ዘመነ ጽጌ  

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

መስከረም ፳፬ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም 

በቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ፣ በአገራችን በኢትዮጵያ የወቅቶች ሥርዓተ ዑደት መሠረት ከመስከረም ፳፮ ቀን ጀምሮ እስከ ታኅሣሥ ፳፭ ቀን ድረስ ያለው ፺ ቀናትን የሚያጠቃልለው ጊዜ ‹ዘመነ መጸው› ይባላል፡፡ ‹መጸው› ማለት ‹ወርኀ ነፋስ› (የነፋስ ወቅት) ማለት ሲኾን ይኸውም ‹መጸወ ባጀ፤ መጽለወ ጠወለገ› ካለው የግእዝ ግስ የተገኘ ነው፡፡ ዘመነ መጸው ከዘመነ ክረምት ቀጥሎ የሚብት (የሚገባ) የልምላሜ፣ አበባ፣ የፍሬ ወቅት ነው፡፡ በውስጡም አምስት ንዑሳን ክፍሎችን የሚያካትት ሲኾን እነዚህም፡- ዘመነ ጽጌ፣ ዘመነ አስተምህሮ፣ ዘመነ ስብከት፣ ዘመነ ብርሃን እና ዘመነ ኖላዊ ናቸው (ያሬድና ዜማው፣ ገጽ ፵፰-፵፱)፡፡

ከአምስቱ የዘመነ መጸው ክፍሎች መካከልም የመጀመሪያው ክፍል ‹ዘመነ ጽጌ› ተብሎ ይጠራል፡፡ ይህም ከመስከረም ፳፮ እስከ ኅዳር ፮ ቀን ድረስ ያሉትን ፵ ቀናት ያጠቃልላል፡፡ ‹ጽጌ› ቃሉ ‹ጸገየ አበበ› ከሚለው የግእዝ ግስ የተገኘ ሲኾን ትርጕሙም አባባ ማለት ነው፡፡ ‹ዘመነ ጽጌ› ደግሞ ‹የአበባ ወቅት፣ የአበባ ጊዜ፣ የአበባ ዘመን› ማለት ነው፡፡ ይህ ወቅት ዕፀዋት በአበባ የሚያጌጡበት፣ ምድር በአበቦች ኅብረ ቀለማት የምታሸበርቅበት፣ ወንዞች ንጹሕ የሚኾኑበት፣ ጥሩ አየር የሚነፍስበት፣ አዕዋፍ በዝማሬ የሚደሰቱበት፣ እኛም የሰው ልጆች ‹‹አሠርጎካ ለምድር በሥነ ጽጌያት፤ አቤቱ ምድርን በአበቦች ውበት አስጌጥሃት›› እያልን የዘመናት አስገኚ እና ባለቤት የኾነውን ልዑል እግዚአብሔርን የምናመሰግንበት፤ ከዚህም ባሻገር እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከተወደደ ልጇ ጋር ከገሊላ ወደ ግብጽ ምድር መሰደዷን የምናስብበት ወቅት ነው፡፡

ጌታችን አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቤተ ልሔም በተወለደ ጊዜ የዘመኑ ንጉሥ ሄሮድስ ሥልጣኔን ይቀማኛል በሚል ቅናት ተነሣሥቶ ጌታችንን ለማስገደል አሰበ፡፡ ጌታችንም በተአምራት መዳን ሲቻለው የትዕግሥት፣ የትሕትና አምላክ ነውና በለበሰው ሥጋ በእናቱ በቅድስት ድንግል ማርያም ጀርባ ታዝሎ በመልአኩ ተራዳኢነት፣ በአረጋዊው ዮሴፍ ጠባቂነትና በሰሎሜ ድጋፍ ከገሊላ ወደ ግብጽ ተሰዶ ሄሮድስ እስኪሞት ድረስ ቆይቷል፡፡ ሄሮድስም ጌታን ያገኘሁ መስሎት በቤተ ልሔምና በአውራጃዋ የሚገኙ የሁለት ዓመት ከዚያ በታች የኾኑ አንድ መቶ ዐርባ አራት ሺሕ ሕፃናትን በሰይፍ አስጨርሷል፡፡

መምህራነ ቤተ ክርስቲያን እንደሚያስተምሩን የጌታችን እና የእመቤታችን የስደት ወቅት በወርኀ ግንቦት ነው፡፡ ነገር ግን ዘመነ ጽጌ የአበባ፣ የፍሬ ወቅት በመኾኑ እመቤታችንን በአበባ፣ ጌታችንን ደግሞ በፍሬ እየመሰሉ ለማመስገንና ለማወደስ በሚያስችል ምሥጢር ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን የስደቱ ጊዜ ከመስከረም እስከ ኅዳር ባለው ጊዜ ውስጥ እንዲዘከር አድርገዋል፡፡ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ለዘለዓለሙ የማይደርቀውን የሕይወት ፍሬ ኢየሱስ ክርስቶስን ያስገኘችልን ንጽሕት የማትጠወልግ አበባ ናትና፡፡ ይህ የእመቤታችን አበባነትና የጌታችን ፍሬነትም እንደ ቅዱስ ያሬድ፣ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫና አባ ጽጌ ድንግል ባሉ ሊቃውንት ድርሰቶች በስፋት ተገልጧል፡፡ በተለይ በአባ ጽጌ ድንግል ድርሰት በማኅሌተ ጽጌ በጥልቀት ተመሥጥሯል፡፡

በአጠቃላይ በዘመነ ጽጌ በማኅሌትና በቅዳሴ ጊዜ የሚቀርቡ መዝሙራትና የሚሰጡ ትምህርቶችም ይህንኑ ምሥጢር የሚመለከቱ ናቸው፡፡ በዚህ ወቅት በሚገኙ ሰንበታት ሊቃውንቱ ሌሊቱን ሙሉ ስለ እመቤታችን አበባነትና ስለ ጌታችን ፍሬነት የሚያትት ትምህርት የያዙትን ማኅሌተ ጽጌና፣ ሰቆቃወ ድንግልን ከቅዱስ ያሬድ ዚቅ ጋር በማስማማት ሲዘምሩ፣ ሲያሸበሽቡ ያድራሉ፡፡ ቅዳሴውም በአባ ሕርያቆስ የተደረሰውና ምሥጢረ ሥጋዌን፣ ምሥጢረ ሥላሴንና ነገረ ማርያምን በጥልቅ ትምህርተ ሃይማኖት የሚያትተው ቅዳሴ ማርያም ነው፡፡ ምንባባቱም ከዚሁ ጋር ተዛማጅነት ያላቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ናቸው፡፡

በተአምረ ማርያም እና በማኅሌተ ጽጌ ተጽፎ እንደሚገኘው ጌታችን በግብጽ ምድር በስደት ሳለ ብዙ ድንቅ ድንቅ ተአምራትን አድርጓል፡፡ ከእነዚህ መካከልም እናቱን እመቤታችንን የዘለፏትን ትዕማንና ኮቲባ የሚባሉ ሴቶችን ከሰውነት ወደ ውሻነት መቀየሩ፤ ውኃ በጠማቸው ጊዜ ውኃ እያፈለቀ ማጠጣቱና ይህንንም ውኃ ክፉዎች እንዳይጠጡት ማምረሩ፤ ለችግረኞችና ለበሽተኞች ግን ጣፋጭ መጠጥና ፈዋሽ ጠበል ማድረጉ፤ ‹‹የሄሮድስ ጭፍሮች ደርሰው ልጅሽን ሊገድሉብሽ ነው›› ብሎ የዮሴፍ ልጅ ዮሳ እመቤታችንን በማስደንገጡ እስከ ዕለተ ምጽአት ድረስ ድንጋይ ኾኖ እንዲቆይ ማዘዙ፤ መንገድ ላይ የተራዳቸው ሽፍታ ሰይፉ በተሰበረች ጊዜ ሰይፉን በተአምራት እንደ ቀድሞው ማደሱ፤ እንደዚሁም የግብጽ ጣዖታትን በአምላክነቱ ቀጥቅጦ ማጥፋቱ ተጠቃሾች ናቸው፡፡

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከልጇ ጋር በተሰደደች ጊዜ የደረሰባትን መከራ በማስታወስ ዘመነ ጽጌን በፈቃዳቸው የሚጾሙ ካህናትና ምእመናን ብዙዎች ናቸው፡፡ ኾኖም ግን የጽጌ ጾም የፈቃድ ጾም እንጂ ከሰባቱ አጽዋማት ጋር የሚመደብ ስላልኾነ ጽጌን የማይጾሙ አባቶች ካህናትንና ምእመናንን ልንነቅፋቸው አይገባም፡፡ የጌታችን አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ፣ የእናቱ ቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት፣ በሄሮድስ እጅ በግፍ የተሠዉ ሕፃናት በረከት አይለየን፡፡ አምላካችን በአበባ የሚመሰለው ሰውነታችን የጽድቅ ፍሬን ሳያፈራ እና ንስሐ ሳንገባ በሞት እንዳንወሰድ መልካም ፈቃዱ ይኹንልን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡