የልደትን ብርሃን መናፈቅ ስብከት፣ ብርሃን ኖላዊ

            በዲ/ን ዘላለም ቻላቸው
መግቢያ

ቅዱስ ጳውሎስ በሮሜ መልእክቱ «በሞቱ እንመስለው ዘንድ ከእርሱ ጋር በጥምቀት ተቀበርን እርሱ ክርስቶስ በአባቱ ጌትነት ከሙታን እንደተነሳ እየተወ እንደ እርሱ አዲስ ሕይወት እንኖራለን» /ሮሜ. 6.4/፤ እንዳለው ክርስትና በጥምቀታችን ከክርስቶስ ጋር ሞተን ከእርሱም ጋር ተነስተን በትንሳኤው ብርሃን በአዲስ ሕይወት የምንመላለስበት የእግዚአብሔርን ፍቅር እየቀመስን ያደረገልንን እያደነቅን ፀጋውን እለት እለት እየተቀበልን፣ እኛ ሞተን ክርስቶስ በእኛ ውስጥ ህያው ሁኖ የምንኖረው ኑሮ ነው፡፡

ይህንንም ዓይነት ኑሮ ለመኖር አምላካችን ያደረገልንን የማዳን ሥራ፣ ስለ ሰው ልጆች ብሎ ያደረጋቸውን ነገሮች ሁሉ /ልደቱን፣ ጥምቀቱን ፣ጾሙን ፣ መከራውን ፣ ስቅለቱን / በተለይም ደግሞ ለትንሳኤያችን በኩር የሆነበትን ትንሳኤውን እና እርገቱን እንዲሁም ዳግም ምጽአቱን ዘወትር ማሰብ ያስፈልጋል፡፡

እነዚህን ድርጊቶች /ነገሮች/ እንደ ትዝታ ማሰብ ብቻ ሳይሆን ልክ በተደረጉበት ወቅት እንደተገኙ ሁኖ መካፈልና መቅመስም የግድ ያስፈልጋል፡፡ ለዚህም ቅዳሴ ዋነኛው መንገድ ነው፡፡ ቅዳሴ ለማስቀደስ በመሰዊያውና በመስዋእቱ ዙሪያ ስንሰበሰብ ልክ ጌታ በተሰቀለበት በዕለት አርብ በቀራንዮ አደባባይ እንደተገኘን ሆነን እንቆማለን፡፡

በአጠቃላይ ሕይወታችን እነዚህን ነገሮች በማስታወስ፣ በማሰብ እና በመካፈል ላይ የተመሠረተ መሆን አለበት፡፡

ዳሩ ግን በኃጢአታችን ምክንያት በጥምቀት የተቀበልነውን አዲስ ሰውነት በማቆሸሻችን እና ራሳችንን ከፀጋ በማራቃችን፣ እንዲሁም በተለያዩ አስፈላጊ እና አላስፈላጊ ጉዳዮች ተጠምደን በወከባ በመኖራችን ይህንን ማድረግ ከባድ ይሆን ብናል፡፡

ስለዚህም ቤተ ክርስቲያን እነዚህን በነገረ ድኅነት ውስጥ ትልቅ ቦታ ያላቸውን ታላላቅ ድርጊቶች ቢያነስ በዓመት አንድ ጊዜ እንድናስባቸው አድርጋለች፡፡ የልደትን፣ የጥምቀትን፣ የስቅለትን፣ የትንሳኤን፣ የዕርገትን … በዓላት የማክበራችን ዋናው ምክንያትም ይኸው ነው፡፡

ነገር ግን አሁንም ቢሆን እነዚህን በዓላት ስናከብር ከሚያስጨንቁንና ህሊናችንን ከሞሉት ነገሮች መልሰን በአንድ ጊዜ ወደ መንፈሳዊ ሃሳብና ተመስጦ መምጣት ስለምንቸገር ቤተ ክርስቲያን ከበዓላቱ በፊት የዝግጅትና የማንቂያ ጊዜያት እና አጽዋማት እንዲኖሩም አድርጋለች፡፡

በእነዚህ ወቅቶች ህሊናችንን ቀስ በቀስ ወደ መንፈሳዊው ሃሳብ እና ወደ በዓሉ ጉዳይ ተመልሶና በዓሉን በናፍቆት ጠብቀን በተገቢው ሁኔታ እንድናከብረው ታደርጋለች፡፡

በዚህም ምክንያት አብዛኞቹ በዓላት ከመከበራቸው በፊት አጽዋማት ይኖራሉ ሥጋ ወደሙን ከመቀበላችንም በፊት እንጾማለን፡፡ ሌሎቹም ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን ከመፈፀማቸው በፊት የጾምና የዝግጅት ወቅቶችን ማሳለፍ ጥንታዊ የቤተ ክርስቲያን ትውፊት ነው፡፡

በዚህ ጽሑፍ ርእስ አድርገን የምንነጋገርበት ጾመ ነቢያት ዋነኛ ዓላማም ምእመናንን የጌታችንን የልደት በዓል እንዲያከብሩ ማዘጋጀት ነው፡፡ በተለይም ከልደት በፊት ያሉት ሦስት ሳምንታት ይህ ጎልቶ እንደሚነገርባቸው ቀጥለን እንመለከታለን፡፡

ብሉይ ኪዳን እና ጾመ ነቢያት

የአዳምን በደል ካሳ ከፍሎ ከራሱ ጋር ሊያስታርቀው ወደዚህ ምድር የመጣውና በተዋህዶ ሰው የሆነው እግዚአብሔር ወልድ በዚህ ምድር ላይ በሥጋ የተገለጠው አዳም የድኅነት ቃልኪዳንን ከእግዚአብሔር ከተቀበለ ከብዙ ሺህ ዓመታት በኋላ ነው፡፡

እነዚህ ዓመታት ለሰው ልጆች በኋላ የሚደረገውን የድኅነት ሥራ /ሥጋዌ፣ ሞት፣ ትንሳኤ/ እንዲረዱ ለማስቻል ዝግጅት የተደረገባቸው ዘመናት ናቸው፡፡ በእነዚህ ዘመናት እግዚአብሔር የራሱ የሆኑ ሕዝቦችን እና ሰዎችን በመምረጥና ከእነዚህ ጋር ቃል ኪዳን በመግባት፣ ለእነዚህ ሕዝቦች ተአምራትን በማድረግና ከጠላቶቻቸው በማዳን፣ ከእነዚህም በላይ ደግሞ ነቢያትን በመላክና በእነርሱ አማካኝነት ሕዝቡን በማስተማር፣ ትንቢት በማስነገርና ተስፋ በመስጠት /በማጽናናት/፣ ሱባኤም በማስቆጠር ማንነቱን እና የሰው ልጆችን ለማዳን ያቀደውን ዕቅድ ቀስ በቀስ፣ በጥቂት በጥቂቱ ገልጧል፡፡

በየዘመኑ የተነሱ ነቢያትም ምንም እንኳን አምላክ ይህን ዓለም እንዴት እንደሚያድነው ሙሉ በሙሉ ግልጥልጥ ብሎ ባይረዱትም እግዚአብሔር ዓለሙን የሚያድንበትን ቀን እንዲያቀርበው እንዲህ እያሉ ይማፀኑ ነበር፡፡

– «አቤቱ እጅህን ከሰማያት ልከህ አድነን» /መዝ. 143.17/
– «ሰማያትን ቀደህ ብትወርድ ምነው)» /ኢሳ.64.1/
ቅዱስ ጴጥሮስ በሁለተኛው መልእክቱ እንደሚነግረንም በመንፈስ እየተነዱ ስለሚመጣው ነገር ሁሉ ትንቢት ተናግረዋል፤ ሱባዔ ቀጥረዋል፤ ህዝቡም የጌታን ማዳን በተስፋ እንዲጠብቅ አስተምረዋል፡፡ ጌታ ሰው ሁኖ የተወለደው ከዚህ ሁሉ ዝግጅት በኋላ ነው፡፡ የአዳኙ መሲህ መወለድ በተለይ ከእስራኤል ዘንድ በጉጉት ይጠበቅ ነበር፡፡

በዚህም ምክንያት ከእስራኤል መካከል ቅን የነበሩትና በእግዚአብሔር መንገድ የተጓዙት፤ «መሲሁን አገኘነው»፤ «ሙሴ በህግ መጻሕፍት፣ ነቢያትም ስለ እርሱ የጻፉለትን የናዝሬቱን ኢየሱስን አገኘነው» /ዮሐ. 1.41፣ ዮሐ. 1.45/ እያሉ ተከትለውታል፡፡

እንግዲህ ይህ ታሪክ ከተፈፀመ ጌታችንም ከተወለደ እነሆ ከ2000 ዓመታት በላይ አልፎታል፡፡ እኛም የተደረገውን ሁሉ በትውፊት ተቀብለን በምስጢራተ ቤተ ክርስቲያን አማካኝነት በዚህ በድኅነት ጉዞ የተሰጡትን ፀጋዎች ተካፍለን ክርስቲያኖች ሆነናል፡፡ በመግቢያችን እንዳየነው ክርስትና እነዚህን ነገሮች ሁሉ ዘወትር እያሰብንና፣ በተመስጦ እንደ አዲስ እየተካፈልን ልንኖረው የሚገባ ኑሮ ነው፡፡

ቤተ ክርስቲያን የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል እንዲከበር ያደረገችው ከእነዚህ ዘወትር ልናስባቸው ከሚገቡ ነገሮች አንዱ የሆነውን ብርሃኑንና ዘወትር ልናየው የሚገባውን የጌታችንን ልደትን ቢያንስ በዓመት አንድ ጊዜ በተመስጦ እንድናስበውና ብርሃኑን እንድናየው ነው፡፡

ይህችን በዓመት አንድ ጊዜ የምትመጣዋን በዓልም ቢሆን ከማክበራችን በፊት አርባ ሦስት ቀናትን በመጾም እንዘጋጃለን፡፡ በመጾም ብቻ ሳይሆን እነዚህ አርባ ሦስት ቀናት ተከፋፍለው የልደት በዓልን በተገቢው መንገድ እንድናከብር የሚያዘጋጁ ትምህርቶችን እንማርባቸዋለን፡፡ በተለይም ከልደት በዓል በፊት ያሉት ሦስት ሳምንታት ይህ ዓላማ አላቸው፡፡

ቤተ ክርስቲያን የጌታችንን የልደቱን ብርሃን ለማየት እንዘጋጅ ዘንድ እነዚህን ሦስት ሳምንታት የጌታችንን ልደት በናፍቆት መበጠበቅ እንደ ብሉይ ኪዳን ሰዎች ሆነን እንድናሳልፍ ታደርጋለች፡፡

በእነዚህ ሳምንታት /በተለይም በእሑዶቹ/ የብሉይ ኪዳን ነቢያት የአዳኙን መምጣትና የጌታን ቀን መገለጥ በመናፈቅ ስላሳለፏቸው ጊዜያት ደጋግመን በመማር እነዚያን የጨለማ ዘመናት እንድናስታውስና እኛም በእነርሱ መንፈስ ተቃኝተን ያለንበትን ሁኔታ በመመርመርና ዘወትር ልንመላለስበት ያጣነውን ነገር ግን በሃጢአታችን ያጣነውን የልደቱን ብርሃን ለማየት እንድንናፍቅ እንደረጋለን፡፡

ሦስቱን ሳምንታት በዚህ ሁኔታ ካሳለፍንና የልደቱን ብርሃን የማየት ፍላጎታችን ከተነሳሳ በኋላ የልደትን በዓል እናከብራለን፡፡ ደጋግመን እንዳልነውም የልደትን በዓል የምናከብረው እንዳለፈ ታሪክ መታሰቢያ አይደለም፡፡ ልክ በዚያች በልደቱ ቀን ከሰብአ ሰገልና ከእረኞች ጋር እንደተገኘን ሆነን እናከብራለን የልደቱን ብርሃን እናያለን እንጂ፡፡

ለዚህም ነው የልደትን በዓል ስናከብር
«ዮም ፍስሐ ኮነ በእንተ ልደቱ ለክርስቶስ»
«ዛሬ በክርስቶስ ልደት ደስታ ሃሴት ሆነ፡፡» የምንለው፡፡
«ዮም፣ ዛሬ» ማለታችን በዓሉ የልደት መታሰቢያ /ትዝታ/ ብቻ ሳይሆን በዚያ በልደት ቀን እንደነበርን የምንሆንበት መሆኑን የሚያመለክት ነው፡፡

ስብከት፣ ብርሃን፣ ኖላዊ

እነዚህ ከልደተ በዓል በፊት ያሉት ሦስቱ የጾመ ነቢያት ሳምንታት ስብከት፣ ብርሃን እና ኖላዊ ተብለው ይጠራሉ፡፡

እነዚህ ሳምንታት ነቢያት አምላክ ይህንን ዓለም እንዲያድን ያላቸውን ናፍቆት የገለጡባቸው እና ይህንን አስመልክተው ያስተማሩባቸው ሦስት የተለያዩ መንገዶች እና ጌታችንም ለእነዚህ መልስ የሰጠባቸው ሁኔታዎች ይታሰቡባቸዋል፡፡

1. ስብከት

ስብከት ማለት ማስተማር ማለት ነው፡፡ ይህ ሳምንት ከሙሴ ጀምሮ የነበሩ ነቢያት በሙሉ አዳኝ /መሲህ/ እንደሚመጣ ማስተማራቸው ጌታችንም እነርሱ ይመጣል ብለው ያስተማሩለት እኔ ነኝ ብሎ ራሱን መግለጡ የሚታሰብበት ነው፡፡
ሙሴ ለጊዜው የጌታችን ምሳሌ ለሆነው ለኢያሱ ፍጻሜው ግን ለጌታችን በሆነው ትንቢቱ «አምላክህ እግዚአብሔር ከወንድሞችህ እንደ እኔ ያለ ነቢይ ያስነሳልሃል፤ እርሱንም ስሙት፡፡» ብሎ ለሕዝበ እስራኤል ነግሯቸው ነበር፡፡ /ዘዳ. 18.15/

እግዚአብሔር ወልድም በሥጋ ማርያም በተገለጠ ጊዜ ራሱን ያስተዋወቀው ያ ነቢያት የተናገሩለት አዳኝ /መሲህ/ እንደሆነ ነው፡፡ «ሙሴ እና ነቢያት ሁሉ ስለ እኔ ይናገራሉ፡፡» ይላቸው ነበር፡፡

ትንቢቱን ያውቁ የነበሩ በእግዚአብሔር መንገድ የሚሄዱ እስራኤላውያንም «መሲሁን አገኘነው»፣ «ሙሴ በህግ መጻሕፍት፣ ነበያትም ስለ እርሱ የጻፈለትን የናዝሬቱን ኢየሱስን አገኘነው» እያሉ ተከትለውታል፡፡ /ዮሐ. 1.41፣ ዮሐ. 1.45/

ሐዋርያትና ሌሎቹ ደቀመዛሙርቱም ከጌታችን ሞትና ትንሳኤ በተለይ የተነገሩትን ትንቢቶች ሁሉ ያውቁ ለነበሩት እስራኤላውያን ያስተማሩት እነዚህን የነቢያት ትምህርቶች እና ትንቢቶች እየጠቀሱ ነበር፤

ቅዱስ ጴጥሮስን በቤተ መቅደስ እንዲህ ብሎ አስተምሯል፤ «አሁንም ወንድሞቼ ሆይ አለቆቻችሁ እንዳደረጉ ይህን ባለማወቅ እንዳደረጋችሁት አውቃለሁ፡፡ እግዚአብሔር ግን ክርስቶስ መከራን እንዲቀበል በነቢያት ሁሉ አፍ እንደተናገረ እንዲሁ ፈፀመ» /ሐዋ. 3.17-18/፡፡

በሁለተኛው መልእክቱ ደግሞ እንዲህ ሲል ጽፏል፡- «ወንድሞች ሆይ የቀደሙ ቅዱሳን ነቢያት የተናገሩትን ቃልና ለእኛ ለሐዋርያትም ያዘዘውን የመድኃኒታችንና የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ትእዛዝ ታስቡ ዘንድ… ዕወቁ» /2ኛ ጴጥ. 3.1-3/

ቅዱስ ጳውሎስም በዕብራውያን መልእክቱ መግቢያ ላይ እንዲህ ብሏል፤ «ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዐይነትና በብዙ ጎዳና ለአባቶቻችን በነቢያት ተናገረ፤ በኋላ ዘመን ግን ሁሉን ወራሽ ባደረገው፣ ሁሉን በፈጠረበት በልጁ ነገረን፡፡» /ዕብ. 1.1-2/

2. ብርሃን

ነቢያት የአምላክን ማዳን ከጠበቁባቸው እና ከገለጡባቸው መንገዶች አንዱ ብርሃን ነው፡፡ ዘመነ ብሉይ መከራ ሥጋ፣ መከራ ነፍስ የፀናበት፣ ሁሉ ነገር አስጨናቂ የሆነበት፣ ሰው ብርሃን ከሆነው አምላክ ጋር የተራራቀበት ስለነበር ያሉበትን ዘመን «ጨለማ» ብለው በመግለጥ ይህንን ጨለማ የሚያስወግድና ወደ ትክክለኛው መንገድ የሚመራ ብርሃን እንዲመጣ እንዲህ እያሉ ይፀልዩ ነበር፡፡

«ብርሃንህንና ጽድቅህን ላክ፣ እነርሱም ይምሩኝ፣
አቤቱ ወደ መቅደስህ ተራራና ወደ ማደራያህ ይውሰዱኝ» /መዝ. 42.3/
ጌታችንም ወደዚህ ዓለም በመጣ ጊዜ ለዚህ መልስ ሰጥቷል፤
«እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ» /ዮሐ. 8.12/
ደቀመዛሙርቱም ስለ ብርሃንነቱ በመመስከር ተባብረዋል፤

– ቅዱስ ዮሐንስ ስለጌታችን ሰው መሆን /ሥጋዌ/ በተናገረበት በወንጌሉ የመጀመሪያ ክፍል ጌታችንን ብርሃን ብሎታል፤ «ሕይወት በእርሱ ነበረ፣ ሕይወትም የሰው ብርሃን ነበረ፤ ብርሃንም በጨለማ ያበራል፤ ጨለማም አላሰነፈውም» /ዮሐ. 1.4-5/

ቅዱስ ጳውሎስም ጌታችን በሚያንፀባርቅ ብርሃን አምሳል እንደተገለጠበት ተናግሯል፡፡ «እኩል ቀን በሆነ ጊዜ በመንገድ በሄደ ከፀሐይ ይልቅ የሚበራ መብረቅ በእኔና ከእኔ ጋር ይሄዱ በነበሩት ላይ ከሰማይ ሲያንፀባርቅ አየሁ፤ … አንተ የምታሳድደኝ የናዝሬቱ ኢየሱስ ነኝ አለኝ፡፡» /ሐዋ. 26.13/

3. ኖላዊ

ኖላዊ ማለት እረኛ ማለት ነው፡፡ ነቢያቱ ራሳቸውን እና ሕዝበ እስራኤልን ብሎም ዓለምን እረኛቸው እንደተዋቸው እና እንደተቅበዘበዙ በጎች በመቁጠር እንዲሰበስባቸውና እንዲያሰማራቸው እንዲህ እያሉ እራሳቸውን ይማፀኑ ነበር»

«ዮሴፍን እንደ መንጋ የምትመራ የእስራኤል ጠባቂ /እረኛ/ ሆይ፣ አድምጥ በኪሩቤል ላይ የምትቀመጥ ተገለጥ፡፡» /መዝ. 79.1/

ጌታችንም ለዚህ ጥያቄ እንዲህ ሲል መልስ ሰጥቷል፤ «ቸር ጠባቂ /እረኛ/ እኔ ነኝ፡፡ ቸር ጠባቂ ስለ በጎቹ ነፍሱን ይሰጣል፡፡»  /ዮሐ10.11/

ምን እናድርግ ?

ዛሬም እኛ በኃጢአታችንና በምታዋክበን ዓለም ምክንያት ዘወትር ልናየውና ልንመላለስበት የሚገባን ብርሃነ ልደቱ ተሰውሮብናል፣ ከቸር እረኛችን የራቅን የተቅበዘበዝን በጎች ሁነናል፡፡ በምናስበው ሃሳብ፣ በምንሰራው ሥራ ውስጥም የአምላክ ሰው መሆን ቦታ የለውም፡፡ የምንኖረው ልክ ክርስቶስ እንዳልተወለደ /as if Christ was not born/ ነው፡፡ ስለዚህ እኛም እንደ ብሉይ ኪዳን ሰዎች ያጣነውን ይህንን ፀጋ ለማግኘት፣ ብርሃነ ልደቱን ለማየት፣ በዚያ ውስጥም ለመመላለስ የክርስትናችንን እና የመንፈሳዊነታችንን ጥልቀት ለመጨመር መሻት አለብን፡፡

ስለዚህ እስኪ እኛም በእነዚህ ሳምንታት የብሉይ ኪዳን ሰዎች የነበሩበትን ሁኔታ እየተዘከርን፣ እኛም ያለንበትን ሁኔታ እየመረመርን፣ ስላጣነው ብርሃን ለማሰብ፣ ያጣነውን መልሰን ማየትንና ማግኘትን ለመናፈቅ እንሞክር፡፡ መጻሕፍትን ለማንበብ፣ በጉዳዩ ላይ በተመስጦ ለማሰብ እና ለመወያየት ጊዜ እንውሰድ፡፡ ብርሃነ ልደቱን ለማየት እንዲያበቃን «አቤቱ ብርሃንህንና ጽድቅህን ላክ፤ ቸሩ እረኛችን ሆይ፣ ተቅበዝብዘናልና እባክህ ሰብስበን» እያልን እንፀልይ፡፡ ሰው ከነኃጢአቱ ወደ እግዚአብሔር ብርሃን ሊቀርብ /ሊያየው/ አይችልምና ራሳችንን በንስሃ እናድን፡፡ እነዚህን ቤተ ክርስቲያን ያስቀመጠችልንን የዝግጅት ጊዜያት በሚገባ ከተጠቀምን ትርጉም ያለው፣ በሕይወታችንና በመንገዳችን ላይ ለውጥ የሚያመጣ ልዩ የልደት በዓል እናከብራለን፡፡

አምላካችን ብርሃነ ልደቱን እንድንመለከት ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንልን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር