደ ቤተ መቅድስ ገብቶ ዕጣን የማጠን ተራ ደርሶት /ዕጣ ወጥቶለት/ ወደ ቤተመቅደስ ሲገባ መልአከ እግዚአብሔር ከዕጣን መሠዊያው /ከዕጣን መሥዋዕት ማቅረቢያው/ በስተቀኝ ቆሞ ታየው፡፡ ዘካርያስም ባየው ጊዜ በፍርሃት ተዋጠ፡፡ መልአኩ ግን «ዘካርያስ ሆይ አትፍራ ጸሎተህ ተሰምቷል፤ ሚስትህ ኤልሳቤጥ ወንድ ልጅ ትወልድልሃለች፤ ስሙንም ዮሐንስ ትለዋለህ፡፡ በእርሱ ተድላና ደስታ ታገኛለህ ብዙዎቹም በእርሱ መወለድ ደስ ይላቸዋል፤ በጌታ ፊት ታላቅ ይሆናልና» በማለት ብሥራት ከነገረው በኋላ ስለሚወለደው ልጅ አራት ነገሮችን ነገረው /ሉቃ.1÷13-17/፡፡

ሀ. የወይን ጠጅም ሆነ ሌላ የሚያሰክር መጠጥ አይጠጣም፡፡

በብሉይ ኪዳን ናዝራዊ ለመሆንና እግዚአብሔርን ለማገልገል ከተለዩ በኋላ /ዘኁ.6÷1-4/ የሚያሰክር ነገር መጠጣት ክልክል ነበር፡፡ የእግዚአብሔር መልአክ ለሶምሶን እናት «… ትፀንሳለሽ፤ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፡፡ እንግዲህ ተጠንቀቂ የወይን ጠጅም ሆነ ሌላ የሚያሰክር መጠጥ እንዳትጠጪ፤ … በልጁም ራሱ ላይ ምላጭ አይድረስበት፤ ልጁ ከእናቱ ማኅፀን ጀምሮ ናዝራዊ በመሆን ለእግዚአብሔር የተለየ ይሆናልና» /መሳ.3÷3-5/፡፡ እንዳላት ማለት ነው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስም ለእግዚአብሔር አግልግሎት ተለይቷልና የሚያሰክር ነገር አይጠጣም፡፡

ለ. በእናቱ ማኅፀን ሳለ በመንፈስ ቅዱስ ይሞላል፡፡

ሐ. ከእስራኤል ወገን ብዙዎችን ወደ ጌታ ወደ አምላካቸው ይመልሳል፤

መ. ለጌታ የሚገባ ሕዝብ ለማዘጋጀት በኤልያስ መንፈስና ኃይል በጌታ ፊት ይሔዳል፡፡

ዘካርያስ ይህንን ከመልአኩ በሰማበት ወቅት እርሱ ሸምግሎ ሚስቱም አርጅታና የመውለጃ ዕድሜዋ አልፎ በዚያም ላይ መካን ነበረችና «ይህን በምን አውቃለሁ? እኔ ሽማግሌ ነኝ ሚስቴም በዕድሜ ገፍታለች» በማለት ጥርጣሬውን በጥያቄ መልክ አቀረበ፡፡

በዚህን ጊዜ መልአኩ እንዲህ አለው «እኔ በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው ገብርኤል ነኝ፡፡ ይህን እነግርህና ይህን የምሥራች አመጣልህ ዘንድ ተልኬአለሁ፤ እነሆ ጊዜውን ጠብቆ የሚፈጸመውን ቃሌን ስላላመንህ ይህ እስከሚፈጸምበት ቀን ድረስ ድዳ ትሆናለህ፤ መናገርም አትችልም»

በዚህም መሠረት ዘካርያስ አገልግሎቱን ፈጽሞ ሲወጣ መስማትም ሆነ መናገር አልቻለም ነበር፡፡ መልአኩ እንደነገረውም ሚስቱ ኤልሳቤጥ ፀነሰች፡፡

 

ብሥራተ ድንግል ወጽንሰተ እግዚእ /ሉቃ.1÷26-38/


ይህ ከሆነ ከስድስት ወር በኋላ የቅዱስ ዮሐንስን መፀነስ ለዮሐንስ ያበሠረው መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ከእግዚአብሔር ዘንድ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን እንዲያበሥር ተላከ፡፡ መልአኩ እመቤታችን ወዳለችበት ገብቶ እጅ እየነሣ «ሰላም ላንቺ ይሁን፤ እግዚአብሔር ከአንቺ ጋር ነው፤ ከሴቶች ተለይተሽ አንቺ የተባረክሽ ነሽ፤ በእግዚአብሔር ፊት ሞገስን አግኝተሻል፤» እያለ ካመሰገናት በኋላ «እነሆ ትፀንሻለሽ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ ስሙንም ኢየሱስ ትይዋለሽ እርሱም ታላቅ ይሆናል፤ የልዑል ልጅም ይባላል… ለመንግሥቱ ፍጻሜ የለውም» በማለት አምላክን ጸንሣ እንደምትወለድ አበሠራት፡፡

እርሷም መልሳ «እኔ ወንድ ስለማላውቅ ይህ እንዴት ይሆናል?» ስትለው «መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፣ የልዑል ኃይልም ይጸልልሻል… እነሆ ዘመድሽ ኤልሳቤጥ በእርጅናዋ ወራት ወንድ ልጅ ፀንሳለች፤ መካን የተባለችውም ስድስተኛ ወሯን ይዛለች፤ ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለምና» አላት፡፡

እመቤታችንም «እነሆ እኔ ለእግዚአብሔር ባሪያው ነኝ፤ እንደ ቃልህ ይሁንልኝ» አለችው፡፡ በዚህች ቅጽበትም እግዚአብሔር ወልድ በተለየ አካሉ ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነሥቶ በማኅፀኗ ተጸነሰ፤ ተዋሐደ፡፡

 

እመቤታችንና ኤልሳቤጥ /ሉቃ.1÷39-45/


እመቤታችንም መልአኩ ስለ ኤልሳቤጥ የነገራትን ለማየት በዚያው ሰሞን ፈጥና ወደ ኤልሳቤጥ ሄደች፡፡ ወደ ዘካርያስም ቤት ገብታ ለኤልሳቤጥ ሰላምታ ስታቀርብላት እጅግ የሚያስደንቅ ነገር ተከሰተ፤ ኤልሳቤጥ የእመቤታችንን ሰላምታ በሰማች ጊዜ በማኅፀኗ ያለው ጽንስ ዘለለ፡፡ ኤልሳቤጥም በመንፈስ ቅዱስ ተሞላች ድምጽዋን ከፍ አድርጋ እንዲህ አለች፡- «አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ፤ የማኅፀንሽም ፍሬ የባረከ ነው፡፡ የጌታዬ እናት ወደ እኔ ትመጣ ዘንድ እንዴት ይሆንልኛል? እነሆ የሰላምታሽ ድምፅ በጆሮዬ በመጣ ጊዜ ጽንሱ በማኅፀኔ በደስታ ዘሎአልና፡፡ …»

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ ይህንን አስመልክተው ባስተማሩት ትምህርት እንዲህ ብለዋል፡- «ይህንን ታሪክ ሳስበው ሁለት ነገሮች ጥያቄ ይሆኑብኛል፡፡ የመጀመሪያው «ጽንሱ እንዴት በደስታ ሊዘል ቻለ?» የሚለው ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ «እሷስ ቢሆን የዘለለው በደስታ መሆኑን እንዴት አወቀች?» የሚለው ነው፡፡ ነገሩ የመንፈስ ቅዱስ መሆኑን ስረዳ ግን «ዕፁብ» ብዬ አድንቄ ጥያቄዬን አቆማለሁ፡፡

«ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አብርሃም ልጁን ይስሐቅን መሥዋዕት አድርጎ ባቀረበ ዕለት የተፈጸመውን ሲናገር «አብርሃም ቀኔን ለማየት ተስፋ በማድረግ ተደሰተ፤ አየም፤ ሐሴትም አደረገ» ብሏል /ዮሐ.8÷56/፡፡ በዚህ ዕለት የተፈጸመውም ይኸው ነው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ነቢያት በሙሉ ተስፋ ያደርጉት የነበረውን የጌታን ቀን /የእግዚአብሔርን ሰው መሆን/ በማኅፀን ሆኖ ተመለከተና ፈጽሞ ተደሰተ፤ ያደረገው ነገርም የናፈቀውን ሰው ያገኘ ሕፃን ሮጦ ወደዚያ ሰው እንደሚሄደው ያለ ነው»

ቅዱስ ያሬድ ደግሞ በድጓው «አእሚሮ እምከርሠ እሙ ሰገደ ወልደ መካን ለወልደ ድንግል» «ገና በእናቱ ማኅፀን ሳለ አውቆ የመካኒቱ /የኤልሳቤጥ/ ልጅ ለድንግሊቱ /ለእመቤታችን/ ልጅ ሰገደ» ይላል፡፡

 

የቅዱስ ዮሐንስ ልደት /ሉቃ.1÷67-80/


ኤልሳቤጥ የመውለጃዋ ቀን ደረሰ፤ ወንድ ልጅም ወለደች፡፡ በስምንተኛውም ቀን ጎረቤቶቿና ዘመዶቿ ሕፃኑን ሊገርዙት መጡ፤ በአባቱም ስም ዘካርያስ ሊሉት ፈለጉ፤ እናቱ ግን ለዘካርያስ በቤተ መቅደስ «የሕፃኑ ስም ዮሐንስ ይባላል» ብሎ ያናገረ በመልአኩ በቅዱስ ገብርኤል አማካኝነት መንፈስ ቅዱስ ገልጦላት «ዮሐንስ መባል አለበት» አለች፡፡

ዘካርያስን ለልጁ ምን ስም ሊያወጣለት እንደሚፈልግ ሲጠይቁት መጻፊያ ሰሌዳ እንዲሰጡት ጠይቆ «ስሙ ዮሐንስ ነው» ብሎ ጻፈ ወዲያውም አንደበቱ ተፈታ፡፡ እግዚአብሔርንም እያመሰገነ ይናገር ጀመር፡፡ በዚህም ምክንያት ጎረቤቶቹ ሁሉ በፍርሃት ተመሉ፡፡ ነገሩም በይሁዳ አውራጃ ሁሉ ተወራ፡፡ የሰሙትም ሁሉ «ይህ ሕፃን ምን ይሆን?» እያሉ በመገረም ጠየቁ፡፡

ካህኑ ዘካርያስም በመንፈስ ቅዱስ ተመልቶ ስለ ሕፃኑ ስለ ቅዱስ ዮሐንስ ትንቢት ተናገረ /ሉቃ.1÷67-79/

«የእስራኤል ጌታ አምላክ ይባረክ፤ ጎብኝቶ ለሕዝቡ ቤዛ አድርጓልና፡፡ ከጥንት ጀምሮ በነበሩት በቅዱሳን ነቢያት አፍ እንደተናገረ በብላቴናው በዳዊት ቤት የመዳን ቀንድን አስነሥቷልና፤» ብሎ ዘመነ ሥጋዌ መድረሱን ከተናገረ በኋላ፤ ሕፃኑን በተመለከተ ደግሞ፡-

«ደግሞም አንተ ሕፃን ሆይ የልዑል ነቢይ ትባላለህ፤ መንገዱን ልትጠርግ በጌታ ፊት ትሔዳለህና፤ እንደዚሁም የኃጢአታቸው ሥርየት የሆነውን የመዳን ዕውቀት ለሕዝቡ ትሰጣለህ» በማለት ቅዱስ ዮሐንስ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መንገድ ጠራጊ እንደሚሆን ማለትም ከእርሱ ቀድሞ የሕዝቡ ልብ ጌታችንን እና ትምህርቱን እንዲቀበል የሚያዘጋጅ ትምህርት እንደሚያስተምር ተናገረ፡፡ የቅዱስ ዮሐንስ መንገድ ጠራጊነት በቅዱስ ገብርኤልና በአባቱ በዘካርያስ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ነቢያትም ትንቢት የተነገረለት ነበር፡-

ነቢዩ ኢሳይያስ «የዐዋጅ ነጋሪ ድምፅ እንዲህ ይላል «የእግዚአብሔርን መንገድ በምድረ በዳ አዘጋጁ…» /ኢሳ.4ዐ ÷3/ በማለት ተናግሮ ነበር፡፡

ነቢዩ ሚልክያስ ደግሞ እንዲህ ብሎ ነበር፡፡ «እነሆ በፊቴ መንገድ እንዲያዘጋጅ መልእክተኛዬን እልካለሁ»፣ «እነሆ ታላቁና የሚያሥፈራው የእግዚአብሔር ቀን ከመምጣቱ በፊት ነቢዩ ኤልያስን እልክላችኋለሁ፡፡ …እርሱ የአባቶችን ልብ ወደ ልጆች የልጆችንም ልብ ወደ አባቶች ይመልሳል» /ሚል.3÷1፣ 4÷5-6/

 

የቅዱስ ዮሐንስ ዕድገት


የቅዱስ ሉቃስ ወንጌል «ሕፃኑም አደገ፤ በመንፈስም ጠነከረ፤ ለእስራኤልም ሕዝብ በይፋ እስከታየበት ቀን ድረስ በበረሃ ኖረ» /ሉቃ.1÷8ዐ/ ከማለት ውጪ ወደ በረሃ ስለሔደበት ምክንያትና ስለ አስተዳደጉ ዝርዝር ነገሮችን አይነግረንም፡፡ ሌላውን የምናገኘው ከትውፊትና ከአዋልድ መጻሕፍት ነው፡፡

ሄሮድስ ሕፃናትን ሲያጨፈጭፍ እናቱ ኤልሳቤጥ የልጇን ሕይወት ለማትረፍ ይዛው ወደ ግብፅ በረሃዎች ተሰዳለች፤ በዚያም በስደት ሳሉ እናቱ በመሞቷ በፈቃደ እግዚአብሔር ቶራ የተባለችን እንስሳ ጡት እየጠባ በገዳም እንደአደገ የወንጌል አንድምታችን ያስረዳል፡፡ ቅዱስ ያሬድም በድጓው «ዮሐንስ ምስለ ቶራት በገዳም ልሕቀ» «ዮሐንስ ከቶራዎች ጋር በገዳም አደገ» ይላል፡፡

«የቅዱስ ዮሐንስ ልብሱ የግመል ጠጉር ነበር፡፡ ወገቡም የጠፍር መታጠቂያ ነበር፡፡ ምግቡም አንበጣና የበረሃ ማር ነበር፡፡» /ማቴ.4÷3/

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ስለዚህ ሲያስተምር «በበረሃው ውስጥ እየኖረ ከፀጉር የተሠራ ልብስና መታጠቂያ ከየት አመጣ ብለን እንጠይቅ ይሆን? ይህንን እንደ ችግር የምናየው ከሆነ ሌሎች ብዙ ነገሮችንም መጠየቅ ይኖርብናል፡፡ እንዴት በክረምቶችና በበጋው ሙቀት በበረሃው ውስጥ መኖር ቻለ? ያውም በለጋ ዕድሜውና በማይችል ሰውነቱ? ሌሎችም ብዙ ጥያቄዎች አሉ፡፡ ስለዚህ ጥያቄያችንን አቁመን የእግዚአብሔርን ድንቅ ሥራ ወደ ማድነቅ ብንሔድ ይሻለናል፡፡» ይላል፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ እንዲህ ያለ የትህርምት ኑሮ በመኖሩ ምክንያት ጌታችንም «ዮሐንስ ሳይበላና ሳይጠጣ መጣ» ብሎታል፡፡ /ማቴ.11÷18/

 

የቅዱስ ዮሐንስ ስብከትና አገልግሎት


ቅዱስ ዮሐንስ በበረሃ ለሠላሳ ዓመታት ከቆየ በኋላ «በይሁዳ ምድረ በዳ እየሰበከ መጣ፤ ስብከቱም «መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ» የሚል ነበር፡፡» /ማቴ.3÷1-2/፡፡ አስቀድመው ነቢያቱ በኋላም አባቱ እንደተነበዩለት ቅዱስ ዮሐንስ የጌታችንን መንገድ የመጥረግ አገልግሎቱን ጀመረ፡፡ የአገልግሎቱና የትምህርቱ ዓላማዎች ሁለት ነበሩ፡፡

1. የመጀመሪያውና ዋናው ዓላማ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን እስራኤል እንዲያውቁት ማድረግ ነው፡፡ ይህንም ራሱ እንዲህ ሲል ይነግረናል «… እስራኤል እንዲያውቁት እኔ በውኃ ላጠምቅ መጣሁ፡፡» /ዮሐ.1÷31/፡፡

በዚህም ምክንያት ጌታችን ወደ እርሱ ከመምጣቱና ከመጠመቁ በፊት እየደጋገመ «እኔ በውኃ አጠምቃችኋለሁ፤ ነገር ግን ጫማውን ልሸከም፣ የጫማውንም ማሠሪያ ልፈታ የማይገባኝ ከእኔ በኋላ የሚመጣው እርሱ በመንፈስ ቅዱስና በእሳት ያጠምቃችኋል፡፡» /ማቴ.3÷12/ እያለ ሕዝቡ የጌታን መምጣት እንዲጠባበቁ ያደርግ ነበር፡፡

ጌታችን ወደ እርሱ መጥቶ ከተጠመቀም በኋላ «እነሆ የዓለምን ኀጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ፤ ከእኔ በፊት የነበረው፣ ከእኔ ይበልጣል ያልሁት እርሱ ነው» /ዮሐ.1÷29/፡፡ እያለ ወደ ጌታችን ይመራቸው ነበር፡፡

ከዚህም በተጨማሪ «አብ ወልድን ይወዳል፤ ሁሉን ነገር በእጁ ሰጥቶታል፡፡ በወልድ የሚያመን ሁሉ የዘለዓለም ሕይወት አለው፤ በወልድ የማያምን ግን የእግዚአብሔር ቁጣ በላዩ ይሆናል እንጂ ሕይወትን አያይም» /ዮሐ.3÷35-36/ በማለት የጌታችንን ወልደ እግዚአብሔርነትና በእርሱ የእግዚአብሔር ልጅነት ካላመኑ ሕይወት እንደሌለ አስተምሯል፡፡

2. ሁለተኛ ደረጃ የቅዱስ ዮሐንስ አገልግሎትና ትምህርት ዓላማ ደግሞ «መጥምቁ ዮሐንስ በበረሃ እያጠመቀና ለኃጢአት ሥርየት የንስሐ ጥምቀትን እየሰበከ መጣ፡፡» ተብሎ የተገለጸው /ማር.1÷4/ ሲሆን ይህንን ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንደሚከተለው ያብራራዋል፡፡

«ቅዱስ ዮሐንስ ያጠምቅ የነበረው ጌታችን በሞቱ የበደላችንን ዋጋ ከመክፈሉ በፊት ስለነበር በዚያን ጊዜ ምንም ዓይነት ሥርየት የለም፤ ሥርየት የጌታችን ደም ውጤት ነውና፡፡ ታዲያ «ለኃጢአት ሥርየት የንስሓ ጥምቀት እየሰበከ መጣ» ማለት ምን ማለት ነው? አይሁድ ቸልተኞች ነበሩ፡፡ ኃጢአታቸውንም አያስቡትም ነበር፡፡ ይልቁንም በብዙ ከፍተኛ ጥፋቶች ተጠያቂ ሆነው ሳለ ራሳቸውን በሁሉም ረገድ ትክክለኛ /ጻድቅ/ አድርገው ይቆጥሩ ነበር፡፡ በአባቶቻቸው ላይም አጉል ትምክህት ነበራቸው፤ እነዚህ ነገሮችም ለጥፋቶቻቸው ሁሉ መንሥኤ ሆነዋል፡፡ /ሮሜ.10÷3፣ 9÷3ዐ-32/፡፡ ስለዚህ ይህንን የጥፋታቸውን መንሥኤ ለማስወገድ ቅዱስ ዮሐንስ ኃጢአታቸውን እንዲያስተውሉ እያደረገ፡፡ የለበሰው ልብስ ራሱ ራሳቸውን እንዲመረምሩ የሚያደርግ ነበር፡፡ ስብከቱም ይኸው ነበር፤ «ለንስሓ የሚገባ ፍሬ አፍሩ፡፡ ራሳቸውን በኃጢአታቸው አለመውቀሳቸውና የራሳቸው ሥራ ሳይኖራቸው በአባቶቻቸው ያለ አግባብ መመካታቸው ከክርስቶስ እንዲርቁ አድርጓቸዋል፡፡ ኃጢአታቸውን ማስተዋል ግን መድኀኒታቸውን እንዲፈልጉና እንዲናፍቁ ያደርጋቸዋል፡፡ ቅዱስ ዮሐንስም የመጣው ይህንን ለማድረግ ነው፡፡ ምክንያቱም ራሳቸውን ባይወቅሱ የጌታን ጸጋ አይፈልጉም /አይናፍቁም/፤ ጸጋውን ካልፈለጉ ደግሞ ሥርየትን አያገኙም፡፡ የቅዱስ ዮሐንስ ትምህርትና ጥምቀትም ወደዚሁ የሚመራ ነው፡፡» /Homilies on the Gospel of St. Matew. Homily 10.2/

ስለዚህም «ለንስሐ የሚገባ ፍሬ አፍሩ» እያለ ይመክራቸዋል፤ «ምሳር ዛፎችን ሊቆርጥ ተዘጋጅቷል» እያለ ይገሥጻቸዋል፤ «አብርሃም አባት አለን በማለት ራሳችሁን አታታሉ፤ እግዚአብሔር ከእነዚህ ድንጋዮች ለአብርሃም ልጆች አድርጐ ሊያስነሣለት ይችላል» እያለ ያስጠነቅቃቸዋል፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ ወደ እርሱ ይመጡ የነበሩትን ሰዎች እንዲህ እያስተማረ የንስሐ ጥምቀት እያጠመቀ የጌታችን ተከታዮች ለመሆን ያዘጋጃቸው ነበር፡፡ በአጠቃላይ ያደርግ የነበረው ነገር በአንድ በኩል ለሕዝቡ ኃጢአታቸውን በማሳሰብና አዳኝ /መድኃኒት/ አንደሚያስፈልጋቸው በማሳመን በሌላ በኩል ደግሞ ጌታችን ዓለምን ለማዳን የመጣ መሆኑን በመግለጽ ሕዝቡን ወደ ጌታችን መምራት ነበር፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ይህንን እንዲህ በማለት ይገልጸዋል፡- «በአጠቃላይ መጥምቁ ዮሐንስ ያደረገው ነገር ጌታን እጁን ይዞ ወደ እያንዳንዳቸው ቤት እየወሰደ «በእርሱ እመኑ» እንደማለት ያለ ነው፡፡»

ቅዱስ ያሬድም በድጓው ቅዱስ ዮሐንስን «ሰባኬ ወንጌል በጥዑም ልሳኑ፤ … ፀጉረ ገመል ተከድነ ዘባኑ፤ ለዮሐንስ ሒሩቶ ንዜኑ ንዜኑ» «በጣፋጭ አንደበቱ /ልሳኑ/ ወንጌልን የሚሰብከውን፤ ጀርባው በግመል ፀጉር የተከደነውን የዮሐንስን ቸርነት እንናገራለን» እያለ የትምህርቱን ደገኛነት ያመሰግናል፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ እንዲህ እያደረገ በሚያስተምርበትና ሕዝቡን በሚያጠምቅበት ወቅት ከሕዝቡ ጥያቄ ይቀርብለት ነበር፡፡ «አንተ ማን ነህ? ኤልያስ ነህን? ነቢዩ ነህን? ክርስቶስ ነህን?» እያሉ ይጠይቁት ነበር /ዮሐ.1÷81-22/ እርሱ ግን «እኔ ክርስቶስ አይደለሁም፤ ኤልያስም አይደለሁም፤ እኔ ነቢዩ ኢሳይያስ «የጌታን መንገድ አቅኑ እያለ በምድረ በዳ የሚጮህ ድምፅ» ብሎ የተናገረልኝ ነኝ፡፡ እኔ በውኃ አጠምቃችኋለሁ፤ ከእኔ የሚበልጠውና ከእኔ በኋላ የሚመጣው ግን በመንፈስ ቅዱስ በእሳት ያጠምቃችኋል» በማለት ይመልስላቸው ያስተምራቸው ነበር፡፡

በዚህም ምክንያት ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ «በመመስከር ወደ ኋላ አላለም፤ በግልጽ መሠከረ» ብሎ ጽፎለታል /ዮሐ.1÷2ዐ/፡፡ ቤተ ክርስቲያናችንም ይህ ሳምንት የቅዱስ ዮሐንስ ምስክርነትና ትምህርት የሚታሰብበት የሳምንቱም ስም «ዮሐንስ አኅድአ»፣ «ዮሐንስ መሰከረ» ተብሎ እንዲጠራ አድርጋለች፡፡ በዚህ እሑድ በቤተ ክርስቲያን የሚዜመው መዝሙር እንዲህ የሚል ነው፡፡

«ዮሐንስ አኅድአ፣ እምካልኣኒሁ አንሀ ወክሐ እንዘ ይብል እምላዕሉ ወረደ ቃለ አብ»

«ዮሐንስ መሰከረ፤ ከሌሎች ይልቅ አብዝቶ የአብ ቃል ከሰማይ ወረደ እያለ ጮኸ»

 

ጌታችን እና ቅዱስ ዮሐንስ

ቅዱስ ዮሐንስ እንዲህ ሕዝቡን እያስተማረና እያጠመቀ ባለበት ወቅት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእርሱ ለመጠመቅ ቅዱስ ዮሐንስ ያጠምቅበት ወደነበረበት ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ መጣ፡፡ /ማቴ.3÷13/፡፡

ቅዱስ ዮሐንስም «እኔ በአንተ ልጠመቅ ይገባኛል እንጂ፤ አንተ ወደ እኔ እንዴት ትመጣለህ?» ብሎ ይከለክለው ነበር፡፡ ጌታችን ግን መልሶ «አሁንስ ፍቀድልኝ፤ እንግዲህስ ጽድቅን ሁሉ ልንፈጽም ይገባናል» አለው፡፡ ያን ጊዜም ፈቀደለት፡፡ ጌታችንም በትሕትና በፍጡሩ እጅ ተጠመቀ፡፡ ቅዱስ ዮሐንስም አምላኩን አጥምቋልና «መጥምቀ መለኮት» ይባላል፡፡

ቅዱስ ያሬድም በድጓው ደጋግሞ እንዲህ እያለ ይህንን ድርጊት ያወሳል፡፡

–    ዮሐንስ ካህን እምነቢያት ተለዓለ፤ ረሰየ ሲሳዬ ቈፅለ፤ አጥመቀ ነበልባል ዘአልቦ ወምስለ፡፡

ካህኑ ዮሐንስ ከነቢያት ሁሉ ከፍ ከፍ አለ፤ ምግቡን ቅጠልና ጤዛ አደረገ፤ …         አምሳያ የሌለውን ነበልባል አጠመቀ፡፡

–    ሰባኬ ወንጌል በጥዑም ልሳኑ ርስነ መለኮት ገሰሳት የማኑ … ለዮሐንስ ኂሩቶ ንዜኑ ንዜኑ፡፡

በጣፋጭ አንደበቱ ወንጌልን የሰበከንና ቀኝ እጁ የመለኮትን ትኩሳት /ማቃጠል/ የዳሰሰች የቅዱስ ዮሐንስን ቸርነት እንናገራለን፡፡

–    ዘመጠነ ዝ ትርሲተ ክብር፣ ፈሪሃ ልዑል፣ ትሕትና ወፍቅር፣ ርእዮ ዕባዮ ለዮሐንስ ዘመላእክት ይስግዱ ሎቱ፤ ኃይለ ልዑላን ኪያሁ ይሴብሁ

እንዲህ ያለ /የበዛ/ የክብር ጌጥ፣ እግዚአብሔርን መፍራት፣ ትሕትና እና ፍቅር፤ መላእክት የሚሰግዱለትን ታላቅ ኃይል ያላቸው የሚያመሰግኑትን የቅዱስ ዮሐንስን ክብሩን፣ ከፍ ከፍ ማለቱን ተመልከቱ፡፡

ዳግመኛም ቤተ ክርስቲያን በመልክአ ዮሐንስ /ስላም ለእራኅከ/ ላይ «ሰላም ለእራኅከ ለእግዚአብሔር ቅዱሱ፣ ወለአጻብዒከ ሰላም እሳተ መለኮት እለ ገሰሱ ዮሐንስ ጸሊ ኀበ ሊቅከ ኢያሱ ከመ ይቀድሰኒ ወያንጽሐኒ መንፈሱ «የእግዚአብሔር ቅዱስ ለምትሆን ለአንተ መዳፍ ሰላም እንላለን፡፡ የመለኮት እሳትን የዳሰሱ ጣቶችህንም ሰላም እንላለን፤ በመንፈሱ ይቀድሰንና ያነጻን ዘንድ ወደ መምህርህ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ ጸልይልን» እያለች ትማጸነዋለች፡፡

 

የቅዱስ ዮሐንስ እረፍት /ሰማዕትነት/

ጌታችን በተወለደ ጊዜ የይሁዳ የገሊላ እና የሠማርያ ንጉሥ የነበረውና ሕፃናት ቤቴልሔምን ያስገደለው ታላቁ ሄሮድስ ስድስት ልጆች ነበሩት፡፡

   1. ሄሮድስ ፍሊጶስ ቀዳማዊ
2. ሄሮድስ ፍሊጶስ ዳግማዊ
3. አርኬላዎስ
4. አርስጦቡለስ
5. ሄሮድስ አንቲጳስ
6. አንቲጳጥር

ታላቁ ሄሮድስ ሲሞት ሦስቱ ልጆቹ ሄሮድስ ፍሊጶስ ዳግማዊ፣ አርኬላዎስ እና ሄሮድሰ አንቲጳስ መንግሥቱን ለሦስት ተካፈሉት፡፡ ሄሮድስ ፍሊጶስ ቀዳማዊ ሄሮድያዳ የምትባል ሚስትና ሰሎሜ የምትባል ልጅ ነበሩት፡፡ ይህች ሄሮድስን ባሏን ትታ መጥታ የገሊላ ገዥ የነበረውን የባሏን ወንድም ሔሮድስ አንቲጳስን አገባች፡፡

በዚህን ጊዜ መጥምቁ ዮሐንስ «የወንድምህን የፍልጶስን ሚስት ማግባት አይገባህም» /ማቴ.14÷4/ እያለ በድፍረት ይገስጸው ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት አሲዞ ወደ እስር ቤት አስገባው፤ ሊገድለው ቢፈልግም ሕዝቡ እንደ ነቢይ ይመለከተው ነበርና ተቃውሞ እንዳይነሳበት ፈርቶ ተወው፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ በእስር ቤት ሳለ ጌታ በእርሱ እጅ ከተጠመቀና ዓርባ መዓልትና ዓርባ ሌሊት ከጾመ በኋላ በማድረግ ላይ ያለውን ነገር /ትምህርቱን፣ ተአምራቱን/ በሰማ ጊዜ በደቀመዛሙርቱ አማካኝነት ወደ ጌታችን መልእክት ላከ፤ እንዲህ ሲል፡-

«የሚመጣው አንተ ነህ? ወይስ ተስፋ የምናደርገው ሌላ አለ?» ጌታም መልሶ እንዲህ በማለት በምስጢራዊ ዘይቤ የአዎንታ መልስ ላከለት፡

«ሂዳችሁ ያያችሁትንና የሰማችሁትን ለዮሐንስ ንገሩት፡፡ ዕውሮች ያያሉ፤ አንካሶችም ይሄዳሉ፤ ለምጻሞችም ይነጻሉ፤ ደንቆሮዎችም ይሰማሉ፤ ሙታንም ይነሣሉ፤ ለድሆችም ወንጌል ይሰበካል፡፡ በእኔም የማይሰናከል ብፁዕ ነው፡፡»

መልእክተኞቹ ከሔዱ በኋላም ጌታ አብረውት ለነበሩት ሕዝቦች ቅዱስ ዮሐንስን «ሴቶች ከወለዷቸው ወገን ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ አልተነሣም» እያለ አመስግኖታል፡፡ ይህንን በዝርዝር ወደፊት እናየዋለን፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ ታሥሮ ከጳጉሜን 2 ቀን እስከ መስከረም 2 ቀን በእስር ቤት ቆየ፡፡ ያሳሰረው ሔሮድስ አንቲጳስ መስከረም ሁለት ቀን የልደት በዓሉን ያከብር ነበር፡፡ በዚህ ዕለት የሆነውን ነገር ቅዱስ ማቴዎስ በወንጌሉ በምዕራፍ 14 እንደሚከተለው አስፍሮታል፡፡

«የሄሮድስም የልደቱ ቀን በሆነ ጊዜ የሄሮድያዳን ልጅ /ሰሎሜ/ በመካከለቸው ዘፈነችለት፤ ሄሮድስንም ደስ አሰኘችው፡፡ ስለዚህም የምትለምነውን ሁሉ ሊሰጣት ማለላት፡፡ እርሷ ግን አስቀድማ በእናቷ ዘንድ አውቃ ነበርና የመጥምቁ ዮሐንስን ራስ በወጪት ስጠኝ» አለችው፡፡ (ወጭት እንደ ጎድጓዳ ሳህን ያለ ዕቃ ነው) ንጉሡም አዘነ፤ ነገር ግን ስለ መሐላው፣ አብረውት በማዕድ ተቀምጠው ስላሉት ሰዎች የዮሐንስን ራስ ቆርጠው ይሰጧት ዘንድ አዘዘ፡፡ ልኮም በግዞት በእስር ቤት ሳለ የዮሐንስን ራስ አስቆረጠው፡፡ ራሱንም በወጭት አምጥተው ለዚያች ብላቴና ሰጧት፤ እርስዋም ወስዳ ለእናቷ ሰጠች፡፡ ደቀመዛሙርቱም መጡ፤ በድኑንም ወስደው ቀበሩት መጥተውም ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ነገሩት፡፡» /ማቴ.14÷5-12/

የመጀመሪያ ባሏን ሄሮድስ ፊሊጶስን ትታ የባሏን ወንድም ያገባችው ሄሮድያዳ «የወንድምህን ሚስት ልታገባ አይገባህም» በሚለው በቅዱስ ዮሐንስ ግሣጼ ትበሳጭ ስለነበር የምታጠቃበትን መንገድ ሁልጊዜ ትፈልግ ስለነበር ለልጇ ለሰሎሜ እንዲህ ያለ ምክር መክራ የቅዱስ ዮሐንስ አንገት እንዲቆረጥ አደረገች፡፡

ሄሮድስ አንድ ጊዜ በሰዎች ፊት ቃል ስለ ገባ እንጂ በውሳኔው ደስተኛ አልነበረም፤ አዝኗል፡፡ ምክንያቱ ሁለት ነው፡፡ የመጀመሪያው አስቀድመን እንደጠቀስ ነው ሕዝቡ ቅዱስ ዮሐንስን ይወዱትና ይቀበሉት ስለነበር እንዳይቃወሙት ፈርቶ ነው፡፡ ሁለተኛው የቅዱስ ዮሐንስን ሕይወትና ትምህርት እያስተዋለ ሲሔድ ቅዱስ ዮሐንስ በእውነትም ከእግዚአብሔር ዘንድ የተላከ መሆኑን ስላወቀ ነው፡፡ ይህም ቅዱስ ዮሐንስን አንገቱን ካስቆረጠው በኋላ ጌታችን ያደርጋቸው የነበሩትን ተአምራት በሰማ ጊዜ «ይህ መጥምቁ ዮሐንስ ነው፤ እርሱ ከሙታን ተለይቶ ተነሥቷል፤ ስለዚህ በእርሱ ተአምራት ይደረጋል» /ማቴ.14÷2/ በማለቱ ይታወቃል፡፡

የመስከረም ሁለት ስንክሳር በዚህ ላይ ተጨማሪ አስደናቂ ነገር ይነግረናል፡፡ «በዚያችም ቀን የቅዱስ ዮሐንስ ራስ ከሄሮድያዳ ከእጆቿ ላይ ወደ አየር ስለ በረረች ታላቅ ድንጋጼ ሆነ፡፡ ደግሞም ሄሮድስ ሆይ የወንድምህን ሚስት ልታገባ አይገባህም እያለች በመጮህ ዘልፋዋለችና»

የየካቲት ሠላሳ ስንካሳር ደግሞ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅን ጠቅሶ የሚከተለውን ይጨምራል፡፡

«ሄሮድስ በአዘዘ ጊዜ ቅዱስ ዮሐንስ በእሥር ቤት ሳለ ራሱን በሰይፍ ቆርጠው በጻህል አድርገው ወደ ሄሮድስ አመጡለት፡፡ እርሱም ለሄሮድያዳ ልጅ ሰጣት እርሷም ለእናቷ ወስዳ ሰጠች፡፡

ይህችም የረከሰች አመንዝራ ሴት ልትዳስሳት በወደደች ጊዜ በወጭቱ ውስጥ ጠጉርዋ ተዘርግቶ ወደ አየር በረረች በአየርም ሆና የወንድምህን ሚሰት ልታገባ አይገባህም እያለች አስራ አምስት ዓመት ኖራ በአረቢያ ምድር አርፋ በዚያ ተቀበረች፡፡

ከብዙ ዘመናት በኋላ ያ ቦታ የነጋድያን ማደሪያ ሆነ፡፡ በእግዚአብሔርም ፈቃድ ሁለት አማንያን ነጋዴዎች ወደዚያ ቦታ ደርሰው አደሩ፡፡ ቅዱስ ዮሐንስም በህልም ገለጠላቸውና የከበረች ራሱን ያወጡ ዘንድ አዘዛቸው፡፡ እነርሱም አወጡአት፡፡ ከእርሳቸውም ጋር ወደ ቤታቸው ወስደው ታላቅ ክብርን አከበሩዋት፡፡

ለእግዚአብሔር ምሥጋና ይሁን እኛንም መለኮትን በአጠመቀ በከበረ ዮሐንስ ጸሎት ይማረን ልዩ የሆነች በረከቱም ከእኛ ጋር ትሁን፤ ለዘለዓለሙ አሜን፡፡
      ይቀጥላል
                                          ወስብሐት ለእግዚአብሔር