በአውሮፓ የሕፃናት እና ታዳጊዎች ሥርዓተ ትምህርት ተመረቀ

በእንግሊዝ ንዑስ ማእከል

ኅዳር ፲፫ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም

በምረቃ ሥርዓቱ ላይ የተገኙ የሰሜን ምዕራብ አውሮፓ ሀገረ ስብከት ሠራተኞች እና ካህናት በከፊል

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሰ/ት/ቤ/ማ/መ/ ማኅበረ ቅዱሳን አውሮፓ ማእከል የተተኪ ትውልድ ሥልጠና ክፍል አስተባባሪነት የተዘጋጀ ከኢትዮጵያ ውጪ የሚኖሩ ሕፃናት እና ታዳጊዎችን ለማስተማር የሚያግዝ ሥርዓተ ትምህርት በእንግሊዝ አገር በለንደን ከተማ በደብረ ገነት ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ኅዳር ፫ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም ተመረቀ፡፡

በምረቃ ሥርዓቱ ላይ የሰሜን ምዕራብ አውሮፓ ሀገረ ስብከት ሠራተኞች፣ ከየአብያተ ክርስቲያናት የመጡ ካህናት፣ የሰንበት ት/ቤት አባላት፣ የየአብያተ ክርስቲያናት ተወካዮች፣ የአካባቢው ምእመናንና በማኅበረ ቅዱሳን አውሮፓ ማእከል የእንግሊዝ ንዑስ ማእከል አባላት ተገኝተዋል፡፡

መርሐ ግብሩ በሊቀ አእላፍ ቆሞስ አባ አሮን ሳሙኤል በሰሜን ምዕራብ አውሮፓ ሀገረ ስብከት የሰ/ት/ቤ/ማደራጃ ክፍል ሓላፊ በጸሎት የተከፈተ ሲኾን፣ የሀገረ ስብከቱ ዋና ጸሐፊ ቀሲስ በለጠ የእንኳን ደኅና መጣችሁ መልእክት አስተላልፈው የሥርዓተ ትምህርቱን ምረቃና አጠቃላይ ዝግጅት አስተዋውቀዋል፡፡

ዶ/ር በላቸው ጨከነ በማኅበረ ቅዱሳን የአውሮፓ ማእከል ምክትል ሰብሳቢ እና የሥርዓተ ትምህርቱ ዝግጅት አስተባባሪም የሥርዓተ ትምህርቱ የዝግጅት ሒደት፣ ዓላማ፣ አስፈላጊነት፣ ይዘት እና ቀጣይ ሥራዎችን በተመለከተ ባቀረቡት ገለጻ በሥርዓተ ትምህርት ዝግጅቱ ከሠላሳ የሚበልጡ የቤተ ክርስቲያን ልጆች መሳተፋቸውን አመላክተዋል፡፡

ዶ/ር በላቸው እንዳብራሩት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰሜን ምዕራብ አውሮፓ ሀገረ ስብከት ፈቃድ የተጀመረው የሕፃናትና ታዳጊዎች የሥርዓተ ትምህርት ዝግጅት ከሁለት ዓመታት በላይ የወሰደ ሲኾን፣ ዝግጅቱ ከመጀመሩ አስቀድሞም ከሦስት መቶ በላይ የሚኾኑ በእንግሊዝ አገር የሚኖሩ ምእመናን የተሳተፉበት የየአብያተ ክርስቲያናት ተሞክሮ፣ የልጆች የቋንቋ ክህሎት እና የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ደረጃ፣ እንደዚሁም ወላጆች የተሳተፉበት በችግሮች እና የመፍትሔ አቅጠጫዎች ዙሪያ ያተኮረ የመነሻ ጥናት ተደርጓል፡፡

ጥናቱን መሠረት በማድረግም ለወደፊት የሚመለከታቸውን አካላት ዅሉ ለማሳተፍ የሚያስችል ጥናትና ምክረ ሐሳብ (ፕሮፖዛል) ለሰሜን ምዕራብ አውሮፓ ሀገረ ስብከት ቀርቦ የነበረ ሲኾን፣ የሀገረ ስብከቱ አስተዳደር ጉባኤም የቀረበውን ጥናትና ምክረ ሐሳብ ተቀብሎ በሀገረ ስብከቱ ሥር በሚገኙ አገሮች የወላጆች ኮሚቴ እንዲዋቀር ወስኗል፡፡ ለዚህም የሥራ መመሪያ ተዘጋጅቶ ለየአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት መላኩ ተገልጿል፡፡

እንደ ዶ/ር በላቸው ጨከነ ገለጻ ወጥ የኾነ ሥርዓተ ትምህርት አለመኖር በአውሮፓ የሚኖሩ ታዳጊ ሕፃናትን ለማስተማር ከባድ ከሚያደርጉት ኹኔታዎች ዐቢይ ምክንያት ሲኾን፣ ይህን በመገንዘብ የሰሜን ምዕራብ አውሮፓ ሀገረ ስብከት ባወጣው የሥራ መመሪያ መሠረት በማኅበረ ቅዱሳን አውሮፓ ማእከል የተተኪ ትውልድ ሥልጠና ክፍል ባለሙያዎችን በመመደብ ሥራውን እንዲጀምር ተደርጓል፡፡

ከአምስት እስከ ዘጠኝ ዓመት የዕድሜ ክልል ውስጥ ለሚገኙ ሕፃናትና ታዳጊዎች ታስቦ የተዘጋጀው ሥርዓተ ትምህርቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ትምህርተ ሃይማኖት፣ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን፣ የአማርኛ ቋንቋ እና የመዝሙር ጥናት የተሰኙ አምስት የትምህርት ዘርፎችን ያካተተ ሲኾን፣ የትምህርቶቹ አርእስትና ይዘቶችም በቤተ ክርስቲያን የሚከበሩ በዓላትንና ወቅቶችን መሠረት በማድረግ የተዘጋጁ ናቸው፡፡

የሥርዓተ ትምህርቱ ጥራዞች

በቀጣይነትም በአውሮፓ ማእከል አስተባባሪነት የሕፃናት እና ታዳጊዎች ክፍልን በመላው አውሮፓ በሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ለማቋቋምና ለማጠናከር፣ ለመምህራን ሥልጠና ለመስጠት፣ በየአገሩ የወላጆች ኮሚቴን ለማቋቋም እና ሥርዓተ ትምህርቱን በየአጥቢያው ለማዳረስ መታቀዱን ዶ/ር በላቸው ጨከነ አስረድተዋል፡፡

‹‹የእኛ ትወልድ፣ ነገ በመላው ዓለም ለምትኖረው ቤተ ክርስቲያን ድልድይ ነው፤›› ያሉት ዶ/ር በላቸው ጨከነ ለሥርዓተ ትምህርቱና ለሌሎችም ዕቅዶች ተግባራዊነት የሚመለከታቸው የቤተ ክርስቲያን አካላትና ምእመናን በትጋት ሊሠሩ እንደሚገባ በማሳሰብ መልእክታቸውን አጠቃለዋል፡፡

በምረቃ ሥርዓቱ ላይ የተገኙ ካህናትና ምእመናንም በዚህ ዝግጅት የተሳተፉ ወገኖችን ከማመስገን ጀምሮ ብዙ ጠቃሚ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ ለአብነትም ሊቀ አእላፍ ቆሞስ አባ አሮን ሳሙኤል በሰሜን ምዕራብ አውሮፓ ሀገረ ስብከት የሰ/ት/ቤ/ማደራጃ ክፍል ሓላፊ ዝግጅቱ አስፈላጊና ወቅታዊ መኾኑን ጠቅሰው በሕፃናት ላይ የሚሠራ ሥራ መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት የላቀ ጠቀሜታ እንዳለው ተናግረዋል፡፡

‹‹ይህ ሥራ ችግኝ ተከላ ነው›› ያሉት የለንደን ደብረ ገነት ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ መልአከ ገነት ቀሲስ ከፍያለው አስቻለው በበኩላቸው ሕፃናትን የማስተማር አገልግሎት ለበርካታ ዓመታት በአእምሯቸው ሲመላለስ እንደ ቆየ አውስተው ‹‹ዝግጅቱ የልጆቻችንን ጥያቄ የሚመልስልን በመኾኑ ከአሁን በኋላ ዅላችንም በሓላፊነት ልንሠራበት ይገባል›› ሲሉ አሳስበዋል፡፡

‹‹በውጪ አገር ይህን ያህል ዓመት ስንኖር ዛሬ ገና ስለ ልጆቻችንን ማሰብ በመጀመራችን ደስ ብሎኛል›› በማለት ደስታቸውን የገለጹት ሊቀ ሊቃውንት ገብረ ሥላሴ ዓባይም በሰሜን ምዕራብ አውሮፓ ሀገረ ስብከት የስብከተ ወንጌል ክፍል ሓላፊ፣ ይህ ዝግጅት እንዲፈጸም ላደረገው ለእግዚአብሔር ምስጋና ካቀረቡ በኋላ ለሥራው ተግባራዊነትም ዅሉም ጠንክሮ መሥራት እንደሚገባው አስገንዝበዋል፡፡

በሊቨርፑል ከተማ የመካነ ቅዱሳን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ብርሃኑ ደሳለኝ ደግሞ ቤተ ክርስቲያናችን ያላትን ብዙ ሀብት በሚገባ እየተጠቀምንበት እንዳልኾነ አስታውሰው ዝግጅቱ ተጠናቆ ለምረቃ በመብቃቱም ‹‹ቤተ ክርስቲያናችን እንኳን ደስ ያላት! እናንተም እንኳን ደስ ያላችሁ!›› በማለት የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል፡፡

መጋቤ ሐዲስ ክብረት የለንደን ደብረ ገነት ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን አገልጋይም እንደዚሁ ይህ ዝግጅት ለሕፃናት መንፈሳዊ ሕይወት ከሚኖረው ጠቀሜታ ባሻገር ሕፃናት ከወላጆች ጋር እንዲግባቡ የሚያግዝ ሥራ መኾኑንም መስክረዋል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ አንዳንድ ምእመናንም ለሥራው ውጤታማነት የሚጠቅሙ ገንቢ አስተያየቶችን ሰጥተዋል፡፡

በመጨረሻም የተዘጋጁት የመምህራን መምሪያ እና የሥርዓተ ትምህርት መድብሎች ከየአጥቢያው ለመጡ የሰበካ ጉባኤ ተወካዮች ከተሰጡ በኋላ በሰሜን ምዕራብ አውሮፓ ሀገረ ስብከት ዋና ጸሐፊ ቀሲስ በለጠ መርዕድ የማጠቃለያ መልእክትና ጸሎተ ቡራኬ የምረቃ ሥርዓቱ ተጠናቋል፡፡